ረቂቅ አዋጁ በሺሻና በሌሎች የትምባሆ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርጋል
የአልኮል መጠጦች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በፊት በሚዲያ እንዳይተዋወቁ ይከለክላል
የጤና ዘርፉን የሚመሩና ፖሊሲዎችን የሚያስፈጽሙ አካላት ከትምባሆ አምራች ኩባንያዎችና ከዘርፉ ተዋናዮች ተፅዕኖ እንዳይደረግባቸው በማለም፣ በሁለቱ መካከል የሚኖር ግንኙነትን የሚገድብ ድንጋጌዎችን የያዘ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ።
የምግብና መድኃኒት አስተዳደርን በተመለከተ ለመወሰን የተረቀቀው አዋጅ ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፓርላማ የቀረበ ሲሆን፣ በረቂቁ ክፍል አምስት ሥር ትምባሆን ለመቆጣጠር ከቀረቡ ዝርዝር ድንጋጌዎች መካከል የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል በሚል ንዑስ ርዕስ ዝርዝር አንቀጾች የተካተቱበት ድንጋጌ ተካቷል።
ከእነዚህም መካከል የጤና ፖሊሲ በሚያወጣና በሚያስፈጽም የመንግሥት አካልና በትምባሆ ኢንዱስትሪ መካከል የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት፣ ትምባሆን በአግባቡ ለመቆጣጠር አስፈላጊ ሲሆን ብቻ እንደሚደረግ የሚደነግግ አንቀጽ ይገኝበታል።
በዚህ መሠረት የሚደረገው ግንኙነት ግልጽነት ያለበት ሆኖ እንደ አግባቡ በሰነድ መያዝ እንደሚገባም ያመለክታል።
ማንኛውም የመንግሥት አካል እንዲሁም የጤና ፖሊሲ ላይ የሚሠራ የመንግሥት ሠራተኛ ከትምባሆ ኢንዱስትሪ የሚሰጥ የዓይነትም ሆነ የገንዘብ ስጦታን መቀበል እንደማይችል፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ለማንኛውም የበጎ አድራጎት ሥራ የሚውል የገንዘብ ስጦታ ወይም ማንኛውም የዓይነት ድጋፍ ማድረግ የሚችለው፣ የስጦታው ዓላማ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትምባሆ የማያስተዋውቅ ሲሆንና ስጦታውም በማንኛውም መንገድ ለሕዝብ ይፋ በማይሆንበት ሁኔታ መሆኑን ይደነግጋል።
የትምባሆ ቁጥጥርን በተመለከተ በዚሁ የምርት ዓይነት ሥር የሚወድቀው ሺሻ በኢትዮጵያ እንዳይመረት፣ ከውጭ እንዳይገባና እንዳይሸጥ እንዲሁም እንዳይጨስ ዕገዳ ይጥላል።
በተጨማሪም ማንኛውም የሲጃራ ምርት ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች ለሆነ ሰው መሸጥ እንደማይቻል፣ እንዲሁም 20 ሲጃራዎችን በሚይዝ ፓኮ ታሽጎ ካልሆነ በፍሬ እንዳይሸጥ ይከለክላል።
ሲጃራ በየትኛውም ለሕዝብ ክፍት በሆነ ቦታና በትራንስፖርት መገልገያዎች ላይ እንደማይጨስ ክልከላ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ከዚህ በተለየ ደግሞ በየትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት፣ በመዝናኛ ፓርኮች፣ በጋራ መኖሪያ ቤት ቅጥሮች ውስጥ እንዳይጨስ ይከለክላል።
ረቂቁ በተጨማሪ ከያዛቸው ድንጋጌዎች መካከል የአልኮል ምርት ለማስተዋወቅ በብሮድካስት ሚዲያ (ሬድዮና ቴሌቪዥን) ላይ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ላይ የሚጥለው ገደብ ይገኝበታል።
በዚህም መሠረት የአልኮል መጠኑ ከአሥር በመቶ በታች የሆነ ማንኛውም የአልኮል ምርት፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ብቻ መተላለፍ እንዳለበት ገደብ ይጥላል።
ይህም ማለት በኢትዮጵያ የሚገኙ ቢራ አምራች ኩባንያዎች በቴሌቪዥንም ሆነ በሬዲዮ ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከሁለት በመቶ በታች የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች አያካትትም።
ከመድኃኒትና ምግብ ነክ ምርቶች ጋር የተያያዙ የማኅበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ ጠቃሚ ናቸው የተባሉ በርካታ ድንጋጌዎችን ያካተተው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለሕፃናት፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።