Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነዳጅ አንዳጅ!

አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታፈስባቸው መሠረታዊ አቅርቦቶች ውስጥ ነዳጅ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ በየዓመቱ በአሥር በመቶ ፍላጎቱ እየጨመረ የሚገኘው ይህ ምርት በ2011 በጀት ዓመት ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል፡፡

 ከመጪው ዓመት ጀምሮም ኢትዮጵያ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ እንደምታወጣ ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ የሚፈስበት የነዳጅ ሀብት አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በሥርዓትና በአግባቡ ለተጠቃሚው የማዳረሱ ሥራ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ከዚህ ቀደምም ሆነ ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየታየ ያለው የነዳጅ (በተለይም ቤንዚን) ዕጥረት ነዳጅ ቀድቶ ወደ ዕለት ሥራ መሰማራትን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

የነዳጅ ጉዳይ ከዚህ ቀደም መርከብ ዘገየ፣ መንገድ ተበላሸ እየተባለ ሲፈጠር ከነበረው የአቅርቦት ችግር ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ፈተና እየሆነ ስለመምጣቱም እየሰማን ነው፡፡ ወደ አገር የሚገባው ነዳጅ በትክክል ለተጠቃሚው እንዳይደርስ ምክንያት የሆነውም ነዳጅ በኮንትሮባንድ ከአገር እየወጣ መሆኑ ነው፡፡ በችግር ላይ ሌላ ችግር፡፡ ሆነ ተብሎ የሚፈጸመው ሸፍጥ ለነዳጅ ሥርጭት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱም ታምኖበታል፡፡

ነዳጅ በአግባቡ ስለመሠራጨቱ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ፣ የነዳጅ ዕጥረት እዚህም እዚያም እየታየ ተጠቃሚው በአሰልቺ ሠልፍ እየተማረረ ነው፡፡ በስንት መከራ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የሚገባው ነዳጅ ጭራሹኑ የኮንትሮባንድ ሰለባ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከሰሞኑ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለወልቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ ይህንኑ ጉዳይ በፓርላማ መናገራቸው፣ የነዳጅ ሥርጭትና የችርቻሮው  ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት አመላክቷል፡፡

በነዳጅ ሥርጭት ያለው ችግር እንዲህ ባለው መንገድ ብቻ የሚገልጽ አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መታየት የጀመረው ሌላው ጉዳይ፣ ከጂቡቲም ሆነ ከሱዳን የተጫነ ነዳጅ በወቅቱ ወደ መሀል አገር መግባት አለመቻሉ ነው፡፡ በርካታ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ጭነው ከወጡ በኋላ ቀድሞ ይደርሱበት በነበረው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አለመድረሳቸው ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡

ይህ እንግዳ ጉዳይ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ስለመሆን አለመሆኑ በማረጋገጥ ተገቢ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ እየተጠየቀ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች በዘገዩ ቁጥር እጥረቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ራስ ምታት እየሆነ ካለው ሕገወጥ የቤንዚን ንግድና ኮንትሮባንድ ጎን ለጎን ተሽከርካሪዎቹ ሊያደረሱ የሚችሉትን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉም በላይ አንጡራ የአገር ሀብትን ከሚጠይቀው ወጪ አንፃር ነዳጁ በአግባቡ ስለመሠራጨቱ ለማረጋገጥ ያለው አሠራር ደካማ መሆኑን ለችግሩ መባባስ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከሰሞኑ እንኳን የነዳጅ ሥርጭቱን ያስተጓጎለው ሕገወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድና ሌሎች አሻጥሮች መሆናቸው ተረጋግጧል እየተባለ እንኳን ይህንን ችግር ለመፍታት አለመደከሙ የጠነከረ ቁጥጥር እንደሌለ ያሳያል፡፡

ከነዳጅ ሥርጭትና ዕደላ ጋር ተያይዞ ይመለከታቸዋል የተባሉ እንደ ንግድ ሚኒስቴር፣ ማዕድን ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የየክልሉ ንግድ ቢሮችና የመሳሰሉት ተቋማት ሕገወጥ የነዳጅ ንግድን ለመቆጣጠር በቂ ትጥቅ የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ጭርሱኑ አንዱ ሌላኛውን ኃላፊነቱ የእሱ ነው፣ የዚያኛው ነው እስከ መባባል የደረሱበት ነው፡፡

ሌላው አካል ደግሞ ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት በአዋጅ ቢሰጠውም፣ ይህንን ለማስፈጸም መመርያ የለም ብሎ እጁን አጣጥፎ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ በትክክል አጠቃላይ የነዳጅ ግዥ ማጓጓዝና ሥርጭት ባለቤት አጥቷል ወደሚል ድምዳሜ አድርሶታል፡፡

ከሰሞኑ ከተለያዩ ማደያዎች ቤንዚን በበርሜል ተቀድቶ ሊወጣ ሲል ከተያዘ በኋላ እንኳን ምንም ዓይነት ዕርምጃ ሳይወሰድ ነዳጁ ወደ ማደያው ብቻ እንዲመለስ መደረጉ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ነዳጅ በበርሜል ቀድቶ በሕገወጥ መንገድ መሸጥ ሕግ መጣስ ከሆነ አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰድ ግን አልሆነም፡፡

ስለዚህ አንዱ ዓበይት ጉዳይ በጭንቅና በጥበት በሚገኝ ዶላር የተሸመተ ነዳጅ እንደ ተራ ነገር ቁጥጥር እየተደረገበት አለመሆኑ ችግሩ ሥር እንዲወስድ አድርኋል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የነዳጅ ግብይትና አጠቃላይ ሥርጭት ጉዳይ ባለቤት አጥቷል ወደሚል ድምዳሜ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ የነዳጅ ሥርጭትና አጠቃላይ ግብይትን ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ አሠራር መዘርጋት፣ ለዚህም ባለቤት እንዲኖረው በማድረግና ቁጥጥሩን ማጥበቅ ግድ ይላል፡፡

ይህ ደግሞ ጊዜ የሚሰጠው ነገር አይደለም፡፡ መንግሥት ይህንን ለማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነዳጅ የሚመጣው በሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ በአገር ገንዘብ ነው፡፡ በአገር ሀብት የተገዛ ንብረት ደግሞ በአግባቡ እንዲሠራጭ ግዴታ የመሆኑን ያህል የነዳጅ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ መንግሥት ነዳጁን ገዝቶ ከመጣ በኋላ ከመንግሥት ተረክበው ነዳጁን የማሠራጨት ኃላፊነት ያለባቸው ኩባንያዎች እንዲያሻቸው ያደረጉት ማለት በሕዝብ ገንዘብ እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡

ነዳጅ ደግሞ የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ሆነ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ካለው ቁልፍ ሚና አንፃር በአንዳንዶች የዘፈቀደ አሠራርና ሥውር ሕገወጥ ንግድ ተብሎ ተጠቃሚዎች መማረር የሌለባቸው መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡

ለአገሪቷ ያስፈልጋታል የተባለው ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ገብቷል ቢባልም ነዳጅ በተፈለገው መንገድ አይቀርብልንም የሚሉ ነዳጅ አከፋፋይ ኩባያዎች ይህ አባባለቸው ስለእውነት ትክክል መሆን አለመሆኑም ማረጋገጥ ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ነዳጅ አቅራቢው በሚገባ በቂ ነዳጅ አቅርቤያለሁ ሲል፣ ሌላው እየቀረበልኝ አይደለም ካለ አንድ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሁለት የተለያዩ ሐሳቦች መልስ ለማግኘት ሒሳብ መሥራት ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትም ቢሆን ከሰሞኑ እንደተሰማው ችግሩ የሌሎች ከሆነ ይህንን አሳይቶ ዕርምጃ ማስወሰድ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እሱም ቢሆን የአገሪቱን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች የሚጠቀምባቸው አለመሆኑ እስከ ዛሬም የማጓጓዝ ሥራው ለሌሎች አካላት የመሰጠቱ ነገርም የአገሪቱ የነዳጅ ጉዳይ ከላይ እስከታች መፈተሽ ያለበት ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻም ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት