የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ሁለት ኮሚሽኖችን ለማቋቋም በተረቀቁ የሕግ ሰነዶች ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጆቹን እንዲያፀድቃቸው በላከው መሠረት ኅዳር 20 ቀን ረቂቆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበዋል።
የሕግ ሰነዶቹ እንዲያቋቁሟቸው ከሚፈለጉት ሁለት ተቋማት አንዱ የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የማንነትና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሸን ናቸው።
የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ኅዳር 20 ቀን ለምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ኃላፊነት ጋር የሚጣረስ በመሆኑ፣ በዝርዝር የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይህንን እንዲያጣራ፣ እንዲሁም ፓርላማው ይኼንን ረቂቅ ለማፀደቅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ ይህንን የተመለከተ ግምገማ እንዲያደርግ ጠይቀው ነበር።
የኮሚሽኑ ዓላማ በአዋጁ አንቀጽ አራት ሥር የቀረበ ነው፡፡ ይኸውም ኮሚሽኑ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና ከማንነት ጋር የተያይዙ ግጭቶችንና መንስዔያቸውን በመተንተን የመፍትሔ ሐሳቦችን ለሕዝብ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለአስፈጻሚው አካል ማቅረብ መሆኑን ይደነግጋል። የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር በ11 አንቀጾች ተዘርዝረዋል።
ከእነዚህም መካከል ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችንና ግጭቶችን በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብ፣ በሕዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሠረት አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች ማሻሻያ ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ የመጀመርያዎቹ ናቸው።
አስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወሰኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ በተመለከት አግባብነት ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መርሆች ያገናዘበ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ሥርዓት ወይም የሕግ ማሻሻያ እንዲዘረጋ ጥናት በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ ጎልተው የወጡና በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴራል መንግሥት የሚመሩለትን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦችን መርምሮ የውሳኔ ሕሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ ለኮሚሽኑ የተሰጡ ሥልጣንና ተግባር ናቸው።
በቀጣይነት አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ዕርምጃዎች አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ አስተዳደራዊ ወሰኖችና አካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው የልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው እንዲሆኑ፣ አስተዳደራዊ ወሰኖችን የተመለከተ የፖሊሲ ማዕቀፍ የማመንጨት ሥልጣንም ተሰጥቶታል።
የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በተመለከት የሕዝብ አስተያየት መሰብሰብ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ እንዲሁም ሌሎች ባላድርሻ አካላት አስተያየትና ለጥናቱ የሚሆን ግብዓት መውሰድ ሌላው የሥልጣንና ተግባሩ አካል ነው።
በረቂቁ አንቀጽ 6 ላይ ደግሞ ማንኛውም የአስተዳደር ወሰን ውሳኔ፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በኮሚሽኑ ተጠንቶ አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ እልባት እንደሚያገኝ ተመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ ሥራውን በነፃነትና በገለልተኝነት እንደሚያከናውን፣ የሥራ ዘመኑ ለሦስት ዓመት ሆኖ እንዳስፈላጊነቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል።
አዋጁ እንደሚደነግገው የሚቋቋመው ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየሙና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ይገልጻል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለመጀመርያ ንባብ ለምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት የሕወሓት ተወካይ የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት በረቂቁ ላይ ያቀረቡት ሥጋት አልነበረም። ከሕወሓት ተወካዮች ይልቅ በርከት ያሉ የሌሎች የኢሕአዴግ ድርጅቶች ተወካዮች ረቂቅ አዋጁ ለኮሚሽኑ የሚሰጠው ተልዕኮ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ መሆኑን በመጥቀስ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ይኼንን እንዲያጣራ አሳስበው ነበር። በዚህም መሠረት ረቂቅ አዋጁ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት፣ እንዲሁም ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
ረቁቁን ለማፅደቅ በድጋሚ የተሰበሰበው ፓርላማ
ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር እንዲመለከት የተመራለት የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያደረገውን ግምገማ በመዘርዘር ረቂቁ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ፣ የውሳኔ ሐሳቡን ሐሙስ ታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በዕለቱ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ፣ ረቂቁን ለመመርመር ቋሚ ኮሚቴው የተከተለውን ሒደት አብራርተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ታኅሳስ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትርና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም የሕግ ሰነዱን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎችን በመጋበዝ ውይይት ማድረጉን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።
በወቅቱም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኢሳያስ ካሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕግ ማርቀቅ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን እምሩ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በአስረጅነት ተገኝተው ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር በረቂቁ ላይ መወያየታቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል። በዚህ ውይይት ወቅትም በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ አጠቃላይ ይዘት፣ ሕገ መንግሥታዊነትና የመፅደቁ አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል።
በመቀጠልም ታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ረቂቁን ለመመርመር በተባባሪነት ከተመደበው የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን፣ ሌሎች የምክር ቤት አባላት፣ የምክር ቤቱ የሕግ ክፍልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት በረቂቅ ሕጉ ላይ በዝርዝር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በተደረጉት በእነዚህ ሁለት የውይይት መድረኮች መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመፈጸም ሕግና ሥርዓት በአገሪቱ የማረጋገጥ ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77/9/ የተሰጠው፣ እንዲቋቋም የሚፈለገው ኮሚሽንም ይኼንን ኃላፊነት በብቃት ለመፈጸም የሚያግዝ እንደሆነ፣ ኮሚሽኑ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን በተመለከተ በራሱ የመወሰን ሥልጣን ያልተሰጠው በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች ሕጎች እንደማይጣረስ መረዳት እንደተቻለ አቶ ተስፋዬ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
ይኼንን ግንዛቤ በመያዝም በረቂቁ አንቀጾች ላይ መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ከእነዚህም መካከል የኮሚሽኑን ሥልጣንና ተግባር የተዘረዘረባቸው አንቀጽ 5 መጀመርያ ላይ፣ ‹‹ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለክልሎች የተሰጠ ሥልጣንንና ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ›› የሚል አዲስ መንደርደሪያ ሐረግ እንዲካተት መደረጉን አስታውቀዋል።
በረቂቁ አንቀጽ 6 ላይ ደግሞ ማንኛውም የአስተዳደር ወሰን ውሳኔ፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በኮሚሽኑ ተጠንቶ አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ እልባት ያገኛል በሚል የተገለጸው፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠ ኃላፊነት በመሆኑ ኮሚሽኑ በጉዳዮቹ ላይ ያደረገውን ጥናት ‹‹ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል›› ተብሎ ማሻሻያ እንደተደረገበት ገልጸዋል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ የሚያቀርበውን ጥናት በግብዓትነት የመጠቀም ወይም ያለመጠቀም ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተው ተደርጓል። ሌላው ማሻሻያ ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች በተመለከተ የኮሚሽኑ አባላት በጋራ ስምምነት እንደሚወስኑ በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው አንቀጽ ላይ፣ የጋራ ስምምነት የማይደረስ ከሆነ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ በሚል ተሻሽሏል።
በመሆኑም የኮሚሽኑን መቋቋም አስፈላጊነት እንዲሁም የየትኛውንም ወገን በሕግ የተሰጠ ሥልጣን የማይጋፋ መሆኑን የሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት በሁለት ተቃውሞ የተቀበሉት እንደሆነ በመግለጽ፣ ምክር ቤቱ ረቂቅ ሕጉን እንዲያፀድቀው አቶ ተስፋዬ ጠይቀዋል።
ይኼንን ተከትሎ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ መድረኩን ለውይይት ክፍት በማድረግ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በፈቀዱት መሠረት፣ የሕወሓት ተወካይ የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት በቅድሚያ አስተያየታቸውን ስጥተዋል።
በቀዳሚነትም አቶ አጽብሃ አረጋዊ በሰጡት አስተያየት ረቂቅ ሕጉን እንዲመረምር የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ ሕጉ ላይ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በመጥራት የባለድርሻ አካላትን አለማወያየቱ፣ የምክር ቤቱን የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ የጣስ መሆኑን በመግለጽ ወቅሰዋል።
በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች የሕወሐት አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፣ መፅደቅ የለበትም በማለት ከፍተኛ ክርክር አድርገዋል። የወሰንና የማንነት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ሞግተዋል።
አዋጁን በማፅደቅ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ማድረግ ሕገ መንግሥቱን በሁለት መንገድ እንደሚጣረስ፣ አንድም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን በመንጠቅ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያልተከተለ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ በመጥቀስ ተከራክረዋል።
የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አጽብሃ አረጋዊ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመጥቀስ ከተከራከሩ በኋላ፣ ‹‹በቀላሉ እንደሚፀድቅ እርግጠኛ ነኝ፣ ነገር ግን የሚያመጣውን ጣጣ ቆም ብለን ብናይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ አጽብሃ ይኼንን መናገራቸው በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ላይ ቁጣን ፈጥሯል። ከእነዚህም መካከል የአዴፓ አባል የሆኑት የምክር ቤቱ አባል አቶ አጥናፍ ጌጡ ይገኙበታል።
አቶ አጥናፍ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ጣጣ ያመጣል፣ አደጋ አለው የሚሉ ኃይለ ቃትና ማስፈራሪያዎችን መናገር ለዚህ ምክር ቤት አይመጥንም፤›› ሲሉ የግሳጼ ይዘት ያለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ አዋጅ ለውጡ ያመጣው ዕድልና ለአገሪቱ ሕዝቦች ሰላም የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑን እንዳይቋቋም የሚፈልጉ ወገኖች ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱ የማይሸፍናቸውን የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ጭምር ወደ ኋላ ሄዶ ያያል ከሚል ሥጋት እንደሚቃወሙት ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ ወደ ኋላ ሄዶ ሕገ መንግሥቱ የማይሸፍናቸውን ጉዳዮች ጭምር ሊመረምር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስና ሲኮላሹ የሕገ መንግሥት ጥሰት ጥያቄ ሳይነሳ፣ ለሰላም ፋይዳ ያለው ኮሚሽን እንዳይቋቋም የሕገ መንግሥት መጣረስን እንደ ምክንያት ማቅረብ እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክረዋል።
በረቂቁ ላይ ዝርዝር ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የውጭ ግንኙነትና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በሰጡት ምላሽ፣ የምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመራላቸውን ረቂቅ ሕግ ለመመርመር ሕዝባዊ መድረክ በማዘጋጀት ረቂቅ ሕጉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎችና አካላት ጋር መወያየት እንዳለበት ቢገልጽም፣ አስገዳጅነት እንደ ሌለውና ረቂቅ ሕጎች የሚዳብሩበት አንድ ከማራጭ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል። ቋሚ ኮሚቴው ረቂቁን ለመመርመር ያደረጋቸው የውይይት መድረኮች በቂ ከመሆናቸው ተጨማሪ ውይይቶችን ማድረግ እንዳላስፈለገ ተናግረዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ በቋሚ ኮሚቴው መደረጉን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ኮሚሽኑ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተንና ለሚመለከታቸው ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ብቻ እንደሚኖረውና የኮሚሽኑ መቋቋም ከሕገ መንግሥቱ እንደማይጣረስም አስረድተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነበት ምክረ ሐሳቡን ሊቀበል እንደሚችል፣ በራሱ መንገድም ተመሳሳይ ኃላፊነት ያለው ኮሚሽን ወይም ተቋም እንዳያቋቁም የሚከለክለው ነገር ባለመኖሩ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣረስ አስረድተዋል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በቂ ክርክር እንደተደረገ በመግለጽ ፓርላማው ወደ ድምፅ መስጠት እንዲሸጋገር ሲያደርጉ ከምክር ቤቱ አባላት 33 የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 32 የምክር ቤቱ አባላት የሕወሓት ተወካዮች ሲሆኑ፣ ቀሪው አንድ የተቃውሞ ድምፅ ከምክር ቤቱ የሌላ ፓርቲ ተወካይ የተሰጠ ነው። በተጨማሪም አራት የምክር ቤቱ አባላት ድምፀ ተዓቅቦ ያደረጉ ሲሆን፣ ከእነሱ ውስጥ ሦስቱ ደኢሕዴንን የሚወክሉ አባላት ናቸው፡፡ ቀሪው አንድ ተወካይ የአዴፓ መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሠረት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ በአብላጫ ድምፀ ፀድቋል።
የሕጉ አፀዳደቅ ፖለቲካዊ ነው?
ሪፖርተር ያገኘው ማስረጃ እንደሚያመለክተው የኮሚሽኑ መቋቋም ከሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱ ጋር እንደሚጋጭ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አንስቶ እንደነበር አረጋግጧል።
ለኮሚሽኑ የሚሰጠው ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በሕግ የተሰጠ እንደሆነ፣ ኮሚሽኑን ማቋቋም ሳያስፈልግ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር መሥራት እንደሚቻል የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎች ቋሚ ኮሚቴው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ተገኝተው ጥያቄያቸውን ማሰማታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
መንግሥት ይኼንን ኮሚሽን የሚያቋቁመው ጥናትና ምርምር በማድረግ የግጭቶችን መነሻና አማራጭ መፍትሔዎችን ለመረዳት እንዲያስችለው ከሆነ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እየቻለ ለምን ኮሚሽኑን በአዋጅ ለማቋቋም እንደፈለገ ጭምር የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎች መጠየቃቸው ታውቋል።
ከመንግሥት የተወከሉ ኃላፊዎች በተሰጣቸውም ምላሽ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት ኮሚሽኑን ማቋቋም የሚችል ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች ለሥራ አስፈጻሚው ካቢኔ ብቻ የሚቀርቡ ባለመሆናቸው፣ ማለትም ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦቹን ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር የሚያቀርብ በመሆኑና ይኼንን በአዋጅ በተቋቋመ ተቋም ካልሆነ በስተቀር ማድረግ ስለማይቻል፣ ፓርላማው በሚያወጣው አዋጅ እንዲቋቋም መፈለጉ ተገልጾላቸዋል።
አዋጁ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው ብሎ ያመነ አካል አዋጁ ከፀደቀም በኋላ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል የሕገ መንግሥት ትርጉም በማንሳት መጠየቅ እንደሚችል ማብራሪያ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ አፀዳደቅ ሒደቱን የተከታተሉ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚሽኑን ለማቋቋም በምክር ቤቱ የተደረጉ ክርክሮች በበቂ ሁኔታና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተንሸራሸሩ ቢሆንም፣ የክርክሮቹ ይዘት የሕግ አወጣጥ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ፖለቲካዊ ምልልሶች የበዙበት እንደሆነ ገልጸዋል።