Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ገቢ ንግድ ዋስትና ገባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዶላር ለተገኙ ብድሮች በብር መክፈል እንዲቻል ስምምነት ፈርሟል

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) የኢትዮጵያን የገቢ ንግድ ለመደገፍ የብድር ዋስትና ገባ፡፡

ኢትዮጵያን እየጎበኙ የሚገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፍሊፕ ለ ሆሩ ተቋሙ የኢትዮጵያን የገቢ ንግድ ዘርፍ በተቀመጡ መስኮች ላይ ዋስትና በመስጠት እንደሚያግዝ ሰኞ ታኅሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቀዋል፡፡

 በዓለም ባንክ ጽሕፈት ቤት በተካሄደ የስምምነት ሥነ ሥርዓት ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ባንኮች ለሚቀበሉት የገቢ ንግድ የግዥ ግዴታ ዋስትና ይገባላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የግሉ ዘርፍ በውጭ ለሚያካሂደው ግዥ ኮርፖሬሽኑ የሚሰጠው የዋስትና ድጋፍ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለማቃለል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑና በብሔራዊ ባንክ ስምምነት መሠረት፣ ባንኮች ለሚከፍቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) ኮርፖሬሽኑ ዋስትና ይገባላቸዋል፡፡ ይህም ማለት በኢትዮጵያ የሚገኙ አስመጪዎች ለሚከፍቱት ኤልሲ ዝቅተኛ ተቀማጭ ገንዘብ በማስቀመጥ፣ በአገር ውስጥ ለሚገኘው ባንክ ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡ ሆኖም የግዥውን ሙሉ ክፍያ በኤልሲው ቀነ ገደብ መሠረት መክፈል ባይችሉ አይኤፍሲ ባንኮቹን ወክሎ ክፍያውን ይፈጽማል፡፡

ይህ የገቢ ንግድ ዋስትና እንደ ባንኮቹ አቅምና የውጭ ምንዛሪ የማመንጨት አቅም የሚወሰን ቢሆንም፣ እንደ ብሔራዊ ባንክ ግንዛቤ የዋስትናው መጠን የአገሪቱን የአንድ ዓመት ሙሉ የገቢ ንግድ ሊሸፍን እንደሚችል ይታመናል፡፡

ይህም ሆኖ አይኤፍሲ የኢትዮጵያን የገቢ ንግድ እንደ ባንኮቹ አቅምና ደረጃ መጠን ከሃምሳ በመቶ እስከ ሙሉ በሙሉ ሊሸፍን የሚችልበት አቅም እንዳለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በውጭ ምንዛሪ ብድር ተገብቶባቸው በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ በሚውሉ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ የብድር አከፋፈላቸው በአገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ፣ ማለትም በብር እንዲሆን የሚያስችል ስምምነትም ተፈርሟል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደ አግሪቢዝነስ ያሉ ዘርፎች እንደሆኑም ሪፖርተር ካገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው አይኤፍሲ ያቀረበው የዋስትና ድጋፍ፣ በዓይነቱ የተለየና አዲስ በመሆኑ ለግሉ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

አይኤፍሲ በቅርቡ የ500 ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ከማድረግ ባሻገር፣ ሙሉ ለሙሉ በግሉ ዘርፍ እንዲለሙ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታውሰዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች