Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ገለልተኛ ሆኖ እንዲዋቀር ጥሪ ቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በርካታ ትችቶች የሚሰነዘርበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማዕከላዊ ባንክነቱን ሚና በአግባቡ እንዲጫወት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንደ አዲስ እንዲዋቀር የተለያዩ ባለሙያዎች ሐሳብ ቀረቡ፡፡

ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተከፈተው ሦስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፖለቲካ ሹመኞች ሲመራ በመቆየቱና የመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚ በመሆኑ የማዕከላዊ ባንክ ዋነኛ ኃላፊነቱን መወጣት እንደተነሳው ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት በርካታ ምሁራን መካከል አንዱ የነበሩት የምጣኔ ሀብት ተንታኝ አቶ አብዱልመናን መሐመድ፣ ብሔራዊ ባንክ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት እንዳለበት በአጽንኦት መክረዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ገለልተኛ መሆን አለበት ስንል የተቋቋመበትን ዓላማ ማየት አለብን፤›› ያሉት አቶ አብዱልመናን፣ ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤነኛና የተረጋጋ እንዲሆን ማድረግና ለኢኮኖሚ ዕድገት ድጋፍ ማድረግ፣ ባንኩ የተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ደንቦችን በማውጣት ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በመቆጣጠር የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤነኛ እንዲሆን የሠራው ሥራ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩትም ከሞላ ጎደል ስኬታማ እንደነበርና ለኢኮኖሚ ዕድገት ድጋፍ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን የገለጹት አቶ አብዱልመናን፣ ማዕከላዊ ባንኩ የተቋቋመበት ተቀዳሚ ዓላማ የሆነው የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር በኩል ሲታይ ግን ፈተናውን ወድቋል ብለዋል፡፡

‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት የቻለው፣ ብሔራዊ ባንክ ሥራውን በአግባቡ ባለመሥራቱ ነው፡፡ ባንኩ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ያልቻለው ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲሠራ ስላልተፈቀደለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አብዱልመናን የብሔራዊ ባንክ ዋና ችግር የሚጀምረው ከማቋቋሚያ አዋጁ እንደሆነ በመግለጽ ሞግተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነ የማቋቋሚያ አዋጁ ይጠቁማል ብለው፣ ‹‹ይህ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈለጉትን ሰው ገዥ፣ ምክትል ገዥ አድርገው ይሾማሉ ማለት ነው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲያቸውን ሰዎች መሾም ይችላሉ ማለት ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ባንኩ የፓርቲ ፖሊሲ አስፈጻሚ አካል ሆነ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ አብዱልመናን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጠሪነቱ ለመንግሥት አስፈጻሚ አካል በመሆኑ መንግሥት ገንዘብ ባጠረው ቁጥር እንደ ልቡ ከባንኩ እንዲበደር እንዳስቻለው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለኢኮኖሚ ዕድገት ቅድሚያ በመስጠቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበት ቁጥጥር ሥራውን ወደ ጎን ትቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ብቻ እንዲያተኩር በመደረጉ፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማዕከላዊ ባንክነቱን ሚና በነፃነት እንዲያከናውን ተጠሪነቱ ለአስፈጻሚ አካል ሳይሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ  ባንክ ውስጥ የፖለቲካ ሰዎች አያስፈልጉም፡፡ ገዥው፣ ምክትል ገዥውና የቦርድ አባላቱ የተመሰከረላቸው ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ በክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ተወዳድረው የሚቀጠሩ ብቁ ባለሙያዎች መሆን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የፍሊንትስቶን ሆምስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀደቀ ይሁኔ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱ በርካታ የገንዘብ ችግሮች መንስዔው የብሔራዊ ባንክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባንኩ የዕውቀት ችግር አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት ምን ያህል የኢኮኖሚ ጥናትና ምርምር ጽሑፎች አሳትሟል ብላችሁ ብትፈልጉ አታገኙም፡፡ አንዱ ችግሩ ደግሞ ትችት ለማስተናገድ ፈቃኛ አለመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዋይኤችኤ ኮንሰልቲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀልም፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከዓለም ተነጥሎ ወደ ኋላ የቀረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የባንኩ ኢንዱስትሪ አድጓል የሚባለው ስህተት ነው፣ አላደገም፡፡ ምንም ዓይነት የፈጠራ ሥራ የታከለበት የባንክ አገልግሎት የማይሰጥ፣ ግንብና ግድግዳ ካልያዘ በቀር የማያበድር፣ አትራፊ የሆነው በተሰጠው ከለላ ተጠቅሞ እንጂ ተወዳዳሪ ሆኖ አይደለም፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ሰባት በመቶ ወለድ እየከፈለ ለብድር 18 በመቶ ወለድ እያስከፈለ፣ የውጭ ባንኮች ፉክክር ሳይኖርበት ነው አትራፊ ሆነ የሚባለው፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ኅብረተሰቡ ተገቢ የሆነ የባንክ አገልግሎት እንደማያገኝ፣ በተለይ የብድር አገልግሎት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግል ባንኮች እስከ ዛሬ የሸጡት የአክሲዮን ዋጋ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሆኑን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 100 ሚሊዮን ዶላር አክሲዮን መሸጣቸውን የጠቆሙት አቶ ያሬድ፣ አንድ አነስተኛ የውጭ ባንክ ቢመጣ ብቻውን ሁሉንም ጠቅልሎ ሊገዛ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ሥራው ቁጥጥር ማድረግ ላይ በመወሰኑ ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳላደረገ ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ውስጥ ለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መንስዔ የፖሊሲ ችግር እንደሆነ ጠቁመው፣ በአጠቃላይ ሥር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የስቲሊ አርኤምዋይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ ለማ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጡንቻ እየጠነከረ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ እየበዛ እንደመጣ ማየት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አቶ ተፈራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተጫወታቸውን በጎ ሚናዎችና የታዩ ደካማ ጎኖችን ዘርዝረዋል፡፡

የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር ማድረጉ፣ አስተማማኝ የገንዘብ ሥርዓት እንዲኖር ማድረጉ፣ ሀብት በማሰባሰብ፣ የተበላሹ ብድሮች መጠን በመቆጣጠር ረገድ ባንኩ መልካም ሥራዎችን እንዳከናወነ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ ዝግ የሆነ ኢኮኖሚ እንደምትመራ፣ የብድር እጥረትና በፈጠራ ሥራዎች የታገዙ የባንክ አገልግሎቶች አለመኖር እንደ ዋነኛ ተግዳሮቶች የጠቀሱት አቶ ተፈራ፣ የልማት ባንክ የተበላሹ ብድሮች መጠን 40 በመቶ መድረስ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የነበሯቸው አክሲዮኖች ለኢትዮጵያውያን አስተላልፈው እንዲወጡ መደረጉ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የብድር ጫናና የወጪ ንግድ መዳከም በኢኮኖሚው ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት እንዳለበት፣ የሚከፍለው ደመወዝ ባለሙያውን ሊያቆይ የሚችል እንዳልሆነና መለማመጃ ቤት እየሆነ እንደመጣ ተነግሯል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ባንክ እንደ ማዕከላዊ ባንክ የሚያኮራ እየሆነ አይደለም፤›› ብለዋል አቶ ተፈራ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ በላይ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ከሌሎች የመንግሥት ድርጅቶች ነጥሎ መመልከት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ባንኮችና ኢንሹራንሶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሠራሮች ለማምጣት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ መመልከት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ በላይ፣ ለሁሉም ችግር ብሔራዊ ባንክን መኮንን ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹በብሔራዊ ባንክ በኩል ውስንነቶች ይኖራሉ፡፡ ስላሉት ችግሮች ስንናገር ግልጽ እናድርግ፡፡ በቁጥጥር ሥራዎች ላይ ከሆነ ይህ ችግር አለ ብሎ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በጋራ ተባብሮ ለውጥ ለማምጣት ከሆነ የሚታሰበው ቀርቦ በመመካከር እንጂ፣ ለአገሪቱ ችግር በሙሉ ባንኩን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

አይካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ልምድ የሚለዋወጡበትና በፖሊሲ ጉዳች ላይ የሚያወያዩበት መድረክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች