Saturday, February 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ ከ500 ሺሕ በላይ የተበዝባዥ ሠራተኞች አቤቱታ ይድረስዎ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ ከ500 ሺሕ በላይ የተበዝባዥ ሠራተኞች አቤቱታ ይድረስዎ!

ቀን:

ለክቡርነትዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አቤቱታ የሚያቀርቡት ቁጥራቸው ከ500,000 በላይ የሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ቢሮዎችና የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች፣ የፌዴራል መንግሥት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶችና ኢንተርፕራይዞች፣ እንዲሁም የአንዳንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሹፌሮች፣ የእንግዳ ተቀባዮች፣ የጥበቃና የፅዳት፣ የአትክልት ሠራተኞች ተወካዮችና የቀድሞ ሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች የነበሩ ዜጎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል ቀጥረው ከሚያንቀሳቅሱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ኤለተክትሪክ ኃይልና ኤሌክሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥር የሚንቀሳቀሱ የውኃ ልማትና ሌሎችም ተጠሪ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎችም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትና የመንግሥት ፋብሪካዎች ማለትም፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥር የሚተዳደሩ ፋብሪካዎችና መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት ሆቴሎችና በአገሪቱ ያሉ የመንግሥት ሆስፒታሎች የአደስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋክሊቲን ጨምሮ እንደ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሳሰሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን የመሳሰሉ በርካታ የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎችና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በአጠቃላይ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዘመቻ መልክ የጥበቃ፣ የፅዳት፣ የአትክልት ክብካቤ ሠራተኞችን ሹፌሮችን ጨምሮ ለቁጥጥር አላመቸም በሚል ሰንካላ ሰበብ የሠራተኛ ማኅበራትን በማፈራረስ ከ500,000 በላይ የሰው ኃይል በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሰናበቱ ተደርገዋል፡፡

በጡረታ የተሰናበቱ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩ ሦስት ግለሰቦች ከኮሚሽነርነት ያነሰ ማዕረግ ያላቸው የቀድሞ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከፍተኛ የወታደር ማዕረገኞች የነበሩ ሰዎች፣ ለጥበቃና ለሌላውም የሥራ ዘርፍ የሰው ኃይል አቅራቢ ኤጀንሲዎችን በመክፈት ሲሠሩ ያን ሁሉ የመንግሥት ሠራተኛ ግልጽነት በጎደለው ጨረታ በግፍ እንዲከፋፈሉት ተደርጓል፡፡

ሠራተኛው መንግሥትን ቢሆንም የሚያገለግለው፣ በመንግሥትና በሠራተኛው መካከል እነዚህ ኤጀንሲዎች ጣልቃ እንዲገቡ ተደርጎ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የማይቋረጥ ቋሚ ኮሚሽን እየቆረጡ ኪሳቸውን በሰው ላብ አደልበው አሁንም ድረስ ይሠራሉ፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች ሲያተርፉ ይሰጡን የነበረውን ቦነስ ‹ድርጅቱን ብታገለግሉም እናንተ በሰው ኃይል አቅራቢ ድርጅት በኩል የመጣችሁ በመሆናችሁ አይመለከታችሁም› እየተባልን ጥቅማቸው ወደ ከበርቴዎቹ መኮንኖች እንዲገባ ተደርጓል፡፡

 በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ መሠረት የደንብ ልብስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጥ የነበረበት አግባብ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ ድርጅቶቹ ለዚህ የሰው ኃይልና የሥራ መደብ ያወጡት የነበረው በጀት ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ ሆኖም ገንዘቡ ወደ አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ሥራው ለዚህ ድርጅቶች ለምን ተሰጠ ቢባል ወጪ ለመቀነስ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀረና ወጪው በእጥፍ አደገ፡፡ ዓላማው ያልሠሩበትን ሀብት ለሚፈልጉ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ማዘዋወር ነው፡፡ በአንድ ሰው በወር ሳይወጡ ሳይወርዱ እስከ ሁለት ሺሕ ብር ያገኛሉ፡፡ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞች በወር ስንት ሚሊዮን ብሮች እንደሚያጋብሱ ማሰብ ነው፡፡ ሕጋዊ የዘረፋ መንገድ ተመቻችቶላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ በገዛ አገራችን ቅኝ እንገዛለን፡፡ ጉልበታችን ይበዘበዛል በማለት ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ተመላልሰን አመልክተናል፡፡ በመጀመርያ ጉዳያችንን በጥሩ ሁኔታ ይዘው ሥራው የግድ ለውጭ ቀጣሪ ድርጅቶች ይሰጥ ከተባለ እንኳ የሠራተኛውን ጥቅም ባከበረ መልኩ መሆን አለበት የሚሉ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ እንዲሁም በመንግሥት ፖሊሲ መሠረት ሠራተኛው ተደራጅቶ ራሱ ሊይዘው ይገባል የሚል ሐሳብ በመያዝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ደብዳቤዎችንም ጽፈውልን ነበር፡፡

ጉዳያችን እስከ ቀደምቱ ሚኒስትር ቢደርስም፣ በሒደት ግን እኛን የሚያገሉ ሰዎችን የተመለከቱና ጉዳያችን ያሳዘናቸው አንድ ቅን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ፣ ‹‹ዝም ብላችሁ ነው የምትለፉት›› ብለው ጉዳያችን እንዴት እንደተዳፈነ አረዱን፡፡ ለሕይወታችንም እንደሚያሠጋን አስጠነቀቁን፡፡ እንደተባለውም የፖሊስ ኮሚሽንና የመከላከያ ኔትወርካቸው በመጠቀም በሠራተኛው አስተባባሪዎች ላይ መቀጣጫ እንዲሆን ከባድ ድብደባና አካል የማጉደል ወንጀልን ጨምሮ እሥራትና ማፈን ሲመጣ የከፋውን በመፍራት ጉዳዩን ተውነው፡፡

ይኼውና ለ12 ዓመታት ሙሉ ዓይናችን እያየ ጉልበታችንም እንደባሪያ እየተበዘበዘ ደመወዛችንን እነዚህ የኮሚሽን ድርጅቶችና ባለቤቶቻቸው እየተካፈሉ ለራሳቸው በሕንፃ ላይ ሕንፃ እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ ሠራተኛው ግን ስንት ዓመት ካገለገለበት መሥሪያ ቤት ከቋሚ ሥራው ተነስቶ ‹ወደ ኤጀንሲ ግባና ሥራ፣ መሥሪያ ቤትህ ለኤንሲው ሰጥቶሃል፡፡ አገልግሎትህን ለእኛ ትሰጣለህ ደመወዝህንም ማንኛውም ነገር ከኤጀንሲው ጋር ጨርስ፤› እየተባለ በፊት ከሚያገኘውም አነስተኛ ደመወዝ እየተቀነሰበት መኖሩ በደም ብዛትና በስኳር እንዲያልቅ አደረገው፡፡ የቀረውም አሜን ብሎ በመቀበል የግፍና የዘረፋ ቀንበሩን ተሸክሞ ቀጥሏል፡፡

በአብዛኛው ዘርፉ የተማረውን የሰው ኃይል ስለማያሳትፍ፣ በደሉ ሰሚ አጥቶ ተድበስብሶ ቆይቷል፡፡ በሒደት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች ሥራ በማጣታቸው ምርጫ ስለሌለ በመስኩ ሲቀጠሩ ከሚሠሩበት መንግሥታዊ ተቋም በስማቸው የሚወጣውን የገንዘብ መጠንና የሚከፈላቸውን ገንዘብ በማስተያየት የመብት ጥያቄ ለሚሠሩበት የመንግሥት ተቋም ኃላፊዎች ማንሳት ይጀምራሉ፡፡ ነገር ግን ኤጀንሲውን ጠይቁ ይባላሉ፡፡ ኤጀንሲውን ሲጠይቁም ከሥራ ይባረራሉ፡፡ የኤጀንሲዎቹ ባለቤቶች ከፖሊስና ከመከላከያ ጋር ያላቸውን ኔትወርክ በመጠቀም የመብት ጥያቄዎችን በኃይልና በጉልበት እየተጠቀሙ ሠራተኛውን በማስደብደብና በማስፈራራት ያዳፍናሉ፡፡ የጉልበት ብዝበዛው የባርነት ያህል ነው፡፡ ጥቂቶች ባለሕንፃ እንዲሆኑ ሲባል ከእነቤተሰቦቻችን ከሚሊዮን በላይ በላባችን የምንኖር ዜጎች ደህይተናል፡፡ ተርበናል፡፡ ተሰቃይተናል፡፡

የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ በክልሉ ተነስቶ በነበረው የሕዝብ አመፅ የተስተጋባው አንደኛው ጉዳይ የወጣቶች ጥያቄ እንደሆነ አጢኖ የኤጀንሲዎቹ ተግባርም ብዝበዛ እንደሆነና በተቃውሞው ወቅትም ለፋብሪካዎች መቃጠልና መውደም ሠራተኛው የነበረበት ብሶት አስተዋፅኦ ማድረጉን በማጥናትና በማጣራት የኤጀንሲዎቹን ፈቃድ ሰርዟል፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ በሚገኙ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ሠራተኛው በቀጥታ በአሠሪዎቹ እየተቀጠረ በመሀል ገብተው ከሠራተኛው ቋሚ ኮሚሽን የሚቆርጡትን በዝባዦች እንዲወጡ በማድረግ፣ ሠራተኛው የላቡን እያገኘ የኢንዱስትሪ ሰላም ሰፍኗል፡፡

 በፌዴራልና በአዲስ አበባ እንዲሁም ከኦሮሚያ በስተቀር በሌሎች ክልሎች ሠራተኛው በከፍተኛ ደረጃ እየተበዘበዘ ይገኛል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የግልና የጋራ ንብረቶችም መውደም የለባቸውም ባሉት መሠረት ሠራተኞች ብሶት ገፋፍቷቸው ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እናዳይኬድ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይም ጉዳት እንዳይደርስ ዕርምጃ በመውሰድ የሥራና የኢንዱስትሪ ሰላሙን እንዲያስጠብቁ እንማፀናለን፡፡

እንዲሰጠን የምንፈልገው መፍትሔ

አገልግሎት እየሰጠን የምንገኘው ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደመሆኑ መጠን፣ በእኛና በመንግሥት መሀል እየገቡ የሰው ኃይል አቅራቢ ኤጀንሲ የሚባሉት ድርጅቶችና ባለቤቶቻቸው ብዝበዛና ምሬት አብዝተውብናል፡፡ ኤጀንሲዎች ከዚህ እንዲወጡና ወደ ቀድሞ የመንግሥት ሠራተኝነታችን እንድንመለስ እንዲያደርጉን፣ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም በቋሚም ሆነ በኮንትራት ሠራተኛ መቅጠር ሲፈልግ ማስታወቂያ አውጥቶ አወዳድሮ በቀጥታ ራሱ እንዲቀጥርና የሰው ኃይል አቅራቢ ኤጀንሲ በሚል ከሠራተኛው ደመወዝ ከወር ወር ከዓመት ዓመት ኮሚሽን በመቁረጥ በዝብዞ ሕዝብን ማስበዝበዝ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

የሕዝብን ቅሬታና አቤቱታ ለማስተናገድ ከእንግዲህ አንዱ ሠርቶ አንዱ ሠርቆ አይኖርም በማለት ለሕዝብ በሰጡት ተስፋ መሠረት፣ ቃልዎ ተራ ሽንገላ ተስፋውም የማይጨበጥ እንዳልሆነ ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሥራቸው ላሉት ለሁሉም የመንግሥት ተቋማት እንዲያውቁና እንዲያስተካክሉ ይደረግልን፡፡

ሠራተኛውን በቀጥታ በመቅጠር ወደ ቦታው እንዲመለሱ ጥብቅ መመርያ በመስጠት ለሕዝብ ያለዎትን ቀናዔነት እንዲያሳዩ በመላው ሠራተኛና በሚያስተዳድረው ቤተሰብ ስም እየጠየቅን፣ የኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለሠራተኞች መብትና ጥቅም ያሳየው መቆርቆርና ለአቤቱታዎች የሰጠው መፍትሔና ምላሽ የሌሎች ክልሎች የሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎችም በአርዓያነት እንዲያዩት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን ተሞክሮ እንዲያስፋፋ አቅጣጫ እንዲሰጠውና ተደጋጋሚ አቤቱታ ቀርቦለት መፍትሔ ያልሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጭራሹን አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ውስጥ በራሱ የሰው ኃይል ያከናውናቸው የነበሩትን የሥራ መደቦች፣ የገዛ ሠራተኛውን የትም በትኖ ሥራዎቹን በጥቅም ለተሳሰረው ኤጀንሲ በመስጠቱ ዕርምጃ እንዲወሰድበት እንጠይቃለን፡፡

(የ64 ተወካይ አቤቱታ አቅራቢዎች ስም ዝርዝርና ፊርማ ተያይዞ የቀረበበትና በግልባጭ ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ከተላከው ደብዳቤ ሪፖተርም ደርሶት እንዲህ አስነበበው)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

የፌዴራል መንግሥትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር...

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...