Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያው በኅዳር ወር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ የታየበት ግብይት ማከናወኑን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሐዋሳ አሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከሉን ሥራ አስጀምሯል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኅዳር 2011 ዓ.ም. ያገበያየው ምርት ከዓምናው ኅዳር ወር ያነሰ ቢሆንም፣ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ የተመዘገበበት ግብይት እንደተፈጸመ አስታውቋል፡፡

የምርት ገበያው ወርኃዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በኅዳር 2011 ዓ.ም. 79,663 ቶን የምርት መጠን በ3.9 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ የተገበያየው የምርት መጠን ግን በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ካገበያየው ጋር ሲነፃፀር በ4‚337 ቶን ዝቅ ማለቱ ታይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ያገበያየው የምርት መጠን 84‚000 ቶን ያለው ሲሆን፣ የግብይት ዋጋውም 3.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡

በኅዳር 2011 ዓ.ም. ግብይት በተካሄደባቸው 21 ቀናት ውስጥ 21‚468 ቶን ቡና፣ 8‚095 ቶን ነጭ ቦሎቄና 50‚100 ቶን ሰሊጥ በአጠቃላይ በ3.9 ቢሊዮን ብር ማገበያየት ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ለግብይት ቀርቦ የነበረው 23‚834 ቶን ቡና፣ 56‚894 ቶን ሰሊጥ፣ 3‚277 ቶን ነጭ ቦሎቄ ነበር፡፡ በተለይ የሰሊጥ ምርት ከዓምናው የበለጠ ዋጋ በመስጠቱ፣ የግብይት ዋጋውን ከፍ ቢያደርገውም፣ የቀረበው የምርት መጠን ግን ዓምና በኅዳር ወር ከቀረበው ይልቅ በስድስት ሺሕ ቶን ብልጫ ያለው ነበር፡፡ ቡናም ቢሆን፣ የተገበያየበት ዋጋ ከቀደሙት ጊዜያት የበለጠ ዋጋ የተገኘበት በመሆኑ አቅርቦቱ ቢያንስም የዋጋው ዕድገት ብልጫ ያለው ውጤት እንዲያገኝ አስችሏል፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ለገበያ የቀረበው ምርት በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ ከቀረበው የበለጠ ቢሆንም፣ በግብይት ደረጃ ግን በዚህ ዓመት የተመዘገበው በግማሽ ቢሊዮን ብር ብልጫ አስገኝቷል፡፡

ወቅቱ የሰሊጥ ምርት መሰብሰቢያ በመሆኑ አቅርቦቱ እንደጨመረ የሚጠቅሰው የምርት ገበያው መረጃ፣ በኅዳር ወርም ለምርት ገበያው ያቀረበው ሰሊጥ በጥቅምት ወር ከቀረበው አኳያ ከፍተኛ ብልጫ እንደነበረው አመልክቷል፡፡ በዚህ ዓመት ኅዳር ላይ የነበረው የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ570 በመቶ፣ በዋጋ የ656.1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ በወሩ ለግብይት የቀረበው 50‚100 ቶን ሰሊጥ ደግሞ በ2.4 ቢሊዮን ብር መገበያየት መቻሉ ታውቋል፡፡ የሰሊጥ አማካይ የግብይት ዋጋ በኩንታል 4‚728 ብር ሆኖ እንደተመዘገበ የሚያመለክተው መረጃ ይህም አማካይ የሰሊጥ ዋጋ በኩንታል ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ54 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡

በሰሊጥ ግብይት መድረክ የሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ በገበያው የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በመጠን የ87 በመቶ፣ በዋጋ ደግሞ የ88 በመቶ ድርሻ እንደያዘም ምርት ገበያው ጠቅሷል፡፡ የ2010 ዓ.ም. የኅዳር ወር ግብይት ሲታይ 56‚894 ቶን ሰሊጥ ቀርቦ፣ የግብይት ዋጋው በ1.8 ቢሊዮን ብር የነበረ በመሆኑ ዘንድሮ የሰሊጥ ምርት የተሻለ ዋጋ ማስገኘቱን አስታውሷል፡፡ ዓምና በኅዳር የቀረበው 50‚100 ቶን ሰሊጥ ነበር፡፡ በ2.4 ቢሊዮን ብር ቢገበያይም፣ የዘንድሮው የሰሊጥ የግብይት ዋጋ ግን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየት ችሏል፡፡

የቡና ግብይትን የተመለከተው መረጃ ደግሞ በኅዳር 2011 ዓ.ም. 21‚468 ቶን ቡና በ1.4 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይቱን 52 በመቶ በመጠንና 57 በመቶ በዋጋ ይዟል፡፡ ያልታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ 10‚927 ቶን ቡና በ771.9 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን በግብይቱም የኢሉአባቦራ ቡና በመጠን 22.43 በመቶ በመያዝ ሲመራ፣ የጊምቢ ቡና ደግሞ 22.37 በመቶ በመያዝ ይከተላል፡፡

እንዲሁም 2011 ዓ.ም. 193 ቶን የታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ11.6 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ በግብይት መድረኩም የታጠበ የሲዳማ ቡና በመጠን 30 በመቶ ሲይዝ የሊሙና የኢሉአባቦራ ቡና 23 በመቶና 16 በመቶ በመያዝ ይከተላሉ ተብሏል፡፡ በአንድ ወሩ ውስጥ 2‚628 ቶን ልዩ ቡና (ስፔሻሊቲ ቡና) በ182.8 ሚሊዮን ብር መገበያየቱን የሚመለከተው የምርት ገበያው መረጃ እንዲሁም የቡና ዋና የምርት ቅበላ ወቅትም እየተቃረበ ሲሆን የምርት መጠኑ እንደሚጨምር ከወዲሁ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡ 

በዚሁ ኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. 8‚095 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ126.2 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ የነጭ ቦሎቄ የግብይት መጠንና ዋጋ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን 632 በመቶና በዋጋ 66 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የነጭ ቦሎቄ አማካይ የግብይት ዋጋ በ1.2 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም በመጠንና በዋጋ ደግሞ የ147 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡ እንደ ምርት ገበያው መረጃ በቀጣይ ዓመታት ለምርት ገበያው የቀረቡ ምርቶች መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ያመለክታል፡፡

ቀደም ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2011 በጀት ዓመት በመስከረም ወር 1.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 18,103 ቶን ምርት ያገበያየ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 14,684 ቶን ቡናና 2,060 ቶን ሰሊጥ ይገኝበታል፡፡ በጥቅምት ወር ደግሞ ለምርት ገበያው ቀርቦ የነበረው አጠቃላይ የምርት መጠን 25,221 ቶን በ2.2 ቢሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ 25,577 ቶን ቡናና 7,480 ቶን ሰሊጥ ቀርቦ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርት ገበያው በሐዋሳ ከተማ ያስገነባውን የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል ሥራ አስጀምሯል፡፡ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለምርት ገበያው በሰጠው 130 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከሉ የደቡብ ክልል ኃላፊዎችና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ታኅሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡ ማዕከሉን በማስመልከት በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም አገኝ ነገራ እንደገለጹት፣ በማዕከሉ ውስጥ ለሥልጠናና ለአባላት አገልግሎት የሚውል ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ግንባታም እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ይህ ግንባታ በአጠቃላይ 12.64 ሜትር ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 7.76 ሚሊዮን ብር በምርት ገበያም ሲሸፈን ቀሪው 4.87 ሚሊዮን ብር ከአውሮፓ ኅብረት የተገኘው ድጋፍ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የሐዋሳ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልልና በኦሮሚያ ክልል ጉጂና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች የሚገኙ የቡና አቅራቢዎችና አርሶ አደሮች፣ ሥራ ማኅበራት፣ አስመጪና ላኪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኘው የምርት መቀበያ ማዕከል ያስገቡትን ምርት በዚህ የግብይት መገበያየት እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ በዘመናዊ ግብይት የሠለጠኑ አዲስ ተገበያዮችን ቁጥር ለማሳደግም እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶች ወደ ግብይት ሲገቡ እነሱንም በማዕከሉ ለማገበያየት አቅም እንደሚኖረው የአቶ ወንድማገኝ ገለጻ ያስረዳል፡፡

ምርት ገበያው ተደራሽነቱን በማስፋፋት በዚህ ዓመት ከቴፒና ከመቱ ባሻገር ተጨማሪ ቅርንጫፎች ለመክፈት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የነቀምትና የሁመራ ኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትም ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የኤሌክትሮኒክ የመስመር ዝርጋታቸው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በጎንደር፣ በጅማ፣ በአዳማና በኮምቦልቻ ተመሳሳይ ማዕከላት ለመክፈትም እየሠራ ስለመሆኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ያሉንን መጋዘኖችም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ማሻሻያ ይደረግባቸዋል፡፡ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ለመጀመርም እየተንቀሳቀስን ነው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ሽምብራና አኩሪ አተር በቅርቡ ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማካተት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሒደት ከዚህ በፊት በድምፅ ማስተጋባት ይከናወን በነበረበት ወቅት ተገበያዮች አንድን ግብይት ለማከናወን በርካታ ሰዓታትን መጠበቅ ይጠበቅባቸው የነበረውን ጊዜ ያስቀረና በግብይት ሥርዓቱ ይፈጠሩ የነበሩ ስህተቶችን ለመከላከልም አግዟል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የምርት ገበያው ግብይት መቶ በመቶ የምርት ገበያው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በሠሩት የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት ብቻ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመርያ አምስት ወራት 10.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 186‚390 ቶን ያህል ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ በሐዋሳም የተመረቀው ማዕከል በዚሁ መልኩ የሚሠራ ነው፡፡

በዚህ የግብይት ሒደት የተገኙትን ውጤቶች በማየት ከዚህ በፊት በዋናው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥሪያ ቤት ብቻ ይከናወን የነበረውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቱን ባመረተበት አካባቢ ሆነው መገበያየት የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሁመራ፣ ጎንደር፣ አዳማ፣ ሐዋሳና ጅማን የመሳሰሉ ከተሞችን ጨምሮ በስድስት የተለያዩ ከተሞች ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች