Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉለውጥና የሽግግር ፍትሕ የ1993 ‹‹ተሃድሶ›› እና የ1997 ጥፋቶችን ኢትዮጵያ ልትደጋግመው ዕድል የላትም

  ለውጥና የሽግግር ፍትሕ የ1993 ‹‹ተሃድሶ›› እና የ1997 ጥፋቶችን ኢትዮጵያ ልትደጋግመው ዕድል የላትም

  ቀን:

  በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

  ኢትዮጵያ በጣም አስቸጋሪ የሽግግር ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ሽግግር ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ብዥታ፣ ብዙ ጫፍ የረገጠ አመለካከትና ተግባር ያለበት ነው፡፡ ከምናወቀው ወደ የምናልመው የሚሄድ በመሆኑ፣ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዘህ ወቅት በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ሁለት መሠረታዊ አስተሳሰቦች ሲንፀባረቁ ይታያሉ፡፡ በሕዝቦቿ መሠረታዊ ጥንካሬ ተማምነው እንወጣዋለን ብለው በጨለማው መሀል ብርሃን እያዩ እሱን በማስፋት፣ አሁን ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንቀርፈዋለን ብለው ተረጋግተው አገራችንን ለመታደግ በተጨባጭ ተስፋ የሚታገሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል አገራችንንና ሕዝቦቿን እየወደዱም ቢሆን ልትፈራርስ በሚል ሥጋት ተሸብረው ሳያስቡ በከንቱ ስሜት እየዘላበዱ፣ ምፅዓትን (ስምንተኛው ሺሕ) የሚያቀላጥፉና በእሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ (Doomsday Delusions) ሰዎችም አሉ፡፡ በመሀል ምንም ሳያደርጉ ባልሆነ ተስፋ የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ፣ በጭንቀትና በሥጋት ጊዜያቸውን የሚያንከባልሉ አልታጡም፡፡ አሁን የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ያለፈውን ጥፋት በሽግግር ፍትሕ በማስመለስ፣ የኢትዮጵያን ብርሃን በማስፋት ዘለቂ ማድረግ ብቻ ነው የእኛ ምርጫ ነው፡፡

  የሽግግር ወቅት ፍትሕ ስንል

  የሽግግር ወቅት ፍትሕ ዓላማ ኅብረተሰባዊ ለውጥን ማምጣት ነው፡፡ ያለፈውን ዕዳ ከመዝጋት ባለፈ ለወደፊቱ ትርጉም የሚኖረውና መተግበር ያለበት በዚያ ምክንያት ነው፡፡ የኅብረተሰባዊ መሠረታዊ ለውጥ ተንታኞች የሽግግር ወቅት ፍትሕ የወደፊቱን ነው የሚያየው ይሉታል፡፡ ነገ የምንገነባውን ሥርዓት እያማተርን የዛሬውን በዚህ መንገድ የምንቃኝበት፣ ዛሬ ያለ ትናንት ስለሌለ ደግሞ የትናንቱንም የምንዳስስበት ነው፡፡ የትናንት የፍትሕ ዕጦት ነገ ለምንፈልገው ፍትሕ በሚያመቻች መንገድ መፍታት ይኖርብናል፡፡ ፍትሕ ስንል የግለሰቦችና የሕግ (Legalistic and Individualistic) ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሆኖ በሕግ የሚሠላ ነው፡፡

  በኢትዮጵያ መጀመሪያ ላይ በ1983 ዓ.ም. የሽግግር ቻርተር ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በመቀጠል በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መፅደቁ፣ ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረግ ጉዞ እንደ ጥሩ ተሞክሮ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታችን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን በላቀ ሁኔታ ያካተተና ከፍተኛ ተስፋ ያዘለ በመሆኑ፣ ችግሩ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጭ እንዳልሆነ አመላካች ነበር ማለት ይቻላል፡፡

  ሆኖም ገና ከመጀመርያው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች እየተተገበሩም፣ እየተሸረሸሩም መምጣታቸውና በተለይም በ1997 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረው እጅግ አነቃቂ የምርጫ ሒደት መደናቀፍ ወርቃማ ዕድል እንዳመለጠን ሊቆጠር ይችላል፡፡ በወቅቱ ተቃዋሚዎች የነበረባቸው ውስንነት እንዳለ ሆኖ፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እጅግ በመደናገጡ ያለ የሌለ ጨቋኝ ሕጐችን በተከታታይ በማውጣት፣ በተግባርም ቀደም  ሲል ከነበረው በባሰ ሁኔታ በመንቀሳቀሱ የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጥሰው፣ አገርና መንግሥት ገዥው ፓርቲ ብቻ የሚሆንበት ሥርዓት እንዲፈጠር አስቻለ፡፡ ችግሮቹ ለልማት ባሳየው ቁርጠኝነት ልክ ትኩረት ሰጥቶ ጥቂትም ቢሆን መሥራት ባለመቻሉ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የተፈጸመው እንዳይደገም ፍትሕ ለማረጋገጥ ያለን ምቹ ሁኔታና ፍትሕ ለጣሱ ያሉትን ተግዳሮቶች አንድ በአንድ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለለውጥ መሠለፍ ለፍትሕ ወሳኝ ነው

  ፀረ ዴሞክራሲንና ሙስናን ለመታገል የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተበጣጠሰ መንገድ ሲያደርጉት የነበረው ትግል በ2007 ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ፣ ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግጭት የተቀላቀለው ከፍተኛ ትግል ተካሄዶ ብዙ መስዋዕትነትም ተከፍሏል፡፡ ገዥው ግንባር ዕድሜውን ለማራዘም ከተሃድሶ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ፣ ይህም አልበቃ ብሎ ሌላ ስሙ በማይታወቅ ተሃድሶ ለወራት ከተገማገሙ በኋላ ያልተገመተ ለውጥ አምጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለውጥ የሚሹ ስለነበር ከጫፍ እስከ ጫፍ ደገፋት፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ፍትሕ ፍለጋ በመሆኑ የሕዝቦች ፍላጎት የሚያሳይ በመሆኑ፣ ብቁ አመራር ካገኘ ፍትሕ ተደላድሎ ዴሞክራሲያዊው ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

  የለውጥ ጅማሮ ለፍትሕ መሠረት ነው

  የእስረኞች መፈታት፣ በትጥቅ ትግል ተሠልፈው ለነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች በሰላም ለመታገል የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸቱ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ ገጾችና ብሎገሮች መለቀቅ፣ ለአፈና የሚያመቻቹ የነበሩት ሕጎች በመሻሻል ሒደት ላይ መሆናቸው፣ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም ግንኙነት፣ ወዘተ የአካታች ፖለቲካ ጅምር ናቸው፡፡ አካታች ፖለቲካ ስንል ብዙኃንነትን ማለትም የአስተሳሰብ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ ወዘተ በሁለም መስክ በተሟላ መንገድ የሚያስተናግድ ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅሞቻቸውንና ክብሮቻቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉዋቸው የተለያዩ ሐሳቦች በሰላማዊና የሕግ የበላይነት በተረጋገጠበት መንገድ ሲያንሸራሽሩ፣ የአገርና የመንግሥት ተቋማት (State and Government Institutions) ሲያመቻቹና ዜጎች በተለያዩ መንገድ ማለት በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበራት፣ ወዘተ ተደራጅተው የተለያዩ አማራጮች ቀምረው በዚህ መሠረት መንግሥት እየተመረጠ መሠረታዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች በቀጣይነት የሚረጋገጥበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው አካታች ፖለቲካ የሚባለው፡፡ ያለ አካታች ፖለቲካ ፍትሕ ሊኖር አይችልም፡፡

  ፍትሕ በምደባም ይንፀባረቃል

  በቅርቡ ሴቶች ወደሚገባቸው ሥልጣን መመደባቸው የለውጡ አንድ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ በመጀመርያው ሽግግር (1983-2010 ዓ.ም.) ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች በማወጅ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርምና በምደባ ለመስተካከል ቢሞከርም፣ በተለይም በከፍተኛው የሥልጣን እርከን ሒደቱ ቀርፋፋ ነበር፡፡ ከሚኒስትሮች ግማሾቹ ሴቶች መሆናቸው በራሱ እመርታ ቢሆንም፣ በቁልፍ ቦታዎች መመደባቸው በራሱ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የመጀመርያዋ ርዕሰ  ብሔር፣ የመጀመርያዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የመጀመርያዋ የመከላከያ ሚኒስትርና ሁሉምና ወሳኝ የሚባሉት የውስጥ ደኅንነት አጠቃልሎ የያዘ የሰላም ሚኒስትር ሴት መሆናቸው አካታች ፖለቲካ በምደባ ማለትም በፆታ፣ በሃይማኖት፣ ብሎም በብሔር ምን እንደሆነ ፍንተው ብሎ የሚያሳይ ነው፡፡ በቀውጢ ጊዜ ማንነታቸውን ያረጋገጡት የመጀመርያዋ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ሲሆኑማ፣ እጅግ የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን ለፍትሕም መሠረት ነው፡፡ ነገር ግን!!

  የመንጋ ፖለቲካ ድባብ ፍትሕን ድምጥማጡን ሊያጠፋው ይችላል

  ከላይ የተገለጹት አበረታች ሥራዎች ቢኖሩም፣ የመንጋ ፖለቲካ ድባብ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እያንዣበበ ነው፡፡ ለውጥ የፖለቲካ አጀንዳ ነው፡፡ እውነተኛ ለውጥ ከሆነ በአካታች ፖለቲካ ይመራል፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እስከሆነ ድረስ ለውጥ መደገፍ፣ መቃወም፣ ወዘተ መብት ነው፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እስከሆነ ድረስ ለውጥ ማደናቀፍም መብት ነው፡፡

  የለውጥ ኃይሎች ነን የሚሉ (በእውነትም በሐሰትም) ፀረ  ለውጥ ናቸው የሚሏቸውን የማሳደድና ተሸብረው እንዲኖሩ እያደረጉ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስኬቶች በመካድ፣ የነበሩትን መሠረታዊ ችግሮች ብቻ በማጉላትና የሁለም ችግሮች ምንጭ አንድ ድርጅትና ጥቂት ግለሰቦች እንደሆኑ አድርገው እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ መብት ዕውቅና አለመስጠት ነው የመንጋ ፖለቲካ፡፡ ‹‹ከኢሕአዴግ መንገድ ውጪ ሁሉም ጥፋት ነው›› የሚለው ፀረ  ዴሞክራሲ አስተሳሰብ፣ ‹‹ከለውጥ ውጪ ሁለም ጥፋት ነው›› የሚል ሌላ ፀረ ዴሞክራሲ መከተል ነው የመንጋ ፖለቲካ፡፡

  የአገር ተቋማት (State Institutions) ሁሉንም አመለካከቶች በእኩልነት ማስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ርዕሰ ብሔሩ የለውጥ ደጋፊ ነኝ ካሉ ወደ አንድ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወግነዋል ማለት ነው፡፡ ወንበሩ ላይ ቢቀመጡም በራሳቸው ፈቃድ ቅቡልነታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል ማለት ነው፡፡ የፖሊስ አዛዡ ሕግ ተላልፈዋል ሳይሆን ለውጥን ለመቀልበስ ሲሠሩ ነበር ብሎ በማስሚዲያ ከደነፋ፣ የመንግሥት ሚዲያዎች የሕዝቦችን መብቶች ማስተጋቢያ መሆናቸው ቀርቶ የጥቂት አለቆች የፖለቲካዊ አመለካከቶች ቀረርቶ ማሠራጫ ከሆኑና አንዱን ደግፎ ሌላውን ማግለል ሲጀመር የመንጋ ፖለቲካ በይፋ ዕውቅና አገኘ ማለት ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ በቀጣይ መሻሻል ቢኖርበትም፣ የፖለቲካዊ ለውጡ ደጋፊዎች ነን ማለት ከጀመረ በከፍተኛ ደረጃ ስንኮንነው የነበረው ‹‹የኢሕአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ነው›› የሚለውን ትቶ ‹‹የለውጥ ምሽግ ነው›› ሆነ ማለት ነው፡፡ የመንጋ ፖለቲካ ይፋዊና ተቋማዊ ዕውቅና ካገኘ የተያያዝነውን ለውጥ ገደል ግባ እንደ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፍትሕ አይታሰብም፡፡

  በገዥው ግንባር ያለው ልዩነት ለፍትሕ አደገኛ ነው

  ገዥው ግንባር በርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ አንድነት አይታይበትም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንከተልም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ይህ ካልሆነ አንገታችን ይቆረጣል የሚሉም አልታጡም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን በማጠናከር ለውጥ እናምጣ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በማፍረስ ለውጥ እናረጋግጣለን የሚሉም አሉ፡፡ ማፍረስና መገንባት የለውጥ ጊዜ ባህሪ ቢሆኑም፣ ገዥው ግንባር አንዱ አካል ለመገንባት ሲንቀሳቀስ ሌላ የሚያፈርስ ከሆነ ግን የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ አሕአዴግ የምን ስብስብ ነው? ስሙን ስለምን አልቀየረም?

  የሚታየው የርዕዮተ ዓለምና የፖለቱካ ልዩነት ወደ ንትርክና እልህ እያስገባ ነው፡፡ የፖለቲካ ማጥቃትና የፀረ ማጥቃት ምልልስ እየታዘብን ነው፡፡ ታክቲካዊ ዝምድና ያላቸው የሚመስሉም ግንኙነታቸው መቼ እንደሚበጠስ ስለማይታወቅ ሲፈነዳ አደገኛ ነው፡፡ በመሆኑም የተያዘው የፖለቲካ እልህና ብሽሽቅ ለፍትሕ እንቅፋት ነው፡፡ በግንባሩ ውስጥ ያሉ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እስካልተፈቱ ድረስ ፖለቲካዊ ጥቃት የሚከሰትበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡

  በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ላይ መወሰድ የተጀመረው ዕርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍርድ አቅርቦ መጠየቁ ጤናማ ኅብረተሰብ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የዚህ ጠቀሜታው ያለውን ሒሳብ አወራርዶ ለመዝጋት ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊቱ እንዳይደገም ከሚሰጠው ትምህርት አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡ በማንኛውም ወቅት ፍትሕን ማስፈን ኅብረተሰብን ከመገንባት አኳያ ከፍተኛ ትርጉም ቢኖረውም፣ በሽግግር ወቅት የሚካሄድ የፍትሕ ግንኙነትና ዳኝነት እጅግ የተለየ ትኩረት የሚፈልግ ነው፡፡

  የበደለው ሥርዓቱ ሲሆን የተበደሉት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተንገሸገሹት፣ በሙስና የተበዘበዙት ሰለባዎች እነሱ ናቸውና፡፡ ነገር ግን ሥለቱ በከፍተኛ ደረጃ የደረሰባቸውን ግለሰቦች ሰለባዎች ናቸው፡፡ ፍትሕ እነሱ የሚሳተፉበትና ዕንባቸውን በሚያብስ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ አጠቃላይ ለውጥ ማድረግ ለሕዝቦች መካሻ ቢሆንም፣ የሥርዓቱ ዋና ተዋንያን በሕግ የሚጠየቁበትና ሌላው በዕርቅ የሚፈታበት መንገድ መፈለጉ ተገቢ ነው፡፡ ሰብዓዊ ጥሰቱም ሆነ ሙስናም ቢሆን እስከ ቀበሌ የሚወርድ ነው፡፡ ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያሉትንም የሚያዳርስ በመሆኑ ሁሉንም ወደ ሕግ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የህሊና ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ በመቋቋም ላይ ያለው የሰላምና የዕርቅ ኮሚሽን ጥሩ መረማመጃ ሊሆን ይችላል፡፡

  ችግሩ የሥርዓቱ በመሆኑ ሥርዓቱ ጠቅላላው መቀየር (Overhaul) አለበት፡፡ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ባለመኖሩ ነው ይህ ሁሉ ግፍ የተፈጸመው፡፡ ገዥው ግንባርና እሱ የሚመራው መንግሥት በመጀመርያ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የወጡት አፋኝ ሕጐች የሥርዓቱ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ሕግ ማውጣት ራሱ ያስጠይቃል፡፡ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታወቅና የተደረገው ምዝበራ ፀሐይ የሞቀው በመሆኑ እያወቁ ዝም ያሉትም አብረው ስለወሰኑም ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ ስላልወሰኑም የላይኞቹን የመንግሥት አመራሮች በሙሉ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ በስኳር ፕሮጀክት ለምሳሌ 77 ቢሊዮን ብር የት እንደገባ አይታወቅም ተብሎ በይፋ ለተወካዮች ምክር ቤት ሲነገር ምክር ቤቱ ምን አደረገ? በዓቃቤ ሕግ ሪፖርት እንደተደረገው 37 ቢሊዮን የውጭ ግዥ ያለ ጨረታ ሲፈጸም ቦርዱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ወዘተ የት ነበሩ? የተቋማቱ ኃላፊዎች የነበሩት መጠየቅ ሲኖርባቸው፣ መመርያቸውና አሠራራቸው በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ እንደ ግለሰቡ የነበረው የአመራር ቦታ ሕገ መንግሥቱንና ሕጐችን በመጣስ የነበረው ሚና ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ባለሥልጣን ሆኖ የአቅሙን ያህል የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስናን ሲታገል የነበረ ዕውቅና የሚሰጠውም ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ከሥልጣን መውረድ ወግ ቢሆንም በአገራችን የልተለመደ በመሆኑ ብዙም አይታይም፡፡

  የሜቴክ ኃላፊዎች ሲታሰሩ የነበረው ሁኔታ የ1993 ዓ.ም. ‹‹ተሃድሶ››ን አስታወሰኝ፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ ከእነ ቤተሰቦቻቸው፣ አቶ ቢተው በላይ፣ አቶ አባተ ኪሾ፣ ወዘተ ሲታሰሩ (በሕዝቡ የሚታወቅ የሚጠረጠሩበት አልነበረም) የፍርድ ሒደቱም፣ ፍርዱም እስከ ምን ድረስ ተልካሻ እንደሆነ ዓይተናል፡፡ ‹‹አንጃዎች›› ከእህት ድርጅቶችና ከሥራ ሲባረሩ ሕግን በመጣስ ነበር፡፡ መገናኛ ብዙኃን የአሸናፊዎች ቱልቱላ ሆነው ሲያቅራሩና የሆኑ ጄኔራሎችም አካኪ ዘራፍ ሲሉ፣ ‹‹አንጃዎች›› የተከለከሉበት የመንጋ ፖለቲካ መሣሪያ የሆነበት ነበር፡፡ ጥቂት ጄኔራሎች ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳን ቤተ መንግሥት ድረስ ዘለቀው ለማስፈራራት ከጅለውም ነበር፡፡ አልተበገሩም እንጂ፡፡ የቂም በቀል ፓለቲካና ሕገወጥነት አንድ ላይ ነው የሚሄዱት፡፡ ከብአዴን በቀና ሦስቱም እህት ድርጅቶች ሕግ በመጣስ በ‹‹ተሃድሶው›› በዋናነት ሲፐወዙ ምቱ የበረታው ግን በሕወሓትና በአባላቱ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ትግራይን ለማዳከም አልተባለም፡፡

  ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ተጠርጥረው ሲታሰሩ በቀረበው ዶክመንተሪ ምክንያት የእልህ/የማጥቃት ፖለቲካ እንደገና ተጀመረ እንዴ እንድንል አድርጓል፡፡ ከሕግ ውጪ ተጠርጣሪ መሆናቸው ቀርቶ ወንጀለኛ ናቸው የሚያሰብል በመሆኑ፡፡ የታሰሩት የሜቴክ ኃላፊዎች ከተለያዩ ብሔረስቦች ቢሆንም፣ የሚበዙት ከትግራይ መሆናቸው ለምንድነው ከሜቴክ አመራሮች ብዙዎቹ ከትግራይ የሆኑት? መመዘኛው ምን ነበር? ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ በትግራይ ተወላጆች ላይ የተደረገ ጥቃት ተደርጐም እየተወሰደ ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. የተወሰደው ዕርምጃ የዘር ፖለቲካ አልተቀባም፡፡ በ2011 ዓ.ም. ግን ገና ከመጀመሩ ሌላ ትርጉም ተሰጠው፡፡ ለምን ይመስላችኋል? የሆነ ሆኖ በለውጥ ግዜ (Perception and Misperception) ትልቅ ቦታ አለው፡፡ በ27 ዓመታት የተሠሩት መልካም ነገሮች ሳይወሱ በነበሩት ጥፋቶች ብቻ እየደነፉ ወደ አንድ እህት ድርጅትና ወደ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ማዕከል ማድረግ ፖለቲካዊ ጥቃትን ሊያመለክት ይችላል፡፡ በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የነበሩ ‹‹ለጣፊም››፣ ‹‹ተለጣፊም›› ሁሉም ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ የመጠየቅ ሒደቱ በተጠናከረ መንገድ መቀጠል ቢኖረበትም ከፖለቲካ ጥላ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡

  ምን ይደረግ?

  የነገን እያየን፣ የዛሬን እየሠራን፣ የትናንቱን ሕጋዊና ገንቢ በሆነ መንገድ መፍታት ካለብን በመጀመሪያ የለውጡ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ የተሟላና ጥልቀት ያለው ፍኖተ ካርታ በዋናነት አካታች ፖለቲካን የሚያጠናክር፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትሕ በአጠቃላይ ሕዝቦችንና የፖለቲካ ኃይሎችን የሚያንቀሳቅስ ደረጃ (በድጋፍም በተቃውሞ) መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ያለዚህ ፍኖተ ካርታ ፍትሕ ሊጐድል ይችላል፡፡

  ባለፉት  27 ዓመታት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ምዝበራዎች ከወገንተኝነት በመፅዳት በሚገባ ተመዝግበው፣ ተሰድረውና ተደራጅተው ስፋቱንና ጥልቀቱን በዓውድ (Context) ማስቀመጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ አሰቃቂ ነገር መግለፅ ብቻ ሳይሆን፣ እዚህም እዚያም የሚፈፀሙ ስህተቶችን ሳይሆን፣ የሥርዓቱ ማሳያ የሚሆኑትን መመዝገብ የግድ ይላል፡፡ ያለፈውን ጊዜ ከአሁኑ ጋር የሚየገናኙ በጐ ነገሮች በተጓዳኝነት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ያለፈውን ጊዜ ሁሉ ጨለማና ቆሻሻ ብቻ አድርጐ ማቅረብ የወደፊት ጉዟችንን በጨለማና በቆሻሻ ላይ ተመሥርተን ማከናወን ስለሚያስቸግረን፣ መነሻ መሠረት እንዳያሳጣን ቢያንስ ቢያንስ በልማቱ ረገድ የተገኙትን የቀደሙ ስኬቶች ከአሁኑ ለውጥ ጋር የምናስተሳስርበት ገመድ ያስፈልጋል፡፡

  በገዥው ግንባር ውስጥ ያለው ከመጠን በላይ የተወጠረ ፖለቲካዊ ንትርክን በማርገብና የማጥቃትና የመልሶ የማጥቃት ፖለቲካችንን በማስወገድ ፍትሕ ከፖለቲካ የፀዳ ጉዞ እንዲኖረን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት (State Institutions) በሕግና በሕግ ብቻ የሚሠሩ እንጂ፣ ፖለቲካዊ ወገንተኛ እንዳይሆኑ መከላከል፣ ሲሳሳቱም በጊዜ ማረም፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰትም ሆነ በሙስና የተጠረጠሩ ተቋማትንም ሆነ ግለሰቦችን ወደ ፍትሕ በምናመጣበት ወቅት ከበቀል የፀዳ ሊያስተምር የሚችልና ሁሉንም የሚያዳርስ አሠራር መከተል የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ከሁሉም ከሁሉም በምንሰጠው ዳኝነት ምክንያት ፍትሕ የአሸናፊዎች ብቻ እንዳይሆን ላቅ ያለ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በመጨረሻም ዕውቁ ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ (ኦዴግ)  ‹‹ፖለቲካዊ ማሻሻል በኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ዕድሎችና ክፍተቶች›› በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ዓውደ ጥናት ፍትሕን በሚመለከት የተባለውን ጥቂት ላካፍላችሁ፡፡ There should be no explicit labeling of groups purely because of their membership in one set of aggregation or another. Particularly the implicit nor implicit accusation of any community should be eschewed with at most emphasis.)

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት (Peace and Security) የዶክትሬት ዕጩ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...