Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ መስፋት እንጂ መጥበብ አይሆንላትም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

‹‹ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ መስፋት እንጂ መጥበብ አይሆንላትም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ተማሪዎችን ዓርብ ኅዳር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ አግኝተው ባወያዩበት ወቅት፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የተሻለች ስለምትሆን የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች የተለየ ፈተና ይዞ ለሚመጣው ጊዜ ካሁኑ የአመራር ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳሰቡ፡፡ አሁን እሳቸውን የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያን የመሩ ነገሥታት እንዳልገጠሟቸው በማስታወስ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያ ሀብታም ስትሆን የሚኖረው ራሱን የቻለ ፈተና እነሱን እንደሚጠብቃቸው በመናገር ተዘጋጁ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ካሁን ቀደም መንግሥት ብቻ ይናገር የነበረውን ልምድ በማስቀረት፣ ሁሉም ሰው ያለውን መረጃ እንዲያጋራና የሚሰማውን እንዲናገር ስላደረገው እሳቸው የተለየ ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን በማስረዳት፣ አሁን ያለው መንግሥት የሚያተኩረው ዴሞክራሲን ማስፋትና ተቋማትን መገንባት ላይ ነው ብለዋል፡፡

‹‹እናንተ ደግሞ እነዚህን ተቋማት ተጠቅማችሁ የተሻለ ለመሥራት የምትጥሩበት ይሁን፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ እድሳቷ ተጠናቅቆ ውብ የሆነች አገር ለእናንተ እንደምናስረክብ በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ፤›› ሲሉም ለተማሪዎቹ ተስፋ ሰጥተዋል፡፡

‹‹አሁን በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ግጭቶችንና የተለያዩ የፀጥታ ችግሮችን በተመለተ ለዕድሜያችሁ የማይመጥን ቢሆንም በዜና ትሰማላችሁ፡፡ ነገር ግን በእድሳት ላይ ያለች አገር ባህርይ ነውና ተስፋ አትቁረጡ፤›› ሲሉም መክረዋል፡፡ አሁን በአገሪቱ የሚታዩ ችግሮችንም እሳቸው ራሳቸው ዲዛይን አድርገው ካሠሩት የቤተ መንግሥቱ ዕድሳት ጋር አመሳስለው ሲናገሩ፣ ‹‹የእኛ ቢሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነትና ክብር ማሳየት አለበት ብለን እያደስን ነበር፡፡ የመጀመርያው ሥራ የነበረው ማፍረስ ነው፡፡ አቧራውና ጩኸቱ ይረብሽ ነበር፡፡ ምንድነው አያበቃም ወይ ዕድሳቱ፣ ጩኸቱ፣ አቧራው… ሲባል ነበር፡፡ ይህ አብቅቶ ሲታይ ደግሞ ጥሩ ነው፤›› እንደተባለ፣ ከዚያም ቀለም መቀባት ሲጀመር ደግሞ ሽታው እንዳስቸገረ ተናግረው፣ ‹‹መቆሸሽ ያሸሻል፤ ይኼ ግን ጠቅልሎ ለመሻሻል ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የቤት መፍረስ ድምፅ መስማት፣ እዚህም እዚያም ጩኸት መስማትና ማየት ለእኛ በእጅጉ ያበረታናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ሳይኖር ሲቀር የመዘናጋትና የመተኛት ሁኔታ ስለሚያጋጥም፣ ተግዳሮቱ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ይበልጥ ጠንክረን ሕልማችንን እንድናሳካ የማያስችለን፣ እንድንተኛ የሚያደርገን፣ ኅብረታችንን የሚያጠናክር፣ መልካም ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች ከዚህም ከዚያም የማያሰባስብ ስለሆነ ከእንግዲህ በኋላ አሁን የምትሰሙት ረብሻ፣ አሁን የምትሰሙት ጥላቻ ቀጥሎ ኢትዮጵያን ያጠባል፣ ያሳንሳል የሚል ሐሳብ በእናንተ ውስጥ እንዳይፀነስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ በኋላ መስፋት እንጂ መጥበብ አይሆንላትም፣ አይገባትም፤›› ሲሉም ተማሪዎቹን አነቃቅተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ከግል አስተሳሰብና ሐሳብ ይልቅ የሌሎችን ሐሳብ በቡድን እየተቀበሉ የሚያስተጋቡ ሰዎች እንደበዙ ገልጸው፣ ‹‹ይኼንን ይዘን አንቀጥልም፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለውም፣ ‹‹የምናሸጋግራችሁ ነፃ ሰዎች በጭንቅላታቸው የሚያስቡባት፣ የለፋ የሚያድግባት፣ የሠራና የተጋ የሚሻሻልባት፣ ጠንክሮ የተማረ ሳይንቲስት፣ ዶክተር የሚሆንባት፣ የሰነፈ በብሔሩ ምክንያት፣ በእምነቱ ምክንያት፣ በቤተሰቡ ምክንያት፣ በጎሳው ምክንያት የሚያገኘው አንዳች የሌለባት ኢትዮጵያ ትሆናለች፡፡ ከየትኛውም ብሔር ብትሆኑ ጠንክራችሁ ካልተማራችሁ፣ ካልለፋችሁ፣ ካልደከማችሁ በብሔራችሁ ምክንያት፣ በጎሳችሁ ምክንያት ወይም በእምነታችሁ ምክንያት የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ትርፍ እያንዳንዱ ጥሮ፣ ያለውን አቅም አስተባብሮና ተደምሮ ኢትዮጵያን ከፍ ሲያደርጋት ብቻ ነው፤›› ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ተማሪዎቹ ሌብነትን እንዲጠሉና አሁን ካሉት መሪዎች የተሻለ ማንነት ለመፍጠር ዛሬን ሳያበላሹ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳር ላይ ቁጭ ብለው ከተማሪዎቹ ጋር ፎቶ የተነሱ ሲሆን፣ ተማሪዎቹም የታደሰውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ጎብኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...