[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሊያገኛቸው ቤታቸው ይሄዳል]
- ክቡር ሚኒስትር በሰላም ነው?
- በሰላም ነው ስትል?
- እልም ብለው ጠፍተዋል፡፡
- ምን ላድርግ ብለህ ነው?
- እኔ እኮ እርስዎን ለማግኘት እንደ ጠበል ቀማሽ በየድግሱ አልጠፋም፡፡
- አልገባኝም?
- በቃ ኤምባሲ ቢሉ መንግሥት፣ ከዚያም አልፎ የከተማችን ሀብታችሞ በሚደግሱት ድግስ እርስዎን ለማግኘት ቀርቼ አላውቅም፡፡
- ማን ይጠራኛል ብለህ ነው?
- በፊትም እኮ ሳይጠሩ ነበር የሚመጡት፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፣ አሁን ግን የድግስ ሰባሪ መሆን ሰልችቶኛል፡፡
- በሰላም ነው ግን?
- ሰላም ነው፣ ሰላም ነው፡፡
- እኔማ ምን ሆነው እንደጠፉ ስጠይቅ ከቤትም እንደማይወጡ ሰማሁ፡፡
- እ. . .
- እንደሰማሁትም ይኸው ቤት ተገኙ፡፡
- አንዳንዴ ማረፍም አይቻልም እንዴ?
- የምን እረፍት ነው?
- በቃ እኔ ማንበብ እወዳለሁ፣ ከዚያም ባለፈ መጻፍ እወዳለሁ፣ ስለዚህ ቤቴ አርፌ እሱን እያደረኩ ነው፡፡
- ያው ጊዜው የለውጥ ነው ብዬ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
- ቢሆንስ ማረፍ አይቻልም?
- በዚህ ጊዜ በከፍተኛ ኃይል መሥራት ነበረብዎት ብዬ ነዋ?
- እሱንማ እንዳላደርግ የድሮው ሥርዓት ናፋቂ እየተባልኩኝ ሰለቸኝ፡፡
- እንደዚህማ ተስፋ አይቁረጡ?
- እኔ ይህቺ አገር 11 በመቶ እንድታድግ ሌት ተቀን ብሠራም፣ የተረፈኝ ስድብና መገለል ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ እኮ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ያስመዘገችው በርካታ ጥፋቶች ተሠርተዋል፡፡
- የምን ጥፋት ነው?
- የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ቢሉ ሙስናውን እያየነው አይደል?
- ታዲያ እኔ በሙስና የምጠረጠር ሰው ነኝ?
- እንዴት ማለት?
- ይኸው የምኖረው እንኳን በመንግሥት ቤት አይደል እንዴ?
- የራስዎትን ቤትማ አከራይተውት ነዋ?
- አንድም በስሜ የተመዘገበ ቤት የለኝም፡፡
- እሱማ ሀብትና ንብረትዎን ጠቅላላ በዘመድ አዝማድ ስም እንዳስመዘገቡት ይታወቃል፡፡
- ከዚህ ተራ አሉባልታ ለመገላገል ነው እኮ ቤቴ አርፌ የተቀመጥኩት፡፡
- እንዲህ በቀላሉ ይገላገላሉ ብለው ነው?
- ደግሞ ሌላ ምን አለ?
- ያው ሁሉም ሰው ባጠፋው ልክ መሠረት ተጠያቂ ይሆናላ፡፡
- የሰማኸው ነገር አለ እንዴ?
- አይ እኔ ስለእርስዎ ሰምቼ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ መንግሥት ፍትሕን አሰፍናለሁ ብሎ አቋም ይዟል ብዬ ነው፡፡
- እና አንተም አይቀርልህም እያልከኝ ነው?
- እሱ እንግዲህ ሥራዎት ነው የሚያወጣዎት፡፡
- በሥራዬማ ንፁህ ነኝ፡፡
- እሱን ወደፊት እናየዋለን፡፡
- ልታስፈራራኝ ነው እንዴ የመጣኸው?
- አመጣጤማ አይጥፉ ለማለት ነው፡፡
- ነገርኩህ እኮ እኔ ማንበብና መጻፍ ብቻ ነው የምፈልገው፡፡
- ለመሆኑ ምንድነው የሚያነቡት?
- ይኸው መደርደሪያውን የሞላው እኮ መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡
- ስለዚህ ይኼ ሁሉ የሚያነቡት መጽሐፍ ነው?
- እህሳ፡፡
- እኔም እንግዲህ ያለኝን መጻሐፍ አውስዎታለሁ፡፡
- ደስ ይለኛል፡፡
- መደርደሪያዎቹ ላይ ከሚታዩት ግን ለየት ይላል፡፡
- ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?
- እኔ መቼም የእምነት ሰው መሆኔን ያውቃሉ?
- መንፈሳዊ መጽሐፍ ልትሰጠኝ ነው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን የሚል መጽሐፍ?
- ሰኔ ጎሎጎታ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ዳዲ ምክር እንድትመክረኝ ነው የመጣሁት?
- የምን ምክር ነው?
- ሰሞኑን በጣም ደስተኛ አይደለሁም፡፡
- በአገሪቱ ሁኔታ ነው ደስተኛ ያልሆንከው?
- ኧረ እኔ ምን አገባኝ?
- ማለቴ በክልሎቹ እሰጣ እገባ ነው ያዘንከው?
- እኔ የራሴ ክልል ጉዳይ ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡
- ምንድነው ደግሞ የአንተ ክልል?
- 8B የሚሉት ክፍል ነዋ፡፡
- 8B ደግሞ ምን ሆነ?
- ዳዲ ከክፍላችን 8B ወጥተን ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንደ ልባችን መጫወት አልቻልንም፡፡
- ለምን?
- የትምህርት ቤቱ ሕጎች እየተጣሱ ናቸው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ለምሳሌ በእረፍት ሰዓት ተማሪ ወጥቶ መናፈስ አለበት የሚለው ሕግ ተጥሶ እኛ ከክፍል እንዳንወጣ እየተደረገ ነው፡፡
- ለምንድነው እንዳትወጡ የተባላችሁት?
- ያው ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ስለሆናችሁ አጥኑ ምናምን ብሎ ነዋ አስተማሪያችን፡፡
- ታዲያ ለእናተው ጥቅም ነዋ አጥኑ ያላችሁ?
- ሕጉ በእረፍት ሰዓት ተማሪ ይዝናና እንጂ ያጥና አይልማ?
- በነገራችን ላይ እኔ ሕግ ይከበር የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡
- ዳዲ የክፍሉ ተማሪ ሁሉ የትምህርት ቤቱ ሕግ ይከበር እያለ ነው፡፡
- ለመሆኑ ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንዳትጫወቱ የተደረጋችሁበትን ምክንያት በትክልል ደርሳችሁበታል?
- እሱማ ርዕሰ መምህራችን ነው እንደዚያ ያስደረገብን፡፡
- እኮ ለምን አስደረገባችሁ?
- እኛ ክፍል ውስጥ ያሉ ጥቂት ተማሪዎች በጣም ስለሚበጠብጡ ለትምህርት ቤቱ አሥጊ ናቸው ተብሎ ነው፡፡
- በጥባጭ ተማሪዎች ክፍላችሁ ውስጥ አሉ?
- እሱማ በጣም ዱርዬዎችና ለትምህርት ቤቱ አሥጊ የሆኑ ተማሪዎች ክፍላችን ውስጥ አሉ፡፡ ግን ለእነሱ ተብሎ እኛ መቀጣት አለብን?
- ታዲያ እናንተ ዱርዬ ተማሪዎቹን ለምን አሳልፋችሁ አትሰጧቸውም?
- እሱንማ ማድረግ አንችልም ዳዲ፡፡
- ለምን?
- የክፍላችን ልጆች ላይ እንዴት ነው አቃጣሪ የምንሆነው?
- ዱርዬዎች እኮ ናቸው?
- ቢሆንም እሱን ማድረግ ከባድ ነው ዳዲ፡፡
- ለምን?
- እንፈራቸዋለን፡፡
- እ. . .
- ዳዲ እነዚህ እኮ ከባድ ዱርዬዎች ስለሆኑ በጣም ነው የሚያስፈራሩን፡፡
- ምን እያሉ ነው የሚያስፈሯሯችሁ?
- አሳልፋችሁ ከሰጣችሁን ከምድረ ገጽ ትጠፋላችሁ ብለው ነዋ፡፡
- ታዲያ ምን ልታደርጉ ነው?
- እኛማ ሕጉ ይከበር ብለን ልንወጣ ነው፡፡
- ምን ልትወጡ?
- ሠልፍ ልንወጣ፡፡
- ሠልፍ ወጥታችሁ ምን ታመጣላችሁ?
- Selfi እንነሳለን፡፡
- ለምን?
- ለፌስቡክ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ አንድ ኢንቨስተር መጣ]
- ክቡር ሚኒስትር ዛሬ ቢሮ የመጣሁት ላመሠግንዎት ነው፡፡
- ስለምኑ?
- ክቡር ሚኒስትር ስንት ጊዜ ያስቸገረኝን ነገር ይኸው በእርስዎ ድጋፍ እኮ ተሳካ፡፡
- እንኳን ደስ አለህ፡፡
- እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡
- ሥራውን ከማወቅ የበለጠ ሰው ማወቅ ጥሩ ነው የሚባለው ለዛ ነው፡፡
- እውነትዎትን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በርካታ ሰዎች ያለ እኔ ሥራ ሞክረው ሲወድቁ አይቻለሁ፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች እኮ ለአገር ይጠቅማሉ፡፡
- ቢሆንም ሰው ማወቅ ወሳኝ ነገር ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከሰው ይልቅ ግን ሲስተም ብንገነባ አይሻልም?
- ሲስተሙ እኮ ሰዎች ላይ ነው የሚገነባው፡፡
- እኔ ከእርስዎ ባላውቅም ሲስተም ሲገነባ በሰዎች ላይ ተመርኩዞ ባይሆን ጥሩ ነው፡፡
- ሲስተም ያለ ሰው ምንም አያደርግም፡፡
- እኔ ለነገሩ ከእርስዎ አላውቅም፡፡
- አሁን ምን እያሰብክ ነው?
- አሁንማ መሬቱም እጄ ገብቷል፣ ፕሮጀክቱም ተፈቅዷል፣ ብድሩም ፀድቋል ወደ ሥራ መግባት ነዋ፡፡
- ምን ያህል ይፈጅብሃል ወደ ሥራ ለመግባት?
- ጥቂት ወራት ነው የሚፈጅብኝ፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ስለዚህ በቀጣይ ጠንክሬ ሠርቼ በኤክስፖርት ዘርፍ አገሬን መጥቀም ነው የምፈልገው፡፡
- አገሪቱ እኮ እንደ አንተ ዓይነት ባለሀብት ነው የሚያስፈልጋት፡፡
- እኔ እኮ ለአገሬ ሟች ነኝ፡፡
- ለውጡ የሚያስፈልገው እንደ አንተ ዓይነቱ ነው፡፡
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወደ ውጭ ልትሄድ ነው እንዴ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- የያዝከው የምን ሻንጣ ነው ብዬ ነው?
- ይኼማ ምሥጋናዬን ለመግለጽ ነው፡፡
- ምንድነው እስኪ ክፈተው?
- ይኸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆነህ ነው ይኼን ይዘህ የመጣኸው?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አውቀኸዋል ምን እንዳመጣህ?
- እርስዎን ለማመስገን ያመጣሁት ብር ነው፡፡
- እኔ እኮ ብር አልቀበልም፡፡
- በተነገረኝ መሠረት እኮ ነው ብሩን ያመጣሁት፡፡
- እኔ ብር አልቀበልም አልኩህ እኮ፡፡
- ይኼንንማ አላምንም፡፡
- ምኑን ነው የማታምነው?
- ማለቴ ያለብር የሚሠሩ ሀቀኛ ሚኒስትር ነዎት?
- እንደ እሱ አልወጣኝም፡፡
- ታዲያ ምን እያሉ ነው?
- ብር አልቀበልም፡፡
- ሌላ የሚቀበሉት ነገር አለ?
- እኔ የምቀበለው በብር አይደለም፡፡
- በምንድነው ታዲያ?
- በዶላር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ተገናኙ]
- ከየት መጣህ ወዳጄ?
- ልሰናበትዎ ነው የመጣሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ስንብት?
- ጠቅልዬ ከአገር ልወጣ ነው፡፡
- በሰላም ነው?
- ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ላይ ብዙ ተስፋ ጥለን ነበር፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ያው እርስዎ የቀድሞ ሥርዓት ደጋፊ ስለነበሩ ለውጡን ያደናቅፉታል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ እርስዎ ግን ከለውጡ ፊት አውራሪዎች ጋር እጅና ጓንት ሆነዋል፡፡
- ወድጄ እኮ አይደለም፡፡
- ስለዚህ እርስዎ ለውጡን መቀልበስ ካቃተዎት እኔ እዚህ አገር ምን እሠራለሁ?
- ከሚመጣው ለውጥ ጋር አንተም ተለውጠህ አትሠራም እንዴ?
- እሱን ከማድረግ ሞቴን እመርጣለሁ፡፡
- ምን ሆነህ ነው? ሀብት ቢሉ ሀብት አለህ፣ መሬት ቢሉ መሬት አለህ?
- አይ መሬት?
- ምነው እኔ እንኳን ስንት መሬት እንዲሰጥህ አድርጌያለሁ አይደል እንዴ?
- አሁን ነበረ ነው የሚባለው፡፡
- እንዴት?
- ተቀማ ክቡር ሚኒስትር?
- ያልሠራህበትን መሬት ብትቀማ ምን ችግር አለው?
- ማን ሠርቶ ያውቅና ነው? ለዚያውም መሀል ቦሌ ላይ የነበረኝ መሬት ቀለጠ፡፡
- ቢሆንም ሌሎች ቦታዎች አሉ አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር አንድ አይሉ ሦስት ቦታዎች ነው የተወሰዱብኝ፡፡
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- አገሪቱ እንደ ዜጋ ስላልቆጠረችኝ እኔም ጠቅልዬ ልሄድ ነው፡፡
- ውጭ አገር ሄደህ ምን ትሠራለህ?
- ክቡር ሚኒስትር በደህና ጊዜ ውጭ ያሸሸሁት ገንዘብ ስላለኝ በእሱ እኖራለሁ፡፡
- ሰሞኑን 36 ቢሊዮን ዶላር ከአገሪቷ ሸሽቷል የሚባለው የአንተም ተጨምሮ ነው?
- መቼም ዓይኔ እያየ አልበላም?
- ይኼ አካሄድህ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በፊት ከዚህ አገር ምን አተረፍክ ስባል መሬት እል ነበር፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ያተረፍኩት መሬት ሳይሆን ሌላ ነው፡፡
- ሌላ ምን?
- ምሬት!