Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ (1917 – 2011)

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ (1917 – 2011)

ቀን:

በሦስት መንግሥታት ከፓርላማ ፕሬዚዳንትነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት ኢትዮጵያን መርተዋል፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሰባት አሠርታት የሥራ ጉዟቸው፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸው በተሰማሩባቸው የተለያዩ መስኮች ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል፡፡ ከበጎ ፈቃድና በጎ አድራጎት አገልግሎት ጋር ስማቸው ይያያዛል፡፡ ከመንግሥታዊ ተግባራቸው ጡረታም ቢወጡ፣ በተፈጥሮ ጥበቃና አካባቢ ክብካቤ ዙሪያ በለም ኢትዮጵያ ያደረጉት ልጨኛ ተግባር ይጠቀሳል፡፡ ለሁለት ተከፍለው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶችን ወደ አንድነት ለማምጣት፣ በኢትዮ ኤርትራ መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ ጥረት ካደረጉ ታዋቂዎች መካከልም ይገኙበታል፡፡

ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት (1994 – 2006) ለ12 ዓመታት የመሩት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቀደም ባሉት ስድስት አሠርታት ውስጥም በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታ ላይ አገልግለዋል፡፡ በዘውዳዊው ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ የልደታ ወረዳ እንደራሴ በመሆን በ1954 ዓ.ም. ለፓርላማ በመመረጥ የሕግ መምርያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ በ52ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡

ፋሺስት ጣሊያን በ1933 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ በጦር ሠራዊት የሬዲዮ መገናኛ ክፍል ባልደረባነት ሥራ የጀመሩት አቶ ግርማ፣ ከገነት ጦር ትምህርት የመኮንንነት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተቀላቅለዋል፡፡

- Advertisement -

ወደ ኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ካመሩ በኋላም በቴክኒክ ክፍል ሹምነት፣ በኤርትራ (በፌዴሬሽን ወቅት) የሲቪል አቪዬሽን ሹም፣ በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በሥራና መገናኛ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡

የደርግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በግንቦት 1968 ዓ.ም. የሰላም ኮሚሽን ሲያቋቁም፣ በኃላፊነት ከተቀመጡት መካከል አቶ ግርማ አንዱ እንደነበሩ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ ዳይሬክተር ነበሩ፡፡

እሳቸው በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እየሠሩ በተጓዳኝ በልማትና ማኅበራዊ ተግባራ ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የቆርኪ ፋብሪካን በሽርክና በመመሥረት፣ የጊቤ እርሻ ልማትን በማቋቋም፣ የከፋና የኢሉባቡር እንጨት ኢንዱስትሪ በሽርክና በመመሥረትና የአዲስ አበባ ዕድሮች አጠቃላይ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ይገኙበታል፡፡ በሥጋ ደዌና በጠንቀኛ ሕመም በጎ አድራጎት ድርጅት በዳይሬክተርነት፣ በለም ኢትዮጵያ መሥራችነትና ፕሬዚዳንትነት ሠርተዋል፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች ባቋቋሙት የሜጫና ቱለማ ድርጅት ውስጥም በአባልነትና በአማካሪነት ማገልገላቸው ይወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዘመን በ1992 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ በምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት 1994 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል፡፡

ከአባታቸው ከግራዝማች ወልደ ጊዮርጊስ ሉጫና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወሰንየለሽ መኩሪያ ታኅሣሥ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተወለዱት መቶ አለቃ ግርማ፣ የፋሺስት ጣሊያን የ1928 ዓ.ም. ወረራ ድረስ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ በወረራው ዘመን (1928 – 1933) በጣሊያን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከወታደራዊ መኮንን ትምህርታቸው ባሻገር በ1940ዎቹ አጋማሽ በአየር ትራፊክ አስተዳደርና ቁጥጥር በተለያዩ አገሮች ኮርስ ወስደዋል፡፡ በድርሰት ዓለምም ከሲቪል አቪዬሽን ጋር የተያያዘ የአየር በረራን የተመለከተና ድሮና ዘንድሮ የተሰኘ መጻሕፍት አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ዓቃቤ ንዋይም ነበሩ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በልደት በዓላቸው አጋጣሚ በዘመነ ዮሐንስ የተዘጋጀው፣ ‹‹ባሪያው ግርማ›› ግለ ታሪክ ለማስመረቅ አቅደው ነበር፡፡

ኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ የነበሩት አቶ ግርማ ከሁለት ዓመት በፊት ካረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሳሌም ጳውሎስ መንአመኖ አምስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡

ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት ፕሬዚዳንት ግርማ በ94 ዓመታቸው ያረፉት ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አጥቢያ ላይ ነው፡፡

ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት፣ ‹‹ክቡር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የኢፌዴሪ መንግሥትን ለአሥራ ሁለት ዓመት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ፣ በልዩ ልዩ ኃላፊነት ለአገራቸው ረዥም ዘመን የሠሩ፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸው ለሕዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ፣ የታታሪነት፣ የቅንነትና፣ የሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ተምሳሌት ነበሩ፤›› ብለዋቸዋል፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሥርዓተ ቀብር በመንግሥታዊ ሥርዓት ለማስፈጸም ኮሚቴ መቋቋሙንና በቅርቡም መግለጫ እንደሚሰጥ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...