የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባልነት ከቀረቡለት ዕጩዎች መካከል፣ በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑትን የአቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያን የሹመት ጥያቄ እንደማይቀበለው በመግለጽ ውድቅ አደረገ።
በአገሪቱ የዳኝነት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የአስተዳደር ሚና ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሕግ መሰጠቱ ይታወቃል። የጉባዔው አባላትም ታዋቂ ሰዎች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሦስት የምክር ቤት አባላት እንደሚሆኑ በሕግ የተደነገገ ነው።
በዚህ መሠረት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምክር ቤቱን በመወከል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል በነበሩት ምትክ በአፈ ጉባዔው የታጩ ሌሎች ሦስት አባላት፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ቀርበዋል።
ምክር ቤቱን በመወከል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት የነበሩትን መተካት ያስፈለገው፣ የዳኝነት ዘርፉን ተዓማኒና ገለልተኛ ለማድረግና ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር አሠራር ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ስለታመነበት እንደሆነ ተገልጿል።
በዕለቱ ምክር ቤቱን በመወከል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል እንዲሆኑ በዕጩነት የቀረቡት ወ/ሮ ሰናይት አንዳርጌ፣ አቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበትና አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ ናቸው።
ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ አባላት ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል በተለየ ሁኔታ፣ አቶ ገብረ እግዚአብሔር የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል ሊሆኑ አይገባም በማለት ተከራክረዋል።
አቶ አስመላሽ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ሆነው ከማገልገላቸው በተጨማሪ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመወከል ለረጅም ዓመታት የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል እንደነበሩና በጉባዔው ውስጥም ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
ይህንን ተከትሎ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ፓርላማውን በመወከል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል የነበሩትን አቶ አስመላሽ እንዲተኩ ቢታጩም፣ ፓርላማው በፍፁም አልተቀበለውም።
የምክር ቤቱ አባላት መከራከሪያ የነበረው የመንግሥት ተጠሪ የሆነን ግለሰብ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አድርጎ መሾም፣ መንግሥት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ ነው የሚል ነበር።
በተጨማሪም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል ሆኖ እንዲሠራ መፈቀዱ፣ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ጉዳት ማድረሱን በመጥቀስ የምክር ቤቱ አባላት ክርክራቸውን አቅርበዋል።
በተለይ በጉባዔው የሚወከሉ የምክር ቤቱ አባላት በቂ የሕግ ዕውቀት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው በመጥቀስ የምክር ቤቱ አባላት የተከራከሩ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የምክር ቤቱ አባላት በጉባዔው ቢወከሉም በአገሪቱ ሲፈጸሙ የነበሩ አስነዋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል እንዳልቻሉ ሞግተዋል።
አሁን የጉባዔው አባል ለመሆን መወከል ያለባቸው ያለፈው ዓይነት የመብት ጥሰትና የተዛባው የዳኝነት ሥርዓት እንዲታረም የተሻለ የሚሠሩና የሕግ ዕውቀት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት መሆን እንደሚገባቸው ተከራክረዋል።
ከዚህም አንፃር ከዕጩዎቹ መካከል አቶ ገብረ እግዚአብሔር ለዕጩነት እንደማይመጥኑ አባላቱ ተሟግተዋል። አቶ ገብረ እግዚአብሔር የቀረበባቸውን ተቃውሞ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፣ “የምክር ቤቱን ሐሳብ ተቀብያለሁ፣ ራሴንም ከዕጩነት አንስቻለሁ፤” ብለዋል። በዚህም መሠረት በአቶ ገብረ እግዚአብሔር ምትክ ሌላ አባል ከምክር ቤቱ ተለይቶ እንዲቀርብ በመስማማት፣ የተቀሩትን ሁለት ዕጩዎች ሹመት ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኝነት ሥርዓቱ በገለልተኝነት እንዲከናወን፣ ዳኞችም ሙያዊ ብቃታቸውን ነፃነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን የመከታተልና ዕርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ ኃላፊነት የተሰጠው ነው። ከኃላፊነቶቹ መካከልም ዕጩ ዳኞችን በመመልመል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት እንዲሾሙ ማድረግ፣ በፓርላማ የተሾሙ ዳኞች ገለልተኝነትንና የዳኝነት ሥነ ምግባርን መጣሳቸው ቅሬታ የቀረበ እንደሆነ፣ ይህንኑ መርምሮ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ዳኞች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ወይም ከዳኝነት እንዲሰናበቱ ለሾማቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ ይገኝበታል።
ቀደም ሲል ምክር ቤቱን በመወከል የጉባዔው አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ተስፋዬ ዳባና ወ/ሮ ገነት ታደሰ ነበሩ። ፓርላማው ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከተመለከታቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መካከል በኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን፣ በግብርናና በሚዲያ ዘርፍ የተፈረመውን የትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ሲሆን፣ ይህንኑ ረቂቅ በተመለከተ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኢትዮጵያ ‹ኢኮኖሚክ ኦፖርቹኒቲ ፕሮግራም› ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል።