Monday, July 15, 2024

የወታደራዊ ፍርድ ቤትና የሰሞኑ ውሳኔው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ያለፈው ሳምንት በሁለት ቀናት ልዩነት በመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሰጡ ሁለት ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አስተናግዷል፡፡ የመጀመርያው ሐሙስ ታኅሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በመኰንኖች ክበብ የተሰጠ መግለጫ ሲሆን፣ በዋናነት በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለማርገብ በመከላከያ ሠራዊቱ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለማብራራት ነበር፡፡ በተጨማሪም ይህ መግለጫ በመከላከያው በዕዝ አዛዥነት ወደ ፊት የመጡ የሠራዊቱን ከፍተኛ አባላትን ለማስተዋወቅ ያገዘም ነበር፡፡ በዚህ መግለጫ ወቅት በስሱ ተነስቶና በርካታ ጥያቄዎችን ቆስቁሶ ያለፈው አንዱ ጉዳይ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በቡራዩ አካባቢ በግዳጅ ላይ ቆይተው ወደ ካምፓቸው ሲመለሱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካላገኘን በማለት ወደ ቤተ መንግሥት ከእነ ትጥቃቸው የዘለቁት የመከላከያ ሠራዊት ኮማንዶዎች ላይ የተሰጠው ፍርድ ነበር፡፡

በመግለጫው ላይ 216 ከሚሆኑት የኮማንዶ አባላት መካከል በ66 ያህሉ ላይ የመከላከያ ሠራዊት የወታደራዊ ፍርድ ቤት ፍርድ ማስተላለፉን ያስታወቁት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ በላይ ሲሆኑ፣ ፍርዱ ምን እንደሆነ በዝርዝር ባለመነገሩ ለተለያዩ ትንታኔዎች ተጋልጦ ነበር፡፡ በርካታ ሰዎችም በደርግ ጊዜ የተረሸኑ 60 ጄኔራሎችን በማስታወስና በማመሳከር፣ በእነዚህም ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዷል ሲሉ ተሰምቷል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ በኮማንዶዎች ድርጊት የተቆጡ የሠራዊቱ አባላት፣ ‹‹እዚሁ ዕርምጃ ይወሰድባቸው›› በማለት ለድርጊቱ ተቃውሟቸውን መግለጻቸውንም አክለው ነበር፡፡ ፍርድ ከተሰጣቸው 66 ኮማንዶዎች በተጨማሪም በተቀሩት ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውም በወቅቱ ተጠቅሶ ነበር፡፡

ይህ አገላለጽ በፈጠረው አረዳድ ምክንያት የመከላከያ ሠራዊቱ ሌላ ክላስተር ሁለተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ የተጠራ ሲሆን፣ ይህም መግለጫ ቅዳሜ ታኅሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በመከላከያ ወታደራዊ ፍትሕ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል መሸሻ አረዳ፣ የመከላከያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቃ ሻለቃ ደሳለኝ ደካና በመከላከያ ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ሻምበል ኃይለ ማርያም ማሞ የተሰጠ ነበር፡፡

የዚህ መግለጫ ጭብጥ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ግዳጃቸውን ፈጽመው በመመለስ ላይ ሳሉ፣ ‹‹ኮማንዶዎች ከእነ ትጥቃቸው ከወታደራዊ ዲሲፕሊን ውጪ የዕዝ ሰንሰለት በመጣስ፣ አገራዊ ግዴታዎችን ለመወጣት መነሻ የሆነውን ሠራዊቱ የተደራጀበትን አደረጃጀት በተለይም ጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ሕዝባዊነትን በመጣስ በሠራዊቱ ታሪክ ጥቁር ጠባሳን የጣለ ድርጊት›› በሚመለከት፣ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተላለፉ ውሳኔዎችን ይፋ ማድረግና ሒደቱንም ግልጽ ማድረግ እንደሆነ ኮሎኔል መሸሻ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግና በ2006 ዓ.ም. የወጣውን የመከላከያ ሠራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 809/2006 በመጣስ ወታደሮቹ ተከሰዋል፡፡ ኮሎኔል መሸሻ ወታደሮች ከድርጊቱ በኋላ ከጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንንና በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ሞቱማ መቃሳ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ‹‹አደራ የበሉ መሆናቸውን በአቋም መግለጫቸው የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል፤›› በማለት፣ በቀጣይ የእያንዳንዱን ሚና ለመለየት ወደ ካምፓቸው ተመልሰው ግምገማ እንዲያደርጉ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የወታራዊ ፍትሕ አካላት አደረጃጀት

የወታደራዊ ፍትሕ አካላት አደረጃጀት የሲቪሉ አደረጃጀት የመስታወት ቅጂ ተደርጎ ለብቻው የተደራጀ ሲሆን፣ በሲቪል የፍትሕ አካላት ውስን የሚካተቱ ሁሉም ተቋማት በወታደራዊ ፍትሕ አካላት መዋቅር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካላትም ወታደራዊ ከመሆን የዘለለ የተለየ የአሠራር ልዩነትም የላቸውም፡፡

እንደ የሲቪል የፍትሕ አካላት ሁሉ የወታደራዊ ፍትሕ አካላት በአራት ክፍሎች የተደራጁ ናቸው፡፡ እነዚህም ወታደራዊ ፖሊስ፣ ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ፣ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችና ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ናቸው፡፡ በወታደራዊ ፍትሕ አካላት ተከላካይ ጠበቃ ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑ በመጠኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡

ወታደራዊ ፖሊስ

ወታደራዊ ፖሊስ በሠራዊቱ ውስጥ በግዳጅ ላይና በካምፕ ውስጥ ተፈጥረዋል የተባሉ ወንጀሎችን የሚመረምር ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎች በግዳጅ ላይ የፈጸሙት ወንጀል ምንነትና የጥፋት ደረጃን ለይቶ ለከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያስተላልፋል፡፡

ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ

ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ የፖሊስን ምርመራ ተከትሎ ተቋሙን በመወከል፣ የወታደራዊ ወንጀል ጥርጣሬ ሲኖር ክስ መሥርቶ ይከራከራል፡፡

ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች

ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆነው የሚቋቋሙ ናቸው፡፡ ክስ በመስጠት፣ በማከራከርና በመመዘን ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በሁለት የተከፈሉ መሆናቸውን ኮሎኔል መሸሻ ያስረዳሉ፡፡ የመጀመርያው ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ሁለተኛው ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የቀዳሚ ፍርድ ቤቱ የመጀመርያ ክርክሮችና ፍርዶች የሚሰጡበት ሲሆን፣ በዚህ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ቅር የተሰኘ አካል ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ያመራል፡፡

ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ

ይህ የወታደራዊ ፍትሕ አካል የሕገ መንግሥት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጣጥሞ ለማስኬድ በማለት ለተከሳሽ ጥብቅና እንዲቆም የተቋቋመ አካል ነው ሲሉ ኮሎኔል መሸሻ ያስረዳሉ፡፡

ቤተ መንግሥት ከእነ ትጥቃቸው የገቡ የሠራዊቱ አባላት ክስ ሒደት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ሁሉንም የወታደራዊ ፍትሕ አካላትን በማሳተፍ የተካሄደ መሆኑን፣ ከ500 በላይ የሠራዊቱ አባላትና የመከላከያ ሚዲያ በተገኘበት በብላቴ ማሠልጠኛ ተቋም የተከናወነ እንደነበር በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡

የከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ሚናዎች

የመከላከያ ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ሻምበል ኃይለ ማርያም መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሳተፉ 66 ተከሳሾች የፍርድ ሒደት የጀመረው የተከሳሾችን የወንጀል ተሳትፎ መለየት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥያቄ አናቅርብ በማለት ከእነ ትጥቃቸው ወደ ቤተ መንግሥት ያመሩ ኮማንዶዎች፣ የወንጀል ተሳትፎዎች ደረጃ የተለያየ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዓቃቤ ሕግ ወታደሩን ለድርጊት ያነሳሱ፣ ወደ ቤተ መንግሥት ሲሄዱ የሲቪል መኪና አስገድደው የተሳፈሩ፣ ቤተ መንግሥት ደርሰው መንገድ የዘጉ፣ እንቅስቃሴ በማስተጓጎልና ቤተ መንግሥት ሲገቡ ትጥቅ ፍቱ ሲባሉ ትጥቅ አንፈታም በማለት የተለያዩ ተሳትፎዎችን ያደረጉ የሠራዊቱ አባላት መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሬጅመንትና የሻምበል አዛዦች ተው አትሂዱ እያሏቸው ትዕዛዝ ጥሰው የሄዱ መለየታቸውን፣ የክስ ሒደቱም ከኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዶ 66 ተከሳሾች ጥፋተኛ መባላቸው ተገልጿል፡፡

ሻምበል ኃይለ ማርያም ሒደቱን፣ ‹‹በአገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት መሠረት የተካሄደ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የተላለፈው ቅጣትም ተከሳሾችንም ሆነ ሌሎቹን የሠራዊቱ አባላት የሚያስተምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በወታደራዊ አመፅ ተሳታፊ በመሆን የተከሰሱት ኮማንዶዎች ከአምስት ዓመት እስከ 14 ዓመት ጽኑ እስራት ሲፈረድባቸው፣ አንድ ተከሳሽ በ14 ዓመት ጹኑ እስራት፣ ሦስት ተከሳሾች በ13 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 11 ተከሳሾች በ12 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 12 ተከሳሾች ከ11 ዓመት ከስድስት ወራት እስከ 11 ዓመት ጽኑ እስራት፣ አራት ተከሳሾች አሥር ዓመት ጽኑ እስራት፣ 16 ተከሳሾች ከዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወራት እስከ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት፣ አሥር ተከሳሾች ከሰባት ዓመት ከስድስት ወራት እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት፣ አምስት ተከሳሾች ከስድስት ዓመት ከስምንት ወራት እስከ ስድስት ዓመትና አንድ ተከሳሽ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

የወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ሚና

ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ለሠራዊቱ ወታደራዊ ጥብቅና እየሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት ሻለቃ ደሳለኝ፣ ‹‹ወታደሩ ግዳጅ ላይ እያለ ለሚፈጽማቸው ወንጀሎች በወታደራዊ ፍርድ ቤትም ሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጥብቅና ይሰጣል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ገለልተኛ የሆነ አንድ ቡድን ነው ያሉት ሻለቃ ደሳለኝ፣ ወታደሩ የፈለገውን ጠበቃ ከውጭ ቀጥሮ ሊያቆም ይችላልም ብለዋል፡፡ ይሁንና ወታደራዊ ፍርድ ቤት በወታደራዊ ጥብቅ ሚስጥሮች ምክንያት ጠበቃ ከውጭ ማቆምን ሊከለክል ይችላል፡፡

ከእነ ትጥቃቸው ወደ ቤተ መንግሥት የገሰገሱት የሠራዊቱ አባላት ክስ እንደ ደረሳቸው ወደ ወታደሮች ካምፕ ብላቴ መወሰዳቸውን በመግለጽ፣ ሁሉም ተከሳሾች ክስ እንዲደርሳቸው በማድረግ የወታደሮቹን የሰብዓዊ መብት አያያዝና በፍርድ ቤት ዕውቅና በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እንዳጣሩ ይገልጻሉ፡፡ ተከሳሾቹም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ቅሬታ እንዳልነበራቸውና በፍርድ ቤት ዕውቅና መታሰራቸውን አረጋግጠው፣ በፍሬ ነገር በሕግና በማስረጃ ረገድ ከተከሳሾቹ ጋር በመወያየት የተከላካይ ማስረጃ መሰብሰባቸውን አስረድተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ክሳቸውን እንዲረዱ ዕገዛ እንደተደረገላቸውና በፍርድ ቤትም የክስ መቃወሚያ በማቅረብ ወደ ዋናው ክርክር በመግባት እስከ ብይን ተደርሷል ያሉትና ራሳቸው የተከሳሾቹ አንዱ ጠበቃ የሆኑት ሻለቃ ደሳለኝ፣ ተከሳሾቹ የቅጣት ማቅለያ አቅርበው ከአምስት እስከ 14 ዓመት ተፈርዶባቸው ወደ ታጠቅ ማረሚያ ቤት ገብተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይግባኝን በሚመለከት እየሠራን ነው፡፡ በውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘንባቸው አሉ፤›› ያሉት ሻለቃ ደሳለኝ፣ በጥፋተኝነትና በፍርድ አሰጣጥ ላይ ይግባኝ ለማለት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አስተዳደራዊ ቅጣቶች

መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቡራዩ ወደ ቤተ መንግሥት ያቀኑ ኮማንዶዎች 216 እንደነበሩ፣ ኮማንዶዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት አድርገውና ፑሽ አፕ ሠርተው ከወጡ በኋላ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ጄኔራል ሰዓረና በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ በሰጡት መግለጫ ላይ ተጠቅሶ ነበር፡፡ ይሁንና ከእነዚህ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው የተፈረደባቸው 66 ብቻ መሆናቸው አንዳንዶችን ግር አሰኝቷል፡፡

እንደ ኮሎኔል መሸሻ ገለጻ፣ ዋና ተሳታፊ የነበሩት 66 ናቸው፡፡ ሆኖም በተቋሙ በሁለት መንገድ ፍትሕን ለማስፈን እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ የመጀመርያው 66 ወታደሮች የተቀጡበት የክስ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አስተዳደራዊ ቅጣት ነው፡፡ እነዚህም፣ ‹‹በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀ ደንብ ከወንጀል በመለስ ያሉ ጥፋቶች የሚታዩበት፤›› ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

በሠራዊቱ ውስጥ አስተዳደራዊ ቅጣት የሚባሉት ፑሽ አፕ፣ ውኃ መቅዳት፣ ከኃላፊነትና ከማዕረግ ዝቅ ማለትና ከሠራዊቱ እስከ መሸኘት የሚደርሱ ዕርምጃዎች እንደሆኑም ያስረዳሉ፡፡

ሆኖም ግን ከ216 ወታደሮች መካከል ምን የሠሩ ተለይተው አስተዳደራዊ ቅጣት እንደተጣለባቸው አልተናገሩም፡፡ በዚህ የፍርድ ሒደት ቅጣት የተጣለባቸው የሠራዊቱ አባላት የጓድ መሪዎች፣ የመቶ መሪዎች፣ ምክትል የቡድን መሪዎችና ተዋጊዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ተቋሙ ሰፊ ትኩረት ያገኘና በርካቶችን ያስደነገጠን ድርጊት የክስ ሒደት በየደረጃው ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነበረበት ሲሉ የሚታዩ አልጠፉም፡፡ በተለይም ክሱ ሲመሠረት ጭብጡን ለሕዝብ በማሳወቅና ሚዲያውም ተሳታፊ እንዲሆን በመጋበዝ፣ ግልጽነትን ማምጣት እንደነበረበት የሚከራከሩና የሚተቹ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከብሔራዊ ደኅንነት አንፃር የግድ ግልጽ መደረግ የሌለባቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ ትችቱን የሚያጣጥሉም አሉ፡፡

የወታደራዊ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ

ወታደራዊ ፍርድ ቤት በተለያዩ አገሮች የሚገኝ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው ወታደራዊ ወንጀሎችን የሚዳኝ አካል ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በተለያዩ መንግሥታት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው ወታደራዊ ወንጀሎችን ሲዳኙ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በስፋት የሚታወቁት በሚስጥራዊነታቸው ነው፡፡

የወታደራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በብዛት የማይታወቁ ሲሆን፣ በበርካቶች ዘንድ ትውስታ ሆኖ የቀረ አንድ የወታደራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ ግን ከብዙዎች አንዱ ሆኖ በታሪክ ይጠቀሳል፡፡ ይህም በግንቦት 1981 ዓ.ም. የተፈጸመውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ የተከናወነ ሲሆን በርካቶች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፡፡

ከወታደራዊ ፍርድ ቤት ውጪ በዘፈቀደ ለሞት የተዳረጉ በኤርትራ የኢትዮጵያ የናደው ዕዝ አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ታሪኩ ዓይኔን ጨምሮ በርካቶች በታሪክ ይጠቀሳሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -