[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነህ?
- እናንተማ ግራ ተጋብታችሁ እኛንም ግራ ታጋቡናላችሁ አይደል?
- እንዴት?
- ባለፈው የተሠራውን አላዩም እንዴ?
- ምን ተሠራ?
- እኛ ግን የእንጀራ ልጆች ነን ማለት ነው?
- ምንድነው የምታወራው?
- ለውጥ ላይ ነን አላላችሁም?
- ለእሱማ ጥርጥር የለውም፡፡
- ታዲያ ለውጡ ሁሉን አቀፍ ነው አልተባለም?
- በትክክል እንጂ፡፡
- ለምንድነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ላይ ያልተጠራነው?
- ያልተጠራችሁበት ምክንያት አለ፡፡
- የእንጀራ ልጆች ስለሆንን ነው?
- ባይሆን የእንጀራ ጋዜጠኞች ስለሆናችሁ ሊሆን ይችላል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በርካታ የሚዲያ ተቋማት ቅር ተሰኝተዋል፡፡
- ለምንድነው ቅር የሚሰኙት?
- እየተገለልን ነው ብለው ነዋ፡፡
- ስማ ሚዲያዎቹ የተመረጡት እኮ የተቀመጠላቸውን መሥፈርት ያሟሉት ብቻ ናቸው፡፡
- መሥፈርቱ ትክክል አይደለማ?
- ታዲያ በየሥርቻው ሚዲያ እያቋቋማችሁ ሁሉም ይጠራ ቢባል እንዴት ይሆናል?
- እንደ እሱ እያልኩ አይደለም፡፡
- ለመሆኑ አንተ የት ነው ምትሠራው?
- እኔማ በየኢንተርኔቱ ምናምን እጽፋለሁ፡፡
- ስለዚህ እንደ አንተ ዓይነቱ ተጠርቶ ፕሬስ ኮንፈረንሱ ስታዲዮም ይደረግ?
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በአሁኑ ወቅት ሲቲዝን ጆርናሊዝም እያላችሁ ሁሉም ሰው እንደ ጋዜጠኛ ያደርገዋል አይደል?
- እነሱ ይጠሩ ማለቴ አይደለም፡፡
- ስለዚህ አሁን የተወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- በቃ ዜና ሲጨርስ ሙዚቃ የሚያሳይ ጣቢያ የተምታታበት ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱ ትልቅ ቦታ ባይጠራ አይገርመኝም፡፡
- እ . . .
- አንዳንዶች ደግሞ ሰርቆ አደሮች ናቸው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የራሳቸው ዘገባ አይሠሩም፣ ዝም ብለው የሌሎቹን ሚዲያዎች ሥራ የራሳቸው አስመስለው ነው የሚለጥፉት፡፡
- እሱስ ልክ ነዎት፡፡
- ስለዚህ ሚዲያዎቹ የተመረጡበት መንገድ ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሚዲያ እኮ የሕዝብ ድምፅ ነው፡፡
- የተመረጡት እኮ የሕዝብ ድምፅ የሆኑት ናቸው፡፡
- ግን በርካቶች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡
- እሱ መብታቸው ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ነው ያለን፡፡
- ታዲያ ምን ላድርግልህ?
- የተለያዩ ሚዲያዎች ወክለውኝ ነው የመጣሁት፡፡
- ለምንድነው የተወከልከው?
- እነዚህ ሚዲያዎች መካተት ይፈልጋሉ፡፡
- ታዲያ ምን ልርዳህ?
- በእርስዎ በኩል ጉዳዩን እንዲጨርሱት ነዋ፡፡
- ለእኔ ጉዳዩን መጨረስ ቀላል ነው፡፡
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔም ግን ከእናንተ የምጠብቀው ነገር አለ፡፡
- ምንድን?
- ኮሚሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ሰሞኑን ተዳከምን አይደል ክቡር ሚኒስትር?
- በምኑ?
- በቃ የቢዝነስ ሐሳብም እያመጣን አይደለም፡፡
- የእኔ ጭንቅላት ቀን ከሌት አርፎ አያውቅም፡፡
- ግን ምን ሐሳብ አለዎት?
- ሰሞኑን ቲቪ ሳይ የመጣልኝ ሐሳብ አለ፡፡
- ንገሩኛ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከፍተኛ አመራሮቹን አላየሃቸውም?
- ምን ሆኑ?
- አለባበሳቸውን ተመልክተኸዋል?
- ያው ዘናጮች ናቸው፡፡
- እሱማ ይታወቃል፡፡
- ታዲያ አለባበሳቸው ሌላ ምን አለው?
- አላስተዋልከውም እንጂ በዓመት አንዴ የሚከበረው በዓል በየሳምንቱ እየተከበረ ነው፡፡
- የምን በዓል ነው?
- የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ነዋ፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በአንዱ ሳምንት የሰሜን ሸዋ በርኖስ ይለበሳል፣ ሌላው ሳምንት የራያ ባህላዊ ልብስ ይለበሳል፡፡
- ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላው ደግሞ የአክሱም ጽዮን የጵጵስና ልብስ ሲለብስ፣ ሌላው ደግሞ የአባ ገዳን ልብስ ይለብሳል፡፡
- ጥሩ ያስተውላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አየህ በፊት እነዚህ ልብሶችን የሚያስተዋውቁት ሞዴሎች ነበሩ፣ አሁን ግን ፖለቲከኞቻችን ጥሩ ሞዴሎች ሆነውልናል፡፡
- ሐሳብዎት እኮ ሁሌ ያስገርመኛል፡፡
- ስለዚህ አሁን ቢዝነሱ የአልባሳት ነው፡፡
- እሱማ ጋርመንት ላይ አተኮሮ የሚሠራ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አለን አይደል እንዴ?
- ስለዚህ ቀጣዩ አዋጭ የቢዝነስ ዘርፍ እሱ ነው፡፡
- ታዲያ ምን እያሉኝ ነው?
- ከአንድ አንድ የምንገባበት ቢዝነስ እሱ ነው፡፡
- ምን?
- ሽመና!
[ክቡር ሚኒስትር ዳያስፖራ ወዳጃቸው ጋ ይደውላሉ]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ምን እያደረጋችሁ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አደረግን?
- ያን ሁሉ ዲስኩር የት አደረሳችሁት?
- የምን ዲስኩር ነው?
- አገር ሰላም ነው አገራችሁ ግቡ ምናምን ያላችሁትን ነዋ፡፡
- አሁንም ጥሪ እያቀረብን እኮ ነው፡፡
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ዳስፖራው እኮ ጥሪውን አክብሮ መጥቶ ነበር፡፡
- ታዲያ ምን አጎደልን?
- አሁንም ሁሉም ተመልሶ እየወጣ ነው፡፡
- ለምን?
- ዲስኩር ወዲያ ሪያሊቲ ወዲህ ሆነበታ?
- አልገባኝም?
- በየዕለቱ የሚሰማው ወሬ አስፈሪ እኮ ነው፡፡
- የምን ወሬ ነው?
- አገሪቱ በየዕለቱ እየተሸነሸነች እኮ ነው፡፡
- ማን ነው የሚሸነሽናት?
- ክቡር ሚኒስትር ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ እያተኮርን ክልልነት በወረዳ ደረጃ መውረዱ አይቀርም፡፡
- እ . . .
- በየቦታው የሚሰማው ግጭት እኮ አስፈሪ ነው፡፡
- ለውጥ ሲኖር ግጭት ያለ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የእኔ ፍራቻ ሌላ ነው፡፡
- ምንድነው ፍራቻህ?
- ከለውጡ ያተረፍነው ግጭት ብቻ እንዳይሆን?
- እ . . .
- ክቡር ሚኒስትር እንደ ዩጎዝላቪያ እንዳንሆን ነው ፍራቻዬ፡፡
- ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዜጎች እኮ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሀብት ማፍራትና መኖር አልቻሉም፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- በየቦታው እኮ መሣሪያ ተያዘ፣ ቦምብ ፈነዳ ሲባል ነው የምንሰማው፡፡
- ስማ ይኼ እኮ በፊትም የነበረ ነው፡፡
- ታዲያ እንዴት አንሰማም ነበር?
- አሁን ሚዲያውን ስለከፋፍትነው ነው ወሬው ሁሉ ቶሎ የሚሰማው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ችግሩ አሳሳቢ ነው፡፡
- ስነግርህ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ችግሩ ይፈታል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፋብሪካዎች እየተዘጉ ነው እኮ፡፡
- እ . . .
- ይኼው ሠራተኞቻቸውን እየቀነሱ እኮ ነው፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ኢኮኖሚውም አሥጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡
- አንተ ግን ለምን ቀና ቀናውን አታስብም? ምን አሁን እናንተም አገር እንደዚሁ ዓይነት ችግር አለ አይደል?
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ ያለው ግን በጣም ትኩረት የሚሻ ነው፡፡
- ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩልህ ለአንድ ጉዳይ ነው፡፡
- ምን ፈለጉ ክቡር ሚኒስትር?
- ያው ገንዘብ እንድታስቀምጥልኝ ፈልጌ ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለምንድነው ገንዘብ አሜሪካ የሚያስቀምጡት?
- ምን ችግር አለው?
- ማለቴ ኢትዮጵያ ሰላም ነው ምናምን እያሉኝ አይደል እንዴ?
- ያው ለሕክምና ምናምን ካስፈለገኝ ብዬ እንጂ አብዛኛው ንብረቴ እኮ እዚህ ነው ያለው፡፡
- እንደዚያ ከሆነ እኮ በጣም ሀብታም ነዎት ማለት ነው፡፡
- እንዴት?
- አብዛኛውን ንብረትዎ ኢትዮጵያ ካለ በእኔ በኩል የላኩት ገንዘብ ራሱ የትየለሌ ነው እኮ፡፡
- እሱስ ሁሉም ሀብቱን ስለሚደብቅ ነው፡፡
- ታዲያ መቼ ነው የሚልኩት?
- እኔማ አሁኑኑ መላክ እችላለሁ፡፡
- በቃ ይላኩት፡፡
- ዋጋው እንደተለመደው ነው አይደል?
- ክቡር ሚኒስትር ትንሽ ጨምሯል፡፡
- ለምን?
- በቃ በሙስና ዘመቻው ምክንያት ሁሉም ሀብቱን እያሸሸ ስለሆነ ተመኑ ተቀይሯል፡፡
- ታዲያ በስንት ነው የምትቀይርልኝ?
- በ40!
[ክቡር ሚኒስትሩ ልጅ አስቸግሮ ትምህርት ቤት ተጠርጠው ከዳይሬክተሩ ጋር እያወሩ ነው]
- በጣም የሥራ ውጥረት እንዳለብኝ አታውቁም?
- እናውቃልን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ለምንድነው የምትጠሩኝ?
- ከምንም በላይ የልጅዎ ጉዳይ ያሳስብዎታል ብለን ነው፡፡
- እናቱ ነበር የምትመጣው አሁን ለጊዜው አገር ውስጥ ስለሌለች ነው፡፡
- ስላስቸገርንዎ እንግዲህ ይቅርታ፡፡
- በነገራችን ላይ ይኼን ሁሉ ገንዘብ እያስከፈላችሁን የረባ እንኳን መጫወቻ የላችሁም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እሱን ሌላ ጊዜ እናወራለን፡፡
- እንዴ ለመሆኑ ልጆቹ ምሳቸውን የት ነው የሚበሉት? ምንም ዓይነት ሼድ አላየሁም?
- የመጡት እኮ እሱን እንድናወራ አይደለም፡፡
- በዚያ ላይ በቂ የመኪና መቆሚያ እንኳን የላችሁም፡፡
- ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
- መናገር ስላለብኝ ነው፣ ጥበቃዎቹ እኮ በጣም ሽማግሌዎች ናቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከመጡበት አጀንዳ በጣም ዳይቨርት ያደረገ ነገር ነው የሚያወሩት፡፡
- ልጄ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ቤት መማሩ ያሳስበኛላ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ደግሞ ልጅዎ ለትምህርት ቤታችን ሥጋት ስለሆነ ልናባርረው ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ተማሪዎቹን ሱስ በማስለመድ፣ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ረብሻና ሁከት በማስነሳት የትምህርት ሥርዓቱን እያስተጓጎለ ነው፡፡
- አልገባኝም?
- ትምህርት ቤቱ ውስጥ የግሩፕ ፀብ በመቀስቀስ ለተማሪዎች ከፍተኛ ሥጋት ሆኗል፡፡
- የእኔ ልጅ ነው እንደዚህ የሚያደርገው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ የምለው ተማሪዎች ጥበብ የሚያገኙት እኮ ከትምህርት ቤት ነው፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የተማሪዎች የሥልጣኔ መገለጫም ትምህርት ቤት ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የትምህርት ቤታችሁ ችግር ሲቀረፍ የእኔም ልጅ ችግር ይቀረፋል፡፡
- አሁን አንድ ተረት አስታወሱኝ፡፡
- ምን የሚል ተረት?
- የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች!