Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጂቡቲ የቱሪዝም ዘርፏን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መሥራት  አስታወቀች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን ለመሳብ ዝግጅት ጀምራለች

ከተለያዩ የዓለም አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ቆይታቸውን በሚያጠናቅቁበት ወቅት ጂቡቲ ተከታይዋ የማረፊያቸው አማራጭ መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ የጂቡቲ ብሔራዊ የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ይፋ እንዳደረገው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰት ከፍተኛ በመሆኑ ሁለቱ አገሮች አብረው በመሥራት ጎብኝዎች የጉዞና የጉብኝ ማዕቀፎቻቸው ውስጥ ጂቡቲንም ማካተት የሚቻልበት አሠራር እንዲዘረጋ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉን ለማቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ለጎብኚዎች የመረጃ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግልና በቱሪዝም ሥራ ለተሰማሩ የሁለቱ አገሮች ድርጅቶችን የሚያቀናጅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደሚከፈት ከጂቡቲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ይህንን ያስታወቁት የአገሪቱ ቱሪዝም ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኡስማን አብዲ ሞሐመድ ናቸው፡፡ በጂቡቲ ለአሥር ቀናት የሚቆየውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መክፈቱን አስመልክቶ ወደ ሥፍራው ከተጓዙት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ኃላፊው እንደጠቀሱት፣ ከኢትዮጵያ ጋር እየዘረጉ በሚገኙት ትስስሮች ውስጥ የቱሪዝም መስክ ላይ ትልቅ ተስፋ ተጥሏል፡፡

ምንም እንኳ ጂቡቲ ያሏት የቱሪስት መዳረሻዎች ከኢትዮጵያ አንፃር ሰፊና ትልቅ ባይሆኑም የውጭ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ማግኘት ያልቻሏቸውን አማራጭ የመዝናኛና የጉብኝት ሥፍራዎች ጂቡቲ ማቅረብ የሚቻልባቸው ዕድሎች እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡ ጂቡቲ የጉብኝታቸው መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቱሪዝም ተዋናዮች ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነቶች ማድረጋቸውንም አብራርተዋል፡፡

 እ.ኤ.አ. በ2018 ጂቡቲን የጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር 140,000 እንደሚደርስ የገለጹት ኃላፊው፣ የጎብኝዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ቱሪዝም ለጂቡቲ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ያለው ድርሻ ሦስት ከመቶ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በሚፈጠረው የተቀናጀ ሥራ፣ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የጎብኚዎችን ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ለማሳደግና አገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን የገቢ ድርሻ ወደ አምስት በመቶ ለማሳደግ አዲስ የቱሪዝም ፓኬጅ ተቀርጾ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል፡፡

ለዚሁ ሥራም የቱሪዝም ስትራቴጂክ ማስተር ፕላን መዘጋጀቱንና የአገሪቱ ካቢኔም በአንድ ወር ውስጥ እንደሚያፀድቀው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ማስተር ፕላኑ ወደ ሥራ ሲገባ የቱሪዝም ሀብታችንን አስፍተን በመጠቀም በአምስት ዓመታት ውስጥ ጂቡቲን ከዓለም አሥር የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ትኩረት ሰጥተን እንሠራበታለን፤›› ያሉት ሚስተር ኡስማን፣ ከኢትዮጵያ በኩል የሚመጡ ጉብኝዎችን ለመሳብ ከወዲሁ ዝግጅቶች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በቱሪዝም በኩል ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ባለቤትና ሊጎበኙ የሚችሉ በርካታ ቦታዎች ያሏት ነች፡፡ አንድ ቱሪስት በኢትዮጵያ ቢያንስ ሦስት ወይም አራት ቀናት ቆይቶ እግረ መንገዱን ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ወደ ጂቡቲ በመምጣት እንዲቆይ ለማድረግ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ የማይገኙ የባህር ዳርቻዎችንና አሳ ነባሪ፣ አንበሬዎችና የመሳሰሉትን የባህር ሀብቶች ጨምሮ የሚጎበኙ የመስህብ ሥፍራዎች በጂቡቲም እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

ከውጭ አገር ጎብኚዎች በተጨማሪ የኢትጵያውያን ጎብኚዎችም ቁጥር ለማሳደግ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም አቶ ኡስማን ገልጸዋል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ስለታሰበው ጉዳይ ሲያስረዱም፣ ሁለቱ አገሮች ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመግባት ከሚደረገው ጥረት ጋር እንደሚያያዝና ለኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችም ወደ ጂቡቲ በሚያቀኑበት ወቅት እንዲያሟሉ የሚጠየቋቸውን ነገሮች ለማቅለል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በጉዞ ወኪልና በአስጎብኚነት ከሚሠሩ አካላት ጋርም በቅብብሎሽ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ከሆነም፣ የሁለቱ አገሮች ባለድርሻዎች እ.ኤ.አ. በ2018 ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባና በጂቡቲ የጋራ ፎረም አዘጋጅተው ውይይት በማድረግ ወደፊትም በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በጂቡቲ በተደረገ ውይይትም፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የማስተር ፕላን ዝግጅትን ጨምሮ የመዳረሻ ቦታዎች ልማትና ሌሎችም ሥራዎች ላይ ድጋፍ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

የጂቡቲ መንግሥት ዕቅዱን ለማሳካት እንዲረዳው በመጪው ወር አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚከፈተው ቅርንጫፍ ቢሮ አማካይነት የጂቡቲን ቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡ በቅርንጫፍ ቢሮው የኢትዮጵያ ባለሀብቶችንና በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የሚመጡ የሌሎች አገሮች ኃላፊዎችንም በጂቡቲ ቱሪዝም ዘርፍ፣ በመዝናኛ ማዕከላትና በሌሎችም ተያያዥ መሠረት ልማቶች ግንባታ ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

ጂቡቲን ባለፉት ዓመታት ከሚጎበኙ የውጭ ዜጎች ውስጥ ቀዳሚው ሥፍራ የሚይዙት ፈረንሣዮች ናቸው፡፡ ተከታዩን ቁጥር የሚይዙት የቻይና፣ የኢትዮጵያና የመካከለኛው ምሥራቅ ጎብኝዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጎብኝዎቿን ቁጥር ለማሳደግ አገራቸው እንደምትሠራ የሚናገሩት ሚስተር ኡስማን፣ ኢትዮጵያውያንን ለመሳብ የጂቡቲ አስጎብኚ ድርጅቶችንና አስጎብኝ ባለሙያዎችን በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማሠልጠን መታሰቡንም ገልጸዋል፡፡ በሒደትም ሁለቱ አገሮች በሚያደርጉት ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች ያለ ውጭ ምንዛሪ ወደ ጂቡቲ መሄድ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በየራሳቸው የመገበያያ ገንዘብ ቢጠቀሙም፣ በኢትዮጵያ ብር ጂቡቲ ውስጥ ግብይት እንደሚካሄድም አመልክተዋል፡፡

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሌሞ ፊታሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ገንዘብ ጂቡቲ ውስጥ መደበኛ ባልሆነ መንገድም ቢሆን ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጎብኚዎች በመጠኑ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በጂቡቲ ተቋማትና በንግድ አውታሮች ውስጥ በኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ግብይት መፈጸም ባይቻልም፣ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ባላቸው የንግድና የኢኮኖሚ ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ ገንዘብ በጂቡቲ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ዝውውር እንዳለው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚ ውህደት ሲጠናከር ወደፊት ሁለቱ አገሮች በአንድ የገበያ ገንዘብ የንግድ ልውውጥ ማካሄድ የሚችሉበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን እንደሚችል ተስፋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች