የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ዝቅተኛው ዕርከን ላይ ተመድቧል
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2010 ዓ.ም. 1.33 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገባቸው ተመለከተ፡፡ 3.7 ቢሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ አውለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንኑ አመላክቷል፡፡ ከሰሞኑ ሪፖርቶቻቸውን ይፋ ካደረጉ ኩባንያዎች የተገኘው መረጃም 17ቱ መድን ድርጅቶች በ2010 ዓ.ም. ከታክስ ተቀናሽ በኋላ ያስመዘገቡት ትርፍ ከ2009 ዓ.ም. አኳያ በ22.5 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
17ቱም ኩባንያዎች በ2006 ዓ.ም. ከታክስ በኋላ ያስመዘገቡት ትርፍ 739.3 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ ትርፍ ከ2005 ዓ.ም. ከነበራቸው አንፃር ሲታይ በ28 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡
በ2007 ዓ.ም. 823.5 ሚሊዮን ብር በማትረፋቸው የ11.4 በመቶ ቅናሽ እንዳስመዘገቡ ያሳያል፡፡ በዓመቱም ከታክስ በፊት ያገኙት ትርፍ 835.3 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ከ2007 ዓ.ም. አኳያ ሲታይ ዕድገቱ የ1.4 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ካቻምና ግን የኩባንያዎቹ የትርፍ ዕድገት በ30 በመቶ ጨምሮ ወደ 1.08 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ዕድገቱ መልሶ በመቀሰኑ ወደ 22 በመቶ ዝቅ እንዳለ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡
ከትርፋቸው ባሻገር የዓረቦን አሰባሰባቸውን የሚያመለክተው መረጃ 17ቱ ኩባንያዎች ባለፈው ዓመት የሰበሰቡት የዓረቦን መጠን 8.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስፍሯል፡፡ ይህም ከካቻምናው አንፃር የ14.4 በመቶ ዕድገት እንደነበረው ያመለክታል፡፡
ሁሉም ኩባንያዎች በ2009 ዓ.ም. ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 7.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2010 ከተሰበሰበው ዓረቦን ውስጥ 95 በመቶው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ ነው፡፡ አምስት በመቶው ወይም ወደ 500 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ የተሰበሰበ ስለመሆኑ መረጃው ያመላክታል፡፡
ይህ የዓረቦን መጠን ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት፣ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. የ2017 የዓለም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን አፈጻጸም የሚያሳየው ሪፖርት፣ ደቡብ አፍሪካ 47.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሰበሰበች ይጠቅሳል፡፡ ሞሮኮ 3.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ኬንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር፣ ግብፅ 1.58 ቢሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 1.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ናሚቢያ 965 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሕይወትና ሕይወት ነክ ካልሆነ ኢንሹራንስ ዘርፎች ዓረቦን መሰብሰብ እንደቻሉ ያመለክታል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የዓረቦን መጠን 309 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በተለይም በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ደረጃ ዝቅተኛው እንደሆነም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት በየዓመቱ የሚሰበሰበው ጠቅላላ ዓረቦን በአጠቃላይ ሲታይ ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ይብሱን ደካማ በመሆኑ፣ ኢንዱስትሪው ፈቅ እንዳይል ማድረጉን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ተንጠልጥለው ያለት በሞተር ኢንሹራንስ ላይ ነው፡፡ በ2010 ከሰበሰቡት ዓረቦን ውስጥ 51 በመቶ የሚሆነው የተገኘው ከሞተር ኢንሹራንስ መሆኑ የኢንዱስትሪው ገጽታ ያሳያል፡፡ እንደ ብሔራዊ ባንክ መረጃ በ2010 ኩባንያዎቹ በጥቅል የከፈሉት ካሳ 3.7 ቢሊዮን ብር እንደከፈሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 205.4 ቢሊዮን ብር ሕይወት ነክ ሲሆን፣ ኢንሹራንስ የተከፈለ ካሳ ነው፡፡
ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተሰበሰበው ዓረቦን ውስጥም እንደቀደሙት ጊዜያት ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡
17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሕይወት ነክ ካልሆነው ዘርፍ ያሰባሰቡት 8.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለሞተር ወይም ለተሽከርካሪዎች ከተሰጠው የዋስትና ሽፋን የተሰበሰበው 4.34 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት ለሕይወት ነክ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተከፈለው የካሳ ክፍያ 3.04 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከ3.04 ቢሊዮን ብር ውስጥ ደግሞ 2.93 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተከፈለው ለሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን ለተሰጠ ዋስትና ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋና ዋና ከሚባሉ የመድን ሽፋን አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የማሪን ወይም የባህር ላይ የመድን ሽፋን በ2010 ዓ.ም. ግን እንደወትሮው ሊሆን እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡
የአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች የማሪን መደበኛ ገቢያቸው እንደቀነሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በ2010 የሒሳብ ዓመት ከተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች መቀነሱን ለእነርሱ የሚገባው የዋስትና ሽፋን በመቀነሱ መሆኑ ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
17ቱ ኩባንያዎች በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ያስመዘገቡት ካፒታል 4.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የካፒታል መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ13.3 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት አነስተኛ የካፒታል ዕድገት የታየውም በ2010 ዓ.ም. ስለመሆኑ መረጃው ያመለክታል፡፡ በቀዳሚዎቹ አምስት ዓመታት የካፒታል ዕድገቱ ከ20 እስከ 40.8 በመቶ ነበር፡፡ ኩባንያዎቹ የደረሱበት የሀብት መጠንም ሲታይ በአማካይ 19 በመቶ እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት ኩባንያዎቹ የሀብት መጠን ያደገው በ18 በመቶ ሲሆን፣ 16.01 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በቀዳሚው ዓመት 13.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር መረጃው ያመለክታል፡፡