የኢትዮጵያ አትሌቲከክስ ፌዴሬሽን ከውጤት ማጣት ባልተናነሰ በተለይ ኦሊምፒክና የዓለም አትለቲክስ ሻምፒዮና ሲመጡ ተቋሙን ለከፋ ትችትና ወቀሳ ከሚዳርጉ ክፍተቶች መካከል ብሔራዊ አትሌቶች የሚመረጡበት መሥፈርት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሐሙስ ታኅሣሥ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጉርድ ሾላ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማወያየት የመምረጫ መሥፈርት መመርያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ ብሔራዊ ቴክኒክ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎና ሌሎችም ሙያተኞች በተገኙበት በተሰጠው መግለጫ፣ ከብሔራዊ አትሌቶች መምረጫ መሥፈርት በተጨማሪ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በውድድር ዓመቱ የሚያከናውናቸው መርሐ ግብሮች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ከውጤት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካላት የሚነሱ አስተያየቶችና ትችቶች ውጤት የሚለካባቸውን ቁጥራዊ ማስረጃዎች መነሻ ያላደረጉ በመሆናቸው ተቋሙን እንደማያሳስበው የቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ ዱቤ ተናግረዋል፡፡
ከብሔራዊ አትሌቶች መምረጫ መሥፈርት ጋር በተያያዘ መሥፈርቱ ከመውጣቱ በፊት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከአትሌቶች ማኅበር፣ ከአሠልጣኞች፣ ከማናጀሮች፣ ከማናጀር ተወካዮችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በተዘጋጀ ተደጋጋሚ መድረኮች ውይይት መደረጉንና ከስምምነት መደረሱንም በመግለጫው ተገልጿል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ተመሳሳይ መግለጫ ሲሰጡ ቆይቷል፡፡ ይሁንና መግለጫውና መሬት ላይ ያለው ስለማይጣጣም የዓለም ሻምፒዮናም ሆነ የኦሊምፒክ ቅድመ ምርጫና ዝግጅቶች ሲቀርቡ፣ ፌዴሬሽኑ በመመርያው መሠረት ከመሥራት ይልቅ የጎንዮሽ አካሄዶችን ስለሚያስቀድም አሁንም በመመርያ መልክ ተዘጋጅቷል በሚል ይፋ የተደረገውን ለማመን ከወራት በኋላ እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መጠበቁ እንደሚሻል የሚናገሩ አትሌቶች አሉ፡፡
ሌላው በዕለቱ መግለጫ የተካተተው ከአሠልጣኞች ደረጃ ጋር ተያይዞ ለረዥም ዓመታት ሲያወዛግብ መቆየቱ የሚነገርለት የአሠልጣኞች የደረጃ ጉዳይ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከዚህ በኋላ ማንኛውም አሠልጣኝ ‹‹አሠልጣኝ›› የሚለውን ስያሜ ለማግኘትም ሆነ ለመያዝ ወይም በየደረጃው ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች በዋና አሠልጣኝነትም ሆነ በምክትል ዋና አሠልጣኝነት ለመመረጥ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የሚሰጡ የአሠልጣኝነት ማስረጃዎችና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያገኟቸው ማስረጃዎች፣ የቋንቋ ችሎታና ተያያዥነት ባላቸው ማስረጃዎች መሠረት እንደሚሆንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡