Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊነት

  ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊነት

  ቀን:

  በበረራ ቢያ

  ባለፈው ሁለተኛ ክፍል ጽሑፌ ‹‹በአገራችን የለውጥ ሒደት የሚታዩ ፈተናዎች መፍትሔዎቹ›› በሚል በመጀመርያ ክፍል ከቀረበው ጽሑፍ የቀጠለውን፣ ‹‹በዴሞክራሲ አተገባበር የሚታዩ ውዥንብሮች›› በሚል የቀረበውን ጽሑፍ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ዕትም የመጨረሻውና ሦስተኛው ተከታይ ጽሑፉን እንደሚከተለው እንይ፡፡ መልካም ንባብ፡፡ ባህል የአንድ ኅብረተሰብ ሥነ ጥበብና የዚሁ መግለጫ የሆነና የሰዎች የአንድ ሕዝብ ወይም ኅብረተሰብ ሐሳብ ልማዶች ማኅበራዊ ባህሪያት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለአጠቃላይ ለሰላም መስፈን በባህል ለውጥነት የሚገለጹት የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ አስፈላጊ ከሆኑት የዕድገት መመዘኛዎች ዋንኛዎቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማንኛውም የዓለም ሌሎች ሕዝቦች የራሱ የሆነ በጎ ባህል አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ወዳድ ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች እንኳ ቢኖሩ የውጭ ጠላት ሲያጋጥም በአንድነት ተረባርቦ የመመከት ትልቅ እሴት ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ለኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች ያለመበገር፣ በ1956 እና በ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ ጦርነትና ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም. የኤርትራ ጦርነት ያሳያቸው አኩሪ ድሎች ለዚህ በአብነት የሚነሱ ናቸው፡፡ በሃይማኖት ልዩነቶች በመቻቻል አብሮ በመኖር ለዓለም በአርዓያነት የሚጠቀስ ሕዝብም ነው፡፡

  ይሁን እንጂ እየተሸረሸሩ የመጡና የበለጠ ልንሠራባቸው የሚገቡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ውስንነቶች በርካታዎች ናቸው፡፡ የመስኩ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የሥነ ጽሑፍና የሥነ ጥበብ ሰዎች ከያኔዎች በተለያየ መንገድ ትኩረት ሰጥተው ይሠሩበታል ብዬ የማምንባቸውን በዚህ ረገድ የሚታዩትን መስተካከል የሚገቡን በአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አገሮችም የሚታዩ ጉድለቶች ጠቅለል ባለ መልኩ እንደሚከተለው ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡

  ግልጽነት ባህል ማነስና ድብቅ መሆን የአሉባልታዎች መብዛት፣ ጥርጣሬን ማብዛትና ደፍሮ ያለመወሰን፣ ይቅር ባይነትን፣ ምሕረት ማድረግን እንደሽንፈት፣ ውርደት መቁጠርና ልዩነቶችን በኃይል መፍታት ላይ ማተኮር፣ ምቀኝነት፣ ስግብግብነት፣ ራስወዳድነት፣ ግለኝነት፣ ማጭበርበር፣ ሌብነት፣ በአቋራጭ መክበር፣ ቂመኝነት፣ ተንኮለኝነት፣ መሰሪነት፣ ብቀላ፣ ጠልፎ መጣል፣ የግትርነት ባህሪያት፣ ሂስና ግለ ሂስ ወይም ስህተቶችን አምኖ ያለመቀበል፣ ሰጥቶ መቀበል ያለመፈለግና ችግሮችን በመደማመጥ በውይይት በመቻቻል ያለመፍታት፣ ምክንያታዊ ያለመሆን፣ በጭፍን መፈረጅና ማግለል፣ ኩርፊያ ብሶተኛነት፣ ኩራትና ጉረኝነት፣ ጀብደኝነት፣ ማንአለብኝነት፣ ጨለምተኝነት፣ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ፣ ስንፍና ለዘብተኝነት፣ አድርባይነት፣ ግድ የለሽነት፣ ለዘብተኝነት፣ ምንቸገረኝነትና በይሉንታ መታጠር፣ መዋሸት፣ በሐሰት መመስከር፣ ጨካኝነት የሰውን ሕይወት ለትንሽ ጥቅም ማጥፋት፣ ሕግን ያለማክበርና ያለመፍራት፣ ጉቦን መቀበልና መስጠትና የማይገባ ጥቅምን ለማግኘት ሲባል ጭምር ለሴቶች ዝቅተኛ አመለካከት መኖር የመሳሰሉት ናቸው፡፡

  እነዚህ ጉዳዮች የአገራችንን ዕድገት ቀፍድደው የያዙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የገጠሙንን መልካም አጋጣሚዎችንም በመጠቀም እነዚህን ባህሪያትና አመለካከቶች ለውጥ ላይ ጠንካራ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡ ከላይ በመጥቀስ ለመግለጽ የተሞከሩት መስተካከል የሚሹ አመለካከቶችና ጎጂ ባህሎች ሀቀኛና ብቁ መሪዎችን ኅብረተሰቡ እንዲያፈራ አያደርጉትም፡፡ ሁኔታዎች የኅብረተሰቡ ውጤት በሆኑት ከኅብረተሰቡ በሚወጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ በግል ክፍለ ኢኮኖሚ በሚሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች መንፀባረቃቸው የማይቀር ነው፡፡

  ቀደም ባለው ጊዜ ኅብረተሰቡ ምክንያታዊ በመሆን ሁኔታዎችን ገምግሞ አቋም ባለመያዝ፣ በአሉባልታና በሐሰተኛ ወሬ ላይ በመመርኮዝ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመፈረጅ የማግለልና ያልተገባውን የመደገፍ ባህሪያት ጎልተው ታይተዋል፡፡ በግልጽነትና በድፍረት ስህተቶች እንዲታረሙ ከማድረግ ማንሾካሾክና ማማት ነው የሚዘወተረው፡፡ በኅብረት ስህተቶች እንዲታረሙ መታገል እምብዛም ነው፡፡ በሚቋቋሙ የሙያና የወል መጠቀሚያ ማኅበራት ተሳትፎም ዝቅተኛ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በየኑሮ ሒደቱ ለመብቱ የሚታገለውንም እንደተጨቃጫቂ በመቁጠር ዝም ከማሰኘት ይልቅ የሞራል ድጋፍ በመስጠት ማበረታታትም ብዙ የተለመደ አይደለም፡፡

  ኅብረተሰቡ ብሶተኛና አኩራፊ ሆኖ ራሱን በማግለል እጁን አጣጥፎ የሚፈለገውን መብቱን ከገዥ ፓርቲ በስጦታ ለማግኘት መጠበቅም አለ፡፡ መብቱን በሥርዓቱ ከማስከበር ይልቅ በገንዘቡ በመግዛትና በአማላጅ በመለማመጥ ለማግኘት የማይገባውን ጥቅም በገንዘብ ኃይል ሕጉ እንዲጣስ አንዳንዶች በሚፈጽሙትም ተግባራት ጎጂ እንደነበሩ ዕውቅ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ሙሰኝነትን የሚቃወም የማይደግፍ ቢሆንም፣ በሙሰኝነት ሀብት ያፈራውን በመንቀፍና በማግለል ፋንታ በማሞገሥና በማክበር ድርጊቱ እንዲበረታታ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› በሚል ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴም ጠንካራም አልነበረም፡፡ ይህ በየአካባቢው የተለመደ የተወሰኑ ዕውቅና ያገኘ እየመሰለ ነው የቆየው፡፡ በቅርቡ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ኃላፊው ይቀርቡ የነበሩት በቀድሞ የኢሕአዴግ አመራር አካላት በጭካኔ የተሞላው በሕዝብ ላይ የደረሰው በደል ከዚሁ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከነበረው ጎጂ ባህሪ የመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡

  እነዚህ ባህሪያት ናቸው የበለጠውን በአገራችን እያጋጠመ ላለው የእርስ በርስ ግጭቶችና የዜጎች ሕይወት መጥፋት የአካል ጉዳት መድረስና የንብረት ውድመት የዳረጉት፡፡ ይህ የሚያሳየው ባለፉት ዓመታት ለደረሱት በርካታ በደሎች የኅብረተሰቡም የቆየ ልምድ አስተዋጽኦ ነበረው ማለት ነው፡፡ በግልጸኝነት ማጣት፣ በጥርጣሬ፣ በፍረጃና የጅምላ ፍርድ የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋት የሚደርሱ ጉዳቶች የመሳሰሉት የታዩት ክስተቶች የዚሁ ውጤት ናቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመር አስተሳሰብ አብዛኛውን እነዚህን የባህል ገጽታዎችን ለመለወጥ ይረዳል፡፡ በእርግጥ በዚህ ረገድ አሁንም በቅርቡ ብዙ ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ተከታታይነት ያላቸው ቅንጅታዊና ተቋማዊ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡ ምንም እንኳ እንደ ቻይና ደም የሚያፋስስ ዓይነት ሳይሆን፣ በባህላችን ላይ መለስተኛ አብዮትም ማካሄድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የኅብረተሰቡ ውጤት የሆነው አራተኛ መንግሥት የሚባለው የመገናኛ ብዙኃን ሁኔታም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ነው፡፡

  የመገናኛ ብዙኃን

  አንዳንድ የግል የብዙኃን መገናኛ አውታሮች በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው ተቃዋሚዎች ሲያደርጉ የነበረንን አካሄድ የመያዝ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ ሁሉንም መንግሥት የሚሠራቸውን መተቸት፣ ጎበዞችና ችሎታ ያላቸው ወይም ጀግና እንዲባሉ መንግሥት የሚያከናውናቸውን አንዳንድ ሥራዎች አቃቂር ማውጣትና ማንኳሰስ፣ የመሳደብ፣ የመዝለፍ፣ የጉልበታማ ዓይነት መገዳደር ባህል ሲንፀባረቅባቸው ነበር፡፡ ሚዛናዊነት ያላቸው አስታራቂ ሐሳቦችን የሚያንሸራሽር የፖለቲካ ባህል እንዲሻሻል ኅብረተሰቡ ላይ የመሥራትና በመርማሪ ጋዜጠኝነት የእውነት ፍለጋ ሥራዎችን በመሥራት በኩል ክፍተት በበርካታ መገናኛ ብዙኃን ይታያል፡፡ አንዳንዶች በዚያው ከተዘፈቁበት ያረጀ ያፈጀው የጥላቻና የተቃርኖ ፖለቲካ ለመውጣት ተቸግረው ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡

  ሚዛናዊ ሆነው ከመዘገብ ይልቅ የወገንተኝነት ባህሪ በመላበስ የፖለቲካ መሪዎችን፣ መንቀፍ፣ በተቃርኖ ሐሳብ ላይ መጠመድ፣ ይኼን በማድረጋቸው እንደሚፈሩና እንደ ጀግና ራስን ከመመልከት ይልቅ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት በአዎንታዊነት መሪዎችን በማክበር እንዲበረታቱና የተሻለ እንዲሠሩ ግፊት በመፍጠር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ በአሁኑ ጊዜ የሚወዳቸውንና የሚያከብራቸውን መሪዎች እንዲዘለፉና እንዲሰድቡ አይፈልግም፡፡ አሁን የጋዜጠኝነት መለኪያው ጀግንነት መሆኑ ተቀይሯል፡፡ መልካም ክንውኖችን በማሳነስ ስህተት ብቻ ፈልጎ በማውጣት በእነ እገሌ የሚመራው ሚዲያ አይፈራም ጀግና ነው ለመባል መተቸት ለውጥን አያመጣም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሐሳቦች የአሉታዊ አቀራረብ ሐሳቦች በመሪዎቹ መደመጥ አይችሉም፡፡ ስለዚህም ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ በአዎንታዊ ግን በጎ ለተሠራው ዕውቅና ሰጥቶ በተረጋጋ መልኩ ስህተቶቹን በመጠቆም መልዕክቱን ማድረስ ነው ከመገናኛ ብዙኃን የሚጠበቀው፡፡ ያለአስፈላጊ ትችቶች ሲበዙ መሪዎችን ያወናብዳል፣ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያሳጣል፣ ተስፋም ያስቆርጣል፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል የቀድሞ ኢሕአዴግ ‹‹ውሾች ይጮኸሉ ግመሎችም ይሄዳሉ›› በሚል ትችቶችን ወደ ጎን በመተው በራሳቸው መንገድና ሐሳብ ብቻ እንዲመሩ የተደረገው፡፡ ይህ በዚህ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡

  ቀደም ባለው ጊዜ አንድ የግል ጋዜጣ ባለቤትን የምታዘጋጁት ጋዜጣ የሚያሸብርና የተጋነኑ ወሬዎች ላይ ከማተኮር ሚዛናዊነትና ትንተናን መሠረት ያደረገ ጽሑፍ ለምን አታወጡም ብዬ ስጠይቅ ሰውየው የመለሱልኝ፣ ‹‹እንደዚያ ዓይነት ጋዜጣን ሕዝቡ አይገዛንም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚገስጽና በስድብ አንጀቱን የሚያርሰውን ነው ሕዝቡ የሚፈልገው፤›› አሉኝ፡፡ በመሆኑም በጀግንነት የሚወደሰው ከመንግሥት ጋር የሚኖርንም ችግር በዲፕሎማሲና በጥበብ ለመፍታት የሚታገል ሳይሆን፣ በጀብደኝነት የሚጋተርን ድርጅት ወይም ግለሰብን ነው ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አካሄድ ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት ትክክል ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን የመገናኛ ብዙኃን በሕዝብ ስሜት ብቻ የሚመሩ ሳይሆን፣ የሕዝብን ስሜት የሚመሩ፣ የሚገሩ መሆን አለባቸው፡፡ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት በሕዝቡ ላይ የሚጭኑ ሳይሆኑ በገለልተኝነት የሕዝብን ሞራልና ሥነ ምግባር ልዕልና የሚገነቡ ሕግና ሥርዓትን የሚያከብሩ ሙስናን፣ አድልኦ የሚፀየፍ መብቱን የሚያስከብር የነቃ ኅብረተሰብ በመገንባት የኢኮኖሚ ዕድገትንና ልማትን የሚያሳልጥ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ነው የመገናኛ ብዙኃን መሥራት ያለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

  በእርግጥ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መንግሥታዊ ባልሆነና በግል መሥርያ ቤቶችም የሚፈጠሩ ስህተቶችን በመርማሪ ጋዜጠኝነት መልክ በመረጃና ማስረጃ በተደገፉ መልኩ ማጋለጥ አግባብነትና መደገፍ የሚገባው ሥራ ነው፡፡ ስለሆነም አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ መንግሥትም ሆነ ሲቪክ ማኅበራት የአቅም ግንባታ ድጋፍና በጎ ተፅዕኖ ሊያደርጉባቸው ይገባል፡፡ ካልሆነ የአገር ሀብት የሚፈስባቸው ሥራቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ተስፋ የሚሰጥ እንጂ ተስፋን የሚያጨልም ሁኔታ በሕዝቡ ውስጥ አይታይም፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ከበሬታ የሚያገኙ መሪዎችን በአፍሪካ አኅጉር ማግኘት እንደ አገር ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ያጣችው በሁሉም የኅብረተሰብ አካል ተቀባይነት ያላቸውን መሪዎችን ነው፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ናቸው ሕዝቡን በአንድነት ወደ በጎ መንገድ በመምራት የባህል ለውጥን ብሎም የኢኮኖሚ ዕድገትን በማምጣት አገርን የሚቀይሩት፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት መሪዎች በሕዝብ ዘንድ ሊከበሩ ይገባል፡፡ እነርሱን ማክበር በሌላ በኩል ሕዝቡንም ማክበር ነው፡፡ ለሚሠሩት በጎ ተግባር ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ጉድለት ካለ በሠለጠነ መንገድ ለዕርምት የሚሆኑ ሐሳቦችን በጽሞና በማቅረብ ማሳመን ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን መሥራት ያለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

  የተፎካካሪ ፓርቲዎች

  ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበሩት አሁን ወደ ተፎካካሪ ፓርቲነት የተቀየሩት (ስማቸው ብቻ ሳይሆን እውነትም አሁን ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነዋል) የፖለቲካ ኃይሎችም እንዲሁ ቀደም ሲል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ የተሟላ ሥራ ሠርተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ እነዚህ ኃይሎች ቀደም ሲል ኢሕአዴግን መቃወምና ከሥልጣን ማውረድ እንጂ፣ ስለሚረከቡት አገር የተሻለ አመራር ጉዳይ የሠሩት ሥራ ጎልቶ አይታይም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር  ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉላቸው ጥሪ ብዙ በውጪ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ጋዜጠኞች ወዘተ. ለውጡን ለማገዝና አገር ቤት ሆነው ትግላቸውን ለማካሄድ ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በለውጡ አመኔታ ፈጥረው ወደ አገር ቤት መምጣታቸው የሚያስደስት ነው፡፡ ከፊሎቹ ለውጡን በመደገፍ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው፡፡ ከፊሎቹም በመረጋጋት አዝማሚያውን በማጥናት ላይ የሚገኙ ይመስላሉ፡፡

  በአጠቃላይ ይህ ኃይል ትልቅ አጋዥ በመሆኑ የለውጡ ኃይል በምን መልኩ እነዚህን መጠቀም እንደሚያሻ የበለጠ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ቀደም ሲል እንደነበረው የመንግሥት ስህተቶች ብቻ እየለቀሙ ከመንቀፍና ከመተቸት ይልቅ ስህተቶቹን በጽሞና ማዳመጥ በሚያስችል ቋንቋ በማቅረብ እንዲስተካከል በማድረግ የጋራ አገርን በጋራ የመገንባት መንፈስን በተከተለ አካሄድ መራመድና ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ወደ አንድነት በመሰባሰብ ጠንካራ አማራጭ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በመመሥረት ረገድ ብዙ እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡ የተፎካካሪው ኃይል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሥልጣን  ላይ ያለውን መንግሥት መቃወም፣ ማዋከብ ወደ መሳሰሉት አሉታዊ አካሄድ ፈጽሞ እንደማይመለስ ይጠበቃል፡፡ የርዕዩተ ዓለምና የሌሎች የአቋም ልዩነቶች እንደተጠበቀ ሆኖ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመገምገም በመጀመርያ ለሰላምና ፀጥታ በሚሰፍንበት ሕዝቡን በማረጋጋት የበለጠ ሊሠራ ይገባል፡፡ አሁንም በዚሁ መልክ እየሠራ የሚገኝ በመሆኑ ይኸንኑ ይቀጥልበታል የሚል እምነት አለ፡፡ ይሁን እንጂ የተፎካካሪዎቹ ፓርቲዎች ቁጥር እጅግ የበዛ በመሆኑ ይህም መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል፡፡

  የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት የሚያስከትለው ተፅዕኖ በአገራችን ከ80 በላይ ፓርቲዎች ተመዝግበው ይገኛሉ ይባላል፡፡  

  ገና ያልተመዘገቡም ስለሚኖሩ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ማለት ነው፡፡ ፓርቲዎች ርዕዩተ ዓለም ልዩነቶች ላይ የተመሠረቱ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በዓለም የሚታዩት ርዕዩተ ዓለሞች ከአራት የማይበልጡ ከመሆናቸውም በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ የሚስማሙ የርዕዩተ ዓለም ቁጥር ሲታይ ከዚህም ያነሰ በመሆኑ ሊኖሩ የሚገባቸውን የፓርቲዎችን ቁጥር ወደ ሁለት ወይም ሦስት የሚያመጣ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ከ80 እስከ 100 በመነሳት ወደዚህ ቁጥር ማምጣት ምን ያህል አስቸጋሪና ጊዜ የሚጠይቅ ተግባር ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በኦሮሚያ የሚታየውን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዛትና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ዘርዘር አድርገን ብናየው መልካም ነው፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ለሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ትኩረት የሰጠሁት በክልሉ የሚታየው የፖለቲካ ግለቱ ከፍ ያለ  በመሆኑና በሌላ በኩል በዚህ አካባቢ የሚካሄዱ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ የወደ ፊት የፖለቲካ ይዘት ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖም ቀላል ባለመሆኑም ነው፡፡

  በኦሮሚያ ብቻ ከ12 ፓርቲዎች በላይ ይንቀሳቀሳሉ ይባላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በቅርብ ጊዜ የወቅቱ መነጋገሪያ የነበረው ከአስመራ የገባው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ የሚገኝበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል የነበረው ኦነግ በአምስት ፓርቲዎች ተከፋፍሎ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ አገር ውስጥ ሲገቡ በአቶ ገላሳ ድልቦ የሚመራው ክንፍ እስካሁንም ወደ አገር ቤት አልገባም፡፡ በእርግጥ አቶ ገላሳ በቅርቡ ለአንድ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ የለውጥ ኃይሉን እንደሚደግፉ ነው ሲናገሩ የተደመጠው፡፡ ስለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የምናወራው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ አንዳንዶች ሁለትና ሦስት ፓርቲዎች በኦሮሚያ ውስጥ ቢኖሩ ዴሞክራሲው ይሰፋል የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ መንፈስ በኦሮሚያም በመራራ ጉዲና (ዶ/ር) የሚመራው ኦፌኮና በአቶ ዳዊድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ተዋህደው አንድ ፓርቲ ሊመሠርቱ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ከኦዴፓ ጋር ሊዋሃዱ ይችላሉ የሚባል ምኞትም ይሁን እውነት ሐሳቦች ይደመጣሉ፡፡ ስለዚህ ሁለት ጠንካራ ፓርቲዎች ስለሚኖሩ ሕዝቡ ከሁለቱ የተሻለውን ስለሚመርጥ ለዴሞክራሲው ዕድገት ጠቀሜታ አለው የሚሉ በርካታዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

  ይህ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ትክክል ይመስላል፡፡ ግን ይህ ንድፈ ሐሳብ የሚሠራው ለዴሞክራሲ ሥርዓት መሟላት የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች  በተሟሉ የዳበረ የፖለቲካ ባህል በሚገኝበት ባደጉ አገሮች እንጂ እንደ እኛ ባለ ሁኔታ አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ ዘርዘር አድርገን እንየው፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ የተለያዩ ፓርቲዎች ቢኖሩና ሁሉም ቢወዳደሩ የድምፅ ቁጥሩ ስለሚከፋፈል ክልሉ ማግኘት የሚገባውን ድምፅ ሊያጣ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም ፓርቲዎች ተጎጂ ነው የሚያደርገው፡፡ ኅብረተሰቡ በስሜት በሚነጉድበትና በቂ ትንተና በማድረግ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን ለይቶ በማይመርጥበት በትናንሽ ጉዳዮች በደቦ አንድን ወገን በአሉታዊ በመፈረጅና ሌላውን በመቃወም እንዲሁም በአካባቢ ልዩነትና በሃይማኖት ጭምር የመደጋገፍ በሚኖርበት በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎች  ባልተሟሉበት ትክክለኛ ምርጫ ስለመደረጉ ዋስትና አይኖርም፡፡ የምርጫ ሒደቱም በሕዝብ መካከል ለመከፋፈልና የማጋጨት ችግርም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዝቅተኛ በሆነበትና ሥልጣን እንደ አንዱ የኑሮ መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ የሚታይበት ሁኔታ ቀደም ሲል የነበሩት ቦታቸውን ላለመልቀቅ የሚደረጉት የድምፅ ማጭበርበርና የመሳሰሉት መሰናክሎች ሊኖሩም ይችላል፡፡ ዋናው ነጥብ ፓርቲያቸው ለመሸነፉ ብቻ አንዳንዶች ችሎታና ብቃት ያላቸው ተመርጠው ሕዝቡን ከማገልገል የሚታቀቡ መሆንና ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በኃላፊነት መድበለ ማሠራት ለወደፊት ሕዝቡን አስተባብረው ፓርቲውን እንዲሸነፍ ያደርጋሉ፣ ሕዝብን ይይዙብናል በሚል ከሥልጣን በማግለል ለሕዝቡ ሊሠሩ የሚችሉ ችሎታ ያላቸውን የሚገድብ በመሆኑ የዚህ ዓይነት ፉክክሩና ውድድሩ ጉዳት ያስከትላል፡፡

  የዴሞክራሲ ምርጫ እኮ በዓለም ላይ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ ፋሽስት የነበሩት ሂትለርና ሙስሎኒየ ተመረጡት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዓለም መነጋገሪያ የሆኑት የአሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም በዴሞክራሲ ምርጫ የተመረጡ ናቸው፡፡ ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆን በጊዜ ሒደት በተገነባው ገጽታ (ብራንድ) ሕዝብ ይመርጠኛል፣ የኦሮሞን ሕዝብ ፖለቲካ የምመራው እኔ መሆን አለብኝ የሚል መኩራራት ውስጥ ገብቶ ስህተት እንዳይፈጽም መጠንቀቅ ያሻል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ በመከፋፈል ድል አይገኝም፡፡ ሕዝቡ ኦነግ የታገለለትን ነፃነት ማጣጣም ጀምሯል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መላ ሕዝብም የነፃነት አየሩን ወደውታል፡፡ ብሎም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጭምር ይህ በኢትዮጵያውያን የተካሄደውን ለውጥ በተስፋ እየተከታተሉት ነው፡፡ ይህን ለውጥ የሕይወት መስዋትዕነትን በሚያስከፍል ሒደት ውስጥ የመሩትና አሁንም በኦሮሞ ሕዝብም ሆነ በተቀሩት ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድጋፍ አገሪቷን እየመሩ ያሉት ከኦሮሞ ሕዝብ የወጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለማ መገርሳ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ የተገኘውን ውጤት አድንቆ ትግሉንም የመሩትን አመሥግኖ መቀላቀል (መደመር) እንጂ ኦሮሚያን ኦነግ ነው መምራት ያለበት (አልተባለም) ግን የሚመስል አቋም በማራመድ ሕዝቡን ለመከፋፈል የሚያስችል ተግባር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡

  ኦነግ የትግሉ ጀማሪ በመሆኔ የኦሮሞን ሕዝብ የመምራት ሥልጣን ይገባኛል የሚል መከራከርያ ቢያነሳ፣ በአሁኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝብ ሥልጣን መስጠት ያለበት ካሉት ተፎካካሪዎች ውስጥ ማነው በተሻለ ብቃት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅምንና የአገሪቷን ጥቅም የሚያስከብረው የሚለው ነው መሆን ያለበት፡፡ ፖለቲካ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ወይም በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅና ጠላት የለም ይባላል፡፡ ስለሆነም ኦነግ የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ አንግቦ ታግሏል አታግሏልም፡፡ ለሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶችም ትግል መሠረት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ጊዜ ግን በግልጽ ያለይሉኝታ መነጋገር ያለብንን የኦሮሞ  ሕዝብ ትግል ከደረሰበት ዕድገት አንፃርና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የመምራት ዕድል የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይል ባገኘበት ወቅት የኦሮሞ ድርጅቶች ወደ አንድ ፓርቲ ተጠቃለው ሥልጣን ሹመቱን በችሎታና ተቀባይነት ላይ በመመሥረት ተከፋፍለው ጠንካራ ፓርቲ መመሥረት ነው፡፡

  በሌላ በኩል ኦዴግ አዲስ አበባ ሲገባ አቶ ሌንጮ ለታ ሲናገሩ በትጥቅ ትግል የሚገቡት ኃይሎች ዴሞክራሲያዊ ሊሆኑ አይችሉም በሰላማዊ ትግል ውጤት የሚያስመዘግቡት ነው የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማምጣት የሚችሉት የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡ ከአገራችንም ሆነ ከሌሎች የጎረቤት አገሮች ጭምር በትጥቅ ትግል ሥልጣን ሲይዙ ዴሞክራሲን ለሕዝብ አላጎናፀፉም፡፡ የጎሬላ የትጥቅ ትግል በተፈጥሮ የዴሞክራሲ ባህሪ ለመጎናፀፍ ያለው ዕድል ጠባብ ነው፡፡ የኦሮሚያ የፖለቲካ ድርጅቶች የተደራጁበት ዓላማና ግቡ ላይ የሚታይ ልዩነት እምብዛም አይታይም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ክልሉን ከሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ ኦዴፓ ጋር እነዚህ የተጠቀሱት ሆኑ ሌሎቹ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሁሉም በኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚታይ የርዕዮተ ዓለም ይሁን የዓላማ ልዩነት ከሌለ ምናልባት ግብ መሆን ለማይችል ሥልጣንን አንደኛው ከሌላኛው የበለጠ ለመቆጣጠር ሲባል ተበታትኖ መደራጀታቸው አስፈላጊ አይደለም፡፡ ስለሆነም በድርድር ወደ አንድ በመምጣት በስምምነት ሥልጣኑንም መከፋፈል ይመረጣል፡፡

  የቀድሞ የኦነግ መሪም የነበሩ በአሁኑ ጊዜ በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦዴግ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ዲማ ነገዎ በቅርቡ በጅማ በተካሄደው የኦሕዴድ ጉባዔ፣ በኦሮሚያ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ፓርቲ እንዲመሠርቱ ሐሳብ ያቀረቡትና ሐሳቡ በጉባዔተኞቹ በከፍተኛ ጭብጨባ ተደጋፊነት ያገኘው፡፡ ይህ የበርካታ ኦሮሞ ኤሊቶች ፍላጎትም ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብም በዚሁ ላይ ነው በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ግፊት እየፈጠረ የሚገኘው፡፡ ይህ በዕድገት ከዝቅተኛ ደረጃ የሚነሱ አገሮች በአገር ደረጃ እንኳን በአንድ ፓርቲ በመመራት ወደ ካፒታሊዝም ሥርዓት መሸጋገር መቻሉን የቻይና ሒደት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኦነግ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ውለታ የዋለ ድርጅት በመሆኑ በዚህ ሒደት የድርጅቱ አባላት ወደ አዲሱ ፓርቲ የሚመጡት እንደተጠበቀ ሆኖ በዕድሜ ምክንያት ለሥልጣን የማይመረጡት አዛውንቶች የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በክብር እንዲኖሩ ሸልመውና አመሥግነው በመንከባከብ ማኖር ነው፡፡

  ስለዚህ የኦሮሞ ሕዝቦች በተለይ ቄሮና ቀሬዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ከስሜት በተላቀቀ መልኩ ምክንያታዊና ሚዛናዊ በመሆን ጉዳዮችን ማጤን ያሻል፡፡ ውስጣዊ ትግል በማካሄድ ከስህተቱ ተምሮ ራሱን በማጥራት ሒደት ላይ የሚገኘው ኦሕዴድ የአሁኑ ኦዴፓ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር በተሻለ ቁመና ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በእርግጥ ለውጡ ከላይ በመጀመሩ እስከ ታች ወርዶ በሚፈለገው ሁኔታ ሕዝቡን አላረካም ይሆናል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ሲናገሩ ትግላችን በመልካም አስተዳደር ማስፈንና በመሳሰሉት የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት 20 ከመቶ በላይ አልሠራም ሲሉ አዳምጫለሁ፡፡ በሌሎች ለውጡን በመምራት በበርካታ ጉዳዮች የተጠመዱ በመሆኑ ይህን እስካሁን ላይሠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሕዝባዊ ግፊቱ መቀጠሉ አግባብ ሆኖ በትዕግሥት ማጣትና ማመዛዘን ጉድለት  ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በመሄድ በሕዝቡ የተገኘው ለውጥ አደጋ እንዳይገጥመው ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ በመደማመጥ፣ በመመካከርና በማመዛዘን በጥንቃቄ መራመድን ይጠይቃል፡፡

  ይህ በመላ አገሪቱ ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በሶማሊያና በሌሎችም በክልል ደረጃ የተደራጁ የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ አንድነት ተጠቃለው የክልላቸውን ሕዝብ የመምራትና ከዚያም ውህደት በመፍጠር ወደ ጠንካራ አገራዊ ፓርቲ ለማደግ ነው መሥራት የሚጠበቅባቸው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደራጁት ደግሞ ቢበዛ በሁለት ትልልቅ ፓርቲዎች ቢደራጁ ለወደፊቱ በተሻለ ሁኔታ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመተግበር ያስችላል፡፡

  መንግሥት (ገዥ ፓርቲ)

  መንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሠራቸው በርካታ የአገራችንን ገጽታ የለውጡ ትላልቅ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም በርካታ ሕዝቡን ያላረካቸው የመብት ጥሰት፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ የሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት በደሎች ስለመፈጸማቸው ሲገለጽ የቆየና በዚህም ሳቢያ በሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ የአመራር ለውጥም የዳረገ በመሆኑ ወደ ዝርዝር ጉዳዮቹ አልገባም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹ ሲጠቃለሉ የዴሞክራሲን መገደብ፣ የመብት ጥሰት፣ የፍትሕ መጓደል፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የሳሐብ ልዩነቶችን በተገቢው ማስተናገድ ያለመቻል፣ በዚህም ሳቢያ በተለይ የተማረውን አብዛኛውን ኃይል ማግለልና የሥርዓቱ ደጋፊ ነው ተብሎ ለተገመተው ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ማድላት ተብሎ ሊጠቃለል ይችላል፡፡

   በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው ኢሕአዴግ እነዚህን ቀደም ሲል የነበሩትን ስህተቶች አርሞ በአዲስ አመለካከትና መንፈስ የሚመራና በራሱ የሚተማመንና ሕዝባዊ ተቀባይነትን ያተረፈ በመሆኑ ከሕዝቡ የሚቀርቡ ገንቢ ሐሳቦችን ተቀብሎ ለመተግበር የሚቸገር አይመስልም፡፡ ለአገር ግንባታ የሚረዱ ሐሳቦች ከማናቸውም ቢቀርቡ ለአቅራቢው ዕውቅና ሰጥቶ አጥንቶ ቢተገብር ሕዝባዊነቱን የሚያረጋግጥለትና የበለጠ ከበሬታን የሚያተርፉለት እንጂ የሚያስንቅ ባለመሆኑ ይህ አዲሱ አመራር ‹‹ውሾችም ይሄዳሉ ግመሎቹም ይሄዳሉ›› ወደሚል አይገባም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ኅብረተሰቡን የበለጠ በለውጡ ሒደት ለማሳተፍ የሚረዱ የተቋማት ግንባታና ሕዝብን ማሳተፍ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር በፍጥነት መጀመር የሚገባቸው ናቸው፡፡

  መንግሥት ወይም የለውጥ ኃይሉ ሊመጣ የሚችልና የፖለቲካ ውድድር ትኩረት ውስጥ ባለማስገባት በቅርቡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ተፎካካሪ የነበረውን ሜጄር ጄኔራል ከማል ጋልቹን ለክልሉ ፀጥታና ደኅንነት ኃላፊነትና ሌሎቹም ተፎካካሪ የፓርቲ ኃላፊዎችን እንዲሁም የአማራ ብሔራዊ ክልልም እንዳሾመው ሌሎችንም ሕዝባዊ ተቀባይነት ያላቸውን ተፎካካሪዎች ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ በሁሉም ክልል በመሾም ያለምንም የፖለቲካ የወደፊት ሒሳብ ማወራረድ ብቃት ያላቸውን ዜጎች ግንዛቤ ሰጥቶ ማሳለፍ ለገዥው ፓርቲ ትልቅ ከበሬታን ያስገኛል፡፡ ለወደፊት አሸናፊነትም በሕዝቡ የበለጠ ታማኝነትን ያተርፉለታል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱንም ለመገንባት ተመራጭ ዘዴ ይሆናል፡፡ የአሠራር ግልጸኝነትንም ያሰፍናል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡን በቀጥታ ማሳተፍ ወደሚያስችል የታችኞቹ እርከን አደረጃጀት ሥራም በዚሁ መልክ ሊካሄድ ይገባል የሚል ሐሳብ ነው የማቀርበው፡፡

  የሕዝብ ተሳትፎ በቀበሌዎችና ወረዳዎች

  በመንግሥታዊ የአስተዳደር ዕርከኖች ከላይ ነው ለውጡ የሚታው እንጂ ወደታች ባሉት በዞኖች፣ በወረዳዎችና በቀበሌዎች አልደረሰም፡፡ በአብዛኛው ሕዝቡን ሲያማርሩ የነበሩ ናቸው አሁንም በሥልጣን ላይ የሚገኙት፣ ሕዝቡ እነዚህን ስላልተቀበለ የታችኛው የመንግሥት ሰንሰለት ፈርሷል የሚባለውን የሕዝብ ቅሬታ በተመለከተ ይህን ክፍተት ለመድፈንና ሕዝቡንም በቀጥታ ተሳታፊ ለማድረግ በቀበሌዎችና በወረዳዎች ምርጫዎች ተካሂደው በሕዝቡ አመኔታና ተቀባይነት ያላቸው የለውጡ አራማጅ የሚሆኑ መሪዎቹን ሕዝቡ እንዲመረጥ ቢደረግ፡፡

  እነዚህኑ የተመረጡትንም የሚያማክርና ኅብረተሰቡንም ለልማት የሚያነሳሳ በሕዝቡ ተቀባይነትና ተደማጭነት ያላቸው በትምህርትና የዕውቀት ዝግጅታቸው የተሻሉ የሆኑ ከኅብረተሰቡ የሚመረጡ አባላትን ያቀፈ አማካሪ ቡድን ቢደራጅ፣ ይህ አማካሪ ቡድን በርካታ ሚናዎች ይኖሩታል፡፡

  የአካባቢውን ሕዝብ የማረጋጋትና ሕግ እንዲከበርና ፀጥታ እንዲጠበቅ ያግዛል፣

  በሕዝቡና በአመራሩ መካከል እንደድልድይ ሆኖ አስተዳደራዊ ቅሬታዎች እንዲቀንሱና የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሙስና እንዲወገድ ይሠራል፣ ኅብረተሰቡን ለልማት በማነሳሳት በወልም ሆነ በግል የልማት ሥራዎችና እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችና የኢንቬስትመንቶች ሥራዎች እንዲካሄዱ ለመንግሥት እገዛ ያደርጋል፣ በአካባቢ ፅዳት ላይም ተሳትፎ ያደርጋል፣ ሐሳቦችን በማመንጨትም ሆነ ከኅብረተሰቡ በማሰባሰብ የለውጥ ሒደቱ የበለጠ የሚጠናከርበት፣ የሕግ የበላይነት በሚከበርበትና የመንግሥት ባጀት ሁሉ በትክክል ለታለመው ዓላማ መዋሉን ጭምር ቁጥጥር በማድረግ የመልካም አስተዳደርን በማስፈን ጭምር ይሠራል፣ ወጣቶች በጥሩ ሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ የመከባበር፣ የመደማመጥና ሌሎች ጠቃሚ የባህል እሴቶች እንዲያድጉና በተለይ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ላይ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፣

  በዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ተሳትፎ በርካታ የልማት፣ የፀጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታትም በላይ ይህ አሠራር በተገባና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የሚረዱ መንግሥት በማዕከል የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶችንና መመርያዎችን በአግባቡ በሕዝብ ለማስረጽ የሚረዳ ይሆናል፡፡

  በዞንና ከዚያ በላይ ባሉት የመንግሥት፣ የአስተዳደር ዕርከኖችም ቢሆን ከተፎካካሪዎች ብቃት ያላቸውና ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ጭምር በማሳተፍ ተቋሞቹን የማጠናከር ሥራም መሥራት፣ በእዚህ ሒደት አሁን እንደተጀመረው የገዢው ፓርቲ አባል ደጋፊ ወይም ተፎካካሪ ከሚለው የመገለል አዙሪት መወጣትና በግለሰቦቹ ብቃትና ለውጥ ደጋፊነት ላይ ብቻ ማተኮር ይመረጣል የሚል እምነት አለ፡፡

  ይህ ሐሳብ ተግባራዊ ቢደረግ ሕዝቡ የለውጡ ሒደት የራሱ እንደሆነ የበለጠ ይገነዘባል፡፡ ሕዝባዊ ተስፋንም ይጭራል፡፡ ሕዝቡም አመኔታውን በመንግሥት ላይ በመጣል ወደ ኢኮኖሚ ግንባታው ይዞራል፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ክልሎች አስበውበት ቢተገብሩ ከሌሎች ሥራዎች ተዳምሮ ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡

  የተቋሞች ግንባታና መጠናከር፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሳታፊነት ሕጎችን ማሻሻል፣ የኢኮኖሚው ግንባታና ሥራ አጥነት መቀነስ ከመሳሰሉት አጀንዳዎች ገዥው ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መወያየት በለውጡ አመራር ሒደት በጋራ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት የሚጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት ለውጡን ተቋማዊ  ለማድረግ  የተጀመረውን ተቋማትን  የመገንባትና የማጠናከር ሥራዎችንም ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡

  የተቋማት ግንባታ

  የተጀመረውን ለውጥ ተቋማዊና ቀጣይነት እንዲኖረው የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከርና መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን በርካታ ልሂቃን ሲያሳስቡ ይደመጣል፡፡ በዚህ ረገድ የሰላምና የዕርቀ ኮሚሽንና የሕዝብ ቅሬታን የሚቀበልና እንዲፈታ የሚያደርግ ተቋማት አስፈላጊነት ይነሳል፡፡ በመሆኑም በአገራችን የተመሠረቱትን እንደየምርጫ ቦርድ፣ የዕንባ ጥበቃ ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመሳሰሉትን አደረጃጀታቸውንና ተልዕኮዎቻቸውን በመፈተሽ ለሕዝብ የበለጠ ተደራሽ በሚሆኑበት ላይ መሥራት ያሻል፡፡

  ስለሆነም የሰላምና የዕርቅ ኮሚሽን ጊዜያዊ በመሆኑ አሁን ያለውን የምርጫ ቦርዱን  ተፎካካሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ተወያይቶ እንደገና በማደራጀትና ወደ ኮሚሽን በማሳደግ፣ ይኸው ተቋም የሰላምና የዕርቅ ኮሚሽን ሥራውን ደርቦ እንዲሠራ ቢደረግስ?

  አሁን ያለው የዕንባ ጥበቃ ኮሚሽን ከመንግሥታዊ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ኮሚሽን ጋር በማዋሃድ የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ቢደራጅ፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በተመለከተ መንግሥታዊ ያልሆነና ገለልተኛ በሕዝብ የሚመሠረት ወይም ከዚህ በፊት የነበረን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን አጠናክሮ እንዲቋቋም የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ እገዛ ቢደረግ፣ ሌላ በሕዝብ የሚቋቋም የመብትና የዴሞክራሲ ተንከባካቢ ድርጅት ጠንካራ የማኅበረሰብ ተቋም (Civic Society) እንዲፈጠር እገዛ ማድረግ፡፡

  • የዚህ ዓይነት ተቋም በገለልተኝነት የሕዝቡን አመኔታ በሚያተርፍ መልኩ የሚሠራ  በመሆኑ የሚከተሉት ተልዕኮዎችና ጠቀሜታዎች ይኖረዋል፣ የዴሞክራሲ ባህል በሕዝቡ እንዲሰርፅ፣ ተግባራዊ እንዲሆንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት አክራሪነትን በመከላከል በአገራችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶች እንዲከበሩ የሚሠራ ይሆናል፡፡
  • የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሙስና እንዲጠፋ፣ የዜጎች የወልና የግል መብት ተከብሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል በነፃነት ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ የሚያበረታታና በመንግሥትም፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ላይ በጎ ተፅዕኖ  በመፍጠር ሥራዎች ግልጸኝነትን በተከተለ እንዲሠሩ የሚያግዝ ይሆናል፡፡
  • ተቋሙ በባህል ማለት የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣና ወጣቱ ትውልድ በሥነ ምግባር የታነፀና የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመደጋገፍ ባህል በኅብረተሰቡ እንዲሰርፅ ይሠራል፡፡
  • ተቋሙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና የሌለው ገለልተኛ ስለሚሆን በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ ተቀባይነትና ተደማጭነት የሚኖረው ይሆናል፡፡
  • በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በአገር አንድነት ሁሉ ገንቢ ሐሳቦችን ለመንግሥትም ሆነ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክርና ሐሳብ በማቅረብ ለአገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡

  በሴቶች መብት አከባበርና በአካባቢ የተፈጥሮ እንክብካቤ ጥበቃና ልማት ረገድም የራሱን ሚና የሚጫወት የራሱ ጋዜጣ፣ መጽሔቶች የሚኖሩት ተቋም ይሆናል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት አደረጃጀትን በመለየት የመንግሥት ቢሮክራሲው ከፖለቲከኞች ቀጥታ ተፅዕኖ የተላቀቀና በዕውቀትና በክህሎት የሚመራ ብቃት ያለው ያልተማከለ የመወሰን ሥልጣን ኖሮት ከኮሚቴ ጋጋታና የፖለቲካ ካድሬ በነፃ መልኩ በራስ መተማመን ላይ በተመሠረተ አካሄድ እንዲሠራ ሁኔታዎችን የማመቻቸቱን ሥራ በማጠናከር ኅብረተሰቡ ወደ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲገባ መሥራት ከመንግሥት የሚጠበቁ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ በቀረበው ሐሳብ ሁላቸውም ኃይሎች የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ሕዝባዊ ለውጡን በማስቀጠል አገራችንን እንታደግ፡፡

       ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...