አዲስ መዋቅርና ሹመት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል
ከምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሹመት በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የበጀት ዓመቱን የመጀመርያ ጉባዔ ለማካሄድ ታኅሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠራ፡፡ ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባዔ ይቀርባሉ ከተባሉ አጀንዳዎች መካከል የበጀት ዓመቱ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በቅርቡ የተካሄደውን የመዋቅር ለውጥ ማፅደቅና ለአዳዲሶቹ መዋቅሮች ተሿሚዎችን መሰየም ይገኙበታል፡፡
ይህንን ጉባዔ ለማካሄድ ታስቦ የነበረው ታኅሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በዕለቱ ሊካሄድ የማይቻል በመሆኑ ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ ጉባዔው በዋናነት ይነጋገራል ተብሎ የሚጠበቀው በመዋቅር ለውጡ ላይ ይሆናል ተብሏል፡፡
በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ተሰብስቦ፣ ለከተማው ይበጃል ያለውን አዲስ የመዋቅር ጥናት አፅድቋል፡፡ ጥናቱ በዋናነት በከተማው አስተዳደር ሥር የነበሩ 114 መሥሪያ ቤቶችን ወደ 64 ዝቅ ያደረገ ሲሆን፣ በሒደት በርካታ መሥሪያ ቤቶች ይታጠፋሉ፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባ መዋቅር ካልተፈተሸ በስተቀር የሌባ ዋሻዎችን መናድ ያስቸግራል፡፡ በሌላ በኩልም የመንግሥትን ወጪ መቆጠብና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው በማለት፣ የመዋቅር ለውጥ የሚደረግበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት የታጠፈ የተግባር ሥራ ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ ተመሳሳይ አደረጃጀትና መዋቅር ያላቸውን ለማዋሀድና የተለጠጡ ተቋማትን ለመሰብሰብ በጥናቱ ተለይቷል ተብሏል፡፡
በዚህ የመዋቅር ለውጥ ምክንያት የአመራር ለውጥ ይኖራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በጉባዔው ሹም ሽር እንደሚኖርም ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቀው በቅርቡ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን የሚተካ ባለሥልጣን ይሾማል፡፡
ወ/ሮ ዳግማዊትን ለመተካት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀኑት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴ ናቸው፡፡
አቶ እንዳወቅ ከኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ፣ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሥራ ጀምረዋል፡፡
ምክር ቤቱ እነዚህን ሹመቶች ከማፅደቅ በተጨማሪ፣ የምክትል ከንቲባው ካቢኔ ያከናወናቸውን ሥራዎች ሪፖርት ሰምቶ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡