Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የተጠረጠሩበትን ትክክለኛ የወንጀል ድርጊት አውቀው መከራከር እንዳልቻሉ ተናገሩ

የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የተጠረጠሩበትን ትክክለኛ የወንጀል ድርጊት አውቀው መከራከር እንዳልቻሉ ተናገሩ

ቀን:

‹‹ባልተጨበጠ የወንጀል ጥርጣሬ ታስረው ከፍርድ በፊት ቅጣት እንዲያወራርዱ እየተደረጉ ነው››

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች

‹‹ከፍርድ በፊት ታስረው ቅጣት እንዲያወራርዱ ሳይሆን ምርመራ እንዳያበላሹብን ነው››

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የምርመራ ሒደቱን በየቀጠሮው እያቀያየረ ስለሚቀርብ የተጠረጠሩበትን ትክክለኛ የወንጀል ድርጊት አውቀው መከራከር እንዳልቻሉ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በጠበቆቻቸው አቶ ዘረሰናይ ምሥግናና አቶ ሀብቶም ተከስተ አማካይነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንደተናገሩትና ቀደም ብለው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ እሳቸውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያበቃ የጥርጣሬ መነሻ የለውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መርማሪ ቡድኑ ለጥርጣሬ መነሻ ናቸው ብሎ ያቀረባቸው ድርጊቶች፣ እሳቸውን የማይመለከቱ መሆናቸውን በመግለጽ ተከራክረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው የ14 ቀናት የምርመራ ሒደት የሠራቸውንና ቀረኝ የሚለውን ምርመራ በመግለጽ 13 ገጽ ዝርዝር የሥራ ሒደት ያቀረበ ቢሆንም ተጠርጣሪው ተቃውመዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በየቀጠሮው የሚያቀርባቸው አዳዲስ የምርመራ ነጥቦች መሆናቸውን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ‹‹አንድ ነገር ካገኘሁ የሚከለክለኝ የለም›› በማለት በዚሁ ከቀጠለ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ማብቂያ እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ ይኼም ተጠርጣሪዎቹን ከፍርድ በፊት በማሰር ቅጣት እንዲያወራርዱ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የሕገ መንግሥቱንና የሕግ ድንጋጌዎችን መጣስ መሆኑንም አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከ14 ቀናት በፊት ያቀረበውን የምርመራ ሒደት ተከትሎ፣ ፍርድ ቤቱ ሰጥቶት የነበረው ትዕዛዝ ቀሩኝ ያላቸውን ምርመራዎች በአግባቡ ሠርቶ እንዲያቀርብ ቢሆንም፣ ቡድኑ ግን ትዕዛዝ የተቀበለበትን የምርመራ ሒደት ምን እንዳደረገው ሳይናገር ሌሎችና አዳዲስ ነጥቦችን ይዞ በመቅረብ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እየጠየቀ መሆኑን ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎ መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪው ተፈጽመዋል ያላቸውን የአውሮፕላኖች መጥፋት፣ የመርከብ ግዥ፣ ስፖንሰር ማድረግ፣ የተለያዩ ግዥዎችና ሌሎችም ድርጊቶች የምርመራ ውጤቶች ምን ላይ እንደደረሱ ለፍርድ ቤቱ ሳያሳውቅ፣ አዳዲስ የምርመራ ሒደቶችን ይዞ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው መርማሪ ቡድኑ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሳይሆን እንደፈለገ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹እኛ እንደ ባለሙያ ደንበኞቻችንን በምን ጉዳይ እንደተጠረጠሩ አውቀን ለማማከርና ለመከራከር አልቻልንም፤›› ሲሉ ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ‹‹ሠራሁት›› ብሎ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበው ዝርዝር ጉዳይ ‹‹የምርመራ ሥራ አይደለም›› ያሉት ጠበቆቹ፣ ለመንግሥት ተቋማት ደብዳቤ መጻፍ፣ ከመንግሥት ተቋማት ሰነድ መሰብሰብ፣ ሰነዶች ለትርጉም ቤት መስጠትና የተተረጎመ ሰነድ መሰብሰብ፣ የቢሮና የፖስተኛ ሥራ ከመሆን ባለፈ የመርማሪ ሥራ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪ ታስሮ ማስረጃ መሰብሰብ ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 17 ድንጋጌ በመተላለፍ ነፃነታቸውን ማሳጣትና ያለ ፍርድ ማሰር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምን ተመልክቶና የምርመራ ሒደቱን አቻችሎ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቅድ እንደሚችል እንዳልገባቸውም አክለዋል፡፡

ምርመራውን የሚመራውና በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዋና ዓቃቤ ሕጉ ለሕዝብ ይፋ በተደረገ መግለጫ እንደተነገረው፣ በሜቴክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ የተደረገው የምርመራ ሒደት ከደኅንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ጋር በጋራ የተሠራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በውስጥና በውጭ ኦዲተር ተረጋግጦና ከፋይናንስ ሕጎች አንፃር ተገናዝቦ የደረሰው ጉዳት መታወቁንና 37 ቢሊዮን ብር መሆኑን ማሳወቃቸውን ጠበቆቹ አስታውሰው፣ ደንበኞቻቸው ክስ ሲጠብቁ ፌዴራል ፖሊስ ጉዳዩን እንደ አዲስ ከሥር ለምን እንደጀመረው እንዳልገባቸውም ጠይቀዋል፡፡ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ከፍተኛ የመንግሥት ተቋም መሪ በሰጡት መግለጫ የምርመራው ሒደት መጠናቀቁን ለመላው ሕዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ አስሮ መመርመር ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 ድንጋጌም ሆነ ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 30 አንፃርም ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ሜቴክን በኃላፊነት ሲመሩ በቢሊዮን በሚቆጠር ብር ግዥ መፈጸማቸውንና ፋብሪካ መግዛታቸውን ሲገልጽ የከረመው መርማሪ ቡድኑ፣ እንደገና ፋብሪካ ግንባታ የሚልና ግራ የሚያጋባ የምርመራ ሒደት እያጣራ እንደሆነ ለፍርድ ቤት አስረድቶ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ ግራ የሚያጋባ መሆኑንም ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ፣ ‹‹‹ሜቴክ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ሲሠራ ቆይቷል ይላል፡፡ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለት የጠየቁት ጠበቆቹ፣ ‹‹የማስታወቂያ ሥራ መሥራትና ማኅበራዊ ግዳጁን አይወጣም ማለት ነው? ይኼንን የሚል ከሆነ ምርመራውን አጠናቋል ማለት ነው?›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ፍፁም የሺጥላና አቶ ዝናህብዙ ፀጋዬ የሜቴክ አባል ወይም ሠራተኛ አለመሆናቸው እየታወቀ፣ አባል እንደሆኑ የሚገልጽ ደብዳቤ በመጻፍና በአበል መልክ የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጣቸው መደረጉን በሚመለከት፣ ማስረጃ ለመስብሰብ መርማሪ ቡድኑ ለባንክና የተለያዩ ድርጅቶች ደብዳቤ እንደጻፈ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ጠበቆቹ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፣ ‹‹የሜቴክ አባል ወይም ሠራተኛ አለመሆናቸው እየታወቀ›› ብሎ ከደመደመ፣ ማስረጃ ለማግኘት ደብዳቤ መጻፍ ለምን አስፈለገ የሚል ነው፡፡ የምርመራው ቡድኑ እንደ ተቋም በእውነት ላይ የተመሠረተ ምርመራ በማድረግ ፍርድ ቤቱንም ያግዛል ተብሎ ስለሚገመት፣ ተገቢና አሳማኝ ያልሆነ የምርመራ ሒደት በማቅረብ ከቀጠለ የጊዜ ቀጠሮ ማብቂያ ሊኖረው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በመሰለውና በፈለገው መንገድ ምርመራውን መቀጠል የሚችል ቢሆንም፣ ሰዎችን አስሮ መሆን ስለሌለበት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ በመጠቆም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቹ ሌላው የተቃወሙትና ተገቢ ባልሆነ ጥርጣሬ ታስረዋል በማለት ክርክራቸውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት፣ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘውን በሚመለከት ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ ለመታሰር ያበቃቸው ወይም የተጠረጠሩት ወንጀል በኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ የጨረታ ሰነድ በማሻሻል በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል መሆኑን ጠበቆቹ አስታውሰዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ የታሰሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ወንድም ስለሆኑ ብቻ ለድርጊቱ ግዝፈት ለመስጠት እንጂ፣ ያን ያህል የከበደ ወንጀል ፈጽመው አለመሆኑ እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው ኃላፊ እንደመሆናቸው ፊርማ መፈረማቸው አግባብ መሆኑን፣ ነገር ግን የሚያስጠይቃቸውም ከሆነ ነፃነታቸው ተገፎና 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እየተጠየቀባቸው ታስረው ሳይሆን፣ በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚገኝን ሰነድ በኦዲት አረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ የግዥ ውል፣ የመንግሥት ዶክመንትና መግለጫ እየገለበጡና እያያያዙ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑንና የሕግ አግባብም እንደሌለው ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ አጽንኦት ሰጥቶ ሊመለከተው እንደሚገባ በማሳሰብ፣ ተጠርጣሪው የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የሠራውን ምርመራና የቀረውን የሥራ ዓይነት በ13 ገጽ ዘርዝሮ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረበው (ሪፖርተር ኅዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በዕለተ ረቡዕ ዕትሙ በዝርዝር ዘግቦታል) መከራከሪያ ሐሳብ ላይ፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የሰጡትን ምላሽ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ሜጀር ጄኔራል ክንፈንም ሆነ አቶ ኢሳያስን ማሰር ያስፈለገው ከፍርድ በፊት ቅጣት እንዲያወራርዱ ሳይሆን፣ ምርመራውን እንዳያበላሹበት መሆኑን በመግለጽ ምላሽ መስጠት የጀመረው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ በየቀጠሮው አዳዲስ የምርመራ ውጤቶችን ለፍርድ ቤት የሚያቀርበው የምርመራ ባህርይ ውጤት የሚያመጣው በመሆኑ ንደሆነ ገልጿል፡፡ ይኼ ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 22 (1) ድንጋጌ መሠረት የተፈቀደ መሆኑንም አክሏል፡፡ ምርመራውን በዘፈቀደና በማናለብኝነት ዝም ብሎ የሚሠራው ሳይሆን ለፍርድ ቤት በማቅረብ፣ በማሳወቅና በማስፈቀድ ከመሆኑ አንፃር ጠበቆች ያቀረቡት ተቃውሞ ተቀባይነት ስለሌለው ውቅድ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑም ሆነ የመንግሥት ዓላማ ተጠርጣሪዎችን ማሰር ሳይሆን ካላቸው ተሰሚነትና ከነበራቸው ሥልጣን አንፃር መረጃ እንዳያጠፉ፣ ምስክሮች እንዳያባብሉ፣ እንዳያስፈራሩና እነሱም ከአገር እንዳይወጡ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ኃላፊዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሙስና መሆኑ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በመገለጹ ምርመራው እንደተጠናቀቀ አድርጎ መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን የተናገረው መርማሪ ቡድኑ፣ መግለጫው ለሕዝብ የተነገረ ጥሬ ሀቅ እንጂ በጥልቀት ምርመራ የተሠራ መረጃና ማስረጃ ባለመሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ ያንን እንዳለ እንደማይወስድ ገልጿል፡፡ ተፈጽመዋል ተብሎ በዋና ዓቃቤ ሕጉ የተገለጸው ዝርዝር መረጃ በኦዲት፣ በባለሙያና በምስክሮች ተጣርቶ ወደ ማስረጃነት መቀየር እንዳለበትና ያንንም መርማሪ ቡድኑ እየሠራ መሆኑን አክሏል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሜቴክ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ሠርቷል የሚልበትን ምክንያት እንዳስረዳው ለመንግሥት ሳያሳውቅ፣ በጀት ሳይመደብለት፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ሳያወጣ ሆቴሎችንና ሕንፃዎችን ገዝቷል፡፡ ዓላማው ግን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም እንዲሠራ እንደነበርም አስታውሷል፡፡ የሆቴሎች ግዥ በመፈጸሙ ብቻ ወንጀል ሠርተዋል እንዳላስባላቸው የጠቆመው መርማሪ ቡድኑ፣ ባንክ 100 ሚሊዮን ብር የገመተውን ሪቬራ ሆቴል በ128 ሚሊዮን ብር እንዲገዛ ማድረጋቸው፣ የነበረበትን የባንክ 67 ሚሊዮን ብር ወለድ መክፈላቸውና የሆቴሉ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም መክፈል የሚገባቸውን 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሜቴክ እንዲከፍል ማድረጋቸው መሆኑንም በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡

ስፖንሰር ማድረግና ማኅበራዊ ግዴታን ሜቴክ መወጣት የለበትም ከሚል አንፃር እንዳልሆነ የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ የሥነ ጥበብ ሰዎች የሜቴክ አባል ወይም ሠራተኛ ሳይሆኑ ወ/ሮ ፍፁም የሺጥላ ለ30 ቀናት፣ አቶ ዝናህብዙ ፀጋዬ ደግሞ ለ20 ቀናት በአሜሪካ ቆይታ እንዲያደርጉ ‹‹አባል ናቸው›› ብሎ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብዳቤ መጻፉን አስረድቷል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች የሜቴክ አባል መሆን አለመሆናቸውን ማጣራት፣ ለማስታወቂያ ተብሎ ለፍፁም ኢንተርቴይመንት የተከፈለ 954,770 ብር የሚመለከት የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይኼንን እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንጂ ገና እያጣራው የሚገኘው 104 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርና የማስታወቂያ ክፍያ ማስረጃ ማግኘቱንም ጠቁሟል፡፡ ዝርዝር ማስረጃም ሆነ ጥቅል ማስረጃ ሲያቀርብ መቃወም ተገቢ አለመሆኑንም አስረድቷል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ ለሚዲያ ፍጆታ ለማዋል አጋኖ እንደሚያቀርብ የገለጹበት ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑንና ሊታረም እንደሚገባ ተናግሮ፣ በምርመራ የተገኘውን እንደሚያቀርብና ሕዝብም የማወቅ መብት ስላለው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተደራሽ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ኢሳያስ ሊያስጠረጥራቸው የቻለውን ዓብይ ምክንያትና ከሜጀር ጄኔራል ክንፈ ጋርም ሊያገናኛቸው የቻለውን ምክንያት እንዲያስረዳ ለመርማሪ ቡድኑ ትዕዛዝ ሰጥቶት አብራርቷል፡፡

አቶ ኢሳያስ የተጠረጠሩት በኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ በሶማሌ ክልልና በባሌ አካባቢ ለቴሌ ታወር ግንባታ ተከላ በ204,981,630 ብር ውል ከተፈራረሙ በኋላ፣ ውሉን ያለማንም ዕውቅና ሥልጣናቸውን በመጠቀም ገንዘቡን ወደ 321,710,424 ብር ከፍ በማድረግና ያለ ምንም ጨረታ ከወንድማቸው ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ የተከላ ሥራውን ለሜቴክ በመስጠታቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ ኮንትራቱን ያሻሻሉት ቀደም ብሎ የተደረገው ውል አንድ ዓመት ከተሠራ በኋላና በነበሩ 260 ሳይቶች ላይ 18 ሳይቶች በመጨመርም መሆኑን አክሏል፡፡ ሥራው ሳይጠናቀቅም አቶ ኢሳያስ 322,628,124 ብር ለሜቴክ እንዲከፈለው ለፋይናንስ ክፍል በመጻፍ ክፍያው እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡ ውሉን ያለ ሥልጣናቸው አሻሽለው በመፈረማቸውና ክፍያ እንዲፈጸም በማድረጋቸው በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ተናግሯል፡፡ የወንጀሉ ዓይነት ሙስናና አንድ ዓይነት በመሆኑ፣ የምርመራ መዝገቡ ተጣምሮ ሊቀርብ መቻሉንም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና በመሀልም የማጣሪያ ጥያቄ እያቀረበ ካከራከረ በኋላ፣ የምርመራ መዝገቡን በአዳር በማስቀረብና በመመልከት ብይን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ በርካታ የምርመራ ሥራዎችን መሥራቱን ከምርመራ መዝገቡ መረዳቱን ገልጾ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኛው ላይ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ፣ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት ፈቅዷል፡፡ ለታኅሳስ 8 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ የተቀጠሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ሐሺም ቶፊቅ (ዶ/ር) ባለቤት ወ/ሮ ዊዳት አህመድ፣ በ60,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ወ/ሮ ዊዳት ተጠርጥረው የታሰሩት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉትን ባለቤታቸውን ፓስፖርት ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶችን ከመኖሪያ ቤታቸው አሽሽተዋል ተብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም ሁለት ሽጉጦች ማሸሻቸውንና ባለቤታቸውም ወደ መቀሌ እንዲሄዱ አስደርገዋል የሚል ጥርጣሬም ቀርቦባቸው ነበር፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ ሲያቀርባቸው ለፍርድ ቤቱና ተጠርጣሪዋ ከገቢያቸው በላይ የሚገመት በወር 10,000 ብር የሚከራይ ቤት እንዳላቸውና ሌላም ንብረት እንዳላቸው በመግለጽ እያጣራ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ አሳማኝ የሆነ ምርመራ እንዳላደረገና እንዳላመነበት በመግለጽ፣ ግለሰቧ በዋስ እንዲወጡ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ወርኃዊ ገቢያቸው ተጠይቆም ከ90,000 ብር በላይ መሆኑን በመናገራቸው በ60,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዷል፡፡

ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተለያዩ መዝናኛ ፕሮግራሞች አስተዋዋቂ የነበሩት ወ/ሮ ፍፁም የሺጥላ፣ ከኅብረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ (ያልተያዘ) ጋር ግንኙነት አላት ተብላ የታሰረችው ወ/ሪት ትዕግሥት ታደሰና በድለላ ሥራ ተሰማርቷል የተባለውና ከአንድ የቻይና ኩባንያ ሜቴክ ትራክተሮችን እንዲገዛ አድርጓል በማለት የተጠረጠረው አቶ ቸርነት ዳናም ቀርበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሰነዶች እያሰባሰበ መሆኑን ጠቅሶ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቆባቸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግን በጠበቆቻቸው አማካይነት ተቃውመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በየቀጠሮው ተመሳሳይ ነገር እያቀረበ ስለሆነና ሰነድ የሚሰበስበውም ከመንግሥት ተቋማት በመሆኑ፣ እነሱን ማሰር ተገቢ ባለመሆኑ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን ተቃውሞ በማለፍ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...