Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አንዳንድ ጊዜ የሚከሰቱ አጋጣሚዎች የቆዩ ነገሮችን ያስታውሳሉ፡፡ ለእዚህ ገጠመኝ መጻፍ ምክንያት የሆነው ከዓመታት በፊት ያጋጠመኝ ጉዳይ ቢሆንም፣ ሰሞኑን በአገር አቀፍ አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው በሰብዓዊ ፍጡራን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ሥቃይ ያሳየን ዶክመንተሪና በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው አክቲቪስቶች በፌስቡክ የሚተላለፈው በሥቃይ ማላገጥ ያንን ትውስታዬን ቀስቅሶታል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች ከነበራቸው ተጠቃሚነት አንፃር በእንዲህ ዓይነቱ ተግባር መሳተፋቸው ባይገርምም፣ አንዳንዴ አንዳንድ የማናስተውላቸውን ጉዳዮች በቅጡ መመልከቱ መልካም ነው እላለሁ፡፡

በ1996 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ በድርጅታችን ኮብራ ላንድክሩዘር እየተጓዝን ነው፡፡ ከፊት አለቃችን፣ ከኋላ ደግሞ ሁለት መሐንዲሶች አለን፡፡ አለቃችን ሾፌሩን በተመጠነ ፍጥነት እንዲነዳ ደጋግመው ይነግሩታል፡፡ የተወሰነ ኪሎ ሜትር ደህና ይነዳና ሳይታሰብ ፍጥነቱን ይጨምራል፡፡ በሁለቱ መካከል ጭቅጭቁ ይቀጥላል፡፡ በዚህ መሀል ጅማ ደርሰን ለምሣ እንቆማለን፡፡ የአለቃችንና የሾፌሩ ጭቅጭቅ ያሳሰበው ጓደኛዬ ከምሣ በኋላ ሾፌሩን ይጠራውና ምክር ይሰጠዋል፡፡ ሾፌሩ ኩርፊያ በተሞላበት መንፈስ መሬቱን በእግሩ እየተመተመ አዳመጠው፡፡ ነገር ግን እልህ ይታይበት ነበር፡፡ ይህ ሾፌር ከማንም ጋር ስለማይቀራረብ ፀባዩን ለማወቅ አይቻልም ነበር፡፡

ከምሣ በኋላ ጉዞ ጀምረን 50 ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዝን ሾፌሩ መኪናውን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ሲያበርረው ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ጓደኛዬ ‹‹እባክህ ፍጥነቱን ቀንስ›› ሲለው፣ ‹‹ደግሞ ይህም ኑሮ ተብሎ እጨቀጨቃለሁ…›› እያለ በአደገኛ ሁኔታ መኪናውን ሲነዳው በአየር ላይ የምንበር ይመስል ነበር፡፡ እንደምንም ተጯጩኸን ፍጥነቱን አስቀንሰን መኪናው እንዲቆም ተደረገ፡፡ ሁኔታው በጣም አስፈሪ ነበር፡፡

- Advertisement -

ሾፌሩ ቁልፉን ነቅሎ ኪሱ ከከተተ በኋላ በሩጫ ዕርምጃ ጥሎን ወደፊት ገሠገሠ፡፡ ከርቀት አንድ አነስተኛ ከተማ ይታይ ስለነበር እኔና መሐንዲሱ ጓደኛዬ ተከትለነው መሮጥ ጀመርን፡፡ የእኛን ከኋላው መምጣት ሲያይ ፍጥነቱን ጨምሮ ሸመጠጠ፡፡ እግር በእግር ብንከተለውም ጎረምሳው ሾፌር ሩጫውን በማሻሻል በከፍተኛ ርቀት ጥሎን ሸመጠጠ፡፡ እኛም እያለከለክን መሮጣችንን ቀጠልን፡፡ በግምት ከአሥራ አምስት ደቂቃዎች በኋላ እዚያች አነስተኛ ከተማ ስንደርስ ሾፌሩን በዓይናችን ማየት አልቻልንም፡፡ በየሆቴሉና በየሻይ ቤቱ እየዞርን ብንፈልገው አጣን፡፡ ትርፋችን ድካም ብቻ ነበር፡፡

በመጨረሻ ፖሊስ ጣቢያ ፈልገን የደረሰብንን ለፖሊሶች ከነገርን በኋላ ለመኪናው ጥበቃ ተመድቦልን አለቃችንን ይዘን ትንሿ ከተማ ገባን፡፡ ሁኔታውን ለዋና መሥሪያ ቤት በስልክ አሳውቀን በአስቸኳይ ሌላ መኪና እንዲላክልን፣ ወይም የዚህኛው መኪና ‹‹ማስተር ኪ›› ከሌላ ሾፌር ጋር እንዲመጣልን ነግረን አነስተኛ ሆቴል ውስጥ አረፍን፡፡ እንዲህም ሆኖ ሾፌሩን ላይና ታች እያልን ብንፈልግ ጠፋብን፡፡ ሲመሽ ያገኘነውን በልተን ተኛን፡፡

በማግሥቱ በጠዋት መኪናችን የቆመበት ቦታ ስንደርስ ጥበቃዎቹ አስረክበውን ሄዱ፡፡ እኛም የሚመጣልንን መኪና ወይም ሌላ ሾፌር ስንጠባበቅ ውለን፣ እኩለ ቀን ላይ የተላከልን ሾፌር በሌላ መኪና ደረሰ፡፡ እኛም ከአዲሱ ሾፌራችን ጋር በሰላም ተጉዘን ጋምቤላ ደረስን፡፡ ከቀናት ቆይታ በኋላ ሥራችንን አጠናቀን በሰላም ተመለስን፡፡ የዚያ ሾፌር ድርጊት ግን ሲያበሳጨን ነበር የከረመው፡፡ ያንን ሾፌር ከዚያ በኋላ ባናገኘውም፣ ዘመዱ ነኝ የሚል ሰው የመኪናውን ቁልፍ ይዞ መጥቶ የነገረን ግን እስከዛሬ ድረስ አይረሳኝም፡፡

ይህ ሾፌር እኛ ዘንድ አንድ ዓመት ያህል ሲሠራ ከማንም ጋር ፀብ ባይኖረውም የሚቀርበው ሰው ግን አልነበረም፡፡ ነገር ግን አንድ አንጋፋ የጥበቃ ሰው በሾፌሩ አኳኋን ግራ ስለሚጋቡ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊውን  ስለሱ አነጋግረዋቸዋል፡፡ የጥበቃ ሠራተኛው ሾፌሩን ባገኙት ቁጥር የመሥሪያ ቤቱ ሰዎች እንደሚጠሉት፣ በእሱ ላይ ሴራ እንደሚሸርቡና ሊያጠፉት እንደሚፈልጉት ይነግራቸዋል፡፡ እሳቸው ይህ ሰው ጤነኛ እንዳልሆነ ገብቷቸው ለጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው ቢነግሩም ሰሚ አላገኙም፡፡  የሾፌሩ ዘመድ ነኝ ያለው ሰው የመኪናውን ቁልፍ ሊመልስ ሲመጣ ግን ችግሩ ታወቀ፡፡ የመሥሪያ ቤቱን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ወንድምና እህቱን፣ አባትና እናቱን፣ እንዲሁም ዘመዶቹን ጭምር ያጠፉኛል ብሎ ይሸሽ ነበር አለ፡፡ ‹‹አሁን ደግሞ ብሶበት አማኑኤል ሆስፒታል ተኝቷል፤›› ሲለን ችግሩ ገባን፡፡ በጣም ቆይቶ ቢሆንም፡፡

አሁንስ እነዚህ በቡድን ተደራጅተው ወንጀለኛን የሚከላከሉት ወፈፌ ላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ ይኖረናል? ጤንነቱ የተቃወሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር እንዲህ በወገኖቹ ሥቃይ በፌስቡክ እያላገጠ የሚሳለቅ ይኖራል ለማለት ከብዶኛል፡፡ እርግጥ ነው ከገዛ ከርሳቸው በላይ ለምንም ነገር ደንታ የሌላቸው እነዚህ እኩዮች በሕዝብ ስም ለማሾፍ ቢፈልጉም፣ ድርጊታቸው ግን የጤነኛ ሰው መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ እንዲህ ጠርጥሬያለሁ፡፡ ሌላውን ግን ለባለሙያዎች እተዋለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ እነዚህን ኃላፊነት የጎደላቸው ከንቱዎች ከሕዝብ በመነጠል አዕምሮአቸውን በማስመርመር አማኑኤል ሆስፒታል ማስተኛት፣ ወይም ፍርድ ቤት አቅርቦ ተገቢውን ፍትሕ ማሰጠት የግድ ይመስለኛል፡፡ ከሰብዓዊነት በማፈንገጥ ሕዝብ ውስጥ መኖራቸው አደጋ ነውና፡፡

(መንክር አወቀ፣ ከሣር ቤት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...