በሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ጅማ የሕክምና ማዕከል ተመረቀ፡፡ ማዕከሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚኖሩ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሚጠቀሙበት ነው ተብሏል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የሚለው የቀድሞው ስያሜውም ጅማ የሕክምና ማዕከል በሚል የተለወጠውም፣ የደቡብ ምዕራብ ሕዝብ የሚገለገልበት እንደመሆኑ ሰፊውን ሕዝብ እንዲወክል በማሰብ እንደሆነ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ ጦሹኔ ተናግረዋል፡፡
ከሆስፒታል ደረጃ አለፍ ያሉ የሕክምና አገልግሎቶች የሚሰጡበት ስለሆነም በሆስፒታል ፈንታ የሕክምና ማዕከል መባሉን የሚናገሩት አቶ ኮራ፣ ማዕከሉ የድኅረ ስፔሻሊቲ አገልግሎቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሠራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ በመሆንም አገሪቱ በሕክምና ሰበብ የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ታስቦ መገንባቱን ገልጸዋል፡፡
የሕክምና ማዕከሉ ግንባታ የተጀመረው ደግሞ ነሐሴ 9 ቀን 1999 ዓ.ም. ነበር፡፡ ግንባታው የተካሄደው በሁለት ክፍል እንደሆነ፣ የመጀመሪያው ክፍል ግንባታ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መጀመሩን፣ የማስፋፊያ ግንባታውም ከሞላ ጎደል 75 በመቶ መጠናቀቁን አሳውቀዋል፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ወሳኝ የሆኑ ነገር ግን በቀድሞው የግንባታ ሒደት ውስጥ ያልተካተቱ የውኃ ማጠራቀሚያና ሌሎች ተጨማሪ ግንባታዎች ታክለውበት ወጪ ከ301 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡
የማስፋፊያ ግንባታው የተጠናቀቀ ቢሆንም በዓይን የማይታዩ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታዎች የተወሰነ እንደሚቀሩት ገልጸዋል፡፡ ምዕራፍ ሁለት የተባለው ይህ ግንባታ በ2006 ዓ.ም. ከ420 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጀመረ ነው፡፡ የሁለቱ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ በዓመታት መዘግየቱን፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት የሆስፒታሉ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት የመሠረታዊ የግንባታ ግብአቶች እጥረት መኖር ነው፡፡ ‹‹በወቅቱ ሲሚንቶ እንኳን በደብዳቤ እየተጠየቀ በሬሽን የሚገዛበት ሁኔታ ነበር፤›› በማለት የነበረውን ችግር አቶ ኮራ አስታውሰዋል፡፡
የሕንፃው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የተጠናቀቀው በ2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሥራ የጀመረው ግን 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ‹‹የሕንፃው ግንባታ ከተጠናቀቀ ለምን አገልግሎት መስጠት አይጀምርም የሚል ጥያቄ ነበረ›› የሚሉት አቶ ኮራ በወቅቱ በኃይል አቅርቦት ችግር ማዕከሉ ወዲያው አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ሆስፒታሉ ግዙፍ ስለሆነ ነባር ኃይል የሚያንቀሳቅሰው ሳይሆን አዳዲስ መስመሮች ሊዘረጉለት ግድ የሚል ነው፡፡ ጅሬን በሚባለው አካባቢ ላይ ይሠራ የነበረው ሰብ ስቴሽን ግንባታ እስኪጠናቀቅ ግንባታ እስኪጠናቀቅ መጠበቅ ግድ ነበር፡፡ የውኃ አገልግሎትም እንዲሁ አዲስ ኃይል ያስፈልገው ስለነበርም እንዲሁ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡
ሆስፒታሉ ራሱን የቻል የኦክሲጂን ፋብሪካ ያለው ሲሆን፣ ለሕክምና አመቺ በሆነ መልኩ የኦክስጂን ማስተላለፊያ ቱቦዎች በግድግዳዎች ውስጥ ተቀብሮ በየክፉሉ እንደሚዞር ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ኦክስጂን በሲሊንደር እየተገፋ በየክፍሉ ይዞር እንደነበር፣ በየሳምንቱ አዲስ አበባ እየመጡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደሚወስዱ አቶ ኮራ አስታውሰዋል፡፡ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና መሰል ቆሻሻዎች የሚቃጠሉበት ኢንሲነሬተርም በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገጥሞለታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በደቡብ ምዕራብ ለሚገኙ ሆስፒታሎች በሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ፋብሪካ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ታካሚዎችን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ ለሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ይነገርለታል፡፡
ለድንገተኛ ሕክምና የሚሄዱ ሕሙማን በብቃት ለማስተናገድ የሕንፃው አናት የአየር አምቡላንስ እንዲያሳርፍ ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ታካሚዎች የሚጠቀሙት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን ነው የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም ባይሆን የተወሰኑትን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ የተመረቀው ሆስፒታሉ የኤምአርአይ፣ የሲቲስካን፣ ዲጂታል ኤክስሬይ፣ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን የተሟላለት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም የጨረር ሕክምና (ራዲዮሎጂ) ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የልብ ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሣሪያም ተከላው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ አዲሱ ሆስፒታል ግንባታው መሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ተኝተው የሚታከሙ 1,000 ሰዎችን የሚያስተናግድ አልጋ ይኖረዋል፡፡ ነባሩ ሆስፒታል ሲታከልበት ሆስፒታሉ በአጠቃላይ 1,400 የሚሆኑ ታካሚዎችን አስተኝቶ የማከም አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የሆስፒታሎችን መኝታ የሚያጨናንቁት የአደጋ ታካሚዎች ናቸው የሚሉት አቶ ኮራ የአደጋ ታካሚዎች የሚስተናገዱበት ራሱን የቻለ የሕክምና ማዕከል የመገንባት ሐሳብ እንዳለም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሆስፒታሉ 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡