ሰሞኑን የፋይናንስ ተቋማት የ2010 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸማቸውን ለባለአክሲዮኖቻቸው ሪፖርት ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡ እንደተለመደውና እንደወትሮው ሁሉም አትራፊ ሆነው ዓመቱን እንዳጠናቀቁ አስታውቀዋል፡፡ ባንኮቹና መድን ኩባንያዎች ሌሎች አትራፊ ተቋማት፣ የውጭም ሆኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የማይወዳደሯቸው አትራፊዎች መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ያስመገቡት ውጤት ከቀደመውም ጊዜ በላይ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡
ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳትና አለመረጋጋት ተፅዕኖ እንዳሳረፈባቸው ቢገልጹም፣ በዚህ ዓይነቱ ፈተና ውስጥም እያለፉም ከአትራፊነት አላጎደላቸውም ነበር፡፡ የተቋማቱ ውጤት ያስደስታል፡፡ ከዓመታዊ የትርፍ ዕድገታቸው ባሻገር የኩባንያዎቹ ማደግ መመንደግ ለአገር ያለው አበርክቶና አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ የግል ኢንሹራንሶችና ባንኮች በጠቅላላው የፈጠሩት የሥራ ዕድል ከ100 ሺሕ በላይ መድረሱ ብቻውን ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡
ይሁንና ከፋይናንስ ተቋማቱ ወቅታዊ ቁመና አንፃር እንየው ከተባለ፣ አሁን የደረሱበት ውጤት በብዙ ድጋፎችና ከለላዎች ውስጥ የተገኘ እንደሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የአገሪቱ ባንኮችና መድን ኩባንያዎች ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታዩ የሥራ ውጤታቸው ወይም አቅማቸው ብዙም የሚዜምለት አይደለም፡፡
ባንኮቹ ፈርጣማ ተወዳዳሪ አለማየታቸው አንደኛው የተንበሸበሸ ትርፍ ለማጋበሳቸው የሚጠቀስ ምክንያት ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ወደፊት እንዲገቡ ሲፈቀድ፣ አፈጻጸማቸው እስካሁን ሲገለጽ በቆየበት መንገድ እንደማይሆን እንገምታለን፡፡ የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዳይገቡ የተደረገው ክልከላ ሊነሳ የሚችልበት መንገድ እየተጠረገ መሆኑ ገሃድ እየሆነ በመምቱ፣ የፋይናንስ ተቋማቱ እስከዛሬ ሲጓዙበት በነበረው መንገድ እንደማይቀጥሉ የሚያሳብቁ ምልክቶች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ትርፍ በትርፍ ሆነናል ከሚለው መግለጫቸው ባሻገር ነገን ያገናዘቡ ዕርምጃዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙበት የሚያስገድድ ሁኔታ እየመጣ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ብዙ ጊዜ ትኩረት የማይደረግበት ግን በቅጡ ሊታሰበብበት የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አካሄድ ላይ ብዙዎቹ የፋይናንስ ተቋማት ትልቁ ጭንቀት ለባለአክሲዮኖች የሚያቀርቡት የትርፍ መጠን ዕድገት ላይ ነው፡፡ የባለአክሲዮኖች ግፊትም በዚሁ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ባንካቸው ብዙ አትርፎ ብዙ የትርፍ ክፍፍል እንዲሰጣቸው መጠበቃቸው ጫናው ቀላል አይደለም፡፡
በእርግጥ ባለአክሲዮን ያዋጣው ገንዘብ እንዲያተርፍለት ቢያስብ ነውር የለበትም፡፡ ማትረፍም አለበት፡፡ ችግሩ ግን የፋይናንስ ባለሙያዎችና ባለአክሲዮኖችን ወክለው በቦርድ አመራርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች በየዓመቱ ጭንቀታቸው የተገኘው ትርፍ ላይ መንጠልጠሉ ነው፡፡ ይህ በኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡ አንድ የባንክ ወይም የኢንሹራንስ ባለአክሲዮን የቱንም ያህል ኢንቨስት ቢያደርግ ትርፉን መሠረት በማድረግ ስለጥቅሙ የሚሞግትበትን መድረክ እየታዘብን ነው፡፡ በአንዳንድ ኩባንያዎች ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ባለአክሲዮኖች በትርፍ ዕድገትና ቅናሽ ላይ፣ በተለይም በትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠን ላይ ብቻ ተመሥርተው የሚያነሱት ሙግት ማስረጃ ይሆናል፡፡
የሁሉም ባለአክሲዮኖች አመለካከት አንድ ነው ባይባልም ብዙውን ጊዜ ባለአክሲዮኖች ያቋቋማቸው ኩባንያዎች ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሚያስችላቸው ቁመና ላይ እንዲገኙ በማሰብ የሚያደርጉት ግፊት አነስተኛ ነው ማለት ይችላል፡፡ ይህ ግን ነገን አለማስተዋል ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜው እየተለወጠ የውጭዎቹም ይገባሉ እየተባለ ነውና፡፡
ሊመጣ እንደሚችል የሚጠበቀውን ዓለም አቀፋዊ ውድድር ተገንዝቦ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር የፋይናንስ ተቋማቱ ተዋህደው ለመሥራት የሚያሳዩት ቀዝቃዛ መነሳሳት ወደ መዋጥ እንዳያደርሳቸው ያሠጋል፡፡ ስለዚህ ጠንካራ አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት እንዲኖሩን ከተፈለገ፣ ከጊዜያዊ ትርፍ በላይ ኢንዱስትሪውን በማደራጀት ጠንካራ ተቋም የመገንባት ሥራ ላይ ባለአክሲዮኖች ትልቅ ሚና እንዳለባቸው መገንዘብ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ በምትጓዝበት የለውጥ ጎዳና በአካባቢ ልጅነት ተሰባስቦ ቢዝነሱን በዘርና በጎሳ ለማራመድ መሞከር ለነገ ህልውና አዋጭ ስለማይሆን፣ ባለአክሲዮኖች እንዲህ ያለውን አካሄድ ማረቅ አለባቸው፡፡ ይህን አለማድረግና አሁን በተናጠል ባላቸው አቅም ብቻ የሚመጣውን ፈተናና ውድድር መመከት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለነገ የሚያስብ፣ ለአገር የሚጨነቅ፣ ቢዝነስ ትኩረቱ ብሔርና ዓመታዊ ትርፍ ብቻ ሳይሆን፣ አገርና አኅጉር ተሻጋሪ አቅም የሚፈጥርና ጥቅምን የሚያስፋፋ ብርቱ ባለአክሲዮን ሆኖ መገኘትም አለበት፡፡
ኩባንያዎችን የሚመሩ ባለሙያዎችና ጠንካራ የቦርድ አባላትም ምሳሌ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ትርፍ እያመጣ ያለው ገንዘብ የሕዝብ ሀብት እንደሆነ ማሳወቅም ተገቢ ነው፡፡
በኢንዱስትሪው ዕውቀት ያላቸውና በቦርድ የሚሰየሙ አመራሮች፣ ኩባንያዎችን ለማሳደግ እንዲህ ማድረግ አለብን ብለው ሐሳብ ሲያቀርቡ ያንን ላለመቀበል የሚደረገው ፍትጊያና አባሪ ተቃዋሚ አሰባስቦ የማሳደም አባዜም ይስተዋላል፡፡ የቱንም ያህል ጠቃሚ ሐሳብ ቢቀርብ፣ አውቀውም ሳያውቁ የሚሞግቱ የባለአክሲዮኖች ድርጊት የባንክና የመድን ኩባንያዎች ፈተና ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች ስለ ኢንዱስትሪው ምንነትና አጠቃላይ ይዘት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
ለአብነት ለካፒታል ማሳደጊያ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከነባር ባለአክሲዮኖች ውጭ ለሌሎች እንዳይሰጥብን ብሎ መሞገት ስሜት አይሰጥም፡፡ ካፒታሉ በተለይ ከየትም በቶሎ ሲገኝ ለኩባንያቸው ጥንካሬ ቢበጅ እንጂ አይጎዳም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት በአብዛኛው ጥቂት ባለአክሲዮኖች የሚፈጥሩት ቡድናዊነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲታይ፣ የባለአክሲዮኖች ውሳኔ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ጋሬጣ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡
አንዳንዱ ባለአክሲዮንም በቦርድ አመራርነት ለመሾም የሚፈጥረው ጫና ለኩባንያው እንቅስቃሴ ጠንቅ ሲሆን ይታያል፡፡ የቦርድ አባል ለመሆን ያለው ስግብግብነት ሊሠሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ሲገፋም ይስተዋላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከጊዜው ጋር ሊራመዱ የሚችሉ አገልጋዮችን ሊያሳጣ ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ የቦርድ አባል ለመሆን ትላልቅ ድምፅ ያላቸው ባለአክሲዮኖች ጫናም ይታያል፡፡ ይህም አደጋ ነው፡፡ በትውውቅ ምርጫ ማካሄድ ጉዳቱ ዛሬ ባይታይ ነገ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መረዳት ያሻል፡፡
በአጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማትን ለማጎልበት የባለአክሲዮኖች ሚና ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ እንዲጓዝና ጠንካራ ተቋም በመፍጠር ላይ ያነጣጠረ ይሁን እንላለን፡፡