Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሥር ባህላዊ መድኃኒቶች ተመርተው የመጀመርያውን ፍተሻ አለፉ

አሥር ባህላዊ መድኃኒቶች ተመርተው የመጀመርያውን ፍተሻ አለፉ

ቀን:

ለሰውና ለእንስሳት የሚያገለግሉ አሥር የባህላዊ ሕክምና መድኃኒቶች ተመርተውና የመጀመርያውን የላብራቶሪ ፍተሻ ማለፋቸውንና ለቀጣይ የሙከራ ሽግግር መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቁ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) እንደገለጹት በኢንስቲትዩቱ የባህል መድኃኒቶች ዳይሬክቶሬት የተመረቱት የእነዚሁ መድኃኒቶች የመጀመርያ ፍተሻ የተከናወነው በእንስሳት ላይ ነው፡፡ በዚህም ፍተሻ በእንስሳቱ ላይ የታየ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለ ሲሆን ፈዋሽነታቸውም ተረጋግጧል፡፡

አሥሩ የባህል መድኃኒቶች መካከል አንደኛው በእንስሳት ቆዳ ላይ የሚመጣውን ፈንገስ የማጥፋትና የመፈወስ ብቃት ያለው መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ውጤታማነቱ መረጋገጡንና በመድኃኒት አምራች ድርጅቶች ተመርቶ ገበያ ላይ የማውጣት ሥራ ብቻ እንደቀረ አመልክተዋል፡፡

የቀሩት ዘጠኝ ባህላዊ መድኃኒቶች የሙከራ ሽግግራቸውን ሳይጨርሱና በተቆጣጣሪው ክፍል ፈቃድ ሳይገኝ ለምን፣ ለምን አገልግሎት እንዲውሉ ከወዲሁ መግለጽ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ለባህል መድኃኒቶች ምቹ ከሆኑት አገሮች አንዱ ናት፡፡ ምቹ ካደረጋትም መካከል አንዱና ዋነኛው የተለያየ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ማኅበረሰቦች ያሉባት በመሆኗ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ የባህል መድኃኒት አሠራር ሒደት ያለው መሆኑ፣ የአገሪቱ ተፈጥሯዊ አቀማመጥና በውስጡ ያሉ ብዛተ ሕይወት (ባዮዳይቨርሲቲ)፣ በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ እንስሳትና ዕፀዋት መኖር ለባህል መድኃኒት ምቹነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ በ1993 ዓ.ም. በወጣው የጤና ፖሊሲ ውስጥ የባህል ሕክምናን በተወሰነ አግባብ ሊደግፉ የሚችሉ አንቀጾች እንደገቡበት፣ ይህም ሆነ ግን በተግባር ወደ መሬት ለማውረድ ራሱን የቻለ ተግዳሮቶች እንዳሉት፣ ፖሊሲው በአሁኑ ጊዜ በክለሳ ሒደት ላይ እንዳለና በዚህም የተነሳ የሚከለሰው የጤና ፖሊሲ ለባህል ሕክምና ተገቢውን ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የባህል መድኃኒቶች አዋጅና ፍኖተ ካርታ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው በባህል ሕክምና መድኃኒቶች ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በተለይ ፍኖተ ካርታው በቅርቡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለግብዓትነት እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኬሬዲን ረዲ (ዶ/ር) ‹‹የባህል ሕክምና አዋቂዎች ከአያቶቻቸውና ከቅድመ አያቶቻቸው ይዘው የመጡትን ዕውቀት የሚስተላልፉት ለልጆቻቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕክምናው እየላላ፣ የመረሳትና የመጥፋት ሁኔታዎች እየታዩ መጥተዋል፤›› ብለዋል፡፡

አሥር ባህላዊ መድኃኒቶች ተመርተው የመጀመርያውን ፍተሻ አለፉ

 

የባህል መድኃኒቶቹ ከእንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ተላቅቀው በብዛት እንዲሠራባቸውና ችሎታም ሳይኖራቸው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ነን የሚሉትን ሕገ ወጦች ለመቆጣጠር፣ በእግረኛ መንገድ መተላለፊያ ላይ አንጥፈው የባህል መድኃኒት የሚቸረችሩትን መስመር ለማስያዝ የፖሊሲው ክለሳና የአዋጁ መውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ዳዊት ዲቃሶ፣ በባህል መድኃኒቶች ዙሪያ ለሦስት አሠርታት የቆየ ምርምርና ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸው፣ ከምርምርና ጥናቶች መካከል አብዛኛዎቹ የዘርፉን ውስብስብነት ገልጦ ለማየትና ግንዛቤ ለመፍጠር ዕገዛ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

የባህል ሕክምና መድኃኒቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የምርምር ተቋማት ከማምረቻ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ፣ ምርቶቹ ከወጡ በኋላ ተፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን አረጋግጦ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ ፈቃድ እንደሚሰጥና ይህ ዓይነቱ ሒደት እየተከለሰ ባለው ፖሊሲ ውስጥ ተያይዞ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነና ከዚህ አንፃር ከአሥሩ ምርቶች መካከል አብዛኞቹ በሚቀጥለው የአምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ ለገበያ ሊበቁ እንደሚችሉ ነው አማካሪው የተናገሩት፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ አቶ መንግሥተአብ ወልደአረጋይ፣ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ለባህል መድኃኒቶች መስፋፋትና በዚያው ልክ ቁጥጥሩንም በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችሉ መስፈርቶችን አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋሉን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አንድ የጥናት ድርሳን እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ካላት ልዩ ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ንብረት ሳቢያ በዓለም ከሚገኙ የዕፀዋትና የእንስሳት ዝርያዎች አብዛኛዎቹን በመያዝ ትታወቃለች፡፡ ይህም ለጥንታዊ የባህል ሕክምና መሠረት የሆኑ በርካታ አገር በቀል ዛፎችንና የመድኃኒት ዕፀዋት ዝርያዎች ባለቤት ለመሆን አብቅቷታል፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ የዕፀዋት ዝርያዎች፣ በእንስሳትና በልዩ ልዩ ማዕድናት ላይ እንደ ዘመናቸው የሥልጣኔ ደረጃ ምርምር በማድረግ ለዛሬው ትውልድ የደረሱና ለሚቀጥለው ትውልድ ሊተላለፉ የሚገቡ በርካታ መድኃኒቶችን ቀምመዋል፡፡

የባህል ሕክምና ከአምስት ሺሕ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ በኢትዮጵያም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ኅብረተሰቡ የባህል ሕክምና ተጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...