Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አበባን የሚያዘምን ፕሮጀክት እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባን የሚያዘምን ፕሮጀክት እየተዘጋጀ ነው

ቀን:

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መዳረሻ በመሆኗ ምክንያት የአፍሪካ መዲና በመባል የምትታወቀውን አዲስ አበባ፣ በእጅጉ ያዘምናል የተባለ ፕሮጀክት ቀረፃ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እጅግ አስደናቂ›› በመባል የተወደሰ ፕሮጀክት፣ በተለይ ለቱሪስቶችና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነች አዲስ አበባን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ከሚሆኑት መካከል የሽቦ ገመድ ባቡር እንደሚገኝበት የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ ይህም ሰዎችን ከሱሉልታ መውጫ ከሚገኘው የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በመነሳት እስከ የካ አባዶ የሚያዘዋውር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ሙዚየሞች፣ ፓርኮችና የወንዞች ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በወንዞች ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተነስተው ወደሚዘጋጅላቸው መኖሪያ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ወንዞችን በመንከባከብ ዙሪያቸው ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች መዝናኛ እንዲሆኑ መታቀዱም ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ በተናጠል ከተተገበሩ ፕሮጀክቶች ግዙፉ እንደሚሆን የሚጠበቀው ፕሮጀክት ቀረፃ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችን ሲያገኙ ቶሎ ቶሎ ሥሩ እያሉ የሚጎተጉቱ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን በቤተ መንግሥት ካወያዩ በኋላ፣ በሥፍራው ያገኟቸውን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ነብዩ ባዬን ተመሳሳይ ጉትጎታ አድርገውባቸዋል፡፡

ይሁንና ፕሮጀክቱ ተቀርፆ ባለማለቁ ምን ያህል ገንዘብ ሊያስወጣ እንደሚችል መናገር እንደማይቻል ምንጮች አክለዋል፡፡

በቅርቡ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ ለገሃር አካባቢ የሚገነባውን የመገበያያ፣ የመኖሪያና የሆቴል መንደር ላገኘችው አዲስ አበባ፣ ይኼኛው ፕሮጀክት አዲስና ትልቅ ጭማሪ ይሆንላታል ተብሏል፡፡ የለገሃሩ ፕሮጀክት ኤግል ሂልስ በተባለ ኩባንያ የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ዲዛይን ያደረጉት የታላቁ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዕድሳት በሁለት ወራት ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ መንግሥት ምንም ወጪ ሳያወጣበት ዕድሳቱ እንደተከናወነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዕድሳቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቋራጮችን ቀጥረው በመላክ ጭምር አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችም በሙያና በተለያዩ መንገዶች  እገዛ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡

ከዚህ ዕድሳት ጋር አብሮ እየተገነባ የሚገኘው የቤተ መንግሥት ፓርክና ሙዚየም በመስከረም ወር ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ የእንስሳት ፓርኩ 260 የሚሆኑ የዱር እንስሳትን የሚይዝ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...