Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር ከጊዜ መለዋወጥ ጋር የሚሄዱ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምን እንመክራለን››

አቶ ሙራድ አብድራህማን ኢሳ፣ በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ የንግድና የፕሮሞሽን ክፍል ከፍተኛ ኦፊሰር

ስዊድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ከምትሠራባቸው መስኮች አንዱ የትራንስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ አለመሳለጥ ተጠቃሚውን ከማጉላላቱም በላይ የብዙዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ ለመመዝገቡ ምክንያት ነው፡፡ ስዊድን ከ50 ዓመታት በፊት የችግሩ ሰለባ የነበረች ሲሆን አሁን ላይ የትራፊክ አደጋን እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሞትንና የአካል ጉዳትን በመቀነስ የትራፊክ አደጋን ከተቆጣጠሩ ቀዳሚ አገሮች ተርታ ተሰልፋለች፡፡ ለዚህም መንግሥት ብቻውን ሳይሆን መኪና አምራች ድርጅቶችም ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይኼንን ልምድ ለማካፈል ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ሲሠራ የቆየው በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ባሳለፍነው ሳምንት ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡ የልምድ ልውውጡ ትኩረትም በኢትዮጵያ የትራፊክ ደኅንነትና ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ያሉበት ፈተናና መፍትሄዎቹ የሚል ነበር፡፡ አቶ ሙራድ አብድራህማን ኢሳ በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ የንግድና የፕሮሞሽን ክፍል ከፍተኛ ኦፊሰር ናቸው፡፡ የስዊድን ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የሚሠራበትን የትራንስፖርት ዘርፍ በኤምባሲው በኩል በበላይነት ይመራሉ፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስዊድን የትራንስፖርት ዘርፉን በማጠናከርና የትራፊክ አደጋን በመቆጣጠር በዓለም በምሳሌነት የምትጠራ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በተቃራኒው በትራፊክ አደጋ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ታጣለች፡፡ ስዊድን ችግሩን ለመቅረፍ ያላት አስተዋፅኦ ምንድነው?

አቶ ሙራድ፡- ስዊድን ትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ካላት ጥሩ ተሞክሮ የተነሳ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፍላጎት አሳይታ ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፉ መተባበር ጀምራለች፡፡ ስዊድኖች በትራፊክ አደጋ ሰው እንዳይሞት ቪዥን ዚሮ የተባለ የረዥም ዓመት ዕቅድ ዘርግተው መተግበር ጀምረዋል፡፡ ትንሽ አደጋ የሚመዘገብበት አገር ለመሆንም የዚህ ዕቅድ መተግበር ረድቷቸዋል፡፡ ትራንስፖርት ላይ ያለው የመሳለጥ ሁኔታም ከዓለም የተቀናጀ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው መንግሥት ብቻውን ሠርቶ አይደለም፡፡ ከትምህርት ቤት ጀምሮ የንግድ ኩባንያዎች በሙሉ ለሰው ሕይወት ዋጋ ሰጥተው አደጋን መቀነስ ዓላማቸው አድርገው በመሥራታቸው ነው፡፡ ለልምድ ልውውጥ ኢትዮጵያ ከመጡት አንዱ ኤሪክሰን የሚሠራው አይቲ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን የትራፊክ ደኅንነትን ዓላማ ያደረገ ሥራም ይሠራል፡፡ ስካኒያና ቮልቮ ኩባንያዎችም መኪኖቻቸውን ደኅንነት የሚያስጠብቁ አድርገው ነው የሚሠሩት፡፡ ኤምባሲውም ቅድሚያውን ወስዶ ኩባንያዎቹ ኢትዮጵያ እንዲመጡና በስዊድን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከልምዳቸው እንዲያካፍሉ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስብሰባውን አካሂደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከስዊድን ተሞክሮ ልምድ እንድታገኝ ኤምባሲው ትብብሩን የጀመረው መቼ ነው?

አቶ ሙራድ፡- ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ነው፡፡ በጊዜው የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ ነበሩ፡፡ ወቅቱ ትራፊክ ላይ ያለው አደጋ ተደጋግሞ ይወራ የነበረበትና ኤምባሲውም ምን ማድረግ እንችላለን ብሎ የተነሳበት ስለነበር በትራፊክ አደጋ ዙሪያ እንዲወያዩ አድርገናል፡፡ መንገድ፣ ትራንስፖርትና ትራፊክ አደጋ የተወያዩባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የስዊድን ልምድም የተቀሰመበት ነው፡፡ በመቀጠልም የሚመለከታቸው 20 አካላትም ስዊድን እንዴት አደጋን መቀነስ እንደቻለችና የመንገድ ደኅንነት መሠረተ ልማቷ ምን እንደሚመስል እንዲያዩ አድርገናል፡፡ በዚህም ከክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች፣ ከፍትሕና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምን ልናደርግ እንችላለን ብለውም የተወሰኑ የለውጥ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ሕግ ላይ ማሻሻያ እስከማድረግም ተሄዷል፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ሲኖሩም ከስዊድን ቮልቮና ስካኒያ ኩባንያዎች እንዲሁም የማማከር ሥራ የሚሠራው ስዊሮድ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እያደረግን ነው፡፡ ቮልቮና ስካኒያ ኩባንያዎች ስዊድን ከዩኒዶ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በሰላም ቪሌጅ ለከፈቱት የቮኬሽናል ትምህርት ቤት መካኒኮች እንደዚህ ዓይነት መኪኖችን እንዴት መንዳትና መጠገን እንዳለባቸው ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡  ትምህርቱም ሦስት ዓመት ይፈጃል፡፡ ይህ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ የምንሠራው ነው፡፡ በባቡር መሠረተ ልማት ላይ የተወሰነ ልምድ ተወስዷል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ካለችበት ዕድገት አንፃር እንዴት የስዊድኑን እናምጣው የሚለው አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ የትራፊክ አደጋ ችግርን መቅረፍ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ የመኪና ኩባንያዎች አደጋን እንዴት መቀነስ እንደሚችሉ ታሳቢ አድርገው እንደሚሠሩት ሁሉ ኢትዮጵያም እንዲህ ያሉ ዘመናዊና አደጋ የሚቀንሱ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት ይኖርባታል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይነት ያለው ትራንስፖርት የልምድ ልውውጡ አንድ አካል ነው፡፡ ስዊድን ትራንስፖርት ዘርፉን እንዴት አሳለጠች? ከ50 ዓመት በፊት የነበራትን ዓይነት መንገድ ኢትዮጵያ አሁንም አላት፡፡ ከስዊድን ምን እንማራለን?

አቶ ሙራድ፡- አዲስ አበባና ዙሪያዋ የምናያቸው የመንገድ ሁኔታዎች ከዓመታት በፊት ስዊድንም ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ለምሳሌ አደባባይ ፍጥነት በመቀነስ ረገድ ጥቅም ቢኖረውም አደባባይ ፈርሶ ወደ መስቀለኛ መንገድ እየተቀየረ ነው፡፡ ስዊድንም እንዲህ ተደርጓል፡፡ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደግሞ ፍጥነት መቀነሻ ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ላይ ልምድ የሚወስድበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ስዊድን የሄዱ የሚመለከታቸው አካላት ሲመለሱ በየከተሞች የፍጥነት መቆጣጠሪያ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ ይህ አደጋን ይቀንሳል፡፡ የሚገኝ ልምድ መሬት እንዲወርድና የመንገድ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጭ ሲሠሩ የስዊድንን ልምድ እንዲቀስሙ እንፈልጋለን፡፡ ትራፊክ ደኅንነት ላይ ኤክስፐርቶች ስላሉ እነሱ እንዲያግዙ እናደርጋለን፡፡ ስዊድን የሚገኘው መንገድ ትራንስፖርት ከኢትዮጵያው ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ እየሞከርን ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ በኩል የሚገጥመን ፈተና በየመሥሪያ ቤቶች የኃላፊዎች መቀያየር ነው፡፡ ስለሆነም በኤክስፐርትና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መደበኛ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥናትና ምርምር ክፍል ጋር ግንኙነት እንዲፈጠርም እየጣርን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል ያለው ተቀባይነት እንዴት ነው? ግንኙነት ከጀመራችሁ በኋላ የተገኙ ለውጦችን ቢነግሩን?

አቶ ሙራድ፡- በሚኒስቴር ደረጃ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል ጥሩ ተሳትፎ አለ፡፡ አዳዲስ ነገር ሲኖር በተቻለ መጠን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፡፡ የልምድ ልውውጥ ለማድረግም አብረን እንሠራለን፡፡ የከበደን ጉዳይ ከሚኒስቴሩ ባለፈ ባለድርሻ አካላት ማለትም የአውቶቡስ፣ የታክሲ ማኅበራት፣ የመንገድ፣ የትራፊክና የአገር አቋራጭ፣ የሞተር አሽከርካሪዎች፣ መንጃ ፈቃድ አሠልጣኞች፣ ፈቃድ ሰጪው አካልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መገናኘት ነው፡፡ በሰዊድን ያለው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ በራሱ ለኢትዮጵያ ልምድ የሚሆን ነው፡፡ መንጃ ፈቃድ ማውጣት የሁለት ዓመት ትምህርት ይፈጃል፡፡ ሕይወትን ከማዳን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የቪዥን ዜሮ ዕቅዳቸውም ሰው ላይ የሚደርስ አደጋንና ሞትን ማጥፋት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና አካል እንዳይጎድል ማድረግ ቅድሚያ ሥራቸው ነው፡፡ ብረቱ (መኪናው) ሰው እንዳይጎዳ እንዴት እናድርግ የሚለው ላይ ደርሰዋል፡፡ የመኪና ኩባንያዎችም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ሰው አደጋ እንዳይደርስበት እየሠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰው ሊገጩ ሲሉ ወይም አደጋ ከፊት ካለ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ፣ እየተነዱ ከሆነም ራሳቸውን ለማቆም የሚታገሉና አሽከርካሪውን የሚያነቁ ዘመናዊ መኪኖች አሉ፡፡ እነዚህን መኪኖች በኢትዮጵያ የብዙኃን ትራንስፖርት ለመጠም ስዊድን የምታደርገው ነገር ይኖራል?

አቶ ሙራድ፡- ይህ የስዊድን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስካኒያዎች በዚህ የተካኑ ናቸው፡፡ መኪናው በራሱ አደጋ እንዳያደርስ እየሠሩ ነው፡፡ ከፊቱ ያለውን በሙሉ እንዲረዳ፣ እንዲያውቅና ራሱ ዕርምጃ እንዲወስድ ከሌሎች የአይቲ ለምሳሌ ከኤሪክሰን ጋር በመተባበር እየሠሩ ነው፡፡ ኤሪክሰንና ስካኒያ በጥምረት የፈጠሩት ቴክኖሎጂ አደጋ ሊያጋጥም ሲል መኪናው በራሱ እንዲያቆም የሚያደርግ ነው፡፡ በስዊድን ቮልቮና ስካኒያ አደጋ ሊያጋጥም ሲል በራሳቸው የሚቆሙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይኼንን መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ የመሸጥ ዕድል አለ፡፡ ይህ ለምን አይደረግም? እያልን እየጠየቀን ነው፡፡ በእርግጥ የታክስ ጉዳይ አለ፡፡ ሆኖም እንደዚህ ዓይነት መኪኖችን ቢያንስ ለብዙኃን ትራንስፖርትና ረዥም ርቀት ለሚጓዙት መጠቀም እንደሚቻል መረጃውን እየሰጠን ነው፡፡ በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ኃላፊነትም በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ ቀንሶ ሞትና አካል ጉዳት እንዲቀር ልምድ መለዋወጥና መረጃ መስጠት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር ከጊዜ መለዋወጥ ጋር የሚሄዱ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምን እንመክራለን፡፡ ከሰው ሕይወት አንፃር ሲታይ ደግሞ ቴክኖሎጂው ውድ ሊባል አይችልም፡፡ ስዊድናውያን በአገራቸው ቅድሚያ የሰጡት የሰው ሕይወት ማዳንን ነው፡፡ ለዚህም በቴክኖሎጂ የታገዘና ውድም ቢሆን ለረዥም ጊዜ በማገልገል ዋጋውን የሚመስል መኪና መጠቀመም ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ የመኪኖቹ ረዥም ዕድሜ መቆየትም የትራንስፖርት ዘርፉን ዘላቂ ያደርገዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...