Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኮርፖሬሽኑን ቤቶች በሕገወጥ መንገድ በያዙና ባስተላለፉ ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል››

አቶ ረሻድ ከማል፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

በኢትዮጵያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የመኖርያ ቤቶች እጥረት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረው እጥረት ነው፡፡ የደርግ ዘመን ካበቃ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በሕዝብ ቁጥር ዕድገቱ ልክ የመኖሪያ ቤቶች ባለመገንባታቸው፣ ጫናው መሰማት የጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1996 ዓ.ም. በኋላ ወደ ቤት ልማት በሰፊው እንዲገባ ሲደረግ፣ ላለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ያለፈውና ቤቶችን የማስተዳደርና የመገንባት ልምድ ያለው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር፣ ዘግይቶ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ) ከግንባታ ውጪ ተደርጎ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ክፍተት አስፈሪ መሆኑን ዘግይቶ የተረዳው የፌዴራል መንግሥት የነበረውን አቋም በመለወጥ፣ ተቋሙ እንደ አዲስ በደንብ ቁጥር 398/2009 እንዲደራጅ በማድረግ ወደ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲገባ ፈቅዷል፡፡ አንጋፋው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም የነበሩበትን ሥር የሰደዱ ችግሮች ፈትቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን እንዲገነባ የተፈቀደለት ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑን እንዲመሩም አቶ ረሻድ ከማል ተሰይመዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ውድነህ ዘነበ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድን አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባለፉት 40 ዓመታት በብዙ መዋቅሮች ውስጥ አልፎ እዚህ ደርሷል፡፡ የተጓዘበትን መንገድ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ረሻድ፡- ተቋማችን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ስሞች ሲጠራ ነበር፡፡ ታኅሳስ 28 ቀን 1967 ዓ.ም. በተቋቋመው የብሔራዊ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሥር የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ማልሚያ መምርያ ሥር ተደራጅቶ ሥራ ጀመረ፡፡ ቀጥሎም በዚያው ዓመት ሐምሌ 15 ቀን 1967 ዓ.ም. መምርያው ከሥራና ቤቶች ሚኒስቴር በተላለፈ ትዕዛዝ በዚህ ሚኒስቴር ሥር የቤቶች አስተዳደር ድርጅት ተቋቁሞ በውርስ የተገኙ ቤቶችን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ለመንግሥት ለማድረግ በወጣው አዋጅ 47/67 ተከትሎ በቦርድ የሚመራ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት (ኪቤአድ) ጥቅምት 25 ቀን 1968 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 59/68 ተቋቋመ፡፡ የኪቤአድ በሚባል ስያሜ እስከ ጥቅምት 1998 ዓ.ም. ድረስ ለ30 ዓመታት ሲተዳደር ቆይቶ፣ በአዋጅ 471/98 ከቤቶች ሽያጭ ጽሕፈት ቤት ጋር ተዋህዶ የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ በሚል ስያሜ ከቆየ በኋላ፣ ታኅሳስ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 555/2000  የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ስያሜን አገኘ፡፡ እስከ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በዚሁ ስም ሲጠራ ቆይቶ የተለያዩ ዓላማዎች ተሰጥተውት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 በኮርፖሬሽን አደረጃጀት ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሆኖ፣ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ሥራውን ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ለማጠናቀቅ ሁለት ወራት ብቻ ይቀሩታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ ላለፉት 27 ዓመታት ከቤቶች ግንባታ ውጪ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ቤቶችን ባለመገንባቱ በአሁኑ ጊዜ የፈጠረው ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ረሻድ፡- ትልቅ ተፅዕኖ ነው የፈጠረው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ተቋም ሥራ የጀመረው ጣሊያን በወረራ ጊዜ የገነባቸው ቤቶች፣ የመሳፍትንና የመኳንንት ትርፍ ቤቶች ወደ መንግሥት ንብረትነት ከተሸጋገሩ አንስቶ ቢሆንም፣ በደርግ ሥርዓት በሰፊው የተለያዩ የቁጠባ ቤቶች፣ ትልልቅ አፓርትመንቶች፣ ሆቴሎች፣ በዘመናዊ አሠራር የተገነቡ 508 የምሥራቅ መኖርያ መንደር ሲኤምሲ ቤቶች እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ተገንብተዋል፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት የቤቶች ልማት በከተማ ልማትና ስትራቴጂ በተለያዩ ፕሮግራሞች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ሌሎች አካላት (የከተማ መስተዳድሮች፣ ክልሎች፣ ባለሀብቶች) እንዲያለሙ ሲደረግ፣ ለዚህ ተቋም በቤት ልማት ረገድ ግልጽ ተግባርና ኃላፊነት ስላልተሰጠ ቤቶችን ሳያለማ ቆይቷል፡፡ ተቋሙ ረዥም ዓመት የቆየ ልምድና ተሞክሮ ቢኖረውም ይህን ሥራ አላከናወነም፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሚንፀባረቀው በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል በጣም ሰፊ የሆነ ክፍተት መፈጠሩ፣ እንዲሁም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ቤቶችን ለተለያዩ አካላት የማቅረብ ግዴታ ስለነበረበትና ይህንንም በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም የሌለው በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ፣ በተቋሙ መልካም ገጽታ፣ በተቋሙ ቤት ፈላጊዎችን የማስተናገድ አቅም ላይ ፈተና ከመሆኑም በላይ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እስኪፈጠር ድረስ የራሱን ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም አመራሩ ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩር አድርግውታል፡፡

ሪፖርተርኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት የተቋቋመበት ሕገ ደንብ ተሻሽሎ ወደ ቤቶች ግንባታ እየገባ ይገኛል፡፡ ግንባታውን ለማካሄድ እያደረጋችሁ ያላችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ ረሻድመንግሥት በአሁኑ ጊዜ ይህ ተቋም በጣም አስፈላጊ መሆኑን አምኖ፣ በመንግሥት የልማት ድርጅት አደረጃጀትና የአሠራር ነፃነት ኖሮት ትርፋማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ኮርፖሬሽን ተደርጎ ሲቋቋም ቤት መገንባት፣ ማስገንባት፣ መግዛትና መሸጥ የሚሉትን ተጨማሪና ተቋሙን ወደፊት ሊያራምድ የሚችሉ ወሳኝ ተልዕኮዎች  ተሰጥቶታል፡፡ ይህን ተግባር ለመፈጸም ደግሞ መሟላት የሚገባውቸው ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እያካሄዳችሁ ካላችሁት ቅድመ ዝግጅት ዋና ዋናዎቹን ቢጠቅሱ?

አቶ ረሻድ፡- መመርያው አደረጃጀት ለመፍጠር ነው፡፡ ይህንን ሥራ የሚያከናውን አቅምና ክህሎት ያለው አደረጃጀት መፍጠር የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የቤት ልማት ሥራውን የሚያከናውንና በቅርበት የሚከታተል በዘርፍ ደረጃ እንዲዋቀር የተደረገ ሲሆን፣ የቤት ልማት ዘርፉ በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃና ከሥሩ ከጥናትና ከዲዛይን ዝግጅት፣ ከመሬትና ከመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ ከኮንትራት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ሦስት ዳይሬክቶሬቶች ተደራጅቶና አመራሮችና መሐንዲሶች ተመድበው ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለተኛው የቤት ልማት ፕሮግራም ሰነድ ማዘጋጀት ነው፡፡ የቤት ልማት ፕሮግራም ሰነድ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ የዲዛይኖች ዝግጅት፣ ነባር ዲዛይኖችን መከለስ፣ አዳዲስ ዲዛይኖች ማዘጋጀት፣ የሳይት መሠረተ ልማት ዲዛይን፣ የአፈር ምርመራ፣ የቅየሳና የኮንትራክተሮች የመጀመርያ ዙር መረጣ የማከናወን ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሦስተኛው የመሬት ዝግጅት ሥራ ነው፡፡

የቤት ልማቱ ሲታሰብ ለግንባታ የሚውሉ መሬቶች መጀመርያ በተቋሙ ይዞታዎች፣ ቀጥሎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ በመጠየቅ በሚገኙ ቦታዎች ላይ መገንባት ነው፡፡ በዚህ መሠረት እስካሁን 18.5 ሔክታር የኮርፖሬሽኑ ይዞታዎች ተለይተዋል፡፡ 18.5 ሔክታር የፕላን ስምምነት ተጠይቋል፡፡ 14.3 ሔክታር  የፕላን ስምምነት ተሰጥቷል፡፡ እንዲሁም የግንባታ ፈቃድ ተጠይቋል፡፡ ዲዛይኖቻቸው ያለቁትን የግንባታ ፈቃድ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ 33 በሚደርሱ ሳይቶች ላይ ያሉ መነሳት የሚገባቸው ይዞታዎች እንዲነሱና መቅረብ የሚገባቸውም እንዲቀርቡ በጥናት ተለይቶ ሥራውን ለሚያከናውኑ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ተቋማት መረጃው ተልኮ፣ ሥራው በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ አራተኛው የፋይናንስ አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ ለቤት ግንባታ የሚውል ገንዘብን በተመለከተ ከሦስት የፋይናንስ ምንጮች እንደሚገኝ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፣ ከራስ ወይም ከኮርፖሬሽኑ ገቢ፣ ከመንግሥት የሚገኝ ድጋፍ፣ የኮርፖሬሽኑን ሕንፃዎች በማስያዝ ከባንክ ብድር ማግኘት ናቸው፡፡ ወደ እንቅስቃሴ ሲገባ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሌሎች ከፍተኛ ትኩረትና በጀት የሚጠይቁ ሥራዎች በመኖራቸው ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለጊዜው ማግኘት ባይቻልም፣ ባሉን ሁለት አማራጮች ማለትም ኮርፖሬሽኑ በራሱ ገቢና ከባንክ ከሚገኝ ብድር የቤቶች ግንባታ ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል፡፡ በዚህ መሠረት ሥራው አሁን ባለን የተወሰነ ገንዘብ ተጀምሮ፣ ሌሎች የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት በትኩረት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን ክለሳ ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ የምናገኝበት ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ የባንክ ብድር ሲሆን፣ ከባንክ ለመበደር የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ለማሟላት በሰፊው እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከባንኮች ብደር ለማግኘት ያሏችሁ ቤቶች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ማወቅ ያስፈልጋልና የሀብት ግመታ ሠርታችኋል?

አቶ ረሻድ፡- ሥራው በአማካሪ ድርጅት በጥናት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ሥራ እንደተጠናቀቀ ከባንክ ብድር የምናገኝበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ለዚህም ያሉንን ቤቶች በሁለት በመክፈል፣ የተሻሉና ጥሩ ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉ ቤቶቻችንን በመለየትና ከአጥኚው ድርጅት ጋር በመስማማት ውል በመፈጸም የሀብት ግመታ የተከናወነ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ አልቆ የጥናቱን ውጤት ተረክበናል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ሁኔታዎች ስንመለከት የሦስት ዓመት ስትራጂካዊ ዕቅድ (ከ2010-2011 ዓ.ም.) ላይ በ2010 ዓ.ም. ተቋሙ ቤት መገንባት እንደሚጀምር ቢያስቀምጥም፣ ግንባታውን ግን በ2010 ዓ.ም. መጀመር አልቻለም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የቅድመ ዝግጅት ሥራ በተሟላ ሁኔታ ሳይሠራ፣ ነባራዊ ሁኔታን በደንብ ተረድቶና ተንትኖ ከማቀድ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ክፍተት ሳቢያ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በአሁኑ ደረጃ ግን እነዚህ ክፍተቶች በደንብ ተለይተውና የተቋሙን ትክክለኛ አቅም በማወቅ ወደ ተጨባጭ የግንባታ ሥራ ለመግባት፣ ኮንትራክተር መረጣ ላይ ስለደረስን በጥር ወር የቤቶች ግንባታ ይጀመራል፡፡ በተጨማሪም ለሌሎች አምስት ሳይቶች ጨረታ ለማውጣት ቅድመ ዝግጀት እያጠናቀቅን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቤቶች ኮርፖሬሽን በልማት ምክንያት ተብሎ በአዲስ አበባ በርካታ ቤቶች ፈርሰውበታል፡፡ ለፈረሱት ቤቶች ተገቢውን ካሳ አግኝቷል ተብሎ ይታመናል?

አቶ ረሻድ– እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ፈርሳ እየተገነባች ነው፡፡ የእኛ ቤቶች በአብዛኛው አንደኛ ደረጃ የሚባሉና ቅድሚያ ይለማሉ ተብለው የታቀዱ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ማልማት አገርን ማልማት ስለሆነ ልማቱ በእኛ በኩል የሚደገፍና የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ከአሁን በፊት ቤቶች ሲፈርሱ የነበሩት ከተቋሙ ዕውቅና ውጪ፣ መረጃዎች ሳይደራጁ፣ ልኬቶች በጥንቃቄ ሳይወሰዱና ተገቢው ካሳ ሳይፈጸም በመሆኑ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በተቋሙ በኩልም ችግሮች ነበሩ፡፡ ቤቶችን በደንብ ባለማወቅና በቂ ክትትል ያለማድረግ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀናጅቶ ያለመሥራት ሁኔታዎች በተጨባጭ የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተቋሙ ጋር በቅርብ በቅንጅት እየሠራን እንገኛለን፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ሲደራጅ ቤቶቹ በሀብትነት የተመዘገቡ ስለሆነ፣ የሚፈርሱ ቤቶችን አውቀን ለልማት የሚፈለገው አዲስ አበባን ቢያለማ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል፣ ሲፈርስም ምትክ ቦታዎችን የምናገኝበት ሁኔታ ተመቻችቶ መሆን እንደሚገባው ተነጋግረን በመተማመን፣ ለዚህም የጋራ መግባቢያ ሰነድ በማዘጋጀት ተፈራርመን አብረን እየሠራን ነው፡፡ እስካሁን የፈረሱብን ቤቶች ስንት እንደሆኑና ካሳ የተከፈለና ያልተከፈለ መሆኑን ለማወቅ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመን በ2010 ዓ.ም. ለይተናል፡፡ በዚህ መሠረት እስካሁን ቆጥረን የደረስንባቸው ቤቶች 1,356 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ 376 ቤቶች ካሳ ተከፍሎባቸዋል፡፡ 980 ቤቶች ግን ካሳ ያልተከፈለባቸው መሆኑን በጋራ ኮሚቴው ተረጋግጦ ለውሳኔ ለካቢኔ ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ በፈረሱ ቤቶች ምክንያት ችግሮች እንደገጠሙት ይነገራል፡፡ ችግሮቹ ምንድናቸው?

አቶ ረሻድ፡- አራት ችግሮች ገጥመውናል፡፡ የመጀመርያ ካሳው ከፈረሱት ቤቶች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ለ376 ቤቶች ሰፋፊ ይዞታዎችን ጨምሮ የተከፈለው ካሳ 123 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑ፣ ሁለተኛ ከእነዚህ ቤቶች በየወሩ የሚገኘው ገቢ መቆሙና ለ980 ቤቶች እስካሁን ምንም ካሳ ያለመከፈሉ የተቋሙ ገቢ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ሦስተኛው የተቋሙ ቤቶች መፍረሳቸው ባለመታወቁ ቤቶች እንዳሉ በመውሰድ (ባለመሰረዛቸው) እንደተሰበሰበ ሒሳብ ተወስዶ ሳይሰበሰብ የቀረ በማለት፣ በየዓመቱ የኦዲት አስተያየት በውጭ ኦዲተር በመቅረቡ በፋይናንስ አስተዳደሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ አራተኛው ከዚህ በተጨማሪም ይለማሉ ተብለው ከኮርፖሬሽኑ የተወሰዱ ይዞታዎች በአልሚዎቹ ወይም በከተማ አስተዳደሩ ለረዥም ጊዜ ታጥረው የተቀመጡ፣ ቤቶቹም በባዶነት የሚገኙ በመሆናቸው የሚንፀባረቁ ችግሮች ስላሉ እነዚህን በጋራ ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡– ኮርፖሬሽኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሉትን ቤቶች በቅጡ አያውቅም ነበር፡፡ የቤቶቹን ቁጥር ባለማወቁ የተፈጠረው ችግር ምንድነው?

አቶ ረሻድ፡- ከቀድሞው ተቋም ጀምሮ በኮርፖሬሽኑ ከሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች መካከል ዋና ከቤቶች መረጃ ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ተቋሙ ቤቶችን በተጣራ ሁኔታ ባለማወቁ ምክንያት የመንግሥት ሀብት የሆኑት ቤቶች ለተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት የቤቶችን መረጃ በተጣራ ሁኔታ ለማወቅ የመጀመርያ ተግባር አድርገን የወሰድነው ጥናት ማድረግ በመሆኑ፣ ችግሩን ለይቶ በማውጣት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ጥናት ተከናውኗል፡፡ በዚህም ጥናት ኮርፖሬሽኑ የቤቶቹን መረጃ ባለማወቁ ምክንያት ከተፈጠሩት ችግሮች ዋና ዋናዎቹ፣  በቀዳሚነት ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን ጠንቅቆ አያውቅም ለሚል አሉታዊ አስተያየት መዳረጉና የተበላሸ ገጽታ እንዲኖረው ማድረጉ አንዱ ነው፡፡ ይህም በቤቶች ላይ ሕገወጥ ተግባራት እንዲፈጸሙና ተገቢ ላልሆነ ተጠቃሚነት በር መክፈቱ፣ ከቤት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ችግር መፍጠሩ፣ ከገቢ አሰባሰብ፣ ከፈረሱ ቤቶች ካሳ አከፋፈል ጋር በተያያዘ መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ያለመኖራቸው፣ በውጭ ኦዲት ከተሰጡ አሉታዊ አስተያቶች መካከል አንዱ የቤቶቹን ቁጥር ጠንቅቆ ያለማወቅ በመሆኑ፣ ለኦዲት የተዛባ አስተያየት መዳረጉና ሌሎችም ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የቤቶች ቆጠራ የተካሄደበት ሒደትና የተገኘው ውጤት ምን ይመስላል?

አቶ ረሻድ፡- ኮርፖሬሽኑ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታት ገጽታውን ለመገንባትና የተሳለጠ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት በአዲሱ አመራር ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ፣ የቤቶች ቆጠራ በማከናወን የተሟላ የቤቶች መረጃ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የቤቶችን ቆጠራ ለማከናወን የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት የውስጥ አቅሙን በመገንባትና አንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያሉና ሌሎች ተቋማትን በማሳተፍ ወደ ቤት ቆጠራ ሥራ ገብቷል፡፡

በቅድሚያ በሥራው ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት፣ ግብዓቶችን በማሟላት፣ ቆጠራውን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል 120 የመረጃ ማሰባሰቢያ ታብሌቶችን ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በመረከብ የቆጠራው ሥራ ተጀምሯል፡፡ በተለይም ቆጠራውን በታብሌት ማከናወኑ የመረጃው ጥራት፣ ትክክለኛነት፣ ወጪ ቆጣቢነት፣ ወቅታዊነት፣ ደኅንነትና ቁጥጥር ላይ የራሱ አዎንታዊ ሚና እንዲኖረው አድርጓል፡፡ አስቀድሞ ለሥራው 7.8 ሚሊዮን ብር የተመደበ ቢሆንም፣ በውስጥ አቅም በመሠረት ሥራው ከተያዘው በጀት በግማሽ በመቀነስ ወጪን በቆጠበ ሁኔታ ለማከናወን ተችሏል፡፡ ይህ የቤት ቆጠራ ሥራ በቅድሚያ ማኅደር ማጥራትን በማጠናቀቅ፣ በማኅደር ያለውን መረጃ በመስክ ላይ የማነፃፀርና የማረጋገጥ ሥራ  ተከናውኗል፡፡ በመቀጠልም የመረጃ ትንተና ለማከናወንና መረጃውን ወደ ሶፍት ኮፒ ለመቀየር የሚያስችል ሥራ ተከናውኗል፡፡ በሒደቱም ማኅደር ሳይኖራቸው በአካል መሬት ላይ ቤቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህም ማኅደሮችንና መረጃዎችን በማጥፋት ቤቶችን ወደ ግለሰብ ለማዞር የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የቤቶቹ ማኅደሮች እያሉ መሬት ላይ ቤቶቹ የማይገኙበት አጋጣሚም በቆጠራው ከታዩ ክስተቶች ሌላው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ሁለት ነበሩ፡፡ ቤቶችን ወደ አንድ በመቀላቀል ሕገወጥ ድርጊት ለመፈጸሙ ምስክር ይሆናሉ፡፡ ይህም ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን ባለመገንባቱ ምክንያት በዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ዓይነት መንገድ ኮርፖሬሽኑ እጅ የሚወጡ ቤቶች አደጋ የሚፈጥሩና ለቤቶች እጥረት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንዲሁም የንግድ ቤቶችን ወደ መኖሪያ፣ የመኖሪያ ቤቶችን ወደ ንግድ የመቀየር፣ ሕገወጥ ግንባታዎችን መፈጸም፣ የኮርፖሬሽኑ ይዞታዎች ላይ በግለሰቦች ግንባታ የሚፈጸም መሆኑ፣ በቁጥርም ሆነ በቤቶቹ ዓይነትና መጠን ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን በቆጠራ ሒደት መለየት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ወደዚህ ውሳኔ ተገብቶ የቤቶች ቆጠራ ማከናወኑ ኮርፖሬሽኑ ላይ ከተጋረጡበት አደጋዎች በቀጣይም ሊፈጠሩ ከሚችሉ ችግሮች ተቋሙን ማዳን ከመቻሉም በላይ፣ የቤት አስተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮርፖሬሽኑ የንግድም ሆነ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ አነስተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህንን ለማስተካከል የጀመራችሁት ሥራ ነበርና ከምን ደረሰ?

አቶ ረሻድ፡- ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ሲደራጅ እንደ ዓላማ ከተሰጡት አንዱ፣ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች የኪራይ ተመን በማጥናት ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ኮርፖሬሽኑ ይህንን ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ ጥናት ማድረግ እንዳለበት ስለታመነ፣ የኮርፖሬሽኑን የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላትና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የጥናቱን ሥራ ለረዥም ጊዜ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጥናት በተገኙት ውጤቶች አሁን እየተሠራበት ያለው የኪራይ ተመን ለረዥም ጊዜ ሳይከለስ የቆየና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና በጣም አነስተኛ መሆኑ፣ እየተከፈለ ያለው ኪራይ ወጥነት የጎደለው፣ በጣም የተዘበራረቀና የተለያየ የኪራይ አከፋፈል ተመን የሚከተል ሲሆን እነዚህም የጨረታ፣ የጨረታ መነሻ፣ መደበኛ፣ የተከራይ አከራይ፣ ለሦስተኛ ወገን ሲተላለፉ የሚከራዩበት የኪራይ አከፋፈል ሥርዓት ችግር የፈጠረ መሆኑ፣ ከሌሎች የመንግሥትም ሆነ የግል የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን አኳያ ሲነፃፀር በጣም የተራራቀና የኮርፖሬሽኑ የኪራይ ተመን አነስተኛ፣ ፍትሐዊነት የጎደለውና በተከራዮች መካከል ጤናማ ያልሆነ ውድድር እንዲኖር ምክንያት ሆኗል፡፡ የኪራይ ተመኑ በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ አንዳንድ ሰዎች ያለምንም ልፋት ቁልፍ በየጊዜው እየሸጡ ያልተገባቸውን ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩ በተጨባጭ የታዩ ችግሮች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ችግሮች በመፍታት የምትወስዷቸው ዕርምጃዎች ምንድናቸው?

አቶ ረሻድ፡- ከእነዚህ ተጨባጭ እውነታዎች በመነሳት እነዚህን ችግሮች ፈትቶ ወደ ትክክለኛ ጎዳና በማምጣት ሕጋዊነትን ማረጋገጥ፣ ጤናማ የገበያ ውድድርን ማጎልበት፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የኪራይ ተመን አሠራሩን ማስተካከልና ወጥ ማድረግ፣ ኮርሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች የተሻለ ገቢ እንዲሰበስብ ማድረግና ለቤት ልማቱ እንዲውል ማድረግ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለመቅረፍ የሄደበት መንገድ ነባር ተከራዮችን በረባ ባልረባ ምክንያት ማፈናቀል መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ እውነት አይደል?

አቶ ረሻድ፡- ይህ የተዛባ አስተያየት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሚመራበት ሕግና ሥርዓት አለው፡፡ ቤቶች እንዴት እንደሚከራዩ፣ እንዴት እንደሚለቀቁና ሌሎችንም የቤት አስተዳደር ሥራን የምንመራበት የቤት አስተዳደር መመርያ በአዲስ ሁኔታ አዘጋጅተናል፡፡ በዚህም ቀድሞ ይንፀባረቁ የነበሩ የፍትሐዊነትና የቅሬታ ምክንያቶችንም በመለየት መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በዚህ ሒደት ሕገወጥ የቤት አጠቃቀምን በነበረበት ሁኔታ ለማስቀጠል፣ ያላግባብ የተያዙ ቤቶች ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ የማድረግ አዝማሚያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ይህንን ለማስተካከል በሕጋዊ መንገድ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከመመርያና ከአሠራር ውጪ የኮርፖሬሽኑን ቤቶች በሕገወጥ መንገድ በያዙና ባስተላለፉ ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ በተለይም ቤት እያላቸው በመንግሥት ቤት የሚኖሩ፣ የኮርፖሬሽኑን ቤት ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፉ፣ ቤት የመሥራት አቅም ኖሯቸው በመንግሥት ቤት እስከ 40 ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ በአነስተኛ ኪራይ እየተገለገሉ የሚገኙ፣ ለቤት ልማት የሚውሉ ሰፋፊ ይዞታዎችን ይዘው የተቀመጡ፣ እንዲሁም በቤቶች ላይ ሕገወጥ ግንባታዎችን የፈጸሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ያላግባብ ዕርምጃ ተወስዶብኛል የሚል አካል ካለ፣ በተዘረጋው የቅሬታ አፈታት ሥርዓት መሠረት በየወቅቱ ቅሬታን እየመረመርን ምላሽ እየሰጠን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከተዋቀረ በኋላ በሪፎርም ውስጥ ይገኛል፡፡ ሪፎርሙ የሚያነጣጥረው ምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ነው?

አቶ ረሻድ፡– የቀድሞው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ወደ ኮርፖሬሽን እንዲለወጥ መነሻ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ፣ የአገልግሎት አሰጣጡና የደንበኞች ዕርካታ ያለበትን የማስፈጸም አቅም ችግሮችን በዝርዝር በመፈተሽ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የሰው ኃይል ሁኔታን ማስተካከል በማስፈለጉ ተቋሙ ወደ ልማት ድርጅትነት እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በዚህ መነሻ በሪፎርማችን ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለው በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የመጀመርያ የአቅም ግንባታ ነው፡፡ የሰው ኃይል ስንል አመራሩና አጠቃላይ በተዋረድ ያለውን ሠራተኛ የሚያጠቃልል ነው፡፡ አመራሩ የለውጥ አመራር ነው ወይ? አመራሩ በዕውቀትና በብቃት ተቋሙን የመምራት ቁመናው ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ምን ይመስላል? የሚጎሉትን ነገሮች ካሉ እንዴት ይሞላል? ‹ኮርፖሬት ገቨርናንስ› ጽንሰ ሐሳብ ገብቶት ለውጤት፣ ለትርፋማነትና ለተወዳዳሪነት እየሠራ ነው ወይ? በተመሳሳይ ሠራተኛው ከትናንትናው አመለካከት ወጥቶ በልማት ድርጅት አስተሳሰብና በአዲስ ትርፋማነት ሐሳብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፣ ተቋሙ ሲያድግ አብሬ አድጋለሁ፣ ትርፋማ ሲሆን እኔም ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ ማሰብና መሥራት ጀምሯል ወይ? የሚለውን አጠቃላይ የአመለካከት ችግሮችን በመቅረፍ አመራሩና ሠራተኛው ተቀራርበው ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግና የማስፈጸም አቅም ክፍተትን የመለየትና ክፍተቱን ለመሙላት የመጀመርያ ደረጃ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ በዚህም ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ታሳቢ ተደርጎ በተጨባጭ በአመራሩም ሆነ በሠራተኛው ላይ ለውጦች እየመጡ ይገኛሉ፡፡ ሁለተኛው የአሠራር ማስተካከያዎች ናቸው፡፡ በአሠራር ረገድ የሚያሠሩና ለውጤታማነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉትን አሠራሮች፣ በጥናት የመለየትና የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም የሚያጠቃልለው አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሚያሰፍኑ መመርያዎችን፣ ማንዋሎችንና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች አዘጋጅተን ተግባር ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው፡፡ ከውጭ ባለድርሻ አካላት፣ በተለይም ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከፍትሕ አካላትና ከሌሎችም ጋር ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነቶችን የማድረግ፣ ከደንበኞች ጋር በቅንጅትና በወጪ መጋራት ለመሥራት የሚያስችሉ ሥራዎችንና መድረኮችን የመፍጠር ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ገቢን የማሳደግና ወጪን የመቆጠብ ሥራዎች ናቸው፡፡ በሪፎርሙ አዳዲስና ተጨማሪ ተልዕኮዎች ለኮርፖሬሽኑ ስለተሰጡ፣ ይህንን የሚያስፈጽምበትን ገቢ ማግኘት የግድ ይላል፡፡ ለዚህም ያሉትን የገቢ ምንጮች በመለየት ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ሥራ  እየተከናወነ ነው፡፡ እስካሁን ያልተለዩትን የገቢ ምንጮች ለምሳሌ ከ20 ዓመታት በላይ ተዘግተው የተቀመጡ መጋዘኖችን ማከራየት፣ ለሚሰጠው አገልግሎት በትንሹ ማስከፈል፣ የአገልግሎት ዓይነቶች መጨመር፣ የኪራይ ተመን ክለሳ ማድረግ፣ ወጪን መቀነስና ገቢን ማሳደግ፣ አገልግሎትን የማዘመንና ለቤት ግንባታ የሚውሉ ገቢዎችን ለማግኘት ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በውጭ ኃይል ለመሥራት በዕቅድ ተይዘው የነበሩትን የጥገና፣ የቤቶች ቆጠራ፣ ንብረትና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የውጭ ቁጠባ ሥራም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ሌላው ከጥገና ጋር ያሉትን ችግሮች የመለየትና የመፍታት ሪፎርም ነው፡፡

የተቋሙ ቤቶች ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ በመሆናቸው በየጊዜው ጥገናና ዕድሳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ብሮች ወጪ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ከሚነሱ የተገልጋይ ቅሬታዎች ቤቶቹ ጥገናና ዕድሳት ጊዜውን ጠብቆ አይደረግም፣ ፍጥነት የላቸውም፣ ጥራት ያለው ጥገና አይካሄድምና የመሳሰሉት ይነሳሉ፡፡ ይህ ችግር በተቋሙ በኩል የሚታዩ ቢሆንም በተገልጋይ በኩልም የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ለጥቃቅን ጥገና ተቋሙን መጠበቅ፣ በአግባቡ ካለመጠቀም የሚፈጠሩ ችግሮች የራስ ችግር አድርጎ ያለመውሰድ፣ የጥገና ወጪን ያለመጋራት፣ ከአቅም በላይ የሆነ ጥገና በየጊዜው መጠየቅና የመሳሰሉት በተገልጋይ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወንን ነው፡፡ የጥገና አሠራችንን በማስተካከል፣ በተቋሙና በተገልጋይ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመለየት የመመርያ አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣ ሁለቱም አካላት መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ የጥገና መመርያ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ የጥገናና ዕድሳት ስታንዳርድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የጥገና ዓይነቶችን በሦስት ደረጃዎች በመክፈል እነዚህ ደረጃዎች የሚወስዱት ጊዜ፣ ገንዘብና ጥራት በማስቀመጥ የጥገና ችግሮችን ለመፍታት እየሠራን እንገኛለኝ፡፡ በዚህም ደንበኞች የሚጠግኑት፣ ኮርፖሬሽኑ የሚጠግናቸውና በውጭ አቅም የሚጠገኑ ሥራዎች በግልጽ እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ በተለይም አነስተኛ የጥገና ሥራዎች በደንበኞች በራሳቸው የሚፈጸምበት አሠራር እንዲኖር ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ እየተካሄደ ያለው ሪፎርም በተሟላ ሁኔታ የተቋሙን መሠረታዊ ችግር እንዲፈታ እየሠራን እንገኛለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በምትጀምሩት የቤቶች ግንባታ የምትከተሉት የግንባታ አሠራር (ቴክኖሎጂ) ምን ዓይነት ቁም ነገሮችን ከግምት ያስገባ ነው?

አቶ ረሻድ፡- በመጀመርያ ምዕራፍ የሚገነቡትን ቤቶች የተለመደውን የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የምንጀምር ሲሆን፣ በቀጣይ ለሚገነቡት የፕሪፋብና ሌሎች አዳዲስ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በፍጥነት በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቁ የሚችሉበትን በጥናት እየለየን እንገኛለን፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እስከ ዛሬ በማገልገል ላይ የሚገኙትን ሕንፃዎችና የቀድሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት አፓርትመንቶች እንደ ዝቅተኛ መነሻ በመውሰድ፣ የተሻሉ ጥራት ያላቸው ሕንፃዎች የሚገለገሉበት የዲዛይን ሰነዶች ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተገጣጣሚ ቤት የግንባታ አማራጭ የያዘ የጥናት ሰነድ ለማዘጋጀት በተያዘው ዕቅድ መሠረት የተገጣጣሚ የሕንፃ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ የተገጣጣሚ የሕንፃ ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት፣ በአገራችን ያለ የተገጣጣሚ ሕንፃ ቴክኖሎጂ ተሞክሮ፣ ኮርፖሬሽኑን የተገጣጣሚንፃ ግንባታ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚገፋፉ እውነታዎች፣ ኮርፖሬሽኑ በራስ ወይም በመንግሥት ፋብሪካውን ለማቋቋም የሚያስኬዱ አማራጮች፣ ወደ ፕሪፋብ ቴክኖሎጂ ቢገባ ሊደረጉ ስለሚገባቸው አካሄዶች ሐሳቦችን ያካተተ ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በለውጥ ሒደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህን የለውጥ ሥራዎች በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ለማከናወን እንዲቻል አመራሩና ሠራተኛው በተቀናጀ ሁኔታ መንቀሳቀሳቸው አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች