Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዕቅድ የገዘፈው አገር አቀፉ ፕሮጀክት በውጤት ሲለካ  በ2000 የሥልጠና ጣቢያዎች 50 ሺሕ...

በዕቅድ የገዘፈው አገር አቀፉ ፕሮጀክት በውጤት ሲለካ  በ2000 የሥልጠና ጣቢያዎች 50 ሺሕ ታዳጊ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው ይነገራል

ቀን:

በአገር አቀፍ ደረጃ 2004 .. ጀምሮ የተቋቋመው የታዳጊ ወጣቶች የሥልጠና ልማት ፕሮግራም፣ በዋናነት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ግቡን አድርጎ የተመሠረተ መሆኑ ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው በስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ሥልጠና ክፍል ያስረዳል፡፡ የክፍሉ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አልዩ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ፕሮጀክቱ ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በዘጠኙ ክልሎች በሚገኙ 2,000 የሥልጠና ጣቢያዎች 50,000 ታዳጊ ወጣቶች መደበኛ የሥልጠና መርሐ ግብር ተይዞላቸው ተከታታይነት ያለው ሥልጠና ይወስዳሉ፡፡

በፕሮጀክቱ መርሐ ግብር መሠረት 17 የስፖርት ዓይነቶች ዕድሜያቸው 13 15 እና 17 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶችን ያካትታል፡፡ ይሁንና በኅብረተሰቡ ዘንድ በብዛት የሚዘወተሩትንና ትኩረት የሚያገኙትን እግር ኳስና አትሌቲክሱን ጨምሮ በተተኪ አትሌቶች ድርቅ እየተመታ መሆኑ የየስፖርት ዓይነቱ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ሰለሞን ግን ችግሩ ክልሎችን ጨምሮ ብዙዎች ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ስፖርቱ በሚፈልገው ልክ ክለብ አልባ መሆናቸው በፕሮጀክቱ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

ይህ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ልማት ፕሮግራም በመሠረታዊነት ተተኪ ስፖርቶችን ለማፍራትና ከታች ጀምሮ ተከታታይነት ያለው ሥልጠና እንዲሰጥ ያለመ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ እንደ መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ውስጥ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ቁጥራቸው 50,000 ታዳጊ ወጣቶች 2,000 የሥልጠና ጣቢያዎች ላይ ዘመኑንና ወቅቱን የጠበቀ ሥልጠና እንዲያገኙ የፕሮግራም ሰነድ ተዘጋጅቶ ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አተገባበሩን በተመለከተ በአገሪቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የፕሮጀክቱ ባለቤት ሆነው ኮሚሽኑ እንደ መንግሥታዊ ተቋም አጠቃላይ ዝርዝር የአፈጻጸም ፕሮግራም መቅረፅና በፕሮጀክቱ በአሠልጣኝነትና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች ለሚመደቡ ሙያተኞች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ዞን የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችንና የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎችን የሚሠራ ስለመሆኑ ጭምር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ኮሚሽኑ ከእነዚህ የሥራ ድርሻዎች በተጨማሪ አልባሳትንና ሌሎች ቁሳቁሶችንም የማሟላት ግዴታ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በየስፖርት ዓይነቶቹ ፕሮጀክቱ የተቀረፀባቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ የሚያዘጋጇቸው የሥልጠና ማኑዋሎች ምን ያህሉ ወደ መሬት ወርደው ውጤታማ ሆነዋል፣ ያልተሳካላቸውስ? የሚሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች እንደየ ፕሮግራሞቻቸው የመፈጸምና የማስፈጸም ኃላፊነት የእነሱ ድርሻ ስለመሆኑ ጭምር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

በመላ አገሪቱ የተቋቋሙት እነዚህ የሥልጠና ጣቢያዎች እንደየ ክልሎቹ የቆዳ ስፋት የሕዝብ አሰፋፈርና እንደየ ስፖርት ዝንባሌያቸው መቀረፁንም ያስረዳሉ፡፡ በዚሁ መሠረት በአማራ 291 በኦሮሚያ 283 በአዲስ አበባ 276 ድሬዳዋ 203 ሱማሌ 71 ጋምቤላ 101 እያለ በተዋረድ በሌሎችም ክልሎች የሥልጠና ጣቢያዎቹ ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቶች በትክክል ለታለመላቸው ዓላማና ግብ እንዲሁም በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ለመሆናቸው ኮሚሽኑ በየዓመቱ የራሱን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከአማራና ከኦሮሚያ በመቀጠል ሰፊ ፕሮጀክት ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስፖርት ኮሚሽኑ ተቆጣጣሪነት የሚተዳደሩት ፕሮጀክቶቹ፣ ለይስሙላ በዓመት አንድ ጊዜ የተወሰኑ ትጥቅና እንደየ ስፖርት ዓይነቱ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን አድርጌያለሁ ለማለት ያህል እንደሚሰጥ፣ የሚቀርቡት ቁሳቁሶችም በፕሮጀክቱ ለታቀፉ አትሌቶች በበቂ በግማሽ እንኳን ማዳረስ እንደማይችሉ የየክፍለ ከተሞቹ ሙያተኞች ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ በተለይ በአዳጊ ክልሎች የሚቋቋሙ ፕሮጀክቶች ለቁጥርና ለሪፖርት ካልሆነ መሬት ላይ የሚሠራ አንዳች ነገር እንደሌለ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

እንደ ኮሚሽኑ ከሆነ ግን፣ ፕሮጀክቶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ እንቅስቃሴያቸውን አስመልክቶ ከኮሚሽኑ ሙያተኞች በተጨማሪ ክልሎቹ ራሳቸው የየራሳቸው ባለሙያ እንዳላቸው ነው የሚናገሩት፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሥልጠና ጣቢያዎች በምሳሌነት የሚጠቅሱት አቶ ሰለሞን በአሥሩም ክፍለ ከተሞች በእያንዳንዱ በአጠቃላይ እስከ ሃያ የሚደርሱ ሱፐርቫይዘሮች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ በክልሎችም ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በኮሚሽኑ በኩል ዓመታዊ መድረኮች እየተዘጋጁ ግምገማዎች ስለመኖራቸውን ጭምር ያብራራሉ፡፡

ሌላው በኮሚሽኑ አስተባባሪነት ሁሉንም ክልልና ከተማ አስተዳደር የሚያሳትፍ ዓመታዊ የምዘና ውድድሮች እንደሚካሄዱ ያከሉት ኃላፊው፣ ይህ ማለት ግን በእያንዳንዱ የሥልጠና ጣቢያ እንዳችም እንከን የለም ማለት እንዳልሆነ፣ ከእግር ኳሱና አትሌቲክሱ ውጪ ያሉት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ክለብ አልባ መሆናቸው የፕሮጀክቶቹን ውጤታማነት በትክክል ለመገምገም አዳጋች እንዳደረገው ጭምር ያስረዳሉ፡፡ 
ለዚህ ደግሞ ትልቁና ዋናው ማሳያ እግር ኳሱን ጨምሮ ሁሉም ስፖርቶች ከነዚህ ፕሮጀክቶች በተገኙ ታዳጊዎች አማካይነት አኅጉራዊም ይሁን ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ውክልና ይዘው ሲሳተፉ አለመታየታቸው አንዱ ሲሆን፣ ሌላው በሁሉም ስፖርቶች ውጤቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱ እንደሆነ የሚያምኑ አሉ፡፡ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ግን በብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚና በጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል በተለይ በአትሌቲክሱ የታዳጊ ወጣቶቹን ተሳትፎ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ እንዚህ ማዕከላት በክልሎች ከሚገኙ የሥልጠና ማዕከላት ታዳጊዎቹን እንደየ ዝንባሌያቸው ሲመለምሉ ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ተጠቅመው ነው፡፡ ሌሎች ክለቦች ይህንን አሠራር እንዲከተሉት ማድረግ ከተቻለ ውጤቱንም በዚያው ልክ ማጣጣም እንደሚቻል ነው አቶ ሰለሞን የሚያምኑት፡፡

ሃምሳ ሺህ የፕሮጀክት ሠልጣኝ ባለበት የተተኪ እጥረት ለምን? 
እንደ መንግሥት ይህ ፕሮጀክት ሲታሰብ አሁን አለ የሚባለውን የተተኪዎች እጥረት ጨምሮ አገሪቱን በዓለም ታላላቅ መድረኮች ሊወክሉ የሚችሉ ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎችን ማፍራት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ኮሚሽኑ ክልሎችም ሆኑ የከተማ አስተዳደሮች በሒደቱ ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች፣ ለፕሮግራሙ ታሳቢ የተደረገው ለምሳሌ ለአሠልጣኝነት የሚመደቡ ሙያተኞች ስለሚደረግላቸው የሙያ ድጋፍና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ክፍተቶች ካሉ በሚል መረጃዎች እንደሚሰበስቡ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከነበሩ ክፍተቶች በመነሳት ለቀጣዩ እንቅስቃሴ ትክክለኛውን ስትራቴጂ ለመንደፍ እንደሆነም ያምናሉ፡፡

የሥልጠና ማዕከላቱ 17 የስፖርት ዓይነቶች ላይ ተመሥርተው ሲቋቋሙ ዕቅዳቸው በእነዚህ ስፖርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን በበቂ ሁኔታ ለማፍራት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በታሰበው ልክ ማዕከላቱ ተተኪዎችን እያፈሩ እንዳልሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው የሥልጠና ማዕከላቱ ዋነኛ ባለድርሻ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ካልሆኑ የተቀሩት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል ክለብ የሌላቸው ናቸው፣ ከዚያም በላይ ማስፋፋት የሚፈልጉት አንድ ወይም ሁለት የስፖርት ዓይነቶችን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሥልጠና ማዕከላቱ ሊኖር የሚገባው የተመጋጋቢነት ሥርዓት ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህም የተተኪዎች እጥረት የበለጠ እንዲጨምር ምክንያት ሆኖ እንዲቆይ የጎላ ድርሻ እንዲኖር አድርጓል፤በማለት ኃላፊው የችግሩን ዓይነትና መንስኤ ያብራራሉ፡፡ ኮሚሽኑ ከተወሰኑ ክልሎች የሰበሰባቸው መረጃዎች የሚያሳየው ይህንኑ እውነታ እንደሆነ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ኮሚሽኑ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ይቻል ዘንድ እያሰበ ያለው የሚሉት ኃላፊው፣በአገር አቀፉ የሥልጠና ጣቢያ የሚሠለጥኑ ሠልጣኞች ወደ ክለብና ማዕከላት የማይገቡ ከሆነ፣ አሠራሩን በየክልሎቹ ዲቪዚዮኖች በማቋቋም ታዳጊዎቹን ያማከለ እንዲሆን ስትራቴጂው እንደገና ለመከለስ ሐሳብ አለ፡፡ ይህም የሥልጠናውን ቀጣይነት አስተማማኝ ያደርገዋል፤ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ በዚህ መልክ የሥልጠናውን ይዘትና ዓይነት ለመገምገም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

እንደ ዘርፉ ሙያተኞች አንድ ታዳጊ በፕሮጀክት ሊኖረው የሚገባው የሥልጠና ጊዜ ቢያንስ ስድስት ዓመት ነው፡፡ ይህም ታዳጊው ለውድድሮች ተሳትፎ መነሻ እንደሚሆነው የሚያምኑት ሙያተኞቹ፣ በዚህ መለኪያ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ አለ ተብሎ የሚታመነው የፕሮጀክት ሥልጠና ውጤታማነቱ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ጥናቶች ይህንኑ እንደሚያመላክቱ ጭምር ያስረዳሉ፣ የኮሚሽኑ ኃላፊም በዚህ ይስማማሉ፡፡

ከዚህ በመነሳት ኮሚሽኑ ሊከተለው ያሰበው ቀጣይ ስትራቴጂ ታዳጊዎቹ በሥልጠና ጣቢያው የሚኖራቸውን የአራት ዓመት ቆይታ እንዳበቁ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እንዲገቡ ማድረግ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም አካዴሚዎቻቸው በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ እያፈሯቸው ካሉት ታዳጊዎች መካከል በተለይ በአትሌቲክሱ የዕድሜ ችግሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ፡፡ ለክለቦችም የሚመግቧቸው አትሌቶች እንዳሉ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በሪዮ ኦሊምፒክና በዓለም ታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን በመመልከት መናገር እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ 
17 የስፖርት ዓይነቶች በአንድ አትሌቲክስ በጥቂት አትሌቶች የተመዘገበ ውጤት መመዘኛ ይሆናል ወይ? ለሚለው አቶ ሰለሞን በቂ አለመሆኑን ያምናሉ፡፡ መሠረታዊ ችግሩም የሽግግር ሥርዓቱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ክፍተቶቹን መነሻ ያደረገ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ያምናሉ፡፡ የሚገርመው ይህ ፕሮግራም ሲታሰብ እያንዳንዱ ክልል በየስፖርት ዓይነቱ ራሱ የሚያንቀሳቅሰው የሥልጠና ማዕከል ይኖረዋል በሚል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ጭምር ኃላፊው አልሸሸጉም፡፡

ኮሚሽኑ የሚያምናቸውን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሰባት የማይበልጡ የሥልጠና ማዕከላት ብቻ እንዳሉ ይታመናል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ብዙዎቹ እግር ኳስና አትሌቲክስ ካልሆነ ለሌሎቹ ብዙም ትኩረት እንደማይሰጡ ነው አቶ ሰለሞን የሚያምኑት፡፡ ለዚህ ማሳያው በትልልቆቹ ክልሎች የተቋቋሙት የሥልጠና ማዕከላት ማለትም በትግራይ ማይጨው፣ በአማራ ደብረ ብርሃን፣ በኦሮሚያ በቆጂና በደቡብ አገረ ሰላም አራቱም አትሌቲክስ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

ለዚህም ነው ስትራቴጂውን እንደገና መመልከት ያስፈለገው የሚሉት ኃላፊው፣ ዝርዝር ጥናቱም ዘንድሮ ይጀመራል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡ የጥናት ቡድኑም ተያይዞ እንደሚታይ ነው ያስረዱት፡፡

በኮሚሽኑ የሙያተኞች አቅም ውስንነት አለ ለኢትዮጵያ ስፖርት ውድቀት ዓይነተኛ ምክንያት ተብሎ ሲነገር የሚደመጠው የስፖርት ኮሚሽኑን ጨምሮ በየደረጃው ሙያተኛ ተብለው የሚቀመጡ ሙያተኞች ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው በሁሉም ስፖርቶች የሚመዘገበውን ውጤት በመመልከት የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ መመዘኛው የትምህርት ዝግጅት መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ኮሚሽኑ ስትራቴጂዎችን ሲያወጣም ሆነ ሲያስፈጽም የሙያተኛውን አቅም ግምት ውስጥ አስገብቶ መሆኑን ያምናሉ፡፡ 

የምዘና ውድድሮች በዓመት አንድ ጊዜ ከመከናወናቸው በፊት በየሦስት ወሩ የመስክ ግምገማ እንደሚደረግ፣ ይህም የሚከናወነው በኮሚሽኑ ሙያተኞች አማካይነት እንደሆነና እያንዳንዱ ግምገማ ደግሞ መሬት ላይ ካለው ነገር ጋር የተጣጣመ መሆን አለመሆኑ ወደ ኋላ ሄዶ የሚረጋገጥበት አሠራር በመኖሩ እግረ መንገዱን ሙያተኛው ማን ነው የሚለውን መልስ የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ ብዙም ችግር እንዳልገጠመው ነው ያስረዱት፡፡ በእርግጥ ኮሚሽኑ እስከ ታች ወርዶ ለመሥራት የሰው ኃይል እጥረት ያለበት መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡

ሥራዎች በአብዛኛው የሚከናወኑት ወረዳዎች ለአውራጃ፣ አውራጃዎች ደግሞ ለክልሎች፣ እያለ ሪፖርቶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው ለኮሚሽኑ የሚደርሱበት አሠራር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችም በራሳቸው መንገድ ሙያተኞቻቸውን በማሰማራት የመስክ ግምገማ እንደሚያደርጉም ያስረዳሉ፡፡ ዓምና በስፖርቱ የታየውን ደካማና ጠንካራ ጎን የሚገመግም መድረክ በመስከረም ወር አዳማ ከተማ ላይ ከሁለም ባለድርሻ አካላት 400 ሰው በላይ የታደሙበት ጉባዔ ተደርጓል፡፡ በዚያ ጉባዔ አሉ የሚባሉ ችግሮችና ተግዳሮቶች ቀርበው ጥልቅ ውይይት ተገርጎባቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ጭምር መቀመጡ የሚታወስ ስለመሆኑ ጭምር ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አደረጃጀቶችን አስመልክቶ በተለይም የስፖርቱ የተጠሪነት ጉዳይ ወጥነት የሌለው ከመሆኑ አኳያ ኃላፊው፣ በዚህ ረገድ ሁሉም ለምንና በምን መመዘኛ እንደተቀመጠ ስለማያውቅ ያን ያህል ችግር እንደማይሆን ነው ያስረዱት፡፡ በአጠቃላይ ግን ስፖርቱን የሚመለከት ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በአገር አቀፍ ደረጃ መቋቋም እንዳለበት፣ አደረጃጀቱም በተዋረድ እስከ ታችኛው እርከን መውረድ እንዳለበት ስምምነት ላይ ስለመደረሱ ጭምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...