በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ አደረገ፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማትሱናና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የዕርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል፡፡
የጃፓን መንግሥት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል፡፡
በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፡፡ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል፡፡
በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በሥሩ ያቀፋቸው ቤተመጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው፡፡ በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል፡፡
እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓምና በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል፡፡