Friday, June 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፍትሕ የሕዝብና የአገር ጋሻ ይሁን!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ተጠምቶ የኖረው ፍትሕ ነው፡፡ ፍትሕ በመጥፋቱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የጭቆና ቀንበር ሲሸከሙ ኖረዋል፡፡ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ንብረታቸው ተዘርፏል፡፡ ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዶ የድህነት መጫወቻ ሆነዋል፡፡ አምባገነኖች እየተፈራረቁባቸው መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ቀጥቅጠዋቸዋል፡፡ ይህ መቼም ቢሆን የማይካድ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት መወገድና ለዘውዳዊው አገዛዝ ማክተም ምክንያቱ የፍትሕ ዕጦት የወለደው መንገፍገፍ ነው፡፡ ለደርግ ሥርዓት መገርሰስ ሰበቡ የፍትሕ መደርመስ ያመጣው ሰቆቃ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የ27 ዓመታት የጭቆና ጉዞ በለውጥ ኃይሎች አማካይነት እንዲያበቃ የተደረገው፣ በፍትሕ ዕጦት ምክንያት የደረሰው ከመጠን ያለፈ መንገሽገሽ ነው፡፡ ሥርዓቶቹ አንዳቸው ከአንዳቸው ስህተትና ውድቀት መማር ባለመቻላቸው በሕዝብ ላይ የዘነበው መከራ፣ የፍትሕ ያለህ ከማለት አልፎ የአገርን ህልውና የሚፈታተን ሥጋት እየደቀነ እዚህ ተደርሷል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ከምንም ነገር በላይ መቅደም ያለበት የአገር ህልውና በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋነኛ ትኩረት ፍትሕ ለማስፈን የሚረዱ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ርብርብ ማድረግ ነው፡፡ ፍትሕ አገራዊ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሥቃይ ሰለባ የሆኑ ወገኖችንና ሥቃይ በመፈጸም የሚጠረጠሩትን ጉዳይ ፈር ለማስያዝ፣ ብሔራዊ ዕርቅ እንደሚያስፈልግ ታስቦ ኮሚሽን ለማደራጀት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይህ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ዓብይ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን ደግሞ የሽግግር ወቅት ፍትሕ በመጠቀም ተጎጂዎች እንዲካሱ፣ በደል ፈጻሚዎች ደግሞ በይፋ ይቅርታ ጠይቀው የቂምና የበቀል ምዕራፍ መዝጋት እንደሚያስፈልግ ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው፡፡ ይህም መደገፍ አለበት፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ጥረቶች በተጨማሪ አጥፊዎች ሕግ ፊት ቀርበው በሕጉ መሠረት አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ጥፋተኛ ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ስለሚገኙ፣ አድልኦ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ፍትሕ ለማስፈን ፍትሐዊ ሆኖ መገኘት ሲገባ፣ በፍትሕ ተጠያቂነት የሚኖርባቸው ደግሞ ብሔርን እየታከኩ ማጭበርበር የለባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በብሔር ምክንያት የጣት መቀሳሰር አጉል አጀንዳ ሰለባ ሳይሆን፣ ፍትሕ በተገቢው መንገድ እንዲሰፍን ጫና ማሳደር አለበት፡፡ ለፍትሕ ዘብ መቆም ይኖርበታል፡፡

በፍትሕ መጥፋት ምክንያት በሥቃይ ውስጥ ያለፉ ወገኖችን ስሜት በቅጡ መረዳት ይገባል፡፡ እነሱ ያለፉበትን ሰቆቃ እየተናገሩ በዚህች አገር ዳግም እንዲህ ዓይነት ነገር መፈጸም የለበትም ሲሉ፣ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ አሳዛኝ ድርጊቶችን በሕግ ማዕቀፍ በማስተናገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምደም አለበት ማለታቸው ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥትም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ የጣለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት አለ ማለት ነው፡፡ አጥፊዎችን ለፍትሕ ማቅረብና በሕዝቡ ውስጥ መተማመን መፍጠር የግድ ይሆናል፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ የተፈጸሙ ሰቆቃዎች ሲተረኩም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲቀርቡ፣ በሕዝብ ውስጥ ስሜታዊነት ተፈጥሮ ወደማይገባ ድርጊት እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ለደቦ ፍርድ የሚያነሳሱ ድርጊቶችን በከፍተኛ ኃላፊነት መቆጣጠር፣ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ በመሸጉ አደገኛ ግለሰቦች እየተቀነቀኑ ያሉ ቁጣ ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳዎችን በሕግ አደብ ማስገዛት ተገቢ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ፍትሕ ማስፈን የሚቻለው ከሕግ በተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂነት ያለባቸውን ኃይሎችና ማኅበረሰቡን አንድ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገውን አደገኛ ሴራ ለመበጣጠስ፣ ፍፁም ሕጋዊ ሆኖ መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ዘግቶ አገራዊ ሰላምና ዕርቅ ማውረድ የሚቻለው፣ እያንዳንዱን ዕርምጃ በጥንቃቄ በመራመድ ብቻ ነው፡፡

የፍትሕ መለያ የሆነችው ዓርማ ዓይኗ በጨርቅ መሸፈኑ፣ ፍትሕ ለማንም የማያዳላና ገለልተኛ የመሆኑ ምሳሌ ነው፡፡ የሰቆቃ ምዕራፍ ተዘግቶ ፈውስ የሚገኘው ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትሕን ሲያስቀድም ነው፡፡ ፍትሕ ተረግጦ ሰቆቃ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች፣ በማናቸውም መንገድ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመቀስቀስ ሲሯሯጡ አብሮ መንጎድ አይገባም፡፡ እነሱ በሰብዓዊ ፍጡራን ሥቃይና ሰቆቃ ላይ እያላገጡ ተጠያቂነትን ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣ ከፆታ፣ ከፖለቲካ አቋምና ከመሳሰሉት ጋር ሲያገናኙ፣ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት መብለጥ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ካሁን በኋላ መቼም ቢሆን ፍትሕ የማንም መጫወቻ እንዳይሆን ለተቋማት ግንባታ መረባረብ ይገባል፡፡ በተለይ የፍርድ ቤቶች፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሚዲያ፣ የደኅንነትና የፀጥታ ኃይሎች ነፃነትና ገለልተኝነት ዕውን እንዲሆን ጥርስን ነክሶ መሥራት የግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም የፍትሕ አካላት ነፃነትና ገለልተኝነት በሕግ ማዕቀፍ ሲረጋገጥ፣ የሥይና የሰቆቃ ታሪካችን ምዕራፍ በአግባቡ ይዘጋል፡፡ ነፃነቱን የሚፈልግ ማንም ሰው ስለኃላፊነቱ ጭምር በመረዳትና ከአጓጉል ድርጊቶች በመታቀብ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ፍትሕ ከሌለ ነፃነት የለም፡፡

አገርን ወደ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማሸጋገር ዋነኛው መንገድ ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ ይህ መግባባት የሚፈጠረው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል መሆናቸውን በመቀበል፣ ከአድሎአዊና ከአግላይ አስተሳሰቦች በመላቀቅ፣ ከኢትዮጵያዊነት መልካም እሴቶችና ጨዋነቶች በተፃራሪ ባለመገኘት፣ ኢሞራላዊ ድርጊቶችን ከመፀየፍ ባሻገር በማጋለጥ፣ ለአምባገነኖች ጠበቃ ባለመሆን፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በመታገል፣ ሕዝብን በማክበርና ለአገር እስከ መስዋዕትነት በሚያደርስ ደረጃ ኃላፊነት በመወጣት ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ቁስሎች ሽረው በነፃነት ለመኖር የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ከስሜታዊነት በመላቀቅ በምክንያታዊነት መመራት አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው በጎ ተግባር እንደሚመሠገን ሁሉ፣ ሲያጠፋ ደግሞ ተጠያቂነት እንዳለበት መተማመን ይገባል፡፡ ሙገሳን ለራስ ወስዶ ተጠያቂነትን ከወጡበት ማኅበረሰብ ጋር ማገናኘት በራሱ ወንጀል ነው፡፡ በዘረፋም ሆነ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚጠረጠር ማንም ሰው በተገቢው መንገድ ፍትሕ ፊት የሚቀርብበት አሠራር ተግባራዊ ከሆነ፣ ሆን ብለው ቅስቀሳ እያደረጉ ሕዝብ ለማጋጨት ያሰፈሰፉ ኃይሎች እርቃናቸውን ይቀራሉ፡፡ የፍትሕ ዓርማ ዓይኗን የሸፈነችበት ጨርቅ የገለልተኝነቷ ምሳሌ መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ፣ ፍትሕ የሕዝብና የአገር ጋሻ እንዲሆን በፅናት እንቁም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት በሁለቱ አገሮች የተያዘውን...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...