Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከታሸገ ኮንቴይነር ቡና የተሰረቀባቸው ላኪዎች እየተበራከቱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

እስካሁን ከ150 ኩንታል በላይ የተሰረቁ እንዳሉ ታውቋል

በቀላሉ እንዳይከፈት በኮንቴይነር ታሽጎ ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ላይ በረቀቀ መንገድ ተከፍቶ ስርቆት የተፈጸመባቸው ላኪዎች ተበራክተዋል፡፡ እስካሁን ስድስት ላኪዎች የሥርቆቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ቴስቲ ኮፊ፣ ሙለጌ፣ አባሃዋ ኩባንያ፣ ሲዳማ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን፣ ፋህም ጄኔራል ትሬዲንግና ሌሎችም ወደ ውጭ በኮንቴይነር አሽገው የላኩት ቡና በረቀቀ መንገድ ጎድሏል፡፡

የቴስቲ ኮፊ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፈይሰል አብዶሽ ዮኒስ፣ ወደ ኮሪያና አውስትራሊያ ከላኩት ቡና ላይ በጠቅላላው 31 ኩንታል እንደጎደለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይኸውም በኮሪያ ቡሳን ከተማ ለሚገኘው ደንበኛው ከላኩት አንድ ኮንቴይነር (210 ኩንታል) ቡና ውስጥ 15 ኩንታል ሲወሰድ፣ ወደ ሲድኒ ከላኩት ውስጥ ደግሞ 16 ኩንታል ጎድሎ መገኘቱን ገዥው እንዳሳወቃቸው ገልጸዋል፡፡

የሲዳማ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን በበኩሉ ወደ ጀርመን ከላከው 210 ኩንታል ቡና ውስጥ 53.6 ኩንታል እንደጎደለ አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ወደ ጃፓን ዮኮሐማ ከተማ ለሚስቱቢሺ ከተላከ ቡና ውስጥ 30 ኬሻ፣ አንዳንዶቹም 100 ኬሻ ወይም 60 ኩንታል የጎደለባቸው እንዳሉ ተሰምቷል፡፡ ፋህም የተሰኘው ላኪ ኩባንያ በትንሹ የ8.4 ኩንታል ቡና ጉድለት እንዳጋጠመው ታውቋል፡፡

እነዚህ መረጃዎች ከዚህም ከዚያም የተገኙ እንጂ በተደራጀ መንገድ የተገኙ ባለመሆናቸው የችግሩ መጠንና ስፋት ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ እንደማያሳይ ይታወቃል፡፡ በዚህ ደረጃ እንኳ የተደረሰበት ጉድለትና የተፈጸመው ስርቆት ወይም ቅሸባ በትንሹ በ150 ኩንታል ቡና ቢገመት እንኳ፣ ከ64 ሺሕ ዶላር በላይ ወይም በ28 ብር ገደማ ምንዛሪ ሲተመን ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማስከተሉን ለመገመት ተችሏል፡፡

ስለተፈጸመው የኮንቴይነር ቅሸባ ለሪፖርተር ያብራሩት በአካካስ ሎጂስቲክስ የመርከብና የወጪ ንግድ ክፍል ኃላፊ አቶ ግርማ ቡታ፣ ኮንቴይነር መቀሸብ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ክስተት ነው ብለዋል፡፡ ኮንቴይነር ሳያስታውቅ ከሚከፈትባቸው ዘዴዎች መካከል እስካሁን የተደረሰባቸው ሦስት መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡  

አንደኛው ኮንቴይነተሩ በቀላሉ እንዳይከፈት ተደርጎ የሚቆለፍባቸውን የማስገቢያ ዘንጎችንና ብሎኖች በመስበር የሚከፈትበት ዘዴ መለየቱን፣ በዚህ መሠረት ኮንቴይነሩ ተከፍቶ  ምርቱ ከተወሰደ በኋላ የተሰበረውን ብሎን በሌላ በመተካት፣ ኮንቴይነሩን እንደነበረ በመዝጋትና የተቆለፈበትን ማሸጊያ ቁልፍ ምንም ሳይሆን ወደ ውጭ ማጓጓዝ አንደኛው የስርቆት ዘዴ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሌላው ደግሞ ኮንቴይነሩ የታሸገበትን የማይከፈት ቁልፍ ሰብሮ በሌላ በመተካት የሚፈጸም ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ የኮንቴይነሩን ጣሪያ በመቅደድ መልሶ እንደነበር አድርጎ በመበየድና ተመሳሳይ ቀለም በመቀባት እንዳይታወቅ ማድረግ፣ እስካሁን ከተደረሰባቸው የስርቆት ዘዴዎች አንዱ መሆኑን አቶ ግርማ አብራርተዋል፡፡

ይህ ድርጊት ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከማሳጣት ባሻገር፣ በቡና ገዥዎች ዘንድ ላኪዎች አመኔታ እንዲያጡ ማድረግ፣ ብሎም ላኪዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አለመግባባት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበትን ዕድል የሚያስከትል ወንጀል እየተፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ድርጊቱ በእነ ማንና የት እንደተፈጸመ ማወቅ ባይቻልም፣ የጎላ ጥርጣሬ ያለው በአገር ውስጥ በተለይም በትራንስፖርት አገልግሎትና በትራንዚት በተሠማሩት ላይ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ጉዳዩ በመሠረታዊነት መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስም ላኪዎች የሚልኩትን ኮንቴይነር ዙሪያ ገባውን፣ ያሸጉበትን ቁልፍና የሚያጓጉዙትን ሾፌሮች ከኮንቴይነሩ በር ላይ መሳ ለመሳ ፎቶ በማንሳት ለማስረጃነት መያዝ በጊዜያዊ መፍትሔነት እንደሚያገለግል አቶ ግርማ ጠቁመው፣ ከዚህ በተጨማሪም በጂቡቲ ወደብ የምድር ሚዛን እንዲተከል አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች