Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ውዝግቡ ባልተቋጨው የረጲ ኃይል ማመንጫ ላይ ድርድር እየተደረገ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ፕሮጀክት ስምምነት በ2005 ዓ.ም. ተፈርሞ ግንባታው ሲጀመር ከአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ በዓመት 50 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት እንደነበር ሲገለጽ ቢቆይም፣ ፕሮጀክቱን ለመገንባት የተዋዋለው ኩባንያ ግን ይኼንን በመቃወም ከመነሻው ከመንግሥት ጋር የተዋዋለው 25 ሜጋ ዋት እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ሥራ ጀምሮ የነበረው የኃይል ማመንጫ ሰሞኑን ሥራ ያቆመው መሥራት ተስኖት እንዳልሆነም አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በፕሮጀክቱ ላይ ድርድር እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ በኋላም ቻይና ናሽናል ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በመሆን ተጣምረው የገነቡት የረጲ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ግንባታው ተጀምሮ እ.ኤ.አ. በ2017 እንደሚጠናቀቅ ቢጠበቅም፣ ለሁለት ዓመት ገደማ ዘግይቶ በቅርቡ ነበር ሙሉ ለሙሉ ግንባታው መጠናቀቁ የተበሰረውና የተመረቀው፡፡

ይሁን እንጂ በካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ፣ የኃይል ማመንጫው ሥራ በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዲያቆም የተደረገው በ‹‹ፕሮሲጀር›› ምክንያት እንጂ ሪፖርተር በዘገበው መሠረት ‹‹ኃይል ማመንጨት አቅቶት›› እንዳልሆነ በመግለጽ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ በቀረበው ዘገባ መሠረት የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ ፕሮፌሰር ሳሃዳት ሁሴን የሰጡትንን ማብራሪያ መሠረት በማድረግ የረጲ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኃይል ለማመንጨት ከሚያስፈልገው ይልቅ፣ ቆሻሻ ለማቃጠል የሚጠይቀው ኃይል ከፍተኛ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይኼንን ዘገባ መነሻ በማድረግ ቅሬታ ያቀረቡት አቶ ሳሙኤል፣ የኃይል ማመንጫው በቀን እስከ 1,400 ቶን ቆሻሻ የማቀነባበር አቅም ያለው ከመሆኑም በላይ ከዚሁ ቆሻሻ 25 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ብለዋል፡፡

ከመንግሥት በተለይም ከፕሮጀክቱ ባለቤት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ በዓመት 85 በመቶ አቅሙ ወይም 7,400 ሰዓት ቢሠራ 185 ጊጋ ዋት አወር ኃይል ለማምረት መስማማቱን፣ ይህም ማለት 25 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሆነ በመግለጽ የተከራከሩት አቶ ሳሙኤል፣ ይሁን እንጂ እያንዳንዳቸው 25 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ሁለት ተርባይኖች መተከላቸውን በማመን ስለተተከሉበት ምክንያትም ያስረዳሉ፡፡

ሁለተኛው ተርባይን የተገጠመው፣ ‹‹ለመጠባበቂያ ተብሎ በተቋራጩ መልካም ፈቃድ ያለ ምንም ተጨማሪ ክፍያ የተገነባ እንጂ›› ስምምነቱ በሚያስገድደው መሠረት ከተጠቀሰው በላይ አሟልቶ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስና ሸሪኩ ፕሮጀክቱን በተደረሰው ስምምነት መሠረት ማጠናቀቁን አቶ ሳሙኤል ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሳይወሰኑም እ.ኤ.አ. ከጁን 24 ቀን 2018 እስከ ሴፕቴምበር 10 ቀን 2018 ድረስ ኃይል ሲያመርት መቆየቱን፣ በዚህ ሒደትም 48 ሺሕ ቶን ቆሻሻ በማቀነባበር 9,750 ሜጋ ዋት አወር ወይም 9.75 ጊጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ማስገባቱን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የቴክኒክ ችግር እንዳልገጠመው በመግለጽ ፕሮጀክቱ በስኬት ስለመጠናቀቁ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል ይኼንን ይበሉ እንጂ አዲሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ግን፣ በፕሮጀክቱ በርካታ ያልተቋጩ ጉዳዮች እንዳሉ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት አቋም ፕሮጀክቱ በተገባለት ውል መሠረት ማጠናቀቅ ነው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተቋራጩና በመንግሥት መካከል የተገባው ውል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል፡፡ በውሉ ላይ 25 ወይም 50 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ የሚለው ላይ የተነካኩ ጉዳዮች አሉ ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹እኛ 50 ሜጋ ዋት ኃይል ከመነሻውም በከፍተኛ የማመንጨት አቅም በውሉ ስለተቀመጠ፣ ይኼንን የኃይል መጠን ካላመነጨ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹የተገባውን ውል መሠረት አድርገን ከኩባንያው ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ኩባንያው የሚያነሳው ጉዳይ አለ፡፡ አስጀምሬያለሁ፣ ያልተከፈለኝ ክፍያ አለ እያለ ነው፡፡ ከመከፈሉ በፊት ግን በስምምነቱ መሠረት መሟላትና መስተካከል ያለባቸው የቴክኒክ ጉዳዮች አሉ፡፡ ያልተጠናቀቁ አቅርቦቶችም አሉ፤›› ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ ያልተጠናቀቁ የሙከራ ሥራዎችም ጭምር ስላሉ ከተቋራጩ ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ተቋራጩ ኩባንያ ለኃይል ማመንጫው ከመንግሥት ጋር ለግንባታ የተዋዋለበትን የ119.85 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በመመለስ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ለመረከብ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እንዳላገኘ አቶ ሳሙኤል ቢናገሩም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግን ይህ ጥያቄ እንዳልቀረበና ከኩባንያው ወገን ለመንግሥት አካል ይኼንን ጥያቄ ያነሳ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቶ ሳሙኤል ፕሮጀክቱን ከመንግሥት ለመረከብ የጠየቁበትን ደብዳቤ ለሪፖርተር አሳይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች