Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሊዝ አዋጁ መዘግየት ቅሬታ አስነሳ

የሊዝ አዋጁ መዘግየት ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጁ ቁጥር 721/2004 ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ከዓመት በፊት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም፣ እስካሁን ፀድቆ ተግባራዊ ባለመሆኑ ቅሬታ አስነሳ፡፡

የሊዝ አዋጁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኅዳር 2004 ዓ.ም. ፀድቆ፣ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ ስተዳደሮች ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሊዝ አዋጁ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ፣ አዋጁ ከፀደቀ ከአምስት ዓመታት በኋላ ጥናት አካሄዶ ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ ካካሄደው ጥናት በተጨማሪ የኦዲት ምርመራ በማካሄድ፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደር አካላት የሊዝ አዋጁን ሲተገብሩ የገጠማቸውን ችግር ለይተው አውጥቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ከዚህ በኋላ ነባሩን የሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. የሚተካ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት፣ በረቂቁ ላይ በርካታ ውይይቶች ተደርገው የመጨረሻው ረቂቅ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ነገር ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት አካሂዶ ረቂቁን ሳያፀድቅ አንድ ዓመት ያለፈው በመሆኑ፣ የአዋጁን መውጣት በተስፋ በሚጠባበቁ ሰዎች ላይ ቅሬታ እየፈጠረ ነው፡፡

ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ያካፈሉ የይዞታ ባለቤቶች እንደሚሉት፣ የሊዝ አዋጁ ከወጣ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአፈጻጸም የተፈጠሩ በርካታ ማነቆዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ማነቆዎች በረቂቅ አዋጁ የተፈቱ ቢሆንም፣ አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ባለመሆኑ ማነቆው ቀጥሏል ይላሉ፡፡

በረቂቁ ሊዝ አዋጅ ከተካተቱና በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚጠብቋቸው ማሻሻያዎች መካከል በአንድ ግቢ የግልና የቀበሌ ቤቶች ሲገኙ፣ አብላጫውን ቦታ የያዘው የግል ባለይዞታው ግለሰብ ከሆነ መጠቅለል የሚችል መሆኑ፣ ዋጋ የሚያንሩ የመሬት ሊዝ ተጫራቾችን ለመቆጣጠር መፍትሔ ያበጀ እንደሆነ፣ ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የማስፋፊያ መሬት የሚፈቅድ በመሆኑ፣ እስካሁን ግልጽ ባይሆንም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መሬት በድርድር ማግኘት የሚችሉበት ተስፋ መያዙ፣ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የገነቡ አካላትን ሕጋዊ የመሆን ተስፋ ያጫረ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ስለሚጠቃለልበትና ሁሉንም ከተሞች ወደ ሊዝ ሥሪት ለማስገባት የሚደነግገው ክፍል ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ከመሆናቸውም በላይ፣ እጃቸው ላይ ሀብት እያለ ሀብቱን ወደ ገንዘብ መቀየር ባልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅ አዋጅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቢኔ በተለያዩ ሪፎርም ሥራዎች ላይ በመጠመዱና አስቸኳይ ጉዳዮችን እያከናወነ ስለሚገኝ፣ እስካሁን ይህንን የሊዝ አዋጅ አልተመለከተውም፡፡

ነገር ግን አዋጁ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ በዚህ ዓመት ይፀድቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ የተለያዩ አዋጆች መካከል የሊዝ አዋጅ አንዱ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...