ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በ2010 ዓ.ም. ጠቅላላ ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር እንደቻለና ከግብር በፊትም 427.2 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታወቀ፡፡
የባንኩ የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ጠቅላላ ገቢውን በ50 በመቶ በማሳደግ 1.39 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን በላይ በማሻገሩ፣ ዓመታዊ ገበያቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር ካደረሱ የግል ባንኮች ጥቂት ባንኮች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ የባንኩ ገቢ በ2009 ዓ.ም. ከተመዘገው በ464 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ከሒሳብ ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባንኩ ዓምና ያስመዘገበው አጠቃላይ የገቢ መጠን 928 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
በአንፃሩ የባንኩ ዓመታዊ ወጪም በእጅጉ ጨምሯል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የባንኩ ጠቅላላ ወጪ በ52.3 በመቶ አድጎ ወደ 965.2 ሚሊዮን ብር አሻቅቦ ነበር፡፡ ዓምና የባንኩ የወጪ መጠን 634 ሚሊዮን ብር እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ ከባንኩ ወጪዎች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ለተቀማጭ ገንዘብ የተከፈለው ወለድ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላው ወጪ ውስጥ የ40 በመቶውን ድርሻ ይዟል፡፡
ይህም ይባል እንጂ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ዕድገት ከፍ ማለቱ የባንኩን የትርፍ መጠን ከ2009 ዓ.ም. አንፃር በ45 በመቶ እንዳሳደገውና ከታክስ በፊትም 427.2 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማስመዝገብ እንዳስቻለው ተጠቅሷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ያስመዘገበው ትርፍ በ133 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠንም 311.6 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ ተቀናሽ በኋላ የተመዘገበው ትርፍ 236.8 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በተመለከተ በ2010 ዓ.ም. 9.15 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ጥበቡ እሸቴ (ኢንጂነር) በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ2009 ዓ.ም. አኳያ በ2.4 ቢሊዮን ብር ወይም በ32.4 በመቶ ነው ብልጫ ታይቶበታል፡፡ በ2009 መጨረሻ የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ 6.8 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
ባንኩ የሰጠው ብድርም በ32.3 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየና በ2010 መጨረሻም የብድር ክምችቱ ወደ 6.9 ቢሊዮን ብር ማደጉ ተመልክቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የባንኩ የብድር ክምችት 5.18 ቢሊዮን ብር የነበረ በመሆኑ፣ ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን በ32.3 በመቶ እንዳደገ ይጠቁማል፡፡ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለወጪና ለገቢ ንግድ የሰጠው ብድር መጠን ነው፡፡ ባንኩ ለወጪና ለገቢ ንግድ የሰጠው ብድር በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ 31 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ 2.16 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ይጠቁማል፡፡
ለወጪና ገቢ ንግዱ የሰጠው ብድር በ2009 ዓ.ም. ከነበረውም ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ባንኩ ለገቢና ወጪ ንግድ የሰጠው የብድር መጠን 840 ሚሊዮን ብር እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡ ከወጪና ከገቢ ንግድ ብድር በመከተል የኮንስትራክሽን ዘርፍ 23 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 15 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት መስክም የባንኩ ገቢ መጨመሩን ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡ ባንኩ 121 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህም በ23.3 በመቶ ጭማሪ የተመዘገበበት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 13 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከ2009 ዓ.ም. አኳያም የ32.3 በመቶ ዕድገት ታይቶበታል፡፡ ቡና ባንክ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ አሥረኛ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከስምንት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ድርሻ የያዙበት የግል ባንክ ነው፡፡ 171 ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ባንኩ ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ሲሆን፣ ለግንባታ ሥራው ባወጣው ጨረታ ሁለት የቻይና እንዲሁም አንድ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቡና ባንክ አዳዲስ የቦርድ አባላትን ለመምረጥ ባለአክሲዮኖች ባካሄዱት ምርጫ፣ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩና በዘንድሮው ምርጫ በድጋሚ ለመወዳደር ቀርበው የነበሩ የቦርድ አባላት ለመመረጥ የሚያስችል ድምፅ እንዳላገኙ ተሰምቷል፡፡