Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለዓይን ባንክ ገቢ የተደረገው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ብሌን

ለዓይን ባንክ ገቢ የተደረገው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ብሌን

ቀን:

‹‹ከሞትኩ በኋላ የዓይኔን ብሌን የምለግሰው፣ አንዱ ለሌላው እያስተላለፈ ማየት የተሳናቸው ካለባቸው ችግር እንዲላቀቅ ለማድረግ ነው፡፡›› ይኼንን ዐረፍተ ነገር ከዓመታት በፊት የተናገሩት ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት ለ12 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ግርማ፣ ከኢትዮጵያ የዓይን ብሌን በመለገስ የመጀመርያው ሰው ናቸው፡፡

አቶ ግርማ ብሌናቸውን ለመስጠት ቃል የገቡት ከ15 ዓመታት በፊት መሆኑን የሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ መሥራችና የባለአደራ ቦርድ አባል ወንዱ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

አቶ ግርማን ለመዘከር ማክሰኞ ታኅሣሥ 9 ቀን በኢትዮጵያ ዓይን ባንክ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ዶ/ር ወንዱ እንደገለጹት፣ ፕሬዚዳንቱ ለመጀመርያ ጊዜ የገቡት ይኼው ቃል ለቀሩት ኢትዮጵያውያን በአርዓያነት ከመታየቱም በላይ ባንኩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ኅብረተሰቡንም በማነቃቃት ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

በዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና ፈር ቀዳጅ የሆነው ይህ የዓይን ባንክ ሥራ በጀመረባቸው በመጀመርያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ነገር ግን እንደነ አቶ ግርማ ያሉ ደጋፊዎች ስለነበሩት አገልግሎቱን ከመስጠት  አልተስተጓጎለም፡፡

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ሜዲካል ዳይሬክተርና የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሐኪም  መነን አያሌው (ዶ/ር)፣ አቶ ግርማ ባንኩ ለሚጠይቃቸው ነገሮች ሁሉ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ከጎን በመቆም በርካቶች ማየት እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ የዓይን ብሌናቸውን ለባንኩ እንዲለግሱ በማድረግ ሒደት ውስጥ ዕድሮች እንዲተባበሩ የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጫ በማከናወን ረገድም አቶ ግርማ ላቅ ያለ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ የዓይን ባንክ ባለሙያዎች መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ብሌናቸውን ለመውሰድ እንደቻሉ የሜዲካል ዳይሬክተሯ ገልጸው፣ የተነቀለውም የዓይን ብሌን አስፈላጊው ፍተሻ ከተደረገለት በኋላ አገልግሎት ላይ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡

የአቶ ግርማ ቤተሰብ ተወካይ አቶ ተሾመ ከተማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ ግርማ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ወደውና ፈቅደው የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ የገቡት ቃል እንዲፈጸም ቤተሰቡ ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳይቷል ይላሉ፡፡ ‹‹አርዓያነቱ ሌሎችን ለማነሳሳት፣ አገልግሎቱም የበለጠ እንዲሰፋ የሚያደርግ ስለሆነ መላው ቤተሰቡ በጣም የሚኮራበት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ለምለም አየለ በ1998 ዓ.ም. በተካሄደ አገር አቀፍ ጥናት ከ300 ሺሕ በላይ ወገኖች በዓይን ብሌን ጠባሳ መጎዳታቸውን፣ እነዚህን ወገኖች ለመታደግም የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ባደረጉት የሦስትዮሽ ስምምነት በ1995 ዓ.ም. ሰኔ መጨረሻ አካባቢ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ እስካሁን ድረስ ጥቂት የማይባሉ ብርሃናቸው እንዲመለስ ምክንያት ሆኗል፡፡  

‹‹ባንኩ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች ለ2,083 ወገኖች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አድርጎ ሰዎቹ ካለማየት ወደ ማየት መጥተዋል፡፡ ይህም ቁጥር ባለፉት 15 ዓመታት በተደረጉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ኅብረተሰቡ ያለው የልገሳ ባህል እንዲዳብር ዓይን ባንኩ የሚችለውን አድርጓል፡፡  

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ በመሥራቱ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን አግኝቷል፡፡ ይህም ደረጃ ለተቀባዮች ወይም ደግሞ የብሌን ንቅለ ተከላ ለሚደረግላቸው የኅብረተሰቡ አካላት ንፁህና ጥራቱን የጠበቀ የዓይን ብሌን በማሠራጨት ረገድ የበኩሉን ዕገዛ እንዳደረገ ከሥራ አስኪያጇ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ብቻ ይሰጥ የነበረውም የንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአምስት ክልሎች ተደራሽ እንደሆነ፣ በአማራ ክልል ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሐዋሳና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎችና በትግራይ ክልል ኵሃ ሆስፒታል የብሌን ንቅለ ተከላ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታትም የብሌን ማሰባሰቢያ ጣቢያዎችን በመክፈት፣ እንዲሁም ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ከመንግሥትና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡ ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች ኅልፈት በሚያጋጥምበት ቅፅበት የሟች ቤተሰቦች ወደ ዓይን ባንክ በመደወል የሟቹን ቃል መፈጸም እንዳለባቸው፣ ይህም የዓይን ብሌን ልገሳ ባህልን በማዳበር በሺዎች ለሚቆጠሩ ብርሃን መስጠት እንደሆነ፣ ከአሁን አሁን ተራ ይደርሰኝ ይሆናል በሚል ተስፋ ብርሃናቸው እስኪመለስ የሚጠባበቁ ሰዎችን ሕይወትም መቀየር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹ብርሃናችሁን አትቅበሩ› የሚል መርህ የሚከተለው የዓይን ባንኩ የአቶ ግርማን ፈለግ በመከተል ዜጎች ማየት ለተሳናቸው ብርሃናቸውን እንዲለግሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...