Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአየር መንገዱን ፈርጀ ብዙነት እንጠቀምበት 

በኢትዮጵያ ስኬታማ ብለን ስም ልንጠቅሳቸው ከምንችላቸው ጥቂት መንግሥታዊ ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በቀዳሚነት የምናስቀምጥበት በርካታ መገለጫዎች አሉት፡፡

ከ70 ዓመታት በላይ መልካም ስሙን ይዞ ተጉዟል፡፡ ባንዲራችንን አንግቦ በዓለም ላይ መብረር መቻሉና ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ሥራው ብቻ ነጥለን ብናየው እንኳ ባለውለታነቱ ይጎላል፡፡

አንድ የቢዝነስ ተቋም ስኬታማነቱን ሊገልጹና ሊያሳዩ የሚችሉ መመዘኛዎችን ስለማሟላቱም በተደጋጋሚ የሚነገርለት፣ ለዚህም ዕውቅና ያልተለየው መሆኑ መገለጫው ነው፡፡ ራሱን የበለጠ እያደራጀ ከዘመን ዘመን መሻገሩና ዓለም አቀፍ ስም ያተረፈ ኩባንያ መሆን መቻሉ፣ አየር መንገዱን ከፍ እንድናደርገው ያስገድደናል፡፡ በአጠቃላይ የአየር መንገዱ የዕድገት ደረጃ ሲታይ ለሌሎች አገር በቀልና አኅጉር አቀፍ ኩባንያዎች ተምሳሌትነቱን የምንጠቅስለት በርካታ መገለጫዎች አሉት፡፡

ይህ ሲባል ግን የአየር መንገዱ የዓመታት የስኬት ጉዞ ጉድለት አልነበረበትም ማለት አይደለም፡፡ በርካታ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ በተለያዩ ወገኖች ሲገለጽ እንሰማለን፡፡ አሉበት ከሚባሉት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቹ በላይ ግን ስኬቶቹ ጎልተው ይታያሉ፡፡ የትናንት ታሪኩ፣ የዛሬ ክንውኑና የነገ ውጥኑ ሚዛን ይደፋሉ፡፡ የአየር መንገዱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጠለቅ ብለን ስናየው፣ እዚህ እየጠቃቀስን ካለውም በላይ አገርና ሕዝብን በሚጠቅም መንገድ ሊከውናቸው የሚገቡ ጉዳዮችም እደሚኖሩ እንገነዘባለን፡፡ በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የቢዝነስ ሥራዎች ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመፍጠር የአየር መንገዱን ጠቀሜታ መስፋት እንደሚቻል ማውሳት እንችላለን፡፡ አየር መንገዱ እየተስፋፋ በመሔድ በአየር መንገዱ መኖር ብቻ የተጓዳኝ ኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ሌሎችም ዕድሎችን በመፍጠር በአየር መንገዱ እንቅስቃሴ የምትተዳደር ከተማ መፍጠር የሚችልበት አቅም ያለው ግዙፍ ኩባንያ እየሆነ እንደሚሄድ ይታሰበኛል፡፡

ይሁንና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው አሠራሮች የደረጀው አየር መንገዱ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አንፃርና ከአገልግሎት አሰጣጡ ባህሪይ አኳያ፣ የቢዝነስ ትስስሮቹ በአብዛኛው ለውጭ ኩባንያዎች ያደሉ ሆነው ይታያሉ፡፡ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ያለው የቢዝነስ ግንኙነት ጎልቶ መታየቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ቁመና ለመያዝ የሚተገብረው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡

የቢዝነስ ትስስሮቹ ሁሉ የግድ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ብቻ መሆን አለበት የሚል አቋም እንደሌለው ዕሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ በብዙዎች ዘንድ እንደሚነገረው፣ ከአገር ውስጥ ተቋማት ጋር ተባብሮ በቀላሉ ሊሠራቸው የሚችላቸው ሥራዎች ላይ ትኩረቱ እምብዛም ነው የሚለው አስተያየት እንዲሁ የሚጣል አይደለም፡፡

ከውጭ ኩባንያዎች ግዥ የሚፈጽምባቸው ጉዳዮች ከአገር ውስጥ ማግኘት የሚችላቸው ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ግዥዎችን መፈጸም የሚችልባቸውን መንገዶች ቢያመቻች፣ ለውጭ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ የሚያወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረት ወይም መቀነስ ይቻል እንደሚቻል ስለሚታመን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማስቀረቱ ብቻም ሳይሆን፣ ለአገር በቀል ኩባንያዎች ሰፊ የገበያ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውና ባለውለታነቱን በሌላ ምግባሩ ልናወድሰው ያስችለን ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ሐሳብ ለመሰንዘር የወደድኩት አንዳንዴ እዚህ አገር ውስጥ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ አንዳንድ ምርቶችን ከውጭ የማስገባቱ አባዜ እየቀነሰ መሄድ አለበት ከሚል መነሻ ነው፡፡

ለምሳሌ አየር መንገዱ ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጣባቸው ግብዓቶች ውስጥ አንዱ በበረራ ወቅት ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን ምግብ ለማዘጋጀትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚጠቀምባቸው ማሸጊያዎችን ከአገር ውስጥ ገበያ ለምን አይገዛም? የሚል ሐሳብ መሰንዘር አንደኛው ነው፡፡ አስተያየቴ ለዚህ ሥራ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ቢያሳትፍ ምናለ? ከሚል አገራዊ ቁጭት የመነጨ ነው፡፡ በራሱ ተቋም ውስጥ እዚሁ ለሚሰናዳው የምግብ ምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከአገር ውስጥ ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ እያለ ለውጭ ገበያ የማድላቱን ነገር ለምን? የሚል ለማለት ነው፡፡  

ከዚህ አኳያ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሳትፎ ብዙም የታሰበበት አለመሆኑ ቢታይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምግብ ዝግጅቱ የሚያስፈልጉ የአትክልት ምርቶችን ከአገር ውስጥ እየገዛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ መልካም ጅምር ሌሎች ግብዓቶችንም ማካተት ይገባዋል፡፡

በየዓመቱ ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው መንገደኛ የሚቀርበው የምግብና መጠጥ ምርት ከውጭ ኩባንያዎች የሚመነጭ ሆኖ መቀጠል የለበትም፡፡ በዚህ ዘርፍ በአገር ውስጥ ምርቶች ለመጠቀም ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ስኳርና ጨው ሳይቀር ከውጭ የሚገዛው እስከ መቼ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡ ለምግብና ማሸጊያዎችስ እዚህ አይመረቱም? አፍ ማበሻ ወረቀትስ የለንም?

የምግብ ግብዓቶችን እንደ ምሳሌ ተነሱ እንጂ አየር መንገዱ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ ከሚያወጣባቸው አጠቃላይ ግዥዎች ውስጥ አንዳንድ ምርቶች በአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲቀርቡ በማድረግ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲበረታቱ ማድረግ ይቻል እንደነበር መጠቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ፎጣ፣ ብርድ ልብስ፣ ካልሲና የመሳሰሉት ሸቀጦች ወጪ ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉትን አገር ውስጥ ማስመረት የሚቻልበት ዕድል የለም ወይ? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ምንም እንኳ አየርመንገዱ ከአገር ውስጥ ብዙም አይገዛም ይባል እንጂ፣ ችግሩ የአቅርቦትና የጥራት እንደሚሆንም ግልጽ ነው፡፡ አየር መንገዱ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በብዛትና በጥራትና በዘላቂነትና በአስተማማኝነት ሊያቀርቡ የሚችሉ ኩባንያዎች የትኞቹ ናቸው ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡ አየር መንገዱ በሚፈልገው የጥራት ደረጃ ልክ ለማምረት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በማወቅ የሚፈለገውን ምርት አምርተው ራሳቸውንም ይጠቅማሉ፡፡ ከውጭ የሚወጣውን በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን በማዳን አገርን በአቅማቸው በታደጉ ነበር፡፡

ይሁንና አየር መንገዱ በጀመራቸው ጥረቶች መሠረት ከአገር ውስጥ እንደሚፈልገው በጥራትና በብዛት ማምረትና ማቅረብ የሚችል አካል ያገኘ አይመስልም፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ደረጃ እንኳ ፍላጎቱን የሚያሟላለት እንዳላገኘ መገንዘብ ተችሏል፡፡ እንዲህ ያለውን አቅመ ደካማነት በአፋጣኝ በመለወጥ አየር መንገዱን መጠጋትና ምርትን እንደሚገባ ማቅረቡ ለአየር መንገዱም፣ ለአቅራቢውም፣ ለአገርም ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያተርፋልና ይታሰብበት፡፡

በተለይ የአየር መንገዱ ሆቴል ሥራ መጀመር በራሱም ሆነ ከሌሎች ተባባሪ ኩባንያዎች ጋር በመሆን አገልግሎቱን ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት በሩን ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ አየር መንግዳችንን የበለጠ የምናወድስበትና ተጨማሪ አገራዊ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲሰጥ የበኩሉን ያድርግ፡፡ በእርግጥም አየር መንገዱ ይህንን ዕድል በመጠቀም አዲስ ነገር እንደሚሠራ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እኛም አብረነው እንበራለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት