በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የመነጋገሪያና የመከራከሪያ አጀንዳ ከሆነ እጅግ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በጦርነትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱና ቁርሾ ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማከም ይቻል ዘንድ፣ አገራዊ ዕርቅና መግባባት ያስፈልጋል የሚሉ በርካቶች ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፡፡
ይሁንና በዚህ ዓመት የተለየ አቋም እስከሚያንፀባርቅ ድረስ፣ የዚህ ሐሳብ ዋነኛ ተቃዋሚ በመሆንና አስፈላጊ አይደለም በማለት ጠንካራ አቋም ይዞ የቆየው ኢሕአዴግ ነበር፡፡ ይህም አኩራፊው በዝቶ ጦር መዛዡ እንዲበራከትና ጫካ የገባውም ሳይወጣ እንዲቀር ያደረገ ክፍተት ፈጥሯል ተብሎ፣ በርካቶች የሰላ ትችት እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲያውም ሟቹ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ለረዥም ጊዜ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ፣ አገራዊ ዕርቅና መግባባት ላይ ሠርተው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከደቡብ አፍሪካ የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንትና የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ ያልተናነሰ ክብርና ጀግንነትን ሊጎናፀፉ ይችሉ ነበር በማለት አስታያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡
ሆኖም ኢሕአዴግ ‹‹የተጣላና የሚታረቅ ሕዝብም ሆነ ብሔር የለም›› በሚል አመክንዮ፣ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲደረግ የሚጠይቁ አካላትን በሙሉ እንደገፋቸውና ክርክራቸውም ሆነ ምክራቸው መና እንዲሆን በስፋት በስፋት ይወቀሳል፡፡ ይህም የኢሕአዴግ ምላሽ እስካሁን በአገሪቱ በነበሩ ታሪካዊ ክስተቶች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለማከም እንዳላስቻለ፣ እነዚህን ቁርሾዎች በሙሉ ልብ ለመፍታት ከተፈለገ አገራዊ ዕርቅና መግባባትን ማምጣት ግድ እንደሚል፣ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ለማቋቋም ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ያስረዳል፡፡
በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ እንዳሰፈረው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ውጤቶችን ለማከም፣ እውነትና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ዕርቅ አስፈላጊ በመሆኑ›› ተብሎ፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲቋቋም መደረጉ ታትቷል፡፡ ረቂቁ በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች የተደነገጉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃዎች ሳይሸራረፉ ለመተግበርና በተደጋጋሚ የተከሰቱ የመብት ጥሰቶችን በመለየት ደግሞ እንዳይከሰቱ ለማድረግ፣ ብሎም አጥፊዎች ተለይተው ይቅርታ እንዲጠይቁና እንዲፀፀቱ የሚያደርግ ሥርዓት በኮሚሽኑ እንደሚበጅ ተደንግጓል፡፡
የአዋጁን ረቂቅ ለማብራራት የቀረበው ሰነድ ይኼንን ቢልም፣ ካሁን በፊት የነበረውን የዕርቀ ሰላም ጉዳይ የተመለከተ አስተሳሰብ በኢሕአዴግ በኩል የተጣላ ብሔርም ሆነ ሕዝብ ባለመኖሩ የሚፈለገው ጉዳይ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ከሆነ፣ ይህ የፖሊሲ ልዩነት ስለሆነ አግባብ ነው በሚልና ሁሉም ለሚከተለው ርዕዮተ ዓለም መታገል እንጂ፣ በዕርቅ የሚፈታ ጉዳይ እንዳልሆነ ክርክር እንዳለ ይገለጻል፡፡ ‹‹ዕርቅ በዳይና ተበዳይ አለ የሚል መልዕክት ስለሚይዝ በዳይ ማን ነው? ይቅርታ ጠያቂውስ የቱ ነው? ይኼንን ለመመርመር ወደ ኋላ ሄደን እናጥና ብንልስ ክርክሩ የከፋ አታካራ አይፈጥርም ወይ?›› በማለት ይኼንን ዓይነቱ አሠራር በአገሪቱ እንዳይተገበር ማድረጉም ተብራርቷል፡፡
ነገር ግን በቃላት ከመጫወት ይልቅ ሁሉም ተበደልኩ ባይ ስለሆነ በሁሉም ልብ ያለውና ከስሜት አልፎ ወደ ተግባር እያለፈ የመጣውን የቂምና የበቀል ስሜት ማስወገድ በማስፈለጉ፣ ኮሚሽኑን ማቋቋም እንዳስፈለገም ተተንትኗል፡፡
ኮሚሽኑም ችግሮችን፣ ተበዳይና በደሎችን፣ የበዳዮችንም ማንነት በመለየትና ቁርሾው ምን እንደሆነ በማጥናትና በመመርመር፣ ‹‹በራሱ እዚያው እያስታረቀ በአገር ደረጃ ዕርቀ ሰላም ለማካሄድ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችና የውሳኔ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ይሆናል፤›› ሲልም የኮሚሽኑን ሥራ ማብራሪያው ይገልጻል፡፡
የዚህ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለይ ከኢሕአዴግ ወገን በመምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱን ሲንጣት በነበረው አመፅ ወቅት፣ ጉዳዩን እንደ ብቸኛ የመፍትሔ አቅጣጫ አድርገው አስታያየታቸውን ሲለግሱ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ከገለልተኛ ተጎጂዎች ወገን ይበል የሚለው ቃል እየተደመጠ ነው፡፡
የዚህ ተስፋም በተወሰነ መልኩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሥልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ገደማ በሰጡት መግለጫ መገለጹን የሚያወሱ አሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የሆኑ እስረኞችን መፍታት፣ ለማኅበራዊ ቁርሾ መታከም ያግዛል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ዕርቀ ሰላም በማውረድና አገራዊ መግባባት በማምጣት ላይ ለመወያየት የአዋጁ መምጣት ምክንያት ጊዜው አሁን እንደሆነ፣ በዚህም ረገድ ረቂቅ አዋጁ በርካታ ጉዳዮችን ለማስተካከል እንደሚረዳ ተስፋ የሰነቀ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለይ ካሁን ቀደም በመንግሥት ገለልተኛ ተብለው የተቋቋሙ ተቋማት ላይ ይቀርቡ የነበሩ ትችቶችን ከጅምሩ ለመቅረፍ ያስችለዋል፣ የሚል ተስፋም በበርካቶች ዘንድ እንዲያድር አድርጓል፡፡
ለዚህም መነሻ የሆነው በአዋጁ መግቢያ ላይ የተደነገገው የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባራትን በተመለከተ የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡
አዋጁ በመግቢያው፣ ‹‹ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ እየፈረሰ የሚሠራ ሳይሆን እየተገነባ የሚሄድ ሥርዓት ለመፍጠር፣ ዴሞክራሲያዊ አገርና ማኅበረሰብ ለመገንባት ሰፊና ተቀባይነት ያለው የእውነተኛ የዕርቅና የሰላም ዓላማ ያነገበ፣ ለግጭትና ለቁርሾ ምክንያት የሆኑትን ዝንፈቶች፣ ምክንያቶችና የስፋት መጠን አጣርቶ እውነታውን በማውጣት ተመልሰው እንዳይመጡ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራዊ ዕርምጃዎችን የሚወስድና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመነጭ ገለልተኛና ነፃ ኮሚሽን፤›› እንደሚቋቋም ተጠቅሷል፡፡ ይህ በተጨማሪ በረቂቅ አንቀጽ 12 ላይ ተደንግጓል፡፡
ምንም እንኳን ከተቃዋሚዎች ጎራም ሆነ ከሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ያገቡኛል ከሚሉ ወገኖች የአዋጁ ጥንስስ በሐሳብ ደረጃ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ በአዋጁ ቅርፅና የተጣደፈ በሚመስለው ዝግጅቱ ምክንያት ትችቶች መቅረባቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ የሚነሳው አንድ ጉዳይ ሰነዱ ምንም ዓይነት ትርጉሞችን ያልያዘና አሻሚ የሆኑ አገላለጾች የበዙበት መሆኑ ነው፡፡
ለአብነት ያህል የአዋጁን ዝግጅት አስመልክተው በእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አስተያየታቸውን ያሠፈሩት የሕግ ባለሙያውና ዓለም አቀፍ አማካሪው አቶ ሳሙኤል ዓለሙ፣ ‹‹ዕርቀ ሰላም ቃሉ ምን ማለት ነው በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አያይዘውም አገሪቱ ፈታኝ ብሔር ተኮርና ማኅበራዊ ግጭቶችን እንዳስተናገደች፣ በግጭቶች ምክንያትም እንደተከፋፈለች ያስረዳሉ፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ሕዝቡ ኑሮውን ለማሸነፍ ቢታገልም፣ የአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ግንኙነቶች ብዙም እንዳልተሻሻሉና እስካሁንም የግጭት ታሪክ እንዳለ ይሞግታሉ፡፡
‹ዴሞክራቲክ ዲያሎግ› ለተባለ ተቋም ጥናት ያቀረቡት ብራንዲን ሀምበርና ግሬይን ኬሊ ለዕርቀ ሰላም መምጣት አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም እርስ በርሱ የሚደጋገፍና ፍትሐዊ የሆነ ማኅበረሰብ የጋራ ራዕይ ማጎልበት፣ ያለፈውን መቀበልና መፍትሔ መስጠት፣ አዎንታዊ ግንኙነቶችን መመሥረት፣ ወሳኝ ባህላዊና የአመለካከት ለውጥ ማምጣትና ግዙፍ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ለውጦችን ማምጣት ናቸው፡፡
ሀምበርና ኬሊ አክለውም፣ ‹‹ከግጭቶች በኋላ ዕርቀ ሰላም አስፈላጊ ሒደት ነው፡፡ ነገር ግን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንጂ አስገዳጅ መሆን እንደማይገባ እናምናለን፤›› ሲሉም ይመክራሉ፡፡ ያምሆነ ይህ ግን፣ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል የዕርቅ ሰላም ትርጉም የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲቋቋም አብሮ እየተነሱ ያሉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች የመጀመርያው፣ አዋጁ ስለብሔራዊ መግባባት ስለሚያወሳ፣ ከብሔራዊ ዕርቅና ከብሔራዊ መግባባት የትኛው መቅደም አለበት የሚለው ነው፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ታዋቂው ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ይህ ቀላል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የሚደረገው ብሔራዊ ዕርቅ ወደ ብሔራዊ መግባባት ይወስዳል ብለውም ያምናሉ፡፡
‹‹በመጀመርያ ይህ ሐሳብ ከኢሕአዴግ መምጣቱ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የተጣላ ስለሌለ ዕርቅ አያስፈልግም ይል ነበርና፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብዙ የጦርነት ታሪክ ያሳለፍን በመሆኑ፣ አንዱ የችግሮቻችን መፍቻ ዕርቀ ሰላም ነው፡፡ ዕርቀ ሰላሙ ለአገራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና ሊጫወት ይችላል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ነገር ግን ለዚህ መሳካት ዋነኛው ተዋናይ ሊሆን የሚችለው ኢሕአዴግ፣ ጉዳዩን እስከ መጨረሻው ለመውሰድ የሚያሳየው ቁርጠኝነት ትልቁን ቦታ ይወስዳል ባይ ናቸው፡፡ ይህም መገለጫው የሚሆነው ፖለቲካውን ማስተካከል እንደሆነና ያለበለዚያ የኮሚሽኑ መቋቋም ከንቱ እንደሚሆን ያክላሉ፡፡
‹‹ቁስሉ መታከም አለበት፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ዕርቅ ሊመጣ የሚችለው ፖለቲካው ሲስተካከል ነው፡፡ ካልሆነ ተጨማሪ ቁርሾ ያመጣል፤›› ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ከዕርቅ በላይ ተጎጂዎችን ሊያክም የሚችለው፣ ፍትሕ እንጂ ዕርቅ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ግለሰቦች ከዕርቅ ይልቅ ፍትሕ ሲያገኙ እንደሚያርፉ፣ ሁልጊዜም የፍትሕ ርትዕነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ (ዶ/ር) ፍትሕ መልካም እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹በዚህ አገር ማን ወንጀለኛ ነው? ማን ንፁህ ነው? የሚለውን መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ኃጢያት አለ በዚህች አገር፡፡ ለምሳሌ በንጉሡ ዘመን የነበሩ ባለሥልጣናት በእነሱ ጊዜ በደል እንዳልተፈጸመና ጥሩ ጊዜ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ የደርግ ባለሥልጣናትም በተመሳሳይ እኛ የመራናት ኢትዮጵያ ትሻል ነበር ይላሉ፡፡ ኢሕአዴግም እኛ ያመጣነው አብዮት መስመር ሊስት ነው ይላል፤›› በማለት ፍትሕን ማረጋገጥ ከባድ እንደሚሆን፣ የቆየውን ቁርሾ በዕርቅ መፍታት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ በሦስት መንግሥታት የተሠራ ግፍ ስለሆነ መለየቱ ከባድ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፍትሕ ሥርዓቱ በራሱ ጉድለቶች ያሉበት በመሆኑ፣ መታየት ያለባቸው ክፍተቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ መረራ (ዶ/ር) ሁሉ ፍትሕን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሚሰጡ በርካቶች ሲሆኑ፣ ፍትሕ ግን ሥርዓት ሊያመጣ እንደማይችል የሚከራከሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ታዋቂው የሕግ ምሁርና ፖለቲከኛ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም. በተካሄደ የብሔራዊ መግባባት ኮሚቴ ላይ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ይኼንን ሐሳብ የንፀባረቁት ዶ/ር ያዕቆብ፣ ‹‹ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰቆቃዎች የደረሱ ቢሆንም፣ በግልጽ የይቅርታና የዕርቅ ጉዳይ ትኩረት የተነፈገው ነው፡፡ ዴሞክራሲና ሰላም ከማለታችን በፊት ብሔራዊ ዕርቅን ማስቀደም አለብን፤›› ብለው፣ ‹‹ቀይ ሽብር ምን እንደሆነ ብዙዎቻችን ዓይተናል፡፡ ነጭ ሽብርም እንዲሁ ምን እንደነበር ብዙዎቻችን ዓይተናል፡፡ ዕልቂት የተስተናገደበት ዘመን ነበር፡፡ እና ያ ሁሉ ዝም ተብሎ በደፈናው ታፍኖ አለፈ እንጂ፣ በሕዝቡ መካከል ዕርቅ አልወረደም፡፡ እርግጥ ነው የቀይ ሽብር ተዋንያን ደርጎችም ጭምር ፍርድ ቤት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ቅጣታቸውን ተቀብለዋል፡፡ ግን ፍርድ ዕርቅ አያመጣም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ዕርቅ አሁንም እጅግ አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የብሔራዊ ዕርቅና የፍትሕ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ የክርክር አጀንዳ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ገጽታም ያለው ነው፡፡ ተመሳሳይ ሒደቶች የታዩበት ከሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በኋላ የነበረው ፍርድ ፍትሕ ያመጣና ሁቱና ቱትሲዎች አብረው ቢኖሩም፣ ዕርቁ ሰፊ ስላልሆነ ጊዜውን የሚጠብቅ ቦምብ ነው ሲሉ የሚተቹ አሉ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተከትሎ ናዚዎች ላይ የተሰየመው የኑረምበርግ ፍርድ ቤት ችሎት፣ በናዚዎች ላይ ቅጣት ቢያስተላልፍም ቁርሾውና ቂሙ እስከዛሬ የዘለቀ ይመስላል፡፡
ስለዚህም የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ሲነሳ የወደፊቱ እየታሰበ መሆን እንዳለበት በማሳሰብ፣ ያለፈውን የክፋት ምዕራፍ በመዝጋት የወደፊቱን ማለም ይገባል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡
እንደ መረራ (ዶ/ር) አመለካከት የኮሚሽኑ ስብጥር ሁሉንም ያካተተ እንደሚሆን እምነት እንዳለ፣ ተቀባይነትና ተዓማኒነት የሚኖረው ኮሚሽን ይሆናል ብለው ተስፋ እያደረጉ፣ ‹‹›በአገሪቱ የነበሩ ነገሮችን ማወቅና አገናዝቦ የተሻለ መፍትሔ የትኛው ነው? አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ምን ዕርምጃ ቢወሰድ ይሻላል በማለት ሕዝብን የሚያስተምር መሆን አለበት፤›› ይላሉ፡፡
ይሁንና እስካሁን በአገሪቱ የዴሞክራሲ ተቋማት የመጡበትን መንገድ ተከትሎ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመሳሰሉት ተቋማት ‹‹የገዢውን ፓርቲ ችግሮች ለመሸፈን›› የሚሠራ ከሆነ፣ ዕጣ ፈንታው ውድቀት እንደሚሆን ያምናሉ፡፡ ‹‹የአባላቱና የመዋቅሩ ጉዳይ ወሳኝ ነው፤›› በማለት፡፡
ምንም እንኳን ዕርቀ ሰላም ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ እንዲቋቋም መደረጉን በበጎ የሚመለከቱ ቢበረክቱም፣ ለሕግ አንዱ የተሰጠው ትኩረትና በሰነዱ ውስጥ ያሉት አሻሚ ቃላትና አገላለጾች ከትችት አላመለጡም፡፡ ረቂቁ በሚገባ ዝግጅት እንዳልተደረገበት፣ የቃላት ትርጓሜን ያልያዘና እንደ ‹‹ዕርቀ ሰላም›› ያሉ ቃላት በለሆሳስ ሳይተረጎሙ ማለፋቸውን በአንድ የሕግ መረጃ ቋት ድረ ገጽ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የኮሚሽኑ ዓላማ በጣም አጭርና ግልጽነት የሚጎድለው እንደሆነ፣ ዕርቀ ሰላም የሚለው የኮሚሽኑ ዋና ሥራ ሆኖ በግልጽ አለመቅረቡና እንደ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዕርቅ›› የሚሉ አሻሚ ሐረጎችን መያዙ፣ ብሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዚዳንት ወይም ፓርላማውን ማለት ሲገባ መንግሥት የሚል አሻሚ ቃል መኖሩ ተተችቷል፡፡
ምንም እንኳን አዋጁ ገና ያልፀደቀ ቢሆንም ይፋ ያልሆኑ የኮሚሽኑ አባላትን ዝርዝር የያዘ ሰነድ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲንሸራሸር ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በተወሰኑ አባላት ላይ ቅሬታ ሲቀርብ ተስተውሏል፡፡
በአዋጁ ዙሪያ የሚነሱ በርካታ ክርክሮች በመኖራቸውና በሁሉም ዘንድ መግባባት ሊያመጣ የሚችል መሆን ስለሚኖርበት፣ ፓርላማው በአዋጁ ላይ ለሰፊ ውይይት የተለያዩ ሐሳቦች ያሏቸውን አንድ ላይ በማምጣት በጥልቀት ሊመለከተው እንደሚገባ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡