Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክረዳት ዳኝነትና ፈተናዎቹ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች

ረዳት ዳኝነትና ፈተናዎቹ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች

ቀን:

በኤልያስ እሸቱ ረዳት ዳኛ

የአንድ አገር የፍትሕ ሥርዓት በተለይም የዳኝነት አካሉ ጥንካሬ ከሚለካባቸው ዋና ዋና መመዘኛዎች ውስጥ ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ገለልተኛ፣ ተደራሽነት፣ ተዓማኒነት ያለውና ቀልጣፋ ፍትሕ መስጠት የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ይኼንኑ ለማሳካት ለቦታው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅትና በቂ ልምድ ያለው የሰው ኃይል ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የዳኝነት ሥራውን በተቀላጠፈ መልኩ ለማካሄድ ዳኞችን የሚያግዙ ረዳት ዳኞች ድርሻ የሚናቅ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኔዘርላንድ፣ በህንድ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎችም አገሮች ረዳት ዳኞች የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ::

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገራችን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ በሕግ ረዳትነትና በኤክስፐርት ይጠሩ የነበሩ ባለሙያዎች በተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 በአንቀጽ 6(1) (መ) መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ  ረዳት ዳኞች ተብለው የተሾሙት በ2004 ዓ.ም. ነው፡፡

ረዳት ዳኞች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት

ረዳት ዳኞች የፍርድ ቤቶችን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት የሚሠሩበት ችሎት የሥራ ጫና እንዲቀንስ ለማስቻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉና የሚደግፉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ክስ ከመሰማቱ በፊት መዝገቡን በመመርመር የክስ አቤቱታውን ሕጋዊ ብቃት በመመርመር የክስ ምክንያት የሌላቸው መሆን አለመሆኑን በማጣራት ውጤቱን ለዳኞች በማሳወቅ ከዳኞች ጋር በመመካከርና ዳኞች በሚሰጡት አቅጣጫ መሠረት ትዕዛዞችን ያዘጋጃሉ፡፡ ክሱ ከተሰማ በኋላም ለምርመራ በተቀጠሩ መዝገቦች ላይ የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያዎችን በመመርመርና ጥናት በማድረግ ትዕዛዞችን ያዘጋጃሉ፡፡ መዝገቡ ለምርመራ በተቀጠረበት በማናቸውም ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን ምርመራ በማድረግ ትዕዛዞችን ያዘጋጃሉ፡፡ በመዝገቡ ላይ የቀረቡ ክርክሮችን የሰነድ ማስረጃዎችንና የምስክር ቃሎችን በመመርመር ፍርድና ውሳኔዎችን አዘጋጅተው ለዳኞች ያቀርባሉ፡፡ ውዝፍ መዝገቦች እንዳይበረክቱ በማድረግ የፍርድ ቤቱን ሥራ ከማቀላጠፍ በተጨማሪ ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔን ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ ጥናቶችን በማካሄድና አዳዲስ አዋጆችና የሰበር ውሳኔዎችን በመመልከት ለመዝገብ ውሳኔ ማጣቀሻዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ዳኞች በተለያዩ እክሎች በሥራ ገበታቸው በማይኖሩበት ጊዜ ቀጠሮ መቀየሩን ይነግራሉ ተመሳሳይ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ አልፎ አልፎ የአስተዳደርን ሥራ ለአብነትም የኢንስፔክሽን ክፍል እንዲሁም የቅሬታ ሰሚ የዲሲፕሊንና ሌሎችም ኮሚቴዎች ውስጥ በተደራቢነት ይሠራሉ፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች (በመጀመርያ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች) ከስልሳ በላይ ረዳት ዳኞችና የሕግ ኤክስፐርቶች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ (ከሃያ የማይበልጡ ከ2005 እስከ 2010 ዓ.ም.) በዳኝነት ሲሾሙ፣ አሁን ከቀሩት (ከአሥር ከማይበልጡ ረዳት ዳኞችና የሕግ ኤክስፐርቶች) በቀር በርካታዎቹ ወደ ጥብቅናና የተሻለ ክፍያ ወደሚከፍሉት የዓቃቤ ሕግና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የግል ተቋማት ሄደዋል፡፡ እነዚህ እንደ እርሳስ ተቀርፀው በሚገባ ሊጽፉ (ሊያገለግሉ) በሚችሉ ጊዜ መሄዳቸው ቀደም ሲል የነበሩትንና አሁንም እያገለገሉ ያሉትን ይህንኑ በሚገባ የሚያውቁ የፍርድ ቤቶቹን አመራር ሊያስቆጭ ይገባ ነበር፡፡

በነሐሴ 2004 ዓ.ም. እና በኅዳር 2006 ዓ.ም. ጉባዔው ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረዳት ዳኞችን የሾመ ሲሆን፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ግን የሾማቸው ረዳት ዳኞች የሉም፡፡

የረዳት ዳኞች ደመወዝ

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በማቋቋሚያ አዋጁ ለጉባዔው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ለሬጂስትራሮችና ለሌሎች የፍርድ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቅራቢነት የደመወዝ ጭማሪና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ ሲያደርግ የረዳት ዳኞች ግን በየጊዜው ተጠንቶ ይቅረብ እየተባለ ጥናት ሲቀርብም ቸል እየተባለ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠራባቸው የክልልና የከተማ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች የክፍያ መጠን ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረዳት ዳኞች ሲነጻጸር ዕጥፍ በሚባል መጠን የተሻለ መሆኑ በጥናት ተደግፎ ለጉባዔው ቢቀርብም፣ ጉባዔው የአህያ ጆሮ ይስጠኝ እንዳለ አለ፡፡ በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. አካባቢ የተደረገው አገር አቀፍ የደመወዝ ጭማሪ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ረዳት ዳኞችን ተሿሚ ናችሁ በማለት ማሻሻያው እንዲያልፋቸው ተደርጓል፡፡ ይኼንን ተከትሎ ጉባዔው አዋጁ የፈቀደልንን ጥቅማ ጥቅም ያለ ምክንያት ከሌሎች የጉባዔው ተሿሚዎች ለይቶ የከለከለን በመሆኑ ከማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በተለየ መልኩ በአንድ በኩል በከባድ ሥራ በሌላ በኩል ተመጣጣኝ ባልሆነ ደመወዝ ተጎጂዎች በመሆናችን ቢያንስ መንግሥት በሥራ ልምድ፣ በደረጃ ዕድገትና በአገራዊ የደመወዝ ጭማሪ ሠራተኞችን ተጠቃሚ በሚያደርግበት ጊዜ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ተጠቃሚ እንድንሆን ሹመቱ ተነስቶልን በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር እንድንተዳደር በወቅቱ ከነበሩ ረዳት ዳኞች ጋር በመሆን ጠይቀን ነበር፡፡ ጥያቄው ጥያቄ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡

  በክልል ፍርድ ቤቶች፣ በከተማ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ጀማሪ ተቀጣሪ ዓቃቤ ሕጎች እንኳን የሚያገኙት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከሚገኙ ረዳት ዳኞች አንፃር ሲታይ በእጥፍ አካባቢ የሚበልጥ ነው፡፡ በምሳሌ ለማሳየት ያህል ከሦስት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ረዳት ዳኛ ወርኃዊ ደመወዙ 5,051 ብር፣ ለቤት ኪራይ 3,150 ብር ይከፈለው የነበረ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ሰርቪስ፣ ለራሱ የሕክምና ወጪ ደረሰኝ ቀርቦበት የሚወራረድ 3,000 ብር፣ ለቤተሰቡ የሕክምና ወጪ 1,500 ብር በዓመት ውስጥ ይሸፈንለት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አንድ ረዳት ዳኛ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ይከፈለው የነበረው ደመወዝ 3,085 ብር ብቻ ነበር፡፡  

የረዳት ዳኞች ወደ ዳኝነት ሹመት ማደግ

የዳኝነት ሙያ ከንድፈ ሐሳባዊው ትምህርት በተጨማሪ የችሎት አመራር ተከራካሪዎች ያሉበት እንደመሆኑ የችሎት አካሄድን ማወቅ ይጠቅማል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጣም ከቀረቡት መካከል ረዳት ዳኞች ከቀዳሚዎቹ ይሠለፋሉ፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በአዋጅ ቁጥር 684/2002 እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ቀደም ሲሉ ከነበሩት ዓመታት በተሻለ መልኩ ለዳኝነት ሹመት የጉባዔው አባላት ይዘው የሚቀርቡት ወይም አስፈጻሚው አካል በተዘዋዋሪ የሚልካቸው መሆኑ ቀርቶ ለዕጩ ዳኝነት በመላው አገሪቱ ማስታወቂያ ወጥቶ ተወዳዳሪዎች ቀርበው የጽሑፍና የቃል ፈተና ተሰጥቶ ኅብረተሰቡም አስተያየት እንዲሰጥባቸው ከተደረገ በኋላ መሾም መጀመሩ እሰየው ያስብላል፡፡

ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረዳት ዳኞች መካከል ከላይ በጠቀስኩት መልኩ ሹመት ከተጀመረ ወዲህ የተወሰኑት ተሹመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

እኔ የዚሁ ጽሑፍ አቅራቢና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕግ ኤክስፐርትነትና በረዳት ዳኝነት በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ችሎቶች ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገልኩ ሲሆን፣ ከዚሁ ሥራ በተጨማሪ በፍርድ ቤቱ የሥነ ምግባር መኰንንነት፣ በፍርድ ቤቱ መጽሔት (ዜና ሙግት) አዘጋጅነትና በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተመድቤ በአቅሜ አገልግያለሁ፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዕጩ ዳኞችን ለመመልመል በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ አመልክቼ የጽሑፍ ፈተና ተፈትኜ እንዲሁም ቃለ መጠይቅ ተደርጎ ሳልመረጥ ቀረሁ፡፡ ሌሎች ረዳት ዳኞች በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. መሾማቸውን ተከትሎ ለዳኝነት ሹመት ያልተመረጥኩበት ምክንያት ለማወቅ ብዙም ፍላጎት ባይኖረኝም፣ አንዳንድ ወዳጆቼ ማወቁ ይጠቅማል ስላሉኝ በወቅቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትንና የዳኞች አስተዳር ጉባዔ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ዳኜ መላኩን ለማነጋገር ወደ ቢሯቸው ሄጄ ለምን እንደመጣሁ እንኳን ሳልነግራቸው፣ ‹‹አንተ ቀድሞ ጋዜጠኛ ነበርክ የአንተን ጉዳይ ተነጋግረን ለበላይ አመራር አትታዘዝም ብለን ነው ከዳኝነት ያስቀረንህ፤›› አሉኝ፡፡ በወቅቱ ምክንያቱ ጨርሶ ያልጠበቅኩት ስለነበረ በዝርዝር እንዲያስረዱኝ ብጠይቅም ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ በእስካሁኑ የፍርድ ቤት ቆይታዬ የግል ማህደሬም እንደሚያሳየው አብሬ የሠራኋቸው ዳኞችም በግልጽ ይመሠክራሉ ብዬ በሙሉ ልቤ እንደማምነው በሥራዬ ቅሬታ ቀርቦብኝ አያውቅም፡፡ በፍርድ ቤቶቹ ከዓመታት በፊት ሊሠሩ በሚገቡ ግን ብዙ ባልተሠራባቸው አንዳንድ ሥራዎች ላይ በአቅሜ ያከናወንኳቸው ተግባራት አሉ፡፡

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔው ላይ እኔ የምሠራበት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አባል በመሆናቸው፣ ስለዚሁ ብጠይቅ ለአቶ ዳኜ እንዲህ አለማለታቸውን ነገሩኝ፡፡ እንዲሁም ሁለቱን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን፣ በወቅቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን በተጨማሪም በጉባዔው የዳኞች ተወካይን ካነጋገርኩ በኋላ ተመልሼ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ፕሬዚዳንት ሳነጋግር እንዲያውም ያልመረጥንህ በቂ ሰው ስላገኘን ነው አሉኝ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲህ ባሉ በሚናገሩ ብቻ እንጂ በማያዳምጡ አንዳንድ ኃላፊዎች እየተመራ ከዚህ ደርሰናል፡፡

ሌላ ማሳያ እንዲሆን አንድ ልጨምር፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከእኛ ጋር በረዳት ዳኝነት የሚሠራ ከፍ ያለ የሥራ ልምድ ያለውና ቅዳሜ እሑድን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ያለ ተጨማሪ ክፍያ ቢሮ እየገባ መዝገብ ይሠራ የነበረ ረዳት ዳኛ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞችን ለመመልመል በወጣው ማስታወቂያ መሠረት በማስታወቂያው ላይ የወጡትን መመዘኛዎች ያሟላ ስለነበረ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ለጽሑፍ ፈተና ስም ዝርዝር ሲወጣ ስሙ አልወጣም፡፡ ምክንያት ያደረጉት አገልግሎቱ በረዳት ዳኝነት እንጂ በዳኝነት አይደለም የሚል ነው፡፡ ሆኖም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቱ ይቀርቡ የነበሩና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክፍሎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ በዳኝነት ቀርቶ በረዳት ዳኝነት ጨርሶ ያልሠሩ በሕግ ተመርቀው የነበሩ ባለሙያዎች ግን ባለፈው ሰኔ 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሹመው የዳኝነት አገልግሎት ጀምረዋል፡፡

ማጠቃለያ  

ረዳት ዳኞች በፍትሕ ሥርዓቱ በተለይም በዳኝነት ውስጥ ያላቸውን ሚና በበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሥራ ተነሳሽነታቸውን ለመጨመር እንዲችሉ፣ ሌሎች ባለሙያዎችንም ለመሳብም ሆነ ለማቆየት ለሚሠሩት ሥራ ዕውቅና ሊሰጣቸውና የሚመሩበት የሥራ ደንብና መመርያ ሲዘጋጅ መብትና ግዴታቸው ተዘርዝሮ ተጠሪነታቸውም ለማን እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦ ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔም ሆነ በጽሕፈት ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራት ግልጽ ባለመሆናቸው ጉባዔው ከሾማቸው ዳኞች ጋር በዓመታት ውስጥ እንደማስታውሰው አንድ ጊዜ ከመገናኘት ውጪ ችግራቸውን በቅርብ የማያውቅ፣ አብዛኞቹ አባላቱም ያሉባቸው ሌሎች ኃላፊነቶች ወደ ፍርድ ቤቶቹ ቀርበው ያሉ ችግሮችን በተገቢው እንዲረዱ ስለማያስችላቸው የአባላቱ ዋነኛ ሥራ የሚቀርቡ የዲሲፕሊን ክሶችን መመርመር ብቻ ሆኗል፣ በማለት ቅሬታ የሚያቀርቡባቸው እየበዙ ነውና ሊያጤኑት ይገባል፡፡

 በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ የሚሉ፣ ተራ አሉባልታና የተሳሳተ መረጃ ጭምር እየሰጡ ጉባዔው ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያደርጉ ሠራተኞች ስላሉ ጉባዔው ይኼንንም ቢፈትሽ ጠቃሚ ነው፡፡    

አዲስ የመጡት አመራሮችም የተሿሚዎች ውይይት ሲኖር ረዳት ዳኞችን እንዲያካትቱ ደመወዝ አበልና ጥቅማጥቅም ስጦታ ሳይሆን መብት ነውና እንዲያስከብሩ፣ ቢቻል ተጨማሪ ረዳት ዳኞች እንዲሾሙ ካልሆነ ደግሞ በለቀቁና በዳኝነት በተሾሙት ቁጥር እንኳን ተጨማሪ ረዳት ዳኞች ቢሾሙ ከተለያዩ የሕግ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለዓመታት ሥራ አጥተው ለሚንከራተቱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ የመዝገብ ክምችትን በመቀነስ ለፍርድ ቤቱና ለተከራካሪው ወገን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው[email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...