Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ንግድ ባንክ ባወጣው የ120 ሚሊዮን ብር የዳታ ሴንተር ማሻሻያ ጨረታ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኩ ቅሬታ ያላቸውን አስተናግዳለሁ ብሏል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎቹን በኔትወርክ በማስተሳሰር የሚጠቀምባቸውን የኔትወርክ መሠረተ ልማቶችና የዳታ ሴንተር ደኅንነት ማስጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው በመወሰን 120 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የሥራ ጨረታ ቢያወጣም፣ በጨረታው የተሳታፉ ኩባንያዎች ሒደቱ ግልጽነት እንደሌለበት በመግለጽ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ባንኩ በቅርቡ ባወጣው ጨረታ ከተሳተፉ ስድስት የኢንፎሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ የተወሰኑት ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት፣ ለዳታ ሴንተር ማሻሻያ የወጣው የመሠረተ ልማት ግንባታ ጨረታ በቴክኒክ ክፍሉ በኩል ያቀረባቸውን መሥፈርቶች በአብዛኛው ቢያሟሉም ከነባር፣ አቅምና ልምድ ካላቸው መካከል አብዛኞቹ አጥጋቢ ባልሆነ መንገድ ከጨረታው መውደቃቸው የተገለጸላቸው አግባብ ባልሆነና ግልጽነት በጎለደው የጨረታ ሒደት ነው፡፡  

በጨረታው አልታ ኮምፒዩተርና አጋሩ፣ ዩኤስአይ፣ ዴሊቨሪ አይሲቲ ኤንድ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ሞቲ ኢንጂነሪንግ፣ ዌብስፕሪክስና አይኢ ኔትወርክ የተሰኙ ኩባንያዎች ቢሳተፉም፣ በቴክኒክ ምዘናው አምስቱ ሲወድቁ ዌብስሪክስ የተሰኘው ኩባንያ በብቸኝነት ለጨረታው ሁለተኛ ምዕራፍ ወይም ለፋይናንስ ምዘናው ማለፉ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው የገለጹት የተቀሩት ኩባንያዎች፣ አንድ ኩባንያ ብቻ 70 በመቶ የጨረታውን የምዘና ክፍል አልፏል መባሉ በመስኩ ካላቸው ልምድ፣ ከሰው ኃይልና አቅም እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከተሳተፉባቸው ተመሳሳይ ሥራዎች አኳያ ውድቅ የተደረጉበትን የጨረታ ምዘና ሒደት እንደማይቀበሉት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 በጨረታ ሰነዱ ላይ የተምታታ የምዘና አኃዝ መቅረቡንም ለመታዘብ ተችሏል፡፡ የሥራው ዋነኛ ክፍል ቴክኒክ ሆኖ ሳለ ለቴክኒክ የቀረበው የምዘና ነጥብ 30 በመቶ፣ የፋይናንስ ምዘና 70 በመቶ ይይዛል ተብሎ ከመቅረቡ ባሻገር፣ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ ኩባንያ 85 በመቶ ማምጣት አለበት የሚለው የባንኩ የጨረታ መሥፈርት በጨረታ ሰነዱ በግልጽ አለመጠቀሱም የተዓማኒነት ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ሁለት ወራት ያስቆጠረው የጨረታ ሒደት ላይ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ኩባንያዎች እንዳብራሩት፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የባንኩ የጨረታ ሥነ ሥርዓት፣ የምዘና ሒደቱ ነጥቦችና በጨረታው ውድቅ የተደረጉ ኩባንያዎችም ስለወደቁበት ምክንያት ግልጽነት የተሞላበት ማብራሪያና ምላሽ ይሰጥ እንደነበር የጠቀሱ ቢሆንም፣ በአሁኑ የጨረታ ሒደት ላቀረቡት ቅሬታ የተሰጣቸው ምላሽ የተድበሰበሰና የተለመደው ግልጽነት የተጓደለበት ሆኖ እንዳገኙት ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ ስለጉዳዩ በሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ እንደ ወትሮው ሁሉ የአሁኑ የዳታ ሴንተር ማሻሻያ ጨረታም በግልጽነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የባንኩ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ እንዳሉት፣ በባንኩ ግዥ መመርያ መሠረት እንዲሁም በባለሙያዎች በተደገፈ ትንታኔ ለቅሬታ አቅራቢዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ባንኩ ከዚህ በፊትም የነበረውን የጨረታ አሠራር እንደተከተለና ምንም ዓይነት ለውጥ እንደሌለ ገልጸው፣ ቅሬታ አቅራቢዎች ላቀረቡበት ምክንያት ምላሽ የተሰጣቸው ኩባንያዎች በቀረበላቸው ምላሽ ካልረኩ፣ ዳግመኛ የሚታይላቸው ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የግልጽነት ጥያቄ ሊነሳ እንደማይችል አቶ በልሁ አስረድተዋል፡፡

ይህም ይባል እንጂ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለወደፊቱ ባንኩ የሚከተላቸው የጨረታ አሠራሮች እንዲስተካከሉ በማሰብ፣ ወደ ቀደመው የግልጽነት አሠራሩ ይመለስ ዘንድ በማሰብ ጉዳዩን ለሪፖርተር ማሳወቅ እንደፈለጉ ተናግረዋል፡፡

ንግድ ባንክ ከ1,200 በላይ ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ በመክፈት 13.3 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳፈራ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከደንበኞቹ መካከል የሞባይል ባንክና የኢንተርኔት ባንክ ተጠቃሚዎች ብዛት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፣ የኤቲኤም ካርድ ያላቸው ከአራት ሚሊዮን የሚልቁ እንደሆኑ፣ ከ1,600 በላይ የአውቶሜትድ የክፍያ ማሽኖችንና ከ7,000 ያላነሱ የሽያጭ መዳረሻ ማሽኖችን (ፖስ) በማሠራጨት እየሠራ እንደሚገኝ የባንኩ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች