Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግጭት በተቀሰቀሰባቸው ሥፍራዎች በወታደራዊ ዕርምጃዎች ብቻ መፍታት ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ተገለጸ

ግጭት በተቀሰቀሰባቸው ሥፍራዎች በወታደራዊ ዕርምጃዎች ብቻ መፍታት ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ተገለጸ

ቀን:

የአገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ መኰንኖች አገራዊ የፀጥታ ሁኔታና የመከላከያ ሪፎርም ሥራዎችን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፣ መከላከያ ፀጥታን ለማስከበር ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሲገባ በቶሎ ግጭቶች የሚረግቡ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በቶሎ የማይረግቡ ግጭቶች የመኖራቸው ምክንያት፣ የፀጥታ ማስከበሩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ወታደራዊ ብቻ ባለመሆኑ ነው ሲሉ አስታወቁ፡፡ ግጭቶችን በወታደራዊ ዕርምጃዎች ብቻ መፍታት ውጤቱ የከፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሐሙስ ታኅሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የልዩ ዘመቻዎች ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል ሞላ ኃይለ ማርያም፣ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና፣ የመከላከያ መረጃ ዋና መምርያ ዋና ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ሐሰን ኢብራሂም፣ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አሥራት ዴኔሮና የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ በላይ ናቸው፡፡

‹‹‹ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የነበርንበት ሁኔታ ይታወቃል፡፡ በሁሉም አካባቢ በሚባል ሁኔታ አለመረጋጋት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ፍጥጫ ነበር፡፡ ይህ አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነበር፤›› ያሉት ሜጄር ጄኔራል ጌታቸው፣ ‹‹በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች ቢኖሩም ካለፈው ጋር ሲነፃፀር ልዩነት አለው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን የሚታዩት ግጭቶች በሁለት ክልሎች ወሰን አካባቢዎችና በአንድ ክልል ውስጥ ባሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ምክንያት የሚከሰቱ እንደሆኑ ያስረዱት ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው፣ በተለያዩ የተሳትፎ መጠኖች በእነዚህ ግጭቶች ከጀርባ ሆነው የሚሳተፉ አሉ ብለዋል፡፡

ሜጀር ጄኔራሉ አክለውም የብሔር ግጭት ገጽታ ያላቸው ግጭቶች ከባድ ጥንቃቄ ስለሚጠይቁ፣ ከማኅበረሰቡና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሥራው ወታደራዊ ብቻ አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ ተሳትፎንና የሕዝብ ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው፡፡ በተረጋጋ ሁኔታ የማይፈጸም ከሆነ ወደ ጅምላ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ችግሮችን ደግሞ እንደ ባህርያቸው መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ወታደራዊ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ መፍታት ይቻል ነበር፤›› ሲሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰላምንና ደኅንነትን በማስከበር ላይ ያሉ ፈተናዎችን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በወታደራዊ ዕርምጃ ብቻ ለመፍታት ከተሄደ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በክልሎች ውስጥ የተወሰኑ የፀጥታ ኃይል አባላት ችግሩ እንዲቀጥል የሚፈልጉ መሆናቸውም አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አክለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሠራዊቱ ምንም እንኳን እስካሁን በርካታ ገድሎችን ሲፈጽም የቆየ ቢሆንም፣ ጥንካሬውን የሚሸረሽሩ ክፍተቶች እንደተለዩና እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን ሪፎርም የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

እንደ ሌተና ጄኔራል ሞላ ገለጻ፣ ሪፎርሙ እየተተገበረ ያለው በስድስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ እነዚህም ሠራዊቱ ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ ለሕዝቡና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ እንዲሆን ለማድረግ፣ ሠራዊቱ በሰው ፍላጎት ሳይሆን በሕግና አሠራር የሚመራ እንዲሆንና የሠራዊቱ ወታደራዊ ንድፈ ሐሳቦችና የውጊያ ሥርዓቶች ከወቅቱ ጋር እንዲሄዱ ለማድረግ፣ የሰው ኃይል ብቃትና ጥራት እንዲኖርና ብቃት ያለው ኃይል ሠራዊቱን እንዲቀላቀል ለማድረግ፣ ግዳጅ ለመፈጸም አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ ትጥቆች እንዲኖሩና በቴክኖሎጂ የታገዙ ለማድረግ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ሥልጠና መስጫዎችን ማዘመንና ተቋማዊ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ናቸው፡፡

ይኼንን ውጤት ለማምጣት አዋጆችን ማሻሻል እንደተጀመረ፣ ደንቦችና መመርያዎችም እየተከለሱ እንዳሉ፣ እንዲሁም የሠራዊቱን አደረጃጀት እንደገና የማዋቀር ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአየር ኃይል፣ የምድር የጦር፣ ልዩ ዘመቻና የባህር ኃይል በሠራዊቱ ውስጥ መደራጀታቸውን፣ ዕዞቹም ከስድስት ወደ አራት ዝቅ ብለው በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በምሥራቅ መከፋፈላቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ድንበር የነበረው በርካታ ጦር ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተቀንሶ እንዲሄድ መደረጉን፣ በዚህም ምክንያት የሠራዊት እንቅስቃሴ መታየቱ ተነግሯል፡፡ ከዚህ አደረጃጀት ጎን ለጎንም ብቃት ላይ የተመሠረተ የብሔር ተዋፅኦን ለማረጋገጥ እንደተሠራ ሌተና ጄኔራል ሞላ ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙ ግልጽነት፣ ለሲቪልና ለዴሞክራሲ መገዛትና ግዳጅ መፈጸም የሚያስችል አቅም ሠራዊቱን ማጎናፀፍ በሚሉ መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት ሌተና ጄኔራል ሐሰን፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ መሠረት ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፖሊሲው እስካሁን ያልተከለሰ ቢሆንም እስከሚከለስ ከምንጠብቅ፣ እየሠራን ሲከለስ የሚነካው ዋና ነገር ካለ ለማሻሻል ታስቦ ነው ሪፎርሙ እየተተገበረ ያለውም፤›› ብለዋል፡፡

በሪፎርሙ የክልል የፀጥታ ኃይሎችን ጠንካራ የማድረግ ዕቅድም የተካተተ ሲሆን፣ ‹‹የክልል የፀጥታ ኃይሎች የአቅም ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው፤›› ሲሉ ሌተና ጄኔራል ሐሰን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የክልል የፀጥታ ኃይል አባላት ሥልጠናና ትጥቅ ምን መሆን እንዳለበት፣ የፌዴራልም በተመሳሳይ ምን መምሰል እንደሚኖርበት ደረጃ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የመከላከያ ሠራዊት እንዲገባ የሚደረግባቸው ችግሮች መጠንና ከክልሎች በላይ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው የሚለው ሳይቀር በግልጽ እንዲቀመጥ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በሪፎርሙ የአመራሮች ምደባ መደረጉን የገለጹት ደግሞ ሜጀር ጄኔራል አሥራት ሲሆኑ፣ ቀደም ብሎ በሠራዊቱ የነበሩና ልምድ ያላቸውን አባላት ወደ ፊት የማምጣት ተግባር ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሠራዊቱ በሥነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...