Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ክልሎች የፓልም ዘይት እንዲያስገቡ የመለመሏቸውን ነጋዴዎች ለፌዴራል መንግሥት እያቀረቡ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በምልመላ ያልተካተቱ ነጋዴዎች ቅሬታ እያሰሙ ነው

ክልሎች የፓልም ምግብ ዘይት ከውጭ አገር እንዲያስገቡ የመለመሏቸውን ድርጅቶች ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማቅረብ ጀመሩ፡፡

ነገር ግን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን መሥፈርት ብናሟላም ተመራጭ አልሆንም ያሉ ነጋዴዎች ቅሬታ ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ክልሎች የመለመሏቸው ነጋዴዎች እያስገቡ ቢሆንም፣ ሁሉም አጠናቀው አላስገቡም፡፡

‹‹ቅሬታ ያላቸው ነጋዴዎች በመጀመርያ ለክልሉ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ምላሽ ካላገኙም ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማቅርብ ይችላሉ፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በድጎማ እንዲገቡ የሚያደርጋቸውን ፓልም የምግብ ዘይት፣ ስኳርና የዳቦ ዱቄት በትክክለኛው መንገድ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ አዳዲስ አሠራሮችን መከተል ጀምሯል፡፡

በዚህ ሒደት በተለይ ከንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበትን የፓልም ምግብ ዘይት በተመለከተ፣ ከተለመደው ወጣ ያለ አዲስ አሠራር ለመከተል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት የፓልም የምግብ ዘይት ከውጭ አስገብተው የሚያከፋፍሉ አሥር ድርጀቶች ናቸው፡፡ እነሱም ከንግድ ዘርፍ አልሳም፣ አፋም (ሆራይዘን ፕላንቴሽን)፣ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ ደብሊውኤ ኢንዱስትሪና ሐማሬሳ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ናቸው፡፡ ከኢንዶውመንት ድርጅቶች ደግሞ ጉና ንግድ፣ አምባሰል ንግድ፣ ቱምሳና ወንዶ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ድርጅት ደግሞ አለ በጅምላ ነው፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እነዚህን አሥር ኩባያዎች ብቻ መርጦ ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን የንግድ ድርጅቶች ችላ ማለቱ ከመጀመርያው ጀምሮ ተቃውሞ ሲያስነሳ የቆየ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ እነዚህን አምስት የግሉ ዘርፍ ኩባንያዎች የመረጠው የዘይት ፋብሪካ እያቋቋሙ በመሆናቸው፣ በቂ ልምድ እንዲያገኙና በትርፍ ለማገዝ ጭምር ነው የሚል አቋም በመያዝ ቅሬታውን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

ከዓመታት በኋላ ግን የንግዱ ማኅበረሰብ ቅሬታ እየገፋ በመምጣቱና በተለይ ሥራው ከተሰጣቸው ውስጥ የዘይት ፋብሪካ ግንባታ የሚያካሂዱ በመኖራቸው፣ አራቱ የኢንዶውመንት ኩባንያዎች አቅም ያላቸው በመሆኑ ወደ ሌላ ሥራ መሄድ አለባቸው የሚል ሐሳብ መሰንዘር ጀምሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሥራው እየሰፋ በመምጣቱና የፓልም ዘይት ተጠቃሚው የኅብረተሰብ ክፍል ቅሬታ እያቀረበ በመሆኑ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዲስ አሠራር ለመዘርጋት ተገዷል፡፡

የንግድ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መላኩ አለበል ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ መንግሥት በዘይት ንግድ የተሰማራውን ነጋዴ ከመደገፍ ይልቅ ዘይት አምራቹን የመደገፍ ዕቅድ ነበረው፡፡

‹‹ቀደም ሲል ግንባታ የጀመሩ፣ ቦታ የወሰዱና ዘይት ወደ ማምረት የገቡ ባለሀብቶችን ብንደግፋቸው የበለጠ ውጤት ያመጣሉ የሚል ሐሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ባለሀብቶች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ግን ፋብሪካ አቋቁመው ወደ ማምረት እየገቡ አይደለም፡፡ ይህ መሻሻል ስላለበት አምራቾቹ ብቻ እንዲጠናከሩ የሚያደርግ መመርያ ተዘጋጅቶ ወደ ክልሎች ወርዷል፤›› በማለት አቶ መላኩ ገልጸው ነበር፡፡  

ለክልሎች የተላከው መመርያ የሚያስቀምጠው መሥፈርት በፓልም ዘይት ንግድ መግባት የሚፈልግ ነጋዴ የዘይት ፋብሪካ እያቋቋመ ያለና 100 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በቂ መጋዘን ሊኖረው ይገባል ይላል፡፡

ክልሎች ከዚህ በመነሳት የመለመሏቸውን ነጋዴዎች ሰሞኑን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ነጋዴዎችን መልምለው ካቀረቡ ክልሎች መካከል የደቡብ ክልል ይገኝበታል፡፡

ከደቡብ ክልል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ብቃት አላቸው የተባሉ አራት ነጋዴዎች መልምሎ አቅርቧል፡፡ ክልሉ በወር 27.5 ሚሊዮን ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት ኮታ የተሰጠው ሲሆን፣ ለእነዚህ አራት ድርቶች ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ሊትር በወር ይደለደልላቸዋል፡፡

ነገር ግን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን መሥፈርት ብናሟላም፣ ተመራጭ አልሆነም ያሉ ነጋዴዎች ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ ለሪፖርተር ቅሬታቸውን የገለጹ ነጋዴዎች እንደሚሉት፣ የፓልም ዘይት ንግድ ሰፊ ሥራ ቢሆንም ክልሎች ግልጽ ባልሆነ መንገድ አላሳተፏቸውም፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያወጣውን መሥፈርት ቢያሟሉም፣ ነገር ግን የወጣውን መሥፈርት የማያሟሉ ጭምር እየተመረጡ እነሱ ግን አድሏዊ በሆነ መንገድ ሳይመረጡ መቅረታቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በፓልም የምግብ ዘይት ንግድ ለመሰማራት የሚፈልጉ ነጋዴዎች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ነገር ግን ክልሉ በተሰጠው  ኮታ መሠረት እንዲያከፋፍሉ አራት ድርጅቶችን ብቻ ነው መመረጥ ያለባቸው በማለት ገልጸው፣ ለምልመላውም ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን መሥፈርት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በዓመት 400 ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል መከፋፈሉን፣ በየዓመቱ በአማካይ 440 ሚሊዮን ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት ወደ አገር እንደሚገባ ሚኒስቴሩ ለክልሎች ባስተላለፈው መመርያ መሠረት የቀረቡለትን አዳዲስ ነጋዴዎች በቅርብ ሥራ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን፣ እንዲሁም ከነባሮቹ የግሉ ዘርፍ አከፋፋዮች ጋር በድምሩ 21 ነጋዴዎች በፓልም ምግብ ዘይት ሥራ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች