ግጭቱን በመሸሽ በርካቶች ወደ ኬንያ ሸሽተዋል
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ በኦሮሞዎችና በሶማሌዎች መካከል ዳግሞ ያገረሸው ግጭት ለተከታታይ ሦስት ቀናት መብረድ ባለመቻሉ፣ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ የሶማሌ ክልል ዓርብ ታኅሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በግጭቱ ከሶማሌ ወገን ብቻ 21 ሰዎች መገደላቸውንና በ66 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ከዚህ መግለጫ አንድ ቀን በፊት የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ በክልሉ ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በተፈጠረ ግጭት 13 ሰዎች መገደላቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑት መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ሁለቱም ክልሎች ባወጡት መግለጫ የተጠቀሰው ቁጥር በወቅቱ በተገኘ የጉዳት መጠን መሆኑንና ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
በግጭቱ ሳቢያ በርካቶች ከአካባቢው ወደ ኬንያ መሸሻቸውን የሶማሌ ክልል ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
የግጭቱን መነሻ ለማወቅ ምርመራ የተጀመረ መሆኑን ሁለቱም ክልሎች በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ነገር ግን የቦረና ዞን ነዋሪዎች ሕግ እንዲከበር የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን የሚጠይቅ ሰላማዊ ሠልፍ ባካሄዱበት ወቅት ግጭቱ መቀስቀሱን፣ ክልሉ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ በአካባቢው የነበረ አንድ የመከላከያ ሠራዊት በተሳሳተ መረጃ በከፈተው ጥቃት 12 ሰዎች በመገደላቸው ምክንያት፣ ወደ 50 ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸው ይታወሳል።
የቦረና ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች በሞያሌ ከተማ በጋራ አብረው ለዘመናት የኖሩ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የወሰን ውዝግብ ውስጥ በመግባት ተደጋጋሚ ግጭቶች እየተቀሰቀሱና የሰዎች ሕይወትም እየጠፋ ነው።
ይህንን ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ኡመር በቀጥታ በመነጋገር ላይ መሆናቸውን፣ በቅርቡም አቶ ሙስጠፋ የኦሮሚያ ክልልን እንደሚጎበኙ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።