Friday, January 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከሉ ይታይ ይገምገም!

የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከሉ ይታይ ይገምገም!

ቀን:

የአገራችን የትምህርት ጥራት ጉድለት የወለደው የአዲስ አበባ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ (Certificate Of Compliance-COC) ማዕከል በ2000 ዓ.ም. በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ አሥር ዓመታት ሞላው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ሙያተኞችን ለማቅረብ ራዕይ ሰንቆ የተመሠረተው ይህ ተቋም፣ ስድስት ኪሎ ግብፅ ኢምባሲ አካባቢ የሚገኘው ዋናውን ቢሮ ጨምሮ በልደታ፣ በመገናኛ፣ በአጎና ሲኒማ አካባቢ፣ በሰሜን ሆቴልና በአራት ኪሎ አካባቢ አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ የምዘና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

እርግጥ ብቁ ሙያተኞችን እያመረተ ነው ወይ? የሚለው ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ይኼንን ለማለት የሚያስደፍረው አጠቃላይ አሠራሩ ከሌብነት አለመፅዳቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሌብነትን ሕጋዊ ለማድረግ መዳዳቱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መስረቅን የተጠየፈ አንገቱን የሚደፋበት፣ በመስረቅ የተካነ የሚሾም የሚሸለምበት ተቋም እየሆነ ነው፡፡ ምን ዓይነት አሠራር ነው ያለው የሚለውን በዝርዝር ከማቅረቤ በፊት ተቋሙ ብቻ የሚጠቀምባቸውን አንዳንድ ቃላት ለውጭ ሰው ባዕድ ሊሆኑ ስለሚችሉ የቃላት ትርጉማቸውን ወይም ፍቺያቸውን በአጭሩ በማስቀመጥ እጀምራለሁ፡፡

ምዘና፡- ማለት በሥልጠና ወይም በልምድ የተገኘ ዕውቀት፣ የክህሎትና አስተሳሰብን ብቃት ለማረጋገጥ በማዕከሉ አስተባባሪነት በመዛኝ የሚከናወን፣ ከተመዛኙ የተግባር አፈጻጸም መረጃ የማሰባሰብና ውሳኔ የመስጠት ሒደት ነው፡፡

መዛኝ፡- ማለት በተወሰነ የሙያ መስመር ተፈላጊ የሆነውን የትምህርት (የሥልጠና) ደረጃና የሥራ ልምድ ዝግጅት አሟልቶ በማዕከሉ የተመለመለ፣ ምዘና ወስዶ ብቃቱ የተረጋገጠ፣ ዕውቅና የተሰጠውና ከማዕከሉ ጋር የውል ስምምነት ገብቶ የምዘና አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ ነው፡፡

ተመዛኝ፡- ማለት በሥልጠና ወይም በልምድ ባገኘው የሙያ መስመር ያለውን የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ ተፈላጊ መረጃዎችን አሟልቶ በራሱ ሙሉ ፈቃድ ወደ ማዕከሉ በመቅረብ ለመመዘን የተመዘገበ ግለሰብ  ነው፡፡

የምዘና መሣሪያ፡- ማለት አንድ በሥልጠና ወይም በልምድ የተገኘ ሙያ ባለቤት በሙያው ብቃት ያለው መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማረጋገጥ ባለሙያው በምዘና ሒደት ውስጥ ሲያልፍ መዛኙ ስለተመዛኙ የተግባር አፈጻጸም ዝርዝር መረጃ የሚሰበስብበት መሣሪያ ነው፡፡

የምዘና ባለሙያ፡- ማለት ማዕከሉ ያወጣውን  መስፈርት አሟልቶ ምዘና ከሚሰጥባቸው ሙያዎች ባንዱ ዘርፍ በምዘና ባለሙያነት ተቀጥሮ በማገልገል ላይ የሚገኝ ግለሰብ ነው፡፡

ሀተታ፡- ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የአሠራር ግድፈቶች በተለያየ ጊዜ ተቋሙን ለሚመሩት የበላይ አመራሮች ቀርቦ ጆሮ ዳባ ልበስ ስለተባለ እንጂ ገመናን ደጅ በማስጣት ማንንም ለመክሰስ ታስቦ እንዳልሆነና የዜግነት ግዴታን ከመወጣት ውጭ ምንም ዓይነት ፍላጎት (Intention or Interest) ከሌለው አንድ ዜጋ የተሰነዘረ ትሁት ጥቆማ እንደሆነ ተረዱልኝ፡፡

የአሠራር ክፍተቶች (እንከኖች) እንደሚከተከለው ይቀርባሉ

አንድ የመንግሥት ተቋም አንድን ባለሙያ በኮንትራትም ሆነ በጊዜያዊነት፣ በቋሚነት ሆነ በትርፍ ሰዓት ሊያሠራ ሲያስብ ግልጽ በሆነ ማስታወቂያ አስነግሮ (አስታውቆ) መሆን አለበት፡፡ ይህ ግን አልሆነም፣ እየሆነም አይደለም፡፡ አንድ የምዘና ባለሙያ መዛኝ አላፈራህም ተብሎ የሚወቀስበት አሠራር መዘርጋት ምን ማለት ነው? ተቋሙ መዛኞችን የመመልመል ትልቅ ኃላፊነት ራሱ ተቋማዊ በሆነ መንገድ መወጣት ሲገባው በጥቂት ባለሙያዎች ጫንቃ ላይ ሥራውን ሁሉ ጥሎ ለብልሹ አሠራር በሩን ወለል አድርጎ ከፍቷል፡፡ ይህ ባለሙያ ሳይፈልግ በግድ በዘርፉ የተማረውን ወዳጁን፣ ጓደኛውን ወይም የጓደኛውን ጓደኛ ወይም ዘመድ አዝማዱን እየመለመለ መዛኝ እንዲያደርግ የይለፍ ፍቃድ መስጠት ምን የሚሉት አሠራር ነው? ምክንያቱም የሚያውቀውን ሰው ነውና ሊመለምል የሚችለው፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ብዙ መዛኝ በማፍራቱ ይሾማል፣ ይሸለማል፡፡ አሠራሩ ችግር እንዳለበት የተረዳ ባለሙያ ‹‹መዛኝ አላፈራም›› ቢል ዕጣው ከደረጃ ማነስ፣ ባስ ሲልም ከሥራ መባረር ሊሆን ይችላል፡፡ ባጭሩ በተዘዋዋሪ ይህ መዛኝ ተጠሪነቱ ለመለመለው የምዘና ባለሙያ ወይም ተቋሙ ውስጥ ለሚሠራ ግለሰብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ጥያቄው ‹‹እገሌን ብቁ አድርግ (አሳልፍ)፣ እገሌን ብቁ አታድርገው (እገሌን ጣል)›› ላለማለቱ ምን ማረጋገጫ አለን? ይኼንን እንዳይል ምን ያግደዋል? ከምታገኘው ገቢ ‹‹ይህን ያህል ድርሻ የእኔ ነው›› ብሎ ተዋውሎስ እንደሆን ምን ማረጋገጫ አለን?፣ መዛኝ መዳቢውም የምዘናው ባለሙያ ስለሆነ ጠቀም ያለ እጅ መንሻ ተቀብሎ ‹‹በዚህ ቀንና ቦታ ከእገሌ ተቋም የሚመጡትን በሙሉ ብቁ እንድታደርግ (እንድታሳልፍ) ይህን ባታደርግ ዋ!›› ቢለው ማን ከልካይ አለው? ‹‹የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍን›› ዘምሮ እኔም ወግ ይድረሰኝ ብሎ ዘመዱን፣ ጓደኛውን መዛኝ ሊያደርግ ሞክሮ በተፈጠረው የጥቅም ትስስር ምክንያት ‹‹ዞር በል ወግድ›› ሲባል እኮ እንዴት? ብሎ አካኪ ዘራፍ ቢል የማን ያለህ ሊባል ነው? በተጨባጭም ‹‹ወዳጄን ለምን መዛኝ አላደርግሽም›› ብሎ ቢሮ ውስጥ የተደባደበ የተቋሙ ሠራተኛ በዲስፕሊን መቀጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለማረጋገጥ የሚፈልግ አካል ካለ ፋይሉን በተቋሙ መዝገብ ቤት ውስጥ ያገኘዋል፡፡

አንድ የልህቀት ማዕከል፣ ብቁ ሰዎችን እንዲያመርት ተልዕኮ የተሰጠው ትልቅ ተቋም እስከዚህ ጥልቅ አዘቅት ድረስ ወርዷል፡፡ በአገር ደረጃ ሙያተኞችን ይመዝናሉ፣ ብቃትን ይፈትሻሉ የተባሉት መዛኞች በሙሉ የመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡ የመጀመርያ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ተመዛኞች በዲፕሎማና ከዚያ በታች ባላቸው መዛኞች መመዘን በየትኛው አመክንዮ ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል? በቀደመው መመርያ ቁጥር 5/2005 አንቀጽ 3.29 ተራ ቁጥር 13 ላይ መዛኞች ዲግሪ እንዲኖራቸው አይገደዱም ነበርና፣ መመርያው ከአምስት ዓመት በኋላ መመርያ ቁጥር 3/2010 ሆኖ የተሻሻለው የቀደሙት መዛኞች ዲግሪ ከያዙ በኋላ ታስቦበት ሳይሆን አይቀርም ለማለት አንችልም፡፡ አሁንም ቢሆን መዛኝ ለመሆን ዲግሪ የማይጠየቅባቸው የሙያ ዘርፎች (Hard Skills) መኖራቸው በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በዲግሪ ለምታስመርቅ አገር እንቆቅልሽ ነው፡፡

 በዚች መከረኛ በሆነች አገር ‹‹እንዲህ ዓይነት ብዙ ችግሮች በየትም ተቋም ሊኖሩ ይችላሉ›› ሊባል ይችላል፡፡ የሲኦሲ ተቋም አሠራር መዝረክረክን አደገኛ የሚያደርገው ትውልድን አምካኝ መሆኑ ነው:: ቀላል ምሳሌ ልስጥ. . . በለብ ለብ ትምህርት የተመረቁ የጤና ባለሙያዎች፣ በለብ ለብ ብቁ (Certified) የሚሆኑ ከሆነ ወደ ሥራ ሲገቡ ብዙ ዜጎችን ስላለመግደላቸው ምን ዋስትና አለን? ለአንድ አገር ዕድገትና ብልፅግና መሠረተ ልማትና ቴክኖሎጂ 40 በመቶ ሲያዋጡ፣ 60 በመቶው ዋልታና ማገር ብቁ የሰው ኃይል መሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ትልቅ ሀብት ከመከነ የነገ የአገራችን ዕጣ ምንድን ነው? 

ሌላው የመሥሪያ ቤቱ ሚስጥሮች በሙሉ መዛኞች ጋር ቀድሞ መድረሱ ነው፡፡ በማን ቢባል ወደዚህ ሥራ ባመጣው የተቋሙ ሠራተኛ ቀድሞ ይነገረዋል፡፡ አንድ መዛኝ ላይ የታየ ክፍተት ካለ አመራር ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት የመለመለው አካል ለመዛኙ ‹‹ጥፋ፣ ወይ እንዲህ ብለህ መልስህን አዘጋጅ አልያ ልትቀጣ ነው›› ብሎ ባስጠነቀቀው መሠረት መልሱን አዘጋጀቶ፣ በመቅረብ ሥራዎች ሁሉ ገና መዳህ ሳይጀምሩ ሽባ ይሆናሉ፡፡

ከላይ በሰፈረው የቃላት ፍቺ መሠረት ‹‹መዛኝ ማለት . . . ከማዕከሉ ጋር የውል ስምምነት ገብቶ የምዘና አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ  ነው፤›› ይላል፡፡ ነገር ግን አንድም መዛኝ አንድም ጊዜ የውል ስምምነት ፈርሞ አያውቅም፡፡ ይህ ደግሞ አንድ መዛኝ ያሻውን ቢያደርግ ለመቅጣት ሆነ ለመግራት የሚያስችል የሕግ መደላድል ቢኖርም ተፈጻሚ ለምን አልሆነም? ይህን ለማስፈጸም ለምን ሰነፍን? ጥያቄው ይኼ ነው፡፡

የጥቅም ግጭት (Conflict of Interest) ስላለው አንድ መዛኝ አሠልጣኝ፣ አንድ  አሠልጣኝም መዛኝ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱን (ፈተናውን) በሙሉ ስለሚያውቀው ያንን ፕሮጀክት ሠልጣኞችን (ተማሪዎችን) በሙሉ አሠልጥኖ ብቁ እንዲሆኑ ይረዳል ወይም የእሱ የሆኑ ሠልጣኞችን (ተማሪዎችን) ሊመዘኑ እሱ ጋር ቢቀርቡ ሁሉንም ብቁ አያደርግም ተብሎ ስለማይታመን ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን በድሮው መመርያ ቁጥር 2/2005ም ሆነ በተሻሻለው (በአሁኑ ሰዓት ሥራ ላይ ባለው) መመርያ ቁጥር 3/2010 ላይ ይኼንን የሚከለክል አንቀጽ የለም፡፡ በተለያዩ መድረኮችና በጽሑፍ ይህ እንከን ቢገለጽም የበላይ አመራሮች ይኼንን አንቀጽ በመመርያው ውስጥ ለማካተት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ስህተቱ ካለማወቅ የመነጨ ከሆነ ስህተቱ ሲጠቆም ለምን ለማካተት ፈቃደኛ ሳይኮን ቀረ?

ምዘና መሣሪያ ቋት (Tool Bank) በተቋሙ የመጨረሻ አመራር አካል በሚስጥር መያዝ ሲኖርበት ይህ ባለመሆኑ ምክንያት የምዘና መሣሪያዎች በተመዛኞች እጅ በተለያየ ጊዜ እጅ ከፍንጅ እየተያዘ ጥቂቶች እየከበሩበት ነው፡፡ ቁርስ በልቶ ምሳ ለመድገም ቅንጦት በሆነበት በመንግሥት ሥራ ደመወዝ መኪና የገዙ አሉ ስንላችሁ ከት ብላችሁ እንዳትስቁ አደራ! ጥያቄው ይህ በሚስጥር ሊያዝ የሚገባው የምዘና መሣሪያ እንዴትና በማን ወጣ ነው?

ተቋሙ ቢሮ ለመሥራት አቅም አጥቶ ነው ለቢሮ ኪራይ በየዓመቱ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጣው? ተቋሙ ቢሮ ለመሥራት አቅም አጥቶ ነው አራት ኪሎ አካባቢ የተሰጠው መሬት የተነጠቀው?

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ይህ ተቋም ትውልድንና አገርን ለመግደል ታስቦ የተቋቋመ እስኪመስል ድረስ ባለቤት አልባ ሆኗል፡፡ የልህቀት ማዕከል እንደመሆኑ በአፈጻጸም የላቁ፣ በሥነ ምግባር ምሥጉን የሆኑ መሪዎች ሊመሩት ሲገባ በዲስፕሊንና በብቃት ማነስ ከሌላ ተቋም ገለል የተደረጉ ግለሰቦች የሚያሾሩት ተቋም እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ገንዘብ ቢዘረፍ ገንዘብ ይተካል፣ ትውልድ ቢመክን በምን ይተካል?! የመከነ ትውልድ የመከነ አገርን ይፈጥራልና በቶሎ መንግሥት ሊደርስለት፣ ለአገርና ለትውልድ የሚገዳቸው ሚዲያዎችም አብዝተው ሊጮሁለት ይገባል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት አንከኖች ከብዙ በጥቂቱ ‹‹ዝርዝር ኪስ ይቀዳል›› በሚል ለማሳያ ያህል ብቻ የቀረቡ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ አበቃሁ!

 (ታማኝ ምንጭነህ (የብዕር ስም)፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...