የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ከቀናቶች በፊት በማዕከላዊ ኮሚቴው ላይ ያካሄደውን ከፍተኛ ሹም ሽር ተከትሎ፣ የክልሉ ምክር ቤት ሰሞኑን ስብሰባውን በማካሄድ አዲስ ካቢኔ እንደሚመሠርት ታወቀ።
በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ምርጫ በቀዳሚነት እንደሚካሄድ፣ ከዚህም በኋላ የክልሉ መንግሥት አዲስ ርዕሰ መስተዳድር እንደሚመረጥ ታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ምርጫ ከተካሄደና ሹመቱም በክልሉ ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ፣ አዲስ ተሿሚው የክልሉ ፕሬዚዳንት ዳግም እንደ አዲስ ለሚመሠርቱት ካቢኔ የሚያቀርቧቸውን ዕጩዎች በመገምገም እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
ክልሉን የሚያስተዳድረው አብዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሦስት ቀናት በክልሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአብዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ ተገኝተው ባስተላለፋት መልዕክት፣ የክልሉ ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረው ለውጥ ጋር የሚጣጣም ለውጥ በድርጅቱና በክልሉ መንግሥት እንዲያካሂድ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበው ነበር።
ከቀናት በፊት በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ የተካሄደው የአብዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ የተደረሰውን ስምምነት መሠረት አድርጎ የተከናወነ ሲሆን፣ በዚህም ለረዥም ዓመታት በፓርቲና በክልሉ መንግሥት አመራርነት የቆዩ 72 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንና መካከለኛ አመራሮችን ከነበሩበት ኃላፊነት በማንሳት በክብር አሰናብቷል።
ከእነዚህም መካከል የአብዴፓ ሊቀመንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ሥዩም አወልና ሌሎች የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በክብር ተሰናብተዋል።
በተካሄደው የአብዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ፕሬዚዲየም ሰብሳቢ የነበሩት አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር እንደገለጹት፣ ከተሰናባቾቹ አመራሮች 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በአመራርነት ያገለገሉ፣ በ1992 አብዴፓ ሲመሠረትም አባል የነበሩና እስካሁንም በኃላፊነት እያገለገሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
በክብር ከተሰናበቱት አባላት የአብዴፓ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሥዩም አወል በተጨማሪ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ እስማኤል አሊሴሮ፣ አቶ ዑስማን አኒሳ፣ አቶ መሐመድ አላሌ፣ አቶ ኤልያስ ሀሰን እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩት አቶ ዓሊ አብደላ፣ አቶ መሐመድ አቡበከር፣ አቶ አሎ አፍኬኤ፣ አቶ መሐመድ ቦልኮ፣ ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ፣ አቶ ዑስማን መቅቡል፣ አቶ መሐመድ ያዩ፣ አቶ ዑስማን መሐመድ ከንዴ፣ አቶ ሙሳ ማህሙዳ በክብር ከተሰናበቱ አመራሮች መሀል ናቸው፡፡
በተጨማሪም የፓርቲው ኦዲት ኮሚሽን አባላት የነበሩት አቶ መሐመድ ጣሂሮ፣ አቶ እድሪስ ኪያርና አቶ አልዩ ሽፋ፣ እንዲሁም የፓርቲው መሥራች አባላት የነበሩት አቶ መሐመድ ቦልኮ፣ ወ/ሮ መዲና ማህሙድና አቶ አወል ወግሪስ ከፓርቲው በክብር ተሰናብተዋል።