Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርክቡር ከንቲባ ወደኋላ እንዳይመልሱን!

ክቡር ከንቲባ ወደኋላ እንዳይመልሱን!

ቀን:

አዲስ አበባ ከ1967 ዓ.ም. በፊት ከነበሯት ከከንቲባ መኮንን ሙላት (ኢንጅነር) በኋላ በዚህ ዘመን የሙያ ብቃት ያላቸው ከንቲባ ካገኘች ስድስት ወራት ልታስቆጥር ነው፡፡ ወጣቱ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በተለይም ከ27 ዓመታት በኋላ የተወሳሰበ ችግር የመጋፈጥ ኃላፊነት ተሸክመዋል፡፡  

ከንቲባው ከነዋሪው ጋር በቀላሉ የሚገናኙበት የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች ተጠቃሚ በመሆናቸውም የሕዝብን አቤቱታና አስተያየትን ለመቀበል ዕድሉን መጠቀም መቻላቸው ይበል ያሰኛል፡፡ ይሁን እንጂ ትክክለኛው አድራሻ ስለማይለይ በሪፖርተር በኩል እንዲደርስዎ መርጫለሁ፡፡

አስተያየት ለመስጠት የተነሳሁት ከዚህ በፊት የነበሩ ከንቲቦች ለመውቀስ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ሁሉም እንደድክመታቸው ሁሉ የየራሳቸው በጎ አስተዋጽዖ እንደነበራቸው የሚካድ አይደለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ የሚቀርበውን የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ከመፍታት አንፃር ሲመጡና ሲሾሙ ነበሩ ወይ ብንል፣ መልሱ አልነበሩም ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ተፅዕኖ እንዳለባቸው ባይታወቅም ከከንቲባ መኮንን ሙላት (ኢንጂነር) በኋላ የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለው የሚሉ የሚመስሉ ከንቲባዎች ከተማዋን ሲፈራረቁባት እንደነበር ታሪክ አይዘነጋውም፡፡

ክቡር ከንቲባ እርስዎም የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆኑ፣ የጀመሩትን የለውጥ ሐደት ሊያጠናክሩት ይገባል፡፡ በከተማችን የነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ለምን በጅምላ ተቀየሩ የሚል አስተያየት የሚያቀርቡ ሠራተኞች ሲያወጉ ሰምቼ ደነቀኝ፡፡ በእኔ እምነት ክቡር ከንቲባው ጥሩ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ያሁኑ ምደባና ሹመት ከቀድሞው ቡድንተኝነት በአመዛኙ የፀዳ ይመስለኛል፡፡

ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደሌላው እያዘዋወሩ መሾም መፍትሔ አላመጣም፡፡ አሁንም ቢሆን በድሮው መንገድና አስተሳሰብ የሚመሩና ለውጡን ለማስተግበር የማይፈልጉትን ከኃላፊነት ማንሳትዎ የሚነቀፍ ሳይሆን፣ የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ ሰው በመለወጥ ብቻ መፍትሔ ይመጣል ባይባልም፣ አብዛኛው በጓደኝነትና በወንዜ ልጅነት ተመራርጠው ሲሿሿሙ የነበሩ፣   ብቃት የሌላቸውን አመራሮች መለወጥዎን በእጅጉ ከሚደግፉ ነዋሪዎች አንዱ ነኝ፡፡

በርካቶቹ ነባር አመራሮች እርስ በርስ የሚደጋገፉ፣ አንዳንዶቹም የጥቅም ግንኙነት ያላቸው፣ ለበላይ አመራር ሲበዛ አድርባይ በመሆናቸው፣ ሕዝብን የሚጎዳ ውሳኔ በበላይ አመራር ሲወሰን በአቋም የማይከራከሩ፣ አልቅሱ ሲባሉ የሚያለቅሱ ነበሩ፡፡ የበታቾቹ ሠራተኞችም ጉዳዩ ሳይገባቸው የቅርብ ኃላፊዎች ስላለቀሱ አብረው የሚያላቅሱ አመራሮች መነሳታቸው ምን ያስከፋል?

ይህ የአመራር ለውጥ በአመዛኙ ያተኮረው የከተማው አመራር ላይ በተለይም በዋና ቢሮና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ቁንጮ አመራር ላይ ያተኮረ ሆነ እንጂ በምክትል ደረጃ ያሉትንና ክፍለ ከተማና ቀበሌ ላይ በተሟላ ሁኔታ አለመፈፀሙ ግን ሊተኮርበት ይገባል፡፡አብዛኛው አመራር ብቃት ያለው ሰው በከተማው እንደሌለ አድርጎ ለድርጅትዎ ስለሚያቀርብ የእርስዎም ድርጅት በሚተዋወቁና በአስመላይ አመራሮች የተሞላ በመሆኑ፣ ከአንዱ ኃላፊነት ወደ ሌላ እያገለባበጡ ሲሾም መቆየቱ የአመራሮች ከእነሱ ውጭ የተሻለ ሰው እንደሌለ ማስመሰላቸው በተንኮል የተሞላውን ዘዴ ሲከተሉ የቆዩ ነበሩ፡፡

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለማጣራት የከተማው አስተዳደር እንደ ሌሎች ክልሎች የተሳካ ተግባር ያላከናወነው አመራሩ የችግሩ አካል ስለነበረ መሆኑ አይካድም፡፡ ከ80 በመቶ በላይ አመራር የትምህርት ማስረጃውን ያላቀረበበት ከተማ እንደነበር ማንም አይዘነጋውም፡፡  ለ27 ዓመታት ሲፈራረቁ የቆዩ ኃላፊዎች የፖለቲካ ድርጅቱን በመጠጋታቸው የመኖሪያ ቤት የተሰጣቸው፣ ሥራ ያልነበራቸውና በትምህርትም ያልገፉ ስለሆኑ ከእነሱ የሚበልጡ የመሰሏቸውን የማያቀርቡ፣ አሳፋሪ የዘረፋ ተግባር ሲፈጽሙ የኖሩ ናቸው፡፡

 ‹የዘመናት የሕዝብ ብሶት የወለደው› የተባለው ድርጅት ለሕዝብ ብሶት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ማለቱ፣ በዘረፋ የተካነና በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽም ሆኖ መቆየና ገንፍሎ የወጣው የሕዝብ ቁጣ ለድርጅቶች የመጨረሻ ቀይ መብራት እንደነበር  የሚታወስ ነው፡፡

አሁንም ቢሆን እነዚህ አመራሮች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው የሚጠብቁትን የኮንዶሚኒየም ቤት አመራር ስለሆኑ ብቻ ከአሥር ዓመት በፊት ጀምሮ በዝቅተኛ ዋጋ ተከራይተው ሲኖሩ የነበሩና ኃላፊነት ከለቀቁ በኋላም በዚሁ ቤት የሚኖሩ፣ ነገር ግን የግል ቤት ያላቸው ጭምር ያለበቂ ማጣራት ኮንዶሚኒየም በኪራይ ተሰጥቷቸው ቤታቸውን እያከራዩ ኮንዶሚኒየም በስማቸው ለማዘዋወር በጽሕፈት ቤት በኩል ለማሳወሰን እንደሚሯሯጡ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በእርግጥ አሁን በኃላፊነት ላይ ያሉና የግል ቤት የሌላቸው ተመልሰው በግለሰብ ቤት ይከራዩ ሊባል አይገባም፡፡ በጅምላ አመራር የነበረ ሁሉ ግን የያዘውን ቤት በስሙ ይዛወርለት ማለቱ ግን ተገቢነት የሌለው ውሳኔ ነው፡፡

ክቡር ከንቲባ፣ ቤት ለማግኘት ሲል ብቻ ንግግሩን አሳምሮ አመራር የተደረገ፣ በተለያየ ችግር ከኃላፊነት የተነሳ፣ ሕዝብን ሲበድልና ሲያስለቅስ የኖረ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት የጎተተ፣ የወሬ እንጂ የተግባር ብቃት የሌለው፣ በሕገወጥነት ከፍተኛ ሀብት ያካበተና በአሁኑ ወቅት የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖረው፣ በተለያዩ መንገዶች በቡድን ተደራጅቶ ሕዝብን የበደለ ጥቅመኛ አመራር፣ አብዛኛው የቤት ፍላጎቱን ካሟላ በኋላ ከአመራርነት ቢለቅ ባይለቅ ምን ጎድሎበት ብለው፡፡

ከነገ ዛሬ ቤት ይደርሰኛል በሚል ተስፋ ያለችውን ጥሪት እየቆጠበ የሚጠባበቀውን ነዋሪ ዕድል እየተሻማ የኮንዶሚኒየም ቤት የሚቀራመተው ስንቱ አመራር እንደሆነ ማንም አያጣውም፡፡ ከተማው እስከመቼ ነው የኮንዶሚኒየም ቤት ለአመራር እያደለ የሚዘልቀው፡፡ ይህ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ አብዛኛው ነዋሪ ቤት እንደሚደርሰው ተስፋ አድርጎ ላለፉት 14 ዓመታት ተመዝግቦ እየቆጠበ ነው፡፡ የአመራሩ ቤቱን መቀራመት ግን ተስፋውን አጨልሞበታል፡፡

ክቡር ከንቲባ ዛሬ ቁጥራቸው ቀነሰ እንጂ በዙሪያዎ ያሉ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ጤናማ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ በርካቶች ሕዝብን ሲያስለቅሱ የነበሩ አሁንም ያልተነኩ አሉ፡፡ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው ተዛውረው የተሾሙ ዘላን ኃላፊዎች የሞሏት ከተማ በመሆኗ ለውጡ በአፈጮሌዎች እንዳይቀለበስ ስጋት አለኝ፡፡ ለውጡን በጽጌረዳ አበባ ልንመስለው እንችላለን፡፡  ጽጌረዳ አበባ ያምራል፡፡ ነገርግን ዙሪያውን በቡድን ተንጠላጥሎ የተሾመው አመራር ግን የጽጌሬዳው እሾህ ማለት ነው፡፡

በአዲስ መልክ የተመደቡት አመራሮችና ሠራተኛው በሕግ አግባብ ሠርተው የሚያሰሩ እንዲሆኑ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሊሰጧቸውና ሊከታተሏቸው ይገባል፡፡ በግምገማ ስም ሠራተኛን ያለበቂ ምክንያት በገፍ ማባረሩ ዛሬ ባይታይም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የሚታዩ የአመራሩ አምባገነንነት ጠባዮች ግን ከወዲሁ መታረም ይገባቸዋል፡፡ ዛሬም ፍትሕ ለማግኘት በየፍርድ ቤቱ የሚመላለሰው ሠራተኛ ምክንያቱን ተጣርቶለት አፈጣኝ አስተዳደራዊ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከተማችን በኦሮሚያ መሐል የምትገኝ እንደመሆኗ በአቅራቢያ የሚገኙ ከተሞችን ሕዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ በቅርቡ በእርስ አስተዳደር ቃል እየተገባው ያለው በልማት ስም ሲፈናቀሉ የነበሩ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የወጠኑት ዕቅድ እጅግ የሚደገፍ ነው፡፡ በተለይ የእርሻ መሬታቸውን በዝቅተኛ ካሳ የለቀቁ የኦሮሚያ አርሶ አደሮች እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ ለግለሰቦች መሬታቸውን ሸጠው ችግር ላይ የወደቁ አርሶ አደሮች ሁሉንም ለመታደግ ባይቻልም፣ ይህ ድርጊት እንደማይቀጥል ቃል መግባታቸው አስደሳች ውሳኔ ነው፡፡ ከተማው የአጎራባች ከተሞችን በመሠረተ ልማት ሊደግፍ ይገባዋል፡፡ የልማት ፕሮግራሞችን በመደገፍ የሚገለጽ ድጋፍ የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከተማችን ላለፉት 130 ዓመታት ያልተላቀቃት የተጎሳቆለ አካባቢን በመልሶ ማልማት አሻሽሎ ነዋሪውንም ከነበረበት ሳይነሳ ባለበት እንዲሠፍር የተቀየሰውም አስደሳች ነው፡፡ ይህ በከተማው በስፋት ይከናወን ከነበረው የመልሶ ማልማት አቅጣጫ የተለየ በመሆኑ፣ ውሳኔው የነፃ እንዲሆን በከተማው መቋቋሚያ ቻርተር ውስጥ እንደ መርኅ ሊቀመጥ ይገባዋል፡፡

የከተማችን ነዋሪ ሌላው ፈተና የሆነበት ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁ በመሰለኝ ያለ በቂ ዕውቀትና ጥናት ከተጀመረው የታክሲ የቀጣና ስምሪት በኋላ እየተባበሰ መምጣቱ ይታያል፡፡ ነዋሪው የትራንስፖርት እጥረት እያለበት አስገዳጅ የታክሲ ስምሪት ችግሩን አለመፍታቱን አይተው ለሙከራ ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል የታክሲ ስምሪቱን ከአስገዳጅ ስምሪት ነፃ በማድረግ ማየቱ የተሻለ ነው፡፡ የታክሲ ስምሪት ተቆጣጣሪዎችን ኪስ የሚያዳብር የቀጣና አሠራር መፍትሔ አለማምጣቱን በሥራ መውጫና መግቢያ ወቅት በተለይ ማታ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓትና ከዚያም በላይ ያለውን የነዋሪውን እንግልት በየመንገዱ ማየት ይቻላል፡፡

ክቡር ከንቲባ፣ በቅርቡ በምክር ቤት እንደሚፀድቅ የሚጠበቀው የከተማው የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት ተስፋ በሚጣልበት አግባብ በጥንቃቄ ሊፈጸም ይገባዋል፡፡ በተለይ የመሬት አስተዳደር ነዋሪውን ሲያስመርር የነበረ በመሆኑ ችግር ፈቺ ተቋም ሆኖ በአንድ ተቋም ሥር ሊደራጅ ይገባዋል፡፡

የከተማችን የፀጥታ ሁኔታ ሲታይ ዝርፊያና ቅሚያን ለመቀነስ ባለፉት ጊዜያት የተሠራው የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሥራ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በእኔ እምነት የደንብ ማስከበርም፣ የማኅበረሰብ ፖሊስ አካል ሆኖ ቢደራጅ እመርጣለሁ፡፡ የከተማችን የፓርኪንግ አገልግሎት የመኪና ስርቆትን ለመቀነስ አውንታዊ ሚና ስለነበረው፣ በሥራ ዕድል ማስገኘት ሚናው ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ይልቁንም የፀጥታ አስከባሪም ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አበቃሁ፡፡

(ዳዊት ታሪኩ ረጋሣ፣ ከመሳለሚያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...