ዋና መነሻውን ለአባል አገሮች የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ማስመዝገብ የሚችሉበትን መንገድ እንዲያመቻችና እንዲደግፋቸው ታስቦ በተባበሩት መንግሥታት ከ60 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ እ.ኤ.አ. በ1958 የተመሠረተበትንና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ዘክሯል፡፡
ሰኞ፣ ታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የመሥሪያ ቤቱ ዋና መገኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ የምሥረታውን ሥነ ሥርዓት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደቀመ መኮንን በተገኙበት አክብሯል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከምሥረታው ጀምሮ በአፍሪካ ወሳኝ የኢኮኖሚ መስኮች ጠቃሚ ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረው፣ በተለይም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲመሠረትና ለስምምነት እንዲበቃ የተጫወተውን ሚና አውስተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ብሎም፣ ‹‹አጀንዳ 2063›› ለተሰጠው የአፍሪካ የልማትና የትራንስፎሜሽን ዕቅድ መጠንሰስና መተግበር እያበረከተ ስለሚገኘው አስተዋጽኦም አቶ ደመቀ ጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በ60 ዓመታት የታሪክ ጉዞዎቹ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ልዩ ተግባራት ማከናወኑን አመላክተው፣ አሁንም ቢሆን በአፍሪካ በርካታ ትኩርትና ትብብር የሚሹ ችግሮች እንዳሉና ኮሚሽኑም ለእነዚህ ችግሮች መፈታት በአኅጉሪቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 አፍሪካ ለ40 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠበቅባታል ያሉት ዋና ጸሐፊዋ፣ እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም በአፍሪካ ሰፋፊና ትልልቅ የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የተመድ አካል የሆነው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በስመ ጥሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ (ነፍስ ኄር) አማካይነት በመስታወት ላይ በተሳለና የኢትዮጵያን ባህላዊ ትሁፊት ከሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች ባህሎችና ጠጋዎች ጋር አዳምሮ ያቀረበ ሥዕል ያሸበረቀው፣ የአፍሪካ አዳራሽ ወይም ‹‹አፍሪካ ሆል›› የተሰኘ ሕንፃ በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ በማስገንባት እንዲበረከት የተደረገበት ታሪካዊ ተቋም ነው፡፡