‹‹በ17ኛው መቶ ዓመት አጋማሽ የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓ ካስጀመረው ከሂዮብ ሉዶልፍ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓውያንና በአሜሪካውያን ተመራማሪዎች ተፅዕኖ ሥር ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ የሂዮብ ሉዶልፍ መምህር የቤተ አምሃራው አባ ጎርጎሪዮስ የነበሩ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ጥናት አባት እየተባለ ዘወትር የሚወሳው ሂዮብ ሉዶልፍ ብቻ ነው፤›› የሚለው ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጥናት ላይ የምዕራባውያን ተፅዕኖ እስከ ቅርብ አሠርታት ድረስ ዘልቆ መቆየቱን፣ ሆኖም፣ የታሪክ ጥናትን አፍሪካ ተኮር ለማድረግ የተጀመረው ዓለም አቀፉን የአፍሪካውያን ንቅናቄ ተከትሎ፣ ኢትጵያውያን ምሁራንም የኢትዮጵያ ጥናት ኢትዮጵያ ተኮር በማድረግ ወሳኝ ጥያቄዎችን ማነሳሳት ከጀመሩ መሰነባበቱንም ይታወሳል፡፡
ይህ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ዓላማም ይህንን ጥያቄ በዋናነት በማንገብ፣ የኢትዮጵያን ጥናት በተለይ ኢትዮጵያ ተኮር፣ በአጠቃላይም አፍሪካ ተኮር በማድረግ አዲስና የተቀናጀ ስልትና ይዘትን ዕውን ማድረግ መሆኑን መሰንበቻውን ተቋሙ ሥራውን በይፋ በጀመረበት ዕለት አስታውቋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ጥናት ላይ የምዕራባውያን ተፅዕኖ ነበረ ማለት፣ የጥናቱ ዋቢ ምንጮችም ሆኑ ተመራማሪዎቹ በዋነኛነት ምዕራባውያን ብቻ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ታሪክና ባህል በአውሮፓውያን አድሏዊ ብይን ሥር ወድቆ ነበር ማለት ነው፤›› ያለው ዩኒቨርሲቲው ያቋቋመው ትምህርት ቤት የሰነቀውን ርዕይ እንዲህ ገልጾታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ምክንያተ ነገር ወይም ምክንያተ ልደት፣ ይህን በምዕራባውያን እይታ የተመላከተውንና በምዕራባውያን ልቡና፣ ኅሊናና ዕብሪት የተቃኘውን፣ የታተተውንና የተሠራጨውን አድሏዊ ይዘት መቀየር ነው፡፡ ያን ይዘት አቃንቶም፣ ታሪኩን፣ ፍቺውንና አስተምህሮውን ለባለቤቷ ለኢትዮጵያና ለባለቤቶቿ ለኢትዮጵያውያን ማስመለስና ማስረከብ ነው፡፡››
በቅርቡ ከኮሌጅነት ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ሥራውን በይፋ የጀመረው ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም ቢሆንም ትምህርቱን ግን አስቀድሞ በጥቅምት ጀምሯል፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው ትምህርት ቤቱ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማስተርስ ኦፍ አርትስ ዲግሪ ደረጃ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በትምህርቱም በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ በብሔረሰቦች ወግና ሥርዓት ሰፊ ጥናትና ጥልቅ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን፤ በሁለተኛው መርሐ ግብርም በትውፊታዊ ሥነ መድኃኒት/ሥነ ፈውስ፣ በትውፊታዊ ሥርዓተ ሕግ፣ በኢትዮጵያ ጥናት ዐውራ ርዕሰ ጉዳዮች የሚተኮርበት ይሆናል፡፡
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የትምህርተ መለኮት አካዴሚ ዲን መምህር ግርማ ባቱ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው አምስት ኮሌጆች አሉት፡፡ እነሱም የትምህርተ መለኮት ኮሌጅ፣ ቅዱስ ያሬድ የዜማና የሥነ ጥበብ ኮሌጅ፣ የማኅበራዊ ጥናትና የነገረ ሰብእና ኮሌጅ፣ የሥራ አመራርና የሕዝብ አስተዳደር ኮሌጅ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ናቸው፡፡
ዩኒቨርሲቲው አምስት ኮሌጅ ይዞ በከፊል ሥራውን በተለይ ትምህርተ መለኮትና የከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ሲጀምር የተቀሩት ለአንድ ዓመት በጥናትና በዝግጅት ቆይተው በ2012 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራሉ፡፡
እንደ ዲኑ አገላለጽ፣ ‹‹የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ ሌሎች ኮሌጆች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ ሊያስተምሩ ቢችሉም በዚህ የምናስተምረው በኢትዮጵያ ዕይታ ነው፡፡ በውጭ መሥፈርት ሳይሆን በራሳችን፣ ቋንቋውን በቋንቋው ተናጋሪዎች ዓይን ማየት ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው ክፍተት ነበረበት፡፡ የኛ ታሪክ፣ የኛ ቋንቋ፣ የኛ ባህል ብለን የትምህርቱ ባለቤቶች ግን ሌሎች መሆናቸው ሊበቃው ይገባል የሚል ትልቅ ሐሳብ ያለበት ነው፡፡››
የቀድሞ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ መጀመሩ ይገልጻል፡፡
ኮሌጁ በ1960ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ ሲዘልቅ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው በተዘጋ በሃያ ዓመቱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በትምህርተ መለኮት ዘርፍ በሦስተኛ፣ በሁለተኛና አንደኛ ዲግሪ በመደበኛና በተከታታይ እንዲሁም በርቀት ትምህርት መርሐ ግብር በግእዝ ቋንቋ በተከታታይ ትምህርት ዲግሪና ዲፕሎማ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት ጀማሪ ማን ነው?
ባህር ማዶዎቹ በተለይም አውሮፓዎቹ በኢትዮጵያ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናትን ማን ጀመረ፣ ማንስ ወጠነ ብለው ይጠይቁና ምላሻቸው ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ በ17ኛ መቶ ክፍለ ዘመን እንደጀመረው፣ የርሱ አስተማሪም አባ ጎርጎርዮስ ዘቤተ አምሃራ (መካነ ኢየሱስ) እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጥናት ከሉዶልፍ በፊት በ16ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ ቫቲካን በደብረ እስጢፋኖስ ገዳም የጀመሩት አባ ተስፋጽዮን መልኅዞ መሆናቸውን የሚሞግቱ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቋንቋ ጥናት በአውሮፓ በደብረ እስጢፋኖስ እንደተጀመረ ከሁሉ በፊት የገለጸ ዮሐንስ ፖትከን የተባለ ጀርመናዊ ነው፡፡ እርሱ ‹‹ከለዳዊት›› ብሎ የሚጠራት የኢትዮጵያ ቋንቋ በሮም ከኢትዮጵያውያን እንደተማረም ይናገራል፡፡ ሰኔ 30 ቀን 1513 በግዕዝ ፊደልን ቀርፆ ለመጀመርያ ጊዜ መጻሕፍትን ያሳተመ ዮሐንስ ፖትከን ነው፡፡ ሲያሳትም የረዱት አባ ቶማስ የሚባሉ መነኩሴ ናቸው፡፡ መነኩሴው በመጽሐፉ መቅድም ‹‹ዮሐንስ ፖትከን ጀርመናዊ የቅዱስ ጊየርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቆሞስ፣ በኮሎን የዳዊት መጽሐፍ ሲያሳትም እኔ ቶማስ ወልደ ሳሙኤል የኢየሩሳሌም ነጋዴ (ተሳላሚ) በሐምሌ 4 ቀን 1513 ዓ.ም. የኢየሱስ ዓመት ከርሱ ጋር እፈርማለሁ፤›› ብለው ጽፈዋል፡፡ ፖትከን በሥራው ውጤታማ በመሆኑ በቋንቋ ጥናትና መጻሕፍትን በማሳተም ለብዙዎች መልካም አርአያ ሆነ፡፡
እንደ አባ አድኃኖም አገላለጽ፣ በደብረ እስጢፋኖስ ከነበሩት ከሁሉ ይበልጥ እንደ አባ ተስፋጽዮን መልኅዞ ስለኢትዮጵያ ትምህርት የደከመና ያስፋፋ የለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1548-49 በግዕዝ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የሐዋርያት አኰቴተ ቁርባንና ሥርዓተ ክርስትና በላቲን ተርጉመው አጠናቀው አሳትመዋል፡፡ በፈረንጅ ‹‹ጴጥሮስ ህንዳዊ›› ተብለው ይጠሩ የነበሩት አባ ተስፋጽዮን እንደተመሰከረላቸው፣ በትምህርታቸውና ትህትና በተሞላበት ፍቅራቸው ካገኟቸው የፈረንጅ ሊቃውንት መጻሕፍትን ከግዕዝ ወደ ላቲን ሲተረጉሙ ጴጥሮስ ጓልትየሪ ሲረዳቸው፣ በርሳቸው ምርኩዝነትም ማርዮ ቪቶርዮ የኢትዮጵያ ነገሥታት ስም በተርታ የያዘ መጽሐፍና ትንሽ የግዕዝ ሰዋስው ለመጀመርያ ጊዜ አሳተመ፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ባሳተሙት መጻሕፍት መሠረትነት ነው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት መጀመሩ የሚገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በ1983 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲካሄድ ጥናታቸውን ያቀረቡት አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት (ዶ/ር)፣ ‹‹በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት አባት መባል ያለባቸው አባ ተስፋጽዮን መልኅዞ እንጂ ሂዮብ ሉዶልፍ አይደለም፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በደብረ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያዊ ኮሌጅ ወርቃዊ ኢዮቤል አጋጣሚ አባ አድኃኖም ሥእሉ ‹‹ከ፲፭ኛው ዘመን ኢትዮጵያውያን ነጋድያን በቫቲካን ውስጥ›› (Pellegrini Etiopici in Vaticano dal sec, XV) በሚል ርዕስ እንደጻፉት፣ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ከኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙዎቹ ከፍ ያለ ዕውቀት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ በአውሮፓ ከነበሩት ብዙዎች ሊቃውንት በራሳቸው ፍላጎት ሆነ በመንግሥታቸው መልዕክተኝነት ወደነርሱ እየመጡ ስለኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ ሰፊ ጥናት ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በጊዜው የነበሩት ፓፓዎችና ነገሥታት መሳፍንትና መኳንንት እየጠሯቸው ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ከፍ ያለ ዕውቀት ይቀስሙ ነበር፡፡ ስለዚህ ስለኢትዮጵያ ጥናት በመላው አውሮፓ ሊዘረጋ የቻለው በዚሁ ገዳም አማካይነት መሆኑን ባለ ታሪኮች ይመሰክራሉ፡፡
ስለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ ዕውቀት ያላቸው ካርዲናል ቲሠራን የኢትዮጵያ ኮሌጅ የተቋቋመበት የ25ኛውን ዓመት ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹የአውሮፓ ሊቃውንት ስለኢትዮጵያ ዕውቀት መገብየት የቻሉት ከቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ነው፤›› ብለዋል፡፡
የደብረ እስጢፋኖስ ምክትል አለቃ የነበሩት አባ አድኃኖም ሥእሉ በድርሳናቸው እንዳወሱት፣ በገዳሙ ከተማሩት ፈረንጆች አንዱ ያዕቆብ ወመርስ የተባለው ዶሚኒካዊ የግዕዝና የላቲን መዝገበ ቃላት ለመጀመርያ ጊዜ ጽፎ አሳትሟል፡፡ ዴንማርካዊው ቴድሮስ ጴጥሮስ በበኩሉም ብዙ የኢትዮጵያ መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ እየመጡ ከተማሩት ሁሉ የተማረውን ይበልጥ ከሙያ ያዋለው ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ ነው፡፡ ሉዶልፍ ከኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ኢየሱስ ተምሮ የኢትዮጵያ ታሪክ ከነትርጉሙና የግዕዝ ግስ ጽፎ አሳትሟል፡፡ የአባ ጎርጎርዮስ በአስተርጓሚነት የረዳው እናቱ ሐበሻ አባቱ ፖርቱጌዝ የሆነው አንጦንዮስ ዳንድራንደ ነበር፡፡