Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እውነተኛ ውድድር ሲመጣ ባንኮቻችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን መሸሸጊያቸው ኅብረተሰቡ ነው›› አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ

አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ፣ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የቢዝነስ ዴቨሎፕመንትና የኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ

አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የቢዝነስ ዴቨሎፕመንትና የኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊና የቦርድ ጸሐፊ በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከህንድ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ በሰው ሀብት አስተዳደርና በተቋም ግንባታ፣ እንዲሁም በጋዜጠኝነትና በኮሙዩኒኬሸን መስክ ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡  በተለይ በኢንሹራንስ ዘርፍ በርካታ የጥናት ወረቀቶች በማቅረብ የሚታወቁት አቶ ፍቅሩ፣ በአሜሪካ የፍሎላይፍ ኦፊስ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ቻርተር፣ በዚሁ ኢንስቲትዩት የሪኢንሹራንስ ተባባሪ አስተዳዳሪ በመሆን እያገለገሉ በለንደን የቻርተርድ ኢንሹራንስ ኢንስቲትዩት ዕውቅና ካገኙባቸው መካከል ይጠቁሳሉ፡፡ በዚህ በርካታ የሥራ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ያካበቱት አቶ ፍቅሩ፣ በኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ13 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉ፣ በተለይም በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ውስጥ በልዩ ልዩ የሥራ መደቦች ውስጥ በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ለውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ገበያ መከፈት እንደሚኖርበት የጥናት ወረቀት አዘጋጅተው ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ዳዊት ታዬ ይህንኑ የጥናት ወረቃታቸውን መሠረት በማድረግ አናግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የኢንሹራንስ ዘርፍ ደካማ ነው፡፡ ለአገራዊ ኢኮኖሚው እያደረገ ያለው አነስተኛ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው፡፡ ዘርፉ በዚህን ያህል ደረጃ ሊገለጽ የቻለው ለምንድነው?

አቶ ፍቅሩ፡- ይኼ የሆነበት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ የመጀመርያው ግን ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚሸጡት አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንደኛ ሰው የሚገዛው የአገልግሎት የመድን ሸፋን ዓይነት ምንድነው? ብሎ ይህንን ከማቅረብ ጋር የተያያዘም ነው፡፡ ከኢንሹራንስ የሚገዛው መፍትሔ ነው፡፡ ችግር የሚቀርፍና ሽፋን የሚሰጥህን አገልግሎት ነው የምትገዛው፡፡ የኢትዮጵያን ስታይ ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በግብርና ላይ ያለ ነው፡፡ ከተማ ላይ ያለውን ኮሜርሻል የሆነውን ኢንሹራንስ የሚፈልገው ሰው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሠሩት ይህንኑ ነው፡፡ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚሸፈን የኢንሹራንስ አገልግሎት የለም፡፡ የግብርና መድን ለአርብቶ አደሮች፣ ለአርሶ አደሮችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሚሆን፣ በጥንቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩ ተብሎ ለእነዚህ የሚሆን ኢንሹራንስ ይዘህ እስካልሄድክ ድረስ ኅብረተሰቡን ተደራሽ ማድረግ አትችልም፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ችግር የአገልግሎት አቅርቦት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ኩባንያዎች የሚሰጡት ምክንያት አትራፊ አይደለም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ተቋም አትራፊ ሊሆን የሚችሉበትን አሠራር መዘርጋት አለመቻላቸው ለምንድነው? ችግሩስ ምንድነው?

አቶ ፍቅሩ፡- ብዙዎቹ ኩባንያዎች ትርፍ ነው የሚያስቡት፡፡ አትራፊ አይደለም ይላሉ፡፡ ለባለአክሲዮኖቻችን ትርፍ ማስገኘት አለብን፣ ዲቪደንድ መክፈል አለብን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኢንሹራንስ በባህሪው ብዙ ኅብረተሰብ በማቀፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሚሊዮን ሕዝብ አለ ስትል በዚህ የሕዝብ ቁጥር የምትሰበስበው ዓረቦን በጣም ብዙ ነው፡፡ ከዚያ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከብዛት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሁለተኛ ዘመናዊ ማድረግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አገልግሎት ውድ የሚያደርገው የሥርጭት ወጪ ነው፡፡ አገልግሎቱን ሰዎች ዘንድ ለማድረስ የሥርጭት ወጪው እስከ 50 በመቶ የሚደርስ መሆኑን ጥናቶች አሳይተዋል፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አሁን ባለው አደረጃጀት መሥራት ይችላሉ፡፡ አሁን እነሱ አንድ ቅርንጫፍ ከፍተው ነው መሥራት የሚፈልጉት፡፡ ኦቨር ሄድ ኮስቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን ባሉ መዋቅሮች ተጠቅመው ወጪ ቀናሽ ሥራ መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ በመንግሥት ከአነስተኛና ጥቃቅን በብድርና ቁጠባ ተቋማት ጋር ሽርክና ፈጥረው ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ፖስታ ቤቶችን ጭምር ተጠቅመው መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ ሌሎች አገሮች በፖስታ ቤቶችና በሱፐር ማርኬቶች ጭምር ኢንሹራንስ ይሸጣሉ፡፡ ከባንኮች ጋር ተቀናጅተው ‹ባንክ አሹራንስ› የሚባለውን መሥራት ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የባንክና የኢንሹራንስ ተደራሽነት እኩል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብረው ቢሠሩ ብዙ ነገር ሊቀየር ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1,300 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ 100 ቅርንጫፎች ያሉት በመሆኑ አገልግሎቱን ለማስፋት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቅርንጫፍ ተጠቅሞ በሽርክና መሥራት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ወጪ በቀነሰ መንገድ ስለማይሠሩ ወጪያቸው ይንራል፡፡ አዋጪ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ሕዝቡ ገብተው ለመሥራት አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነፍስ ወከፍ ገቢን አይተው፣ ኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ አገናዝበው ለዚያ የሚሆን የተመጣጠነ አገልግሎት ይዞ ያለመምጣት ችግር በመኖሩ ዘርፉ ሊያድግ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኢንሹራንስ ሽፋኑን ለማዳረስ እንደ መፍትሔ የሚቀርበው ምንድነው?

አቶ ፍቅሩ፡- መፍትሔው በጥራት ላይ የተመሠረተና ኅብረተሰቡን የሚጠቅም አገልግሎት ይዞ መምጣት ነው፡፡ ሁለተኛ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኅብረተሰቡ መግባት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የጤና መድን ሽፋን መጥቶ ነበር፡፡ ይህ ሽፋን አሁን የሚሰጠው በጤና ጥበቃ ሥር ባለ ኤጀንሲ ሥር ሆኗል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አዲስ አገልግሎት ይዘው ባለመወጣታቸው ነው፡፡ ገፍተው አዲስ ፕሮጀክት ይዘው አይመጡም፡፡ ስለዚህ በጤና መድን ሽፋኑ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸው ኢንሹራንስ ሰጪ፣ ከሙያቸው ውጪ ተቆጣጣሪ ሆነው ሊሠሩ ነው ማለት ነው፡፡ መፍትሔው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥናት ላይ የተመረኮዘና ኅብረተሰቡን ሊያነቃ የሚችል አገልግሎት ማቅረብ ነው፡፡ ኅብረተሰቡን ያገናዘቡ አዳዲስ አገልግሎቶች ይዘው መምጣት አለባቸው፡፡ ብዙ አማራጮችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 40 በመቶው ሙስሊም ኅብረተሰብ ነው ይባላል፡፡ ለእነሱ የሚሆን የኢንሹራንስ አገልግሎት አለ፡፡ በተለያዩ የዓረብ አገሮች ይህ የኢንሹራንስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ በባንኩ ዘርፍ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ለሙስሊም ኅብረተሰብ የሚሆን ብዙ የመድን ሽፋን የሚሰጥበት አገልግሎት አለ፡፡ ይህንን ይዞ ለመሥራት የደፈረ ኩባንያ ግን የለም፡፡ ስለዚህ የኅብረተሰቡን ፍላጎት እያየ አገልግሎት የሚሰጥበት አሠራር መፈጠር አለበት፡፡   

ሪፖርተር፡- ሌላው ብዙ የአክሲዮን ኩባንያዎች ተደራሽነት ላይ ሳይሆን ዓመታዊ ትርፍ ላይ መንጠልጠላቸው የኢንሹራንስ ዘርፍ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ይባላል፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- ቢዝነስ ሲሠራ በአካውንቲንግም ‹ቢዝነስ ኮንትውኒቲ ፕሪንስፕል› የምንለው አለ፡፡ ቀጣይነት ያለው ሥራ ላይ መሠራት አለበት፡፡ አሁን እኮ የባንክና የኢንሹራንስ ተደራሽነት ስለሌለ ነው ኩባንያዎች እያደጉ ነው የሚባለው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የግሽበት ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ አምና የነበረ መኪና ዘንድሮ ሊጨምር ስለሚችልና ፕሪሚየሙ (ዓረቦን) እየጨመረ ስለሚመጣ ሊሆን ይችላል እንጂ አደገ የሚባለው ተደራሽነትን በማስፋት አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ከ55 በመቶ በላይ የሚሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቅርንጫፎች ከተማ ውስጥ ናቸው፡፡ ወደ ታች አልወረደም፡፡ ኅብረተሰቡ ከተማ ብቻ አይደለም ያለው ገጠርም ነው፡፡ ስለዚህ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትርፍን ብቻ ማየት ሳይሆን ዘለቄታዊነትን ማሰብ አለባቸው፡፡ ዘለቄታ ላይ ወይም ለረዥም ጊዜ ትርፍ የሚያመጡ ሥራዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡ አንዴ ማክሮ ኢንሹራንስ ላይ ጥናት አድርገን ነበር፡፡ ከ15 ሚሊዮን በላይ አባወራ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ እዚያ ውስጥ ገብተው ቢሠሩ በጣም ብዙ ቢሊዮን ብር የኢንሹራንስ ዓረቦን ይገኛል፡፡ አሥርና 15 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ማግኘት ይቻላል፡፡ አሁን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል ዓመታዊ ዓረቦናቸው 8.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህንን ቢሠሩ ግን ዓረቦኑን 20 ቢሊዮን ብር ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በአፍሪካ ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ሲታይ ወደ ኋላ የቀረ፣ ተደራሽነቱ ከሁሉም ያነሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለዚህ ደግሞ እርስዎ አሁን የገለጹልኝ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ያለመከፈቱ የፈጠረው ተፅዕኖ ነው ይባላል፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- አዎ፡፡ አንዱ ምክንያት ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት አለመሆኑ ነው፡፡ አሁን ያሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ክሬሙን ነው ከላይ እየወሰዱ ያሉት፡፡ መርጠው ነው ኢንሹር የሚያደርጉት፡፡ ሁሉም ትርፍ ነው የሚያስበው፣ እሱ ነው ክሬሙ፡፡ መፍትሔ ግን እየሰጡ አይደለም፡፡ በአሁን ወቅት ግን ኬንያ ከኛ ብዙ ርቀት ሄዳለች፡፡ ዓመታዊ የዓረቦን መጠኗ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የእኛ በአጠቃላይ ሲታይ 280 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ 16 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ እኛ ይህንን ሁሉ ሕዝብ ይዘን 16 ሚሊዮን ዶላር ከሕይወት ኢንሹራንስ ሲገኝ ኬንያ ከእኛ ከግማሽ በታች የሚያንስ 46 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ ከእኛ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ አፈጻጸም አላት፡፡ ስለዚህ ሌላውን ትተን የሕይወት ኢንሹራንስ ለውጭ ኩባንያ ብንከፍት ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ማክሮ ኢንሹራንስ ነው ያስፋፉት፡፡ አሁን የእኛን ኩባንያዎች ብትጠይቃቸው ይህንን ጀምሩ ብትላቸው ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል ይሉሃል፡፡ ሌላም ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ኬንያ ውስጥ ግን ሁሉንም ነገር ተቋቁመው ውጤታማ የሚያደርጋቸውን መርጠው ነው ያስፋፉት፡፡ ኬንያን ከእኛ ጋር ስታወዳድር የተለየ ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ እንዲያውም የኛ ጂዲፒ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ መንገዱን ማጣት ነው እንጂ ትርፋማ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኬንያ ከኢትዮጵያ በእጅጉ የተሻለ የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት የቻለችው የውጭ ኩባንያዎችን ማስገባት በመቻሏ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ፍቅሩ፡- በሁለቱም ነው ጠንክረው የሚሠሩት፡፡ የውጭ ኩባንያ ይመጣል ማለት ሁላችንም ተጠራርገን እንወጣለን ማለት አይደለም፡፡ በጋራ የምንሠራባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሌሎች አገሮች ሕግ አውጪው ተስማሚ ይሆናል የሚለውን ሕግ ያወጣል፡፡ ለውጭ ኩባንያዎች በራቸውን ከፍተው ሲገቡ ሕጉ የሚለው እዚህ ከሠራህ ከምትቀጥረው ሠራተኛ 80 በመቶ ወይም 50 በመቶው የአገሬው ዜጋ መሆን አለበት ሊሉ ይችላሉ፡፡ አክሲዮን ሲሸጡ እዚህ ድረስ ነው መያዝ የምትችሉት ብለው ሕግ ያወጣሉ፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ እየተለወጠ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ባቀረቡት ጥናት ላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ እንዴት ?

አቶ ፍቅሩ፡- ይኼ ጉዳይ እኮ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ ገበያው መከፈት አለበት መባሉ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ አማራጩ መቼና እንዴት የሚለው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ አስገዳጅ ነገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ውጪ ደሴት ሆና ልትቀር አትችልም፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ግድ ነው፡፡ ገበያችሁን ክፈቱ የሚሉ ሌሎች ግፊቶችም አሉ፡፡ እስካሁን በይደር ያቆየነውን ገበያ የመክፈት ጉዳይ አሁንም ቆይ እየተባለ መቆየት አይቻልም፡፡ የሆነ ቦታ ላይ መወሰን አለበት፡፡ ይከፈት ከተባለም እኮ በአንዴ የሚሆን ነገር አይደለም፣ ጊዜ ይሰጣል፡፡ ግን መከፈት አለበት፡፡ ነገር ግን በየትኛውም መንገድ ቢሆን የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለምክክር የሚቀርበው እንዴትና መቼ ነው የሚሆነው የሚለው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከለውጡ ወዲህ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ትልልቅ ተቋማትን ድርሻ ለመሸጥ ታቅዷል፡፡ ከዚህ አንፃር የፋይናንስ ተቋማትን በተመለከተ ግን ምንም አልተባለም፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- ብሔራዊ ባንክ ይህንን በአንድ መመርያ ሊያነሳው ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ዘርፍ ፖሊሲ ይቀየር ሲባል መመርያ ያወጣል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ማዕቀፍ እስኪያወጣ፣ ኩባንያዎችም አቅማቸውን እስኪገነቡ እንዴት የሚለውን ልንመልስ እንችላለን፡፡  አሠራሮቹን እንዴት እናድርጋቸው የሚለው ነው፡፡ አብረን እንሥራ? 50 በመቶ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና እንሥራ? 50 በመቶ የውጭ ኩባንያዎች ይሁን? ወይስ 80 በመቶ የአገር ውስጥ ቀሪው የውጭዎቹ ይሆን? የሚሉ የተለያዩ አማራጮችን በማየት እንዴት አድርገን እንጀምረው የሚለው ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት ይቻላል፡፡ መቼ ለሚለውም ደግሞ ዝግጅት እስክናደርግ ድረስ፣ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ቁጥሩን እስኪያጠናክር ድረስ፣ ኩባንያዎቹም ራሳቸውን ከጊዜው ጋር እስኪያዋህዱ ድረስና በቴክኖሎጂ እስኪደራጁና እስኪያጠናክሩ ድረስ ጊዜ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ግዴታ ነው፡፡ ሁለተኛ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ጥሩ አትራፊ ነው፡፡ በየዓመቱ ይህንኑ ያሳውቃል፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ከዚህ ዘርፍ ተጠቅሟል ወይ? ስትል እየተጠቀመ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ተጠቃሚ አይደለም ሲባል ከምን አንፃር ነው?

አቶ ፍቅሩ፡- ኅብረተሰቡ ከዚህ ዘርፍ እየተጠቀመ አይደለም የምለው ለምሳሌ ችርቻሮ ውስጥ ገብተው እየሰጡ አይደለም፡፡ ዛሬ እኔና አንተ ብድር ስጡን ብንል የሚሰጠን የለም፡፡ ሌሎች አገሮች ግን የብድር ታሪክህ ጥሩ እስከሆነ ድረስ ያበድሩሃል፡፡ ለቤት፣ ለመኪና፣ ለቤት ዕቃዎች፣ ወዘተ. ብድር ይሰጡሃል፡፡ ግዴታ ፎቅ ለመሥራት ወይም ኤክስፖርተር ስለሆንክ ብቻ ሳይሆን ብድር ሊሰጥህ ይገባል፡፡ ችግር ካለብህ ለችግርህ የሚሆን ብድር ልታገኝ ይገባል፡፡ ለገሬው የእርሻ መሣሪያ የሚያበድሩ ሁሉ አሉ ሌሎች ብዙ ነገሮች የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ለኢንሹራንስም ደግሞ እንዲሁ የሚቀርብ ተስማሚ አገልግሎት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ስለዚህ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ አገልግሎቶችን ስለማይሰጡ አብዛኛው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች ቢገቡ እንዲህ ያለውን ክፍተት ሊሞሉ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳለዎ ከጥናትዎ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገቡ እንደ ተግዳሮትና መልካም ዕድል የሚያዩት ነገር ምንድነው?

አቶ ፍቅሩ፡- መልካም ዕድሉ ነፃ ገበያ ይኖራል፣ ውድድር ይኖራል፡፡ እኛ ዘንድ ሲገቡ  ተደራሽነትን ይጨምሩናል ውድድር ራሱ ከፍተኛ ተጠቃሚነት ያመጣል፡፡ ትክክለኛ አገልግሎት እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ውድድር ውስጥ ከገባህ ደግሞ ሰው የሚፈልገውን ነው የምታመጣው፡፡ አሁን ሞተር ኢንሹራንስ የሚገዛው ተገዶ ነው፡፡ ቦንድ የሚገዛው ቢድ ቦንድ አቅርብ ሲባል ነው፡፡ ይህንን ኢንሹራንስ ሳይሆን ታክስ በለው፡፡ ግዴታ ሲሆን ማለት ነው፡፡ እነዚያ ግን አስማምተውህ ጥቅሙን አሳይተውህና አስተምረውህ ነው አገልግሎታቸውን የሚሸጡልህ፡፡ ስለዚህ ጥቅሙን አይቶ መግዛትና ተገዶ መግዛት የተለያዩ ናቸው፡፡ ጥቅሙን ካላሳዩህ አትገዛም፡፡ ስለመጡ ብቻ አትገዛም፡፡ ያንን አገልግሎት የምንገዛቸው ጥቅሙን አሳይተውን ስለሚሸጡ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ተቆጣጣሪው (ብሔራዊ ባንክ) አሁንም የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን በመቆጣጠር ጠንካራ ነው፡፡ የውጭዎቹንም በአግባቡ ከተቆጣጠራቸው በሥርዓቱ እንዲሠሩና እንዲነግዱ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ይቆጣጠራል ሲባል ጡንቻ ማሳየት ብቻ አይደለም፡፡ ኃላፊነቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተደራሽነት እንዲሰፋ፣ አሁን እየተነጋገርንበት እንዳለነው የውጭ ኩባንያዎችን ጠቀሜታ አውቆ ለዚያ የሚሆን መደላድል ሲፈጥርም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከተመዘነ አሁንም ደካማ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የተጠናከረ አይደለም እየተባለ  እንዴት ነው የውጭ ኩባንያዎችን ሊያስተናግድ የሚችል አቅም የሚኖረው?  

አቶ ፍቅሩ፡- የቁጥጥር አቅሙን ማጠናከር አለበት፡፡ አቅሙን እንዲያጠናክር በተለያየ ጊዜ እኮ ድጋፍ እያገኘ ነበር፡፡ ይህንን የሚሰጡ የውጭ ሰዎች አሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ነገሮች ተጠቅሞ ራሱን ማብቃት መቻል አለበት፡፡ ራሱን ሳያበቃ መቆጣጠር አይችልም፡፡ ቢያንስ ዘመናዊ ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ደረጃ ላይ መድረስ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼ ሲባል ግን ለምሳሌ የኬንያን እየው፡፡ በምን ዓይነት ሰዎች ነው የሚመሩት? ይህንን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጥናት ማድረግ ሲባል እኮ ይህንን ማየት ነው፡፡ ተዓምር ይፍጠሩ አይደለም፡፡ ምን ዓይነት ሕግ ይዞ ነው? ምን ዓይነት ባለሙያዎችን ይዞ ነው የሚሠራው? በማለት ሩቅ ሳንሄድ ቅርባችን ያለውን የኬንያን አሠራር መመልከት ነው፡፡ ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ በአጭር ጊዜ ራሱን ማዘጋጀት ይችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ለማስቻል ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል? በእርስዎስ ግምት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ዕውን ይሆናል የሚል እምነት አለ? ወይም በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይገባል ብለው ያምናሉ?

አቶ ፍቅሩ፡- በእኔ እምነት ምንም መቆየት የሚያስፈልግበት ምክንያት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ እየተላለፈ ቆይ እንዘጋጅ እየተባለ የሚቆየው እስከ መቼ ነው? ተመሳሳይ ግጥም፣ ተመሳሳይ ዜማና ዘፈን እየሰማህ እስከ መቼ ትቆያለህ? ይህ ያሰለቻል፡፡ ሁሌም ለውጭ ኩባንያዎች ገበያው ሊከፈት ነው ሲባል ተረባርቦ አልተዘጋጀንም ይባላል፡፡ መጀመርያ ድጋፍ ሊሰጠን ይገባል ይባላል፡፡ አዎ ከለላ ያስፈልገናል፡፡ ግን ይኼ ነገር እየጠቀመ ያለው የተወሰኑ ባለሀብቶችንና ትርፍ የሚያገኙ ሰዎችን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አሁንም አልተጠቀመም፡፡ እውነተኛ ውድድር ሲመጣ ከከተማ አንወጣም የሚሉ ባንኮች መሸሸጊያቸው ኅብረተሰቡ ይሆናል፡፡ ወደ ታች ይወርዳሉ፡፡ ከተማ ላይ የተከማቹ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን እውነተኛ ውድድር ሲመጣ ትርፋቸውንም ቀንሰው ቢሆን ወደ ኅብረተሰቡ ይወርዳሉ፡፡ ምክንያቱም መሸሸጊያቸው ኅብረተሰቡ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አሁን ግን ትልቅ የሆነውን የትርፍ ህዳፍ ላለማጣት ሲሉ መውጣት አይፈልጉም፡፡ እውነተኛ ውድድር ሲመጣ የውጭዎቹ መጥተው ወደ ታች ሄደው መሥራታቸውን ሲያዩ እነሱም ታች ሄደው መሥራት ይጀምራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ምናልባትም ለዓመታት በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ቢገቡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ያጠፋሉ በሚል ሲሰበክ ቆይቷል፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ሊያጠፉ ይችላሉ የሚለው አመለካከት በእርግጥ ትክክል ነበር? ደግሞስ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች አቅማቸው እስኪደራጅ የውጭ ኩባንያዎች አይግቡ የሚለውስ? በተለይ በአሁኑ ወቅት ሊያስኬድ ይችላል?

አቶ ፍቅሩ፡- ይህ ትክክል አይደለም፡፡ እኔ አሁን ባለኝ ግንዛቤና ባለኝ ልምድ ማንም አያጠፋንም፡፡ እንዲያውም ያሳድጉናል፣ ያሻሽሉናል፣ ያነቃቁናል፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች መጡ ማለት አገልግሎት ይሸጡልሃል፡፡ አገልግሎቱ ካልጣማቸው ኅብረተሰቡ አይገዛም፡፡ ኅብረተሰቡ ይዘውለት የመጡት አገልግሎት ካልጣመው ወደ ራሳችን ባንኮችና ኢንሹራንሶች ይመለሳል፡፡ ስለዚህ እንዴት ነው ሊያጠፉን የሚችሉት? ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ማን አጠፋቸው? ክፍት አድርገው እየሠሩ ነው፡፡ ገበያውን ክፍት በማድረጋቸው አገልግሎታቸው አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘንድ ደረሰ፡፡ ቴክኖሎጂም ኢንሹራንሱም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ታች ድረስ እንዲዘልቅ ዕድል ሰጣቸው፡፡ ብዙዎችን ተጠቃሚ አደረገ፡፡ ስለዚህ መቼ ጠፉ? እንደውም ኬንያውያን ከእኛ በተሻለ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ እንዲይዙ አስቻላቸው፡፡ እኛን በተለየ ሊያጠፉን ይችላሉ የሚባልበት ምክንያት ምንድነው? ነገሩ ከራሳችን ባህል ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጠላት ሲመጣብን ተባብረን እናባርራለን፡፡ እንገፋለን፡፡ ከዚያ በኋላ የምንመሠርተው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ አይሆንም፡፡ ፋይናንሱ ላይ በተመሳሳይ አይግቡ ብለን እንታገላለን፡፡ አይግቡብን ብለን ተቆጣጣሪዎችን እንቀሰቅሳለን፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እኛ አንሠራም፡፡ የሚፈለገውን አገልግሎት አንሰጥም፡፡ ከዚህ ከለላ እያተረፉ ያሉ ዘርፎች አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ በጣም ግፊት ስለሚያደርጉና ስለሚታወቁ መንግሥትን በመቀስቀስ ጉዳዩ እንዳይነሳ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያ ያንን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ ይቀራሉ፡፡ አያተርፈንም ይላሉ፡፡ ለኅብረተሰቡ ሳይሆን ለባለሀብቶች ብቻ የሚሆን አገልግሎት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ባለሀብት የሚሆኑ የባንክ አገልግሎት ይዘው ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ለውጥ ምክንያት መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች በፋይናንስ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችሉ ምልክቶች እያሳየ ነው ብለው ያስባሉ? በጉዳዩ ላይ ምን እያደረገ ነው? ከዚህስ በኋላ ምን ያደርጋል ብለው ያምናሉ?

አቶ ፍቅሩ፡- መንግሥት ይህንን በደንብ ተረድቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህንን ጥናት ሳይደረግ ያነጋገርኳቸው ሰዎች ነበሩና ከዚያ የተረዳሁት ይህንን ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ወደ ግል እንዲዞር ለማድረግ ፈተናዎቹን ተረድተዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በተለይ የሕይወት ኢንሹራንስ አለማደጉ ግንዛቤ ተወስዶበታል፡፡ ማክሮ ኢንሹራንስ ለዓመታት በሙከራ ላይ ሆኖ ማደግ ያቃተው ነው፡፡ እዚህ ላይ የፈሰሰውን ፈንድ፣ የተደረገውን ዕርዳታና ፕሮጀክት ስታስተያየው አይገናኝም፡፡ እስከ መቼ ነው በሙከራ ደረጃ የሚቆየው? በሁለት እግሩ ይቆማል ተብሎ የሚጠበቀው? ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሁሉም አካላት፣ ብሔራዊ ባንክም በዚህ ጉዳይ አዎንታዊ ሆነው ይሠራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ መንግሥት በጣም ጠቃሚ ናቸው የሚባሉትን እንደ ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለውጭ ገበያ ልከፍት ነው እያለ ብዙም ጥቅም የማያስገኝለትን የኢንሹራንስ ዘርፍ መከላከል ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በአስተሳሰብ ደረጃም ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡  ኩባንያዎቻችንም ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሳቸውን ማደርጀት ጭምር ይጠይቃቸዋል፡፡ እንዲያውም ኩባንያዎቻችን ጠንከር ብለው ሁለት ሦስቱ መዋሀድ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የፋይናንስ ኩባንያዎች መዋሀድ ላይ የሚነሳ  ሥጋት አለ፡፡ ይህም  አብዛኛዎቹ የፋይናንስ ተቋማት አፈጣጠር ከብሔር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለተሻለ ነገር እንኳን ተዋሀዱ ቢባሉ አፈጣጠራቸው እንቅፋት ይሆናል የሚል ሥጋት በተደጋጋሚ መነሳቱ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ደግሞ አገር በቀል ተቋማት ጠንክረው እንዲወጡ ከተፈለገ አሁን ያሉት ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየራሳቸው ተዋህደው አምስትና ስድስት ጠንካራ ባንኮች፣ ስድስትና ሰባት ጥሩ ተፎካካሪ የሚሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መፈጠር አለባቸው ብለው ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ አፈጣጠራቸው ተፅዕኖ አያሳድርም?

አቶ ፍቅሩ፡- ይኼ ጉዳይ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ አንዳንዶቹ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተቋቋሙት ብሔርን መሠረት በማድረግ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች የያዙዋቸውም ናቸው የሚባል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን የሞትና ሽረት ጉዳይ ሲመጣ ግን የማይስማሙበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም ቢዝነስ ነው፡፡ አሁን እኮ በየኩባንያዎቹ ውስጥ ይህንን ጉዳይ የሚረዱ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በየጊዜው ስትራቴጂ የሚያዘጋጁ ሰዎች አሉ፡፡ ይኼ ነገር አስገዳጅ ከሆነ ወደ አንድ የማይመጡበት ምክንያት የለም፡፡ ባለአክሲዮኖች ራሳቸው ያለውን ሥጋት ዓይተው ወደዚያ አስተሳሰብ ይሄዳሉ፡፡ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ምቾት ላይ ናቸው፡፡ ትርፋማ ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ያንን አይፈልግም፡፡ ማንም ቢዝነሱን ሊያጣ አይፈልግም፡፡ ይህ ዘርፍ ከሌሎቹ ቢዝነሶች የበለጠ አትራፊ ነው፡፡ ኢንቨስተሮችን የሚስብ ዘርፍ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ግን አፈጣጠራቸውም ቢሆን ይስተካከላል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት? በምን ዓይነት ዘዴ?

አቶ ፍቅሩ፡- አንድ መሥፈርት ከመጣ ይስተካከሉ፡፡ ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ ካፒታላችሁን አሳድጉ ይላል፡፡ ይህንን ካፒታል ለማሟላት የጊዜ ገደብ ይሰጣቸዋል፡፡ አሁንም ከተቀመጠው በላይ ካፒታል ማሳደግ ካልቻሉ ወደ ውህደት ይሄዳሉ፣ ሌሎች አገሮችም ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ደረጃ የሌሎች አገሮች ልምድ አለ?

አቶ ፍቅሩ፡- አዎ! ግን ሲወሰን ኩባንያዎቹ እርስ በርስ ብቻ ይዋሀዳሉ ማለት አይደለም፡፡ ከውጭ ኩባንያዎች ጋርም በጥምረት የሚሠሩበት አሠራር ሊፈጠር ይችላል፡፡ የሚጎድላቸውን የሚሟላላቸው የውጭ ኩባንያ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው ለመሠራት የሚፈልጉ በጣም ብዙ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሉ፡፡ አክሲዮኖች ገዝተው መግባት የሚፈልጉ አሉ፡፡ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ሸሪክ በመሆን ያሉትን ነገር ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሌላ የሚነሳ ነገር አለ፡፡ እስካሁን ድረስ ኢንዱስትሪው በግሉ ዘርፍ ሊብራላይዝ ተደርጓል ቢባልም ይህ እየሆነ አይደለም እየተባለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ፍቅሩ፡- በብዙ ነገሮች መንግሥት ከሌሎች ባንኮች የተለየ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለየ ይደግፈዋል፡፡ የግል ዘርፉ ራሱ ተፎካክሮ በውድድር የመንግሥት ተቋማትን የኢንሹራንስ ሽፋን አግኝቶ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተከለለት አካባቢ ነው የሚሠራው፡፡ ከግሉ ዘርፍ የሚያገኘው ከ20 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ያገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከአጠቃላይ ገበያው ድርሻው  አሁን ወደ 35 በመቶ ወርዷል፡፡ ግን የግል ዘርፉን ስታይ ደግሞ ከ20 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ካልሆነ አንገባም ይሉ ነበር፡፡ ገበያው ተከፍቶ ለብዙ ጊዜ ይኼ አመለካከት ነበርና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ ይኼ ግን ቀስ በቀስ እየተቀየረ መጣ፡፡ የገበያ ድርሻውን የግል ኢንሹራንሶች እየወሰዱ መጡ፡፡ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አገልግሎት በመመልከቱ የተለወጠ ነው፡፡ ልክ እንዲሁ የውጭዎቹ መጥተው ደግሞ ጥሩ ነገር ካለማመዱት የሚቀየር ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ ገበያውን ነፃ ማድረግ የሚጠቅመው ኅብረተሰቡን ነው፡፡ የተሻሉ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች፣ ሰምተናቸው የማናውቃቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ጭምር ይዘውልን ይመጣሉ የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ካነሱት ውስጥ አንዱ፣ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ቢከፈት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም የዳሰሰ ነበር፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- ለምሳሌ በጥናቱ እንደ ተግዳሮቶች በተነሱት ላይ አቅም የለንም የሚል አለ፡፡ ለምሳሌ ፕራይቬታይዝ ቢደረግና የውጭ ኩባንያዎች ቢገቡ በቴክኖሎጂም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ስለሚበልጡን ይጠቀልሉናል፣ አቅም የለንም እየተባለ ገበያው ለረዥም ጊዜ ተከልሎ ቆይቷል፡፡ ገበያው ደግሞ ይህንን ዕድል አልተጠቀመበትም፡፡ አቅሙን አልገነባም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ራሱ ማሠልጠኛ እንኳን የለውም፡፡ የነበረውና በብሔራዊ ባንክ ሥር ያለው ተሽመድምዷል፡፡ አለ የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ድሮ የረዥም ጊዜ ፕሮግራሞችን ቀርፆ መደበኛ ትምህርት የሚሰጠው ተቋም፣ የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን እንኳን የሚሰጥበት መንገድ ደካማ ነው፡፡ እሱንም ደግሞ ደረጃውን ባልጠበቀ መንገድ ነው የሚያካሂደው እየተባለ ነው፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ አንዱ ልንሠራ የሚገባን ጉዳይ የሰው ኃይል ማፍራት ነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለውጭ ተዘግቶ ለብቻችን እንድንሠራ ዕድል ቢሰጠንም ምንም እየሠራን አይደለም፡፡ ዝግጁነት የለም፡፡ ብቻ የውጭ ኩባንያዎች ጉዳይ ሲነሳ ይራዘምልን የሚለው ነገር ይዘመራል፡፡ ለምን መግባት እንደ ሌለባቸው በትክክል መልስ የሚሰጥህ የለም፡፡ እንዲህ እየተባለ መቆየት አይቻልም፡፡ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ ሌላኛውን የቢዝነስ መንገድ ማየት መጀመር አለብን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚነሱት ክርክሮች በሙሉ መቀየር አለባቸው፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ ኅብረተሰቡ ዘንድ ስትሄድ የሚፈለገውን የኢንሹራንስ አገልግሎት በአግባቡ እንዲሁም በጥራት እያገኘ ያለመሆኑን ታያለህ፡፡ ስለዚህ ዘርፉ ለውጭ ካልተከፈተ አያድግም፡፡ ዝግ የሆነው በር መከፈት አለበት፣ ይከፈትና ይሠራ፡፡ ሲከፈት ግን በቁጥጥር የምትሠራበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ ወይም ሌላ መንገድ በመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡ መቼና እንዴት የሚለው ላይ ተነጋግሮ መወሰን ይቻላል፡፡ ከተፈለገም እስኪ የተወሰነውን ለእነሱ ሰጥተን እንጀምረው ማለት ይቻላል፡፡ የተወሰኑትን የአገልግሎት ዘርፎች ለነሱ ሰጥተን ለምሳሌ የእኛ ኩባንያዎች 80 በመቶውን ይዘን በሙከራ ፕሮግራም እንያቸው፡፡ ሌሎችንም ነገር አድርገን ብንሠራ ብለን ማሰብ አለብን እንጂ፣ ድጋሚ ይዘጋ የሚለው ነገር ሊቀጥል አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ ሲባል ዘርፉ ለዳያስፖራውም ተከልክሎ ነበርና እነሱንም ማሰብ አይቀርም፡፡ በዚህ ዘርፍ የዳያስፖራዎች ሚና  ትልቅ ሊሆን ቢችልም፣ ከእነሱ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ዳያስፖራዎች በዚህ ዘርፍ ሊኖራቸው የሚገባው ሚና ምን መሆን አለበት?

አቶ ፍቅሩ፡- የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ሒደት ከቀደሙት ሥራዎች ጀምሮ ዓይተናል፡፡ አሁን ያለውም በጣም ዝግና ኢንዱስትሪውን ያቀጨጨ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎች አገሮች ክፍት እየሆኑና እየተሻሻሉ ለውጭ ዜጎች ጭምር ያለምንም ገደብ ገበያ እየከፈቱ እየሰጡ ባለበት ወቅት፣ እኛ ዘንድ ጭራሽ ኢትዮጵያዊ የሆነው ዳያስፖራ እንዳይገባ የሚል አዋጅ ነው ያለው፡፡ ይኼ ደግሞ ብዙዎችን ያስከፋ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን አደረጉ? እነዚህ ሰዎች እኮ ሀብት አፍርተው አገራቸው መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ምን ችግር አለው? ጉዳቱ ምንድነው? አገሪቱ የምትሄድበትን አቅጣጫ በሒደት ደረጃ በደረጃ እንከፍታለን የሚለውን ዕድል ራሱ የሚያዳክምና የሚያቀጭጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ዳያስፖራዎች ላይ የተወሰነው ውሳኔ ግልጽ አይደለም፡፡ አሁንም  ሰዎችን እንደሌለና እንዲጠራጠሩ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዳያስፖራዎችን ተሳትፎ በተመለከተ አሁንም እየተሠራ አይደለም የሚል ነገር አለ? የፋይናንስ ዘርፉ ቀድሞ ለእነሱ ቢከፈት መልካም እንደሆነ ቢታወቅም በዚህ ረገድ የሚታይ እንቅስቃሴ የለም፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- ገበያ ይከፈት ከተባለ መጀመርያ ዕድል ሊሰጣቸው የሚገባቸው እነሱ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ማን እምነት ይኖረዋል የሚልም ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ሰዎች እኮ እምነት አጥተዋል፡፡ ዳያስፖራ ባለአክሲዮኖች ከነገዱ በኋላ አክሲዮናቸውን አውጡና ሽጡ ተብለዋል፡፡ አክሲዮናቸው በብዙ እጥፍ ተሽጧል፡፡ እንደገና ኑ ሲባሉ ደግሞ በዚህ ዙሪያ የተፈጠረው ነገር መቀየሩን በሚገባ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር አሳምኖ ማምጣት ራሱ ሌላ ሥራ ነው፡፡ ነገ ዋስትና የለንም ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የነበሩት 13 የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሀብታቸውን ተወርሰው ነው የወጡት፡፡ ከዚያ ትንሽ አገግሞ ነው የግል ዘርፉ ወደ ኢንዱስትሪው የገባው፡፡ ከተነጠቁ በኋላ እንደገና አምጡ ሲባል ማነው ዋስትና የሚሰጠን ሊሉ ይችላሉ፡፡ አይደለም የውጭዎቹ ዳያስፖራዎች አስተማማኝ ነገር ይፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዳያስፖራው በዚህ ዘርፍ ውስጥ እንዲገባ ከተፈለገ በቅርቡ አክሲዮኖቻችሁን ሽጡና ውጡ እንደተባሉት ሁሉ፣ ድጋሚ እንደዚያ ዓይነት ድርጊት እንደማይፈጸም ለማረጋገጥ ራሱን የቻለ ሥራ መሠራት አለበት እያሉኝ ነው?

አቶ ፍቅሩ፡- አዎ! በአሁን ወቅት እኮ በኢንሹራንሶችና ባንኮች ዜግነትና መታወቂያ ማየት ተጀምሯል፡፡ ይኼ ራሱ ወደ ኋላ መመለስ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የተለየን አገር አይደለንም፡፡ ዘርፉን ላለመክፈት ምንድነው የተለየ የሚያደርገን? ለምሳሌ በራቸውን ከፍተው እየሠሩ ያሉ አገሮች አልተጎዱም፡፡ ምናልባት የተወሰኑ አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እዚህ ለምን አልተከፈተም ሲባል በዚህ ጉዳይ ያልተሳካላቸውን አገሮች ፈልገን እንደ ምሳሌ እናመጣለን፡፡ የውጭ ኩባንያዎችን ያስገቡ 99 በመቶ የሚሆኑት አገሮች ውጤታማ መሆናቸውን ነው የምንሰማው፡፡ እዚህ ግን አውቀን የወደቁትን እየጠቀስን እኛም እንወድቃለን እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደጠቀሱልኝ በዚህም ሆነ በሌላ ዘርፍ ለምን የውጭ ኩባንያዎች ገብተው ዘርፉን እያሳድጉም ሲባል ጥሩ ምሳሌ የማይሆኑ አገሮች ስም ይነሳል፡፡

አቶ ፍቅሩ፡- እሱን ብለን ደግሞ በራችንን ዘግተን ያተረፍነው ነገር የለም፡፡ አገልግሎቱ እያደገ አይደለም፡፡ የአሁኑን ተወውና ወደፊትስ ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አሁን እያደገ ባለበት ደረጃ ሲሄድ ምን መሆን አለበት የሚለውንም ግምት ውስጥ ማስገባት አለብህ፡፡ አሁን ባለን የሕዝብ ቁጥር ከአፍሪካ ሁለተኛ ነን፡፡ በሒደት በአፍሪካ ትልቁን የሕዝብ ቁጥር የሚይዝ አገር አለን፡፡ ስለዚህ ያን ጊዜ ማነው ያንን ሕዝብ የሚያገለግለው? ስለዚህ አሁን ባለን እሳቤ ከሄድን ያንን የምንደርስበት አቅም ላይ አይደለንም፡፡ ይህንን የሚረዳ አሠራር መዘርጋት ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ምንም ሳይዘገይ ቢከፈት አዲስ መንገድ ይሆናል፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን ካለው መነቃቃት መንግሥት ፕራይቬታይዜሽን ላይ ካለው መልካም አመለካከት አንፃር፣ በቀላሉ ከባንክ ቀድሞ የኢንሹራንስ ገበያውን ቢከፍተው ምንም የሚያመጣው ጫና የለም፡፡ በነገራችን ላይ አሁን እኮ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ የኢሹራንስ ኢንዱስትሪው በተወሰነ ደረጃ የተከፈተ ነው የሚያስብል ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ከምን አንፃር?

አቶ ፍቅሩ፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የሰበሰቡትን ገንዘብ በሪኢንሹራንስ መልክ ወደ ውጭ ያወጣሉ፡፡ ከውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመርያ ገበያ ውስጥ ነው እንጂ ያልገቡት በጠለፋ እኮ አብረውን እየሠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ገበያ ውስጥ አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነውን የአገራችን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዓረቦን በጠለፋ ይወጣል፡፡ የኢንሹራንስ ገበያውን ለውጭ ኩባንያዎች ሳይዘገይ መክፈቱ ለባንክ ኢንዱስትሪውም መማሪያና መለማመጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መቼና እንዴት የሚለው ላይ መንግሥት ቶሎ ሠርቶ፣ የውጭ ኩባንያዎች የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...