Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቤቶች ኮርፖሬሽን ባደረገው የንግድ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ደንበኞች ቅሬታ አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኮርፖሬሽኑ ጭማሪው ከገበያ ዋጋ በታች ነው ብሏል

በሚያስተዳድሯቸው ንግድ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ላይ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ የቆየው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ከጥር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚያደርገውን አዲስ ጭማሪ ይፋ ሲያደርግ ከደንበኞች ቅሬታ ተነሳ፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከታኅሳስ ወር መጀመርያ ጀምሮ በ6,635 የንግድ ቤቶቹ ላይ የኪራይ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ተከራይ ነጋዴዎችና የድርጅት ባለቤቶች በጭማሪው ላይ አምስት ጥያቄዎችን በማንሳት ቅሬታቸውን መግለጽ ጀምረዋል፡፡

ቅሬታቸውን ያቀረቡት ደንበኞች በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩ ሲሆኑ፣ በአንድ ጊዜ እጅግ በጣም የተጋነነ ጭማሪ እንደተደረገባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአማካይ በወር ሁለት ሺሕ ብር ይከፍሉ የነበሩ እስከ 40 ሺሕ ብር ሲጠየቁ፣ ዘጠኝ ሺሕ ብር ይከፍል የነበረ ሆቴል ደግሞ 108 ሺሕ እንዲከፍል መጠየቁን ለሪፖርተር አሳውቀዋል፡፡

የመጀመርያው ጥያቄ ለዓመታት ሲከፍሉት ከቆዩት ክፍያ በብዙ ዕጥፍ ብልጫ ያለው ጭማሪ በድንገት መደረጉ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው የክፍያ ተመን ማሻሻያ ሲደረግ አልተሳተፍንም የሚል ሲሆን፣ ሦስተኛ ኮርፖሬሽኑ የሚቀርብለትን ቅሬታ ያደምጣል ወይ? አራተኛ የመጀመርያ የውል ጊዜ ሳይጠናቀቅ በተሻሻለው የክፍያ ተመን ውል እንዲገባ መደረጉ አግባብ ነው ወይ? አምስተኛው  ደግሞ የክፍያ ተመን ለማሻሻል ይህ ወቅት ለምን ተመረጠ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከደንበኞቹ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መዋቅሮች አልፎ አሁን ላይ ቢደርስም፣ ለበርካታ ዓመታት የዋጋ ማስተካከያ አለማድረጉን ይገልጻል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ባልተስተካከለ የክፍያ ተመንና በአነስተኛ ክፍያ ሲያከራይ የቆየ በመሆኑ፣ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት እንቅፋት ተፈጥሮብኛል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ የክፍያ ተመን ማስተካከያ ሳያደርግ ለበርካታ ዓመታት በመዝለቁ፣ የኪራይ ዋጋው ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ ቆይቷል ሲል አስረድቷል፡፡ የክፍያ ዋጋውም ከግሉ ዘርፍ ጋር ከፍተኛ ልዩነት ያለው በመሆኑ የንግድ ውድድሩ እንዲዛባ አድርጓል በማለት የሚገልጸው ኮርፖሬሽኑ፣ የአሁኑን ጭማሪ በመቶኛ ማስላትም አግባብ ካለመሆኑም በላይ አሁንም ቢሆን ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው ብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለሁለተኛው የደንበኞች ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ የክፍያ ተመን ማሻሻያ ሲጠና ለደንበኞች መጠይቅ ተበትኖ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በየሩብ ዓመቱ በሚካሄደው የኮርፖሬሽኑና የደንበኞች መድረክ በዋጋ ማሻሻያው ላይ ውይይት የተደረገ ከመሆኑም ባሻገር፣ በካፒታል ሆቴል ከደንበኞች ጋር ውይይት ተደርጎ በውይይቱም መግባባት ላይ መደረሱን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ለሦስተኛው ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ምላሽ የንግድና የድርጅት ተከራይ ደንበኞች፣ የክፍያ ተመን ማሻሻያ አስመልክቶ የሚያቀርቧቸውን የፍትሐዊነት ጥያቄዎች የሚያዳምጥና መፍትሔ የሚሰጥ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በሁሉም የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተቋቁሟል ብሏል፡፡ በቅርንጫፎች ምላሽ ካልተገኘ ደግሞ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡

ለአራተኛው የደንበኞች ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ምላሽ የተሻሻለው የክፍያ ተመን ጥናት የትግበራ ምዕራፍ ላይ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ተግዳሮቶች መካከል፣ ያልተጠናቀቁ የክፍያ ውሎች ጉዳይ አንዱ መሆኑን አስታውሷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንዳለው በኮርፖሬሽኑና በደንበኞች መካከል የተደረጉ አብዛኞቹ ውሎች የጊዜ ገደባቸው አልፏል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የጊዜ ገደባቸው ያልተጠናቀቁ ውሎች ካሉ በልዩ ሁኔታ እንደሚታዩ ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡

የክፍያ ተመን ለማሻሻል ይህ ወቅት ለምን ተመረጠ በማለት ከደንበኞች እየቀረበ ለሚገኘው ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ምላሽ፣ የንግድ ቤቶችና ድርጅቶች የክፍያ ተመን ለማሻሻል ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ጥናት ሲካሄድ ነበር ብሏል፡፡ የጥናቱ መነሻ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው ሪፎርም በዜጎች መካከል የተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር መፈለጉ ነው ሲልም አክሏል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የንግድ ቤቶች መካከል የተለያየ የክፍያ ተመን እየተተገበረ በመሆኑ፣ በደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎች ለመፍታት ባልተመጣጠነና ገበያውን ባላማከለ የኮርፖሬሽኑ ተመን ምክንያት ያላግባብ በአቋራጭ የበለፀጉ ዜጎች በመፈጠራቸውና ለችግሩ ፍትሐዊ ምላሽ መስጠት አስፈልጓል ብሏል፡፡

 የኮርፖሬሽኑ ቤቶች የክፍያ ተመን አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ ሕገወጥነት ያላቸው ክስተቶች መፈጠራቸው በተለይም የሦስተኛ ወገን የአከራይ ተከራይና ቁልፍ ሽያጭ ለማስቀረት፣ የኮርፖሬሽኑ ቤቶች ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ስለሆነ ለጥገና፣ እንዲሁም አዳዲስ ሕንፃዎችን ለመገንባት ከዚህ የተሻለ አማራጭ ወቅት የለም ብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንደሚለው የሚያስተዳድራቸው ቤቶች የክፍያ ተመን ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከግሉ ዘርፍ አንፃር ሲታይ ደግሞ አሁንም ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡

ለአብነት ኮርፖሬሽኑ እንደገለጸው ከ6,635 የንግድ ቤቶች ውስጥ 279 ያህሉ በካሬ ሜትር ከአንድ ብር በታች እንደሚከራዩ፣ 2,057 የሚሆኑት የንግድ ቤቶች ደግሞ በካሬ ሜትር ከአሥር ብር በታች እየተከራዩ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲሱ የኪራይ ጭማሪ መሠረት በካሬ ሜትር እያሰላ ማስከፈል የሚጀምር ሲሆን፣ በካሬ ሜትር እስከ 500 ብር መጠየቁ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ በማድረግ የረጅም ጊዜ ደንበኞችን ማመሰቃቀል፣ ከበስተጀርባው የተደበቀ ሴራ አለው ሲሉ ተከራዮች ብሶታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ግን አሁን ካለው የገበያ ዋጋ አንፃር እንዲህ ያለ ብሶት ማቅረብ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡ ጥናቱ ይፋ በተደረገበት የካፒታል ሆቴል ስብሰባ ወቅት አንዳችም ተቃውሞ ሳይቀርብ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር አስታውሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች