ለአንድ ዓመት የሚቆየው አገራዊ የታክስ ንቅናቄ ለገቢው መሻሻል ተስፋ ተደርጓል
የገቢዎች ሚኒስቴር በዚህ ዓመት እንዲሰበስብ የተቀመጠለትን የ213 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ እንደሚያሳካ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡ ይሁንና በአገሪቱ የሚታዩት ግጭቶች በገቢው ላይ ፈተና እንደሚሆኑበት ሥጋቶች ተፈጥረዋል፡፡
ገቢዎች ሚኒስቴር እንደ አዲስ ከተዋቀረ ወዲህ ተቋሙን በሚኒስትርነት መምራት የጀመሩት ወ/ሮ አዳነች፣ በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ፣ የታክስ ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚወሰዱ የሕግ ማስተካከያዎችና ዕርምጃዎች ገቢው እንደታሰበው እንዲሳካ የሚያስችሉ መነሻዎች ስለመሆናቸው ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የ50 ቢሊዮን ብር ጉድለት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡ የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አብራሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ይህንኑ በማስመልከት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዚህን ዓመት በጀት ለማፀደቅ ባስረዱበት ወቅት፣ ከፍተኛ የታክስ አሰባሰብ ችግሮች እንደነበሩ ገልጸው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበው ነበር፡፡
መንግሥት የታክስ ሥርዓቱን ለማሻሻል እየወሰዳቸው ከሚገኙ ዕርምጃዎች መካከል በተለይም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል የተሰኘና በቀጥታ በታክስ ጉዳዮች ላይ የሚመክር አካል መዋቀሩን ጠቅሰዋል፡፡ ገቢዎች ሚኒስቴርን ጨምሮ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽንና ሌሎችም የተካተቱበት ይህ ግብረ ኃይል በየጊዜው በቋሚነት እየተገናኘ የታክስ ችግሮች ላይ ውሳኔ በመስጠት መፍታት እንደጀመረ በአስረጅነት የጠቀሱት አንድ ዕርምጃ ነበር፡፡ ይኸውም በሞጆ ደረቅ ወደብ የተከማቹ ዕቃዎችን ያስመጡ ነጋዴዎች ዕቃዎቹን ማንሳት ያልቻሉት በገጠማቸው የገንዘብ እጥረት መሆኑ በመረጋገጡ፣ በባንክ ዋስትና ዕቃቸውን እንዲያነሱ መፈቀዱ ነው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ውሳኔ ተብሎ የተጠቀሰው፡፡
ከዚህ ቀደም ብሎ ግን በደረቅ ወደቦች የተከማቹ ዕቃዎች እንዲወረሱ መንግሥት ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር በጉምሩክ አካባቢም ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ የሆነ የጉምሩክ ፖሊስ በማቋቋም በየኬላው የሚታየውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመግታት ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስትሯ አዳነች መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በመመለስ የታክስ ጉዳዮች ላይ መተማመንን በማስፈን መንግሥት መሰብሰብ የሚጠበቅበትን ገቢ እንዲሰበሰብ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በየጊዜው እየተከሰቱ የሚታዩት ግጭቶችና የሰላም ዕጦት፣ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው የሚያገናኙ መንገዶች እየተዘገቡ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እየተፈጠረ ያለው መስተጓጎልና ሌሎችም መሠረታዊ የፀጥታ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የ213 ቢሊዮን ብር የገቢ ዕቅድ የመሳካቱ ጉዳይ ምን ያህል አሳማኝ እንደሆነ ከሪፖርተር ጥያቄው የቀረበላቸው ሚኒስትሯ፣ መንግሥት መውሰድ በጀመራቸው ዕርምጃዎች ምክንያት ግጭቶች እንዲስፋፉ ፋይናንስ እየተደረጉ ነው በማለት ችግሮቹን ለመፍታት ከሕዝብ ጋር ግልጽ ውይይቶች እንደሚደረጉና እየተደረጉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
በአብዛኛው የግጭቶች መነሻ ታክስ ያጭበረበሩ፣ በህቡዕ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፣ የኮንትሮባንድ ሥራዎች ውስጥ እጃቸውን ያስረዘሙ አካላት የሚያከናውኑት ተግባር እንዲቆም ሕዝብ መተባበር አለበት ያሉት ወ/ሮ አዳነች፣ መወሰድ በጀመሩ ዕርምጃዎች ሳቢያ በየጊዜው በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የሚያዙ የውጭና የአገር ውስጥ መገበያያ ገንዘቦችን በአስረጅነት አውስተዋል፡፡
ይህም ሆኖ መንግሥት የልማት ሥራዎችን በአግባቡ ለማስኬድና ፋይናንስ ለማድረግ ‹‹መብቴን እጠይቃለሁ፣ ግዴታን እወጣለሁ›› በሚል መርህ፣ ለአንድ ዓመት በተለያዩ ክንውኖች የሚተገበር የግንዛቤ ማስጨበጫ አገር አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ ንቅናቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ፣ ታኅሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አስጀምረውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ታክስ መክፈል መንግሥት አስቻይ የፍትሕ ሥርዓትን ለማስፋት፣ ሰላምን ለማስፈንና ፍትሐዊ የታክስ ሥርዓትን ለማስፈን ያስችላል በማለት፣ የኢኮኖሚስ አባት እየተባለ የሚታወቀውን የዕውቁ አዳም ስሚዝ አባባል ጠቅሰዋል፡፡